“በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል” እንዲሉ የመንጋው በረት ውስጥ እንደተለቀቀ አመፀኛ ኮርማ አገርና ህዝብን ሰላም ነስቶ ሲያተራምስ ሶስት አስርት ዓመታትን በዙፋን ላይ የቆየው የህወሓት ቡድን፤ ውሎ አድሮ ዛሬ ላይ የሰራው ስራ ዋጋውን ከፍሎታል፡፡ ኢትዮጵያ ስትፈርስ ቆሞ ማየትን የተመኙ ርዝራዦችና ቀለብተኞቹም፤ ህወሓት ሲፈርስ እና ኢትዮጵያ በልጆቿ ቀና ስትል ለመመልከት የግድ ብሏቸዋል፡፡
ዘመኑን ሙሉ “ለእኔ” እንጂ “ለአገር እና ህዝብ” ብሎ የማያውቀው የህወሓት ቡድን፤ በዘመኑ አገር እንዳትረጋጋ፣ ህዝቦች በሰላም አብረው እንዳይኖሩ፤ ፍቅርና አንድነታቸው እንዲከስም፤ እርስ በእርሳቸው እንዲገፋፉና አለፍ ሲልም እንዲጠፋፉ ስትራቴጂ ነድፎ ሲሰራ ኖሯል፡፡ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ አውርቶ የማይጠግበው ይህ ቡድን፤ ለአገር ቀርቶ ቆሜለታለው የሚለውን የትግራይ ህዝብ እንኳን ለአፈና እና ለሴፍቲኔት ጥገኝነት ዳርጎት የስልጣን ዙፋኑን ሲያደላድል ኖሯል፡፡
በህዝቦች ስም የሚምል የሚገዘተው የህወሓት ቡድን፤ ህዝቦችን እርስ በእርሳቸው በማጋጨት ዜጎች እንዲፈናቀሉና ለአደጋ እንዲዳረጉ በማድረግ ህዝቦች እርስ በእርሳቸው እንዳይረዳዱ እንኳን እድል በመንፈግ በተጎጂዎች ስም ከዓለማቀፍ ተቋማት ሀብት በማሰባሰብ የግል ካዝናውን እየሞላ፤ የትግራይ ህዝብም ከሌሎች ወንድሞቹ እንዲነጠል የጥላቻን ስብከት ሲዘራ ኖሯል፡፡
ዛሬም ቡድኑ በፈረሰበት ማግስት ጨው እንደቀመሰች ፍየል በሚያቅበዘብዛቸው የጥቅም ለማዳ ቅልብተኞቹ እና በውስጥም በውጭም ባሉ ርዝራዦቹ አማካኝነት በትግራይ ክልል የተካሄደውን ህግ የማስከበር እርምጃ ተከትሎ በርካታ ዜጎች ተጎድተው በችግር ውስጥ እንዳሉ፤ መንግስትም እየደረሰላቸው እንዳልሆነ አስመስሎ በማቅረብ የቀደመ የጥቅም ድርሻቸውን ለማስጠበቅ መሯሯጣቸው የአደባባይ ምስጢር ሆኗል፡፡ በዚህም እነዚህ ራስ ወዳድ ቡድኖች ስለ ራሳቸው ጥቅም ማግኘት እንጂ ስለ ህዝብና አገር ጉዳያቸው አለመሆኑን ከትናንቱ ይልቅ ዛሬ በደንብ አሳይተዋል፡፡
እነዚህ ቡድኖች፤ “በክልሉ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ ህዝቦች ለከፋ ችግር ተዳርገዋል፤ መንግስት እርዳታ እያደረሰ አይደለም፤ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪዎችም ወደ ስፍራው እንዳይገቡ ሆኗል፤ በክልሉ ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየተካሄደ ነው፤” የሚሉና ሌሎችም የሀሰት አሉባልታዎችን በማራገብ በህዝቡ ስም መነገድን ተቀዳሚ ተግባራቸው አድርገውታል፡፡
ይሁን እንጂ እነሱ እንደሚሉት ሳይሆን ጁንታው አውድሟቸውና ዘርፏቸው የሄደውን መሰረተ ልማቶች በፍጥነት ተጠግነው ወደ ስራ እንዲገቡ፤ በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ (ምግብና መድሃኒትን ጨምሮ) እንዲደርሱ፤ ዓለማቀፍ ተቋማት ጭምር በስፍራው በመገኘት ሁኔታውን እንዲመለከቱ እና እንዲደግፉ ማድረግ ተችሏል፡፡
በስፍራው የተገኙ ዓለማቀፍ ተቋማት፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የተቋማት ተወካዮችና ዲፕሎማቶችም በክልሉ መንግስት እየተከናወነ ያለው ስራና ድጋፍም አበረታች ስለመሆኑ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም የህወሓት ቡድን የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በመንግስት በኩል የተወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ የሚደገፍ ስለመሆኑ፤ የህግ ማስከበር እርምጃው ደግሞ የዘር ጭፍጨፋ አለ መሆኑንም አስረግጠው ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡
እውነቱ በዚህ መልኩ የሚገለፀው በክልሉ ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ፤ በእስካሁን ሂደቱ 70 በመቶ የሚሆነው በኢትዮጵያ መንግስት አቅም የተከናወነ ነው፡፡ ከመንግስት ባለፈም ወገን ለወገን ደራሽነቱን ያረጋገጡ የህዝብ ድጋፎች በስፋት የታዩበት ሲሆን፤ ዛሬም ድረስ በግልም፣ በቡድንም፣ በተቋምና በድርጅቶች ስም የተቀናጀ የድጋፍ ማሰባሰብና ማድረስ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ይህ ድጋፍም በትግራይ ክልል የወገንን ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ብቻ ሳይሆን፤ በመሰል ችግር ውስጥ ለሚገኙ ለመተከል ተፈናቃዮች ጭምር እየተከናወነ ያለ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡
ልንገነዘብ የሚገባው ዋናው ጉዳይም የህወሓት ቡድን መወገድ ለትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ የቆየውን የዘረኝነት አስተሳሰብ፣ ሙስና፣ የእርስ በእርስ መገፋፋትና ግጭትን የመሳሰሉ ክፉ ሀሳብና ድርጊቶች እንዲወገዱ እድል የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ መተሳሰብ፣ አንድነት፣ መደጋገፍና መረዳዳትን ማዕከል ያደረገ ሰላምና ልማት እውን ይሆናል፡፡
ምክንያቱም ዛሬ ላይ ይህ እንዳይሆን ዘብ ሆኖ ሲጠብቅ የነበረው የህወሓት ቡድን ተወግዷል፤ የትግራይ ህዝብም ከጭቆና ተላቋል፤ ዛሬ ላይ የገጠመውን ችግር እንዲሻገርም መላው ኢትዮጵያውያን ከመንግስት ጎን ሆነው ለወገናቸው እንደሚደርሱ እያረጋገጡ ይገኛል፡፡
ይህ ሲሆን የክልሉ ህዝብ አሁን ያለበትን ችግር መሻገር ብቻ ሳይሆን ለዘመናት እንዲኖር ከተወሰነበት የሴፍቲኔት ችግር እንዲላቀቅ ማድረግ ይቻላል፡፡ እናም የትግራይ ህዝብ ዛሬን እንዲሻገር ብቻ ሳይሆን ነገውም ብሩህ እንዲሆን በሁሉም መስክ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ሂደቱም የሁሉንም ተሳትፎ እንደሚፈልግ ተገንዝቦ መስራት ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 03/2013