አንተነህ ቸሬ
ዛሬ በብዙዎች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነውን ‹‹ወግ›› የተሰኘውን የስነ-ጽሑፍ ዘውግ የጀመረና ፈር ያስያዘ አንጋፋ ባለሙያ ነው። ወጣት ደራሲያን ይህን የስነ-ጽሑፍ ዘርፍ እንዲሞክሩትና ተወዳጅነትን እንዲያተርፉበት በር የከፈተላቸው እርሱ ነው። ወጎቹን በሬዲዮ ጭምር በመተረክ ሕብረተሰቡ ለወግ ቅርበት እንዲኖረው ማድረግ ችሏል። ስራዎቹ ከትምህርት ሰጪነታቸው ባሻገር የማዝናናትም ኃይል እንዳላቸው የስነ-ጽሑፍ ባለሙያዎችና አንባቢያን ይመሰክራሉ። ብዙዎች በእርሱ ስራዎች ላይ ተመርኩዘው የመመረቂያ ጽሑፎችንና ሌሎች የጥናት ስራዎችን አቅርበዋል። ከደራሲነቱ ባሻገር መምህርና ሃያሲም ሆኖ ግዙፍ አስተዋፅኦ አበርክቷል … ወግ ቀማሪው ደራሲና ሃያሲ መስፍን ሀብተማርያም!
ከአቶ ሀብተማርያም ሞገስ እና ከወይዘሮ ደስታ አየለ በ1937 ዓ.ም ሞጆ ከተማ ውስጥ የተወለደው መስፍን፤ ቤተሰቦቹ ያወጡለት ስም ‹‹የት ነበርክ›› የሚል ነበር። ‹‹የኋላሸት››፣ ‹‹ሲሳይ››፣ ‹‹እንግዳወርቅ›፣ ‹‹ሞጆ›› የሚባሉ ቤተ ዘመዱ፣ ወዳጅና ጐረቤት ያወጡለት ስሞችም ነበሩት። እህቱ ያወጡለት ‹‹መስፍን›› የሚለው ሥም ግን መጠሪያውና መታወቂያው ሆኖ ዘለቀ።
መስፍን በልጅነቱ የቤተ ክህነት ትምህርት ተምሯል። በ1942 ዓ.ም ወደ መደበኛ/ዘመናዊ ትምህርት ቤት ገብቶ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በተወለደበት ሞጆ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን (ከስምንተኛ ክፍል ጀምሮ) ደግሞ በአምቦ ተምሯል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተማረባት አምቦ ከድርሰት ጋር የተዋወቀባትና ቁርኝት የፈጠረባት ናት። መስፍን በአምቦ ቆይታው በአማርኛና በእንግሊዝኛ የተፃፉ በርካታ መፃሕፍትን አንብቧል፤ የሥነ ጽሑፍ ዕውቀቱ ከፍ እንዲል የረዱት መምህራንን አግኝቷል፤ ግጥሞችን፣ ትያትሮችንና ልቦለዶችን ጽፏል። መስፍንም ስለአምቦ ጊዜው በአንድ ወቅት ‹‹የድርሰት ሽታው፣ መዓዛው በጭንቅላቴ መቀረጽ የጀመረው የኪነ ጥበብ ፍቅር በእድሜዬ ክልል ጉልህ ሆኖ የታየኝም አምቦ ነው›› ብሎ ተናግሮ ነበር።
ከመደበኛ ትምህርቱ ጐን ለጐን ግጥም በመፃፍና ቴአትር ጽፎ በመተወን ይሳተፍ የነበረው መስፍን ሀብተማርያም፤ የሰፈሩን ልጆች ሰብስቦ የሰውን አነጋገርና አካሄድ በማስመሰል የማሳየት ችሎታ ነበረው። ይህ ተሳትፎውና ታዋቂነቱም የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር የሚያነቧቸውን መፃሕፍት እንዲያወሱት እድል ፈጥሮለታል። አማርኛ ያስተማሩት መምህሩም የድርሰት ፍቅር እንዲያድርበት ካደረጉት ሰዎች መካከል አንዱ ነበሩ።
ብርሃኑ ሰሙ ‹‹ደራሲ መስፍን ሀብማርያም ስለራሱ ምን ብሎ ነበር›› በሚል ርዕስ ባሰፈረው ጽሑፍ ላይ እንዲህ ይላል …
‹‹ … ግንቦት 4 ቀን 1949 ዓ.ም ከሞጆ በአምስት ኪሎ ሜትር በሚርቅ ስፍራ ላይ ልዑል መኮንን ኃይለሥላሴ የመኪና አደጋ ባጋጠማቸው ማግስት፤ በሞጆ ከተማ የሚገኙ ተማሪዎች ወደ ስፍራው ሄደው ሀዘናቸውን እንዲገልፁ ተደርጐ ነበር። በዚህ ሥነ ስርዓት ወቅት ሄሊኮፕተር ይመጣና ወረቀት በትኖ ይሄዳል። ከተበተኑት አንዱን ያገኘው ታዳጊው መስፍን ሀብተማርያም፤ በሎሚ ዛፍ ጥላ ስር ቁጭ ብሎ በወረቀቱ የሰፈረውን ግጥም ያነባል። የሀዘን ግጥሞቹን ወደ ቤቱ ይዞ በመሄድ ደጋግሞ ካነበባቸው በኋላ፣ በማግስቱ አንድ ገጽ የሀዘን ግጥም ፃፈ። በግጥሙ ውስጥ
ያ ልዑል መኮንን የድሆች በረንዳ ፣ ተለይቶን ሄደ ጥሎብን ብዙ ዕዳ›› የሚሉ ስንኞች ይገኙበታል። ይህንን ለአማርኛ አስተማሪው ወስዶ ሲያሳያቸው፣ ‹‹በርታ፤ ወደፊት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ገብተህ ጆርናሊዝም (ጋዜጠኝነት) ትማራለህ›› አሉት …››
መስፍን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ፈተናውን በጥሩ ውጤት አልፎ በ1958 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ ‹‹አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ››)ን ተቀላቀለ።
በዩኒቨርሲቲው ቋንቋና ስነ-ጽሑፍን ማጥናት ጀመረ። መስፍን ገና ከተማሪነት ሕይወቱ ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይቀርቡ በነበሩ ‹‹የኮሌጅ ቀን ግጥሞች›› መድረክ ውስጥ ተሳታፊ ነበር። በዚህም ምክንያት ከእነ ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ (ገሞራው) ጋር ቅርርብ ነበረው። መስፍን ‹‹በረከተ መርገም›› የተሰኘውን ዘለግ ያለውን የኃይሉ ገብረዮሐንስን ግጥም በቃሉ ይዞት ስለነበር ‹‹ተጓዡ በረከተ መርገም›› የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶት ነበር። በወቅቱ በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የነበረው የለውጥ ፈላጊነት እንቅስቃሴ ከሚንፀባረቅባቸው መድረኮች መካከል አንዱ ግጥም ነበር። መስፍን በዘመኑ የሚያቀርባቸው ግጥሞቹ ወጣቶች በብዕር ያደርጉት የነበረውን የትግል አቅጣጫ ወደ ሌላ የመራ እንደሚመስላቸው የሚናገሩ ባለሙያዎችም አሉ።
በ1959 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለ፣ በክረምት ወቅት አስመራ ያሉ መምህራንን እንዲያስተምሩ ከተላኩት 10 ሰዎች መካከል አንዱ መስፍን ሀብተማርያም ነበር። በአስመራና በምፅዋ ከተሞች የአማርኛ ቋንቋ አስተማሪ ሆኖ አገልግሏል።
መስፍን በ1962 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቆ ከኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪውን በማዕረግ ተመረቀ። ለሁለት ዓመታት ያህል በመምህርነት ካገለገለ በኋላ የውጭ አገር የትምህርት እድል አግኝቶ ወደ ካናዳ ሄደ። በዚያም በቫንኮቨር ከተማ፣ በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ (University of British Columbia) የፈጠራ ስነ-ጽሑፍ (Creative Writing) በተሰኘው የትምህርት መስክ የማስተርስ ዲግሪውን አገኘ። ይህም በዘርፉ ከሰለጠኑ ፈር ቀዳጅ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ እንዲሆን አስችሎታል።
የካናዳ ትምህርቱን አጠናቆ ከመጣ በኋላም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሩን ቀጠለ። በዩኒቨርሲቲው ልዩ ልዩ የትምህርት ኮርሶችን እያስተማረ በኢትዮጵያ ሬዲዮ እና የኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ውስጥም ይሰራ ነበር። ተወዳጅ የወግ መጽሐፍቱን ማሳተም የጀመረውም በዚሁ ጊዜ ነበር። የመጀመሪያ ስራውም ‹‹የቡና ቤት ስዕሎችና ሌሎችም ወጎች›› የተሰኘ የወግ መጽሐፍ ነው። ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ‹‹የምወደው ደራሲ ትዝ አለኝ – መስፍን ሀብተማርያም›› በሚለው ጽሑፉ ስለመስፍን ስራዎች እንዲህ በማለት አብራርቷል።
‹‹ … መስፍን ሐብተማርያም በዩኒቨርሲቲው ልዩ ልዩ የትምህርት ኮርሶችን በመስጠት በማስተማር ይታወቃል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እያስተማረም በኢትዮጵያ ሬዲዮ እና የኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ውስጥም ይሰራ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ከማስተማሩ ባሻገርም በኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ ውስጥ በእጅጉ ተወዳጅ የሆኑትን መጽሐፎቹን ማሳተም ጀመረ። በህትመት ደረጃ የመጀመሪያው የሆነችው ስራው ‹‹የቡና ቤት ስዕሎችና ሌሎችም ወጎች›› የምትሰኘዋ ነች። በዚህች መጽሐፍ ውስጥ የተነሱት ርዕሰ ጉዳዮች በዘመኑ አንባቢያን ዘንድ በእጅጉ ተወዳጅ ነበሩ። በተለይ ራሱ መስፍን ሐብተማርያም ወጎቹን በኢትዮጵያ ራዲዮ በራሱ ድምፅ ግሩም አድርጎ ሲተርካቸው ደግሞ ተቀባይነታቸው እያደገ ሔደ።
ይህ ‹‹የቡና ቤት ስዕሎችና ሌሎችም ወጎች›› የተሰኘው የመስፍን መጽሐፍ እንደታተመ የመግቢያ አስተያየት የሰጠው ታዋቂው የሥነ-ፅሁፍ ሊቅ እና ባለቅኔው ደበበ ሰይፉ ነበር። ደበበ በወቅቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እጅግ ታዋቂ መምህር ከመሆኑም ባሻገር የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርንም በፕሬዚዳንትነት ይመራ ነበር። እናም ደበበ ‹በዚህ መፅሐፍ ውስጥ መስፍን መልካም የሚባሉ ወጎችን አቅርቦልናል። የሚወያይባቸውን ጉዳዮች በሚገባ ከማወቁ ጋር በጉዳዮቹ መነሾነት ወደ ወጎቹ የገቡትን ሰዎች ድርጊትና አባባል በብሩህ አእምሮ እንዳስተዋለውና እንደተረዳውም ሊያስገነዝበን የቻለ ይመስለኛል። በድክመታቸው ሳያመር እኛን ተደራሲያኑንም ሳያስመርር በግርምት ትንሽ ጠንከር ሲልም ለትዝብት ያህል ብቻ ስቀን ተቀብለን ስቀን እንድንሸኛቸው ያደርገናል። ይህ በራሱ ቀላል አይደለም› ሲል ስለ መስፍን መፅሐፍ ጽፎለታል … ››
መስፍን በ1976 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርነቱ በፈቃዱ ለቀቀ። ጋዜጠኛ ጥበቡ በጽሑፉ እንደሚያስረዳው መስፍን ከዩኒቨርሲቲው ከለቀቀ በኋላ ህይወት ብዙም የተመቸው ሰው አልነበረም። የህይወት ውጣ ውረዶች ምስቅልቅሎች አጋጥመውታል። ‹‹መስፍን ግን በነዚህ ሁሉ የህይወት ጫናዎች ውስጥ ሆኖ ፍካትን፣ ደስታን፣ ሳቅን፣ ጨዋታን የሚያዘወትር ሰው ነበር›› ይላል። ከዩኒቨርሲቲ መምህርነቱ ከለቀቀ በኋላም በተለያዩ መስሪያ ቤቶችና ተቋማት ውስጥ በግሉ ሲሰራ ቆይቷል።
መስፍን ‹‹የቡና ቤት ስዕሎችና ሌሎችም ወጎች›› ከተሰኘው የመጀመሪያ መፅሐፉ በተጨማሪም ‹‹አውዳመትና ሌሎች ወጎች››፣ ‹‹የሌሊት ድምፆች››፣ ‹‹አዜብና ሌሎች አጫጭር ልብ ወለዶችን›› የተሰኙና ሌሎች ስራዎችን አሳትሟል። በወግ አፃፃፍ ስልቱ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ በር የከፈተው ፊታውራሪው ደራሲ መስፍን ሀብተማርያም፤ በመጽሐፍ ካሳተማቸው ስራዎቹ በተጨማሪ እጅግ በርካታ ወጎችን በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ጽፏል። የተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች አዘጋጅ ሆኖም ሰርቷል።
መስፍን ሃያሲም ነበር። ደራሲ ደረጀ በላይነህ ‹‹የጋሽ መስፍን ናፍቆት›› በሚለው ጽሑፉ ስለደራሲ መስፍን ሀብተማርያም የድርሰትና የሂስ ችሎታ ሲያብራራ ‹‹ … ደራሲና ሃያሲ መስፍን ሀብተማርያም በሀገራችን ሥነ-ጽሑፍ ደማቅ ታሪክ ያለው፣ በተለይም በወግ ጽሑፎቹ የሚታወቅና በርካታ መጽሐፍትን ለሕዝብ ያቀረበ ሰው ነው። ልቡ ወደ ደሳሳ ጐጆዎች፣ ሃሳቡ ወደ ምስኪኖች ድንኳን ገብቶ፣ የየዕለት እንጀራውንና ኑሮውን፣ አንብቦ ጽፎልናል። ዓውደ ዓመትና አዘቦቱን፣ ክብሩንና ውርደቱን አሳይቶናል። የሚያሳዝነውን ሕይወት፣ የትራጀዲውን ሥዕል ቀለም ነክሮ እያሳቀና እያስደመመ ጠቢብነቱን አስመስክሯል። ጋሽ መስፍን የዩኒቨርሲቲም መምህር ነበር። ለዚያውም ጐበዝ መምህር! … በተለይ ያለፉትን ዘመናት መጽሔቶች፣ በተለይ ‹‹የካቲት››ን ስታገላብጡ፣ የሠራቸውን ሂሶች አድናቆት ይፈጥሩባችኋል። ጋሽ መስፍን ደፋር ነው፤ በተለይ በትርጉም ሥራዎች ላይ የሠራቸው ሂሶች ግሩም ነበሩ። ስለ ፈሊጣዊ አነጋገር ብቁ ዕውቀት የሌላቸው ሰዎች ተርጉመው ያስነበቡንን ገላልጦ ሲያሳይ አጀብ ያሰኛል … ›› ብሏል።
ደራሲ መስፍን ሀብተማርያም በ‹‹ፈርጥ›› መጽሔት የየካቲት ወር 1988 ዓ.ም እትም ላይ ስለራሱ ማንነት ባቀረበው ጽሑፍ ‹‹አዜብ›› የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፉ ታትሞ ከተሰራጨ በኋላ መጽሐፉን ያከፋፈሉለት ነጋዴዎች ‹‹ትርፍህ ነው ብለው ስምንት ሺህ ብር እንደሰጡት ጠቅሶ፤ አጋጣሚውንም ‹‹በሕይወቴ የተደሰትኩበት ቀን›› ብሎታል። ‹‹ወይ ጉድ! ለካ ገንዘብ ማለት አነስተኛም ሆኖ እንዴት ያለ የሥነ ልቦና ቶርች ነው! አጃኢብ ነው…›› ሲልም ገልፆታል።
‹‹በምፅፍበት ወቅት የምመርጠው ቦታና ጊዜ የለም። የግድ ብቸኛ መሆንም የለብኝም። ጭንቀትና የኑሮ ክርን ካረፈብኝ ግን ቢጨፈልቁኝም ምንም አይወጣኝም›› በማለት የጻፈው ደራሲና ሃያሲ መስፍን፤ በሕይወት ሳለ የእውቅናና የክብር መድረኮች ተዘጋጅተውለታል። የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማህበር በ2002 ዓ.ም 65ኛ የልደት በዓሉን በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት በድምቀት አክብሮለታል። የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ደግሞ በ2006 ዓ.ም መግቢያ የዕውቅናና የምስጋና መድረክ አዘጋጅቶ ደራሲና ሃያሲ መስፍን ሀብተማርያምን አወድሷል።
ስለደራሲና ሃያሲ መስፍን ሀብተማርያም ከተሰጡ ምስክርነቶች መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡-
‹‹ … መስፍን ሀብተማርያም በሁለት በኩል አስተዋፅኦ አበርክቷል። አንደኛው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በወግ ስነ-ፅሁፍ ዘውግና በሌላውም ዘርፍ ከ10 ዓመት በላይ አስተምሯል። መስፍን ራሱ ከሚፅፈው ውጭ የሚፅፉ የፈጠራ ሰዎችን በመፍጠር ከፍተኛ ድርሻ ነበረው። ውጭ አገር በወግ አፃፃፍ፣ በአጫጭር ልቦለድና በሌሎች ስነፅሁፎች ላይ ትምህርቱን ተከታትሎ ከመጣ በኋላ፣ የተማረውን ወደ ተማሪዎች በማስተላለፍ ብዙ ፀሐፍትን አፍርቷል።
ሁለተኛው ከዩኒቨርሲቲ ከወጣ በኋላ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ውስጥ በሰራበት ወቅት ያበረከተው አስተዋፅኦ ነው። በዚያን ወቅት ቦርዱ ያሳለፋቸውን መጽሐፍት ‹‹ይህን አሟላ፣ ይህን ቀንስ፣ ይህን አዳብር›› እያለ መጽሐፍት ለአንባቢው እንዲመጥኑ ሆነው እንዲወጡ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል። አርታኢ፣ ገምጋሚና ሀያሲ ሆኖ ሰርቷል። ጽሑፎቹም የአገር ሀብትና አስተማሪ ናቸው።
ስብዕናውን በተመለከተ በቅርበት ባላውቀውም ግልፅና ቅን ሰው መሆኑን በተለያዩ የስራ አጋጣሚዎች በተገናኘን ጊዜ ለመረዳት ችያለሁ። በመጽሐፍት ምረቃ፣ በስነ ፅሁፍ ውይይቶች እና መሰል ዝግጅቶች ላይ ተጋብዞ ሲመጣ፤ ለግማሽ ቀን፣ ለሙሉ ቀን አሊያም ለሁለት እና ሶስት ሰዓታት ስንገናኝ ቅንነቱ ጎልቶ ይታያል። የሚጠየቀውንም ጥያቄ አቅሙ እስከፈቀደ ድረስ ለመመለስ ጥረት ሲያደርግ እመለከታለሁ። በተለያዩ መፅሄቶች በርካታ ፅሁፎቹን ሳነብ በጣም ያዝናናኝ ነበር።
አንድ መጽሔት ላይ የመስፍን ጽሑፍ ካለ፣ ሳያስጨንቅ ሕይወትን በጽሑፍ ስለሚያሳይ መጽሔቱን ገዝቼ መጀመሪያ የማነበው የእሱን ጽሑፍ ነው። በ1970ዎቹ ከጋዜጠኛ ታደሰ ሙሉነህና ከነመዓዛ ብሩ ጋር የእሁድ ፕሮግራም ሬዲዮ ዝግጅት ላይ ሲካፈል በነበረበት ጊዜ፣ በጣም በጣም ተወዳጅ ነበር … ›› ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል
***
‹‹ … በኢትዮጵያ ስነ-ፅሁፍ የመጀመሪያውን የወግ አፃፃፍ መንገድ ከዘረጉት ውስጥ የሚመደብ ነው። የዝቅተኛውን ማህበረሰብ ህይወትም እንድናስተውል ያደረገን ጋሽ መስፍን ነው። … ጋሽ መስፍን የማይከብድ፣ ከቀረቡት ሰዓት ጀምሮ እንደራስ አካል የሚታይና የሚገርም ሰው ነው። አቅሙ በፈቀደው መጠንም ሰዎችን ለመርዳት ሙከራዎችን ሲያደርግ ማየቴን አስታውሳለሁ።
ወጣት ደራሲያንን በመፍጠር በኩል ያደረገው አስተዋፅኦ በቃላት የሚገለፅ አይደለም … በማዘግምበትና በማስብበት ጊዜ ሁሉ ‹‹ከምርጥ ምርጡ ላይ አተኩር›› የሚለው የጋሽ መስፍን ምክር አብሮኝ አለ። ጋሽ መስፍን መደበኛ ባልሆነ መልኩ አስተምሮኛል ማለት እችላለሁ። በህይወቱም ቀለል ብሎ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅሎ ነበር የሚኖረው …›› ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ
***
‹‹ … ጋሽ መስፍን ሀብተማርያም በኢትዮጵያ ስነ-ጽሑፍ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ሰው ነው። የአማርኛ ወግም የተጀመረው በእሱ ነው ብዬ አምናለሁ። የተጀመረው ብቻ ሳይሆን ፈር የያዘውም በመስፍን ሃብተማርያም ነው … ወግ የሚባለው የስነ-ፅሁፍ ዘውግ የደረሰን በጋሽ መስፍን ነው። እሱ የሳይንሳዊ እውቀቱም አለው፤ ተሰጥኦውም አለው። ይሄንንም ከ250 በላይ ወጎችን በመፃፍ አሳይቷል። ጋሽ መስፍን ወግ መጀመር ብቻ ሳይሆን ተስፋፍቶ በወጣት ደራስያን እንዲቀጥል አድርጓል። በኢትዮጵያ ሬዲዮ ጭምር ወጎቹን በመተረክ ህብረተሰቡ ለወግ ቅርበት እንዲኖረው ማድረግ ችሏል።
በእነ በዕውቀቱ ስዩም፣ በእነ በሃይሉ ገብረእግዚአብሔር፣ በእነ ኤፍሬም ስዩም… የታየው ወግ፣ ያኔ በጋሽ መስፍን ተፅዕኖ የመጣ ነው። በእንግሊዝ እነ ፍራንሲስ ቤከን የወግ ጀማሪ የሆኑትን ያህል በአማርኛም የወግ ጀማሪው ጋሽ መስፍን ነው። እነፍራንሲስ ቤከን በአገራቸው እንደጀማሪነታቸው ያገኙትን ክብር ጋሽ መስፍንም ሊያገኝ ይገባል ባይ ነኝ … እኔ ጋሽ መስፍንን በሁለት የህይወቴ ጫፍ ሁለት ጊዜ አግኝቼዋለሁ። በመጀመሪያ ስነ-ፅሁፍ ምን ማለት እንደሆነ እንኳን በወጉ ሳይገባኝ፣ ምንም በነበርኩበት ጊዜ አግኝቼው ያናገረኝ በከፍተኛ ትህትናና ፍቅር ነው። ስለ ስነ-ፅሁፉም ቢሆን ሲያበረታታኝ ነበር … ለማንም ቢሆን ጥሩ ወዳጅ ነበር። ጋሽ መስፍን ለወጣቶቹ እንደመሸሸጊያ ጥላ ነበር … የጋሽ መስፍን መልካም ባህሪ ስነ-ፅሁፉን አግዞታል የሚል እምነት አለኝ … ›› ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ
ለወግ የስነ-ጽሑፍ ዘውግ የላቀ አስተዋፅኦ ያበረከተው ደራሲና ሃያሲ መስፍን ሀብተማርያም ሐምሌ 6 ቀን 2006 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ስርዓተ ቀብሩ ሐምሌ 8 ቀን 2006 ዓ.ም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈፅሟል። ደራሲና ሃያሲ መስፍን የሁለት ወንዶችና የአራት ሴት ልጆች አባት እንደነበረም የሕይወት ታሪኩ ይናገራል።
አዲስ ዘመን የካቲት 03/2013