የመጪው ትውልዶችን ዕጣ ፈንታ የተሻለ ለማድረግ !

ከፍተኛ እድገት እያስመዘገቡ ያሉ፤ በኢኮኖሚ አቅማቸው አንቱ የተባሉ ሀገራት ለደረሱበት ሁለንተናዊ እድገት ብዙ ዋጋ ለመክፈል የተገደዱ ትውልዶች አሏቸው። ዋጋ ሳይከፈል አልጋ በአልጋ በሆነ የታሪክ ጉዞ ውስጥ ወደ ብልፅግና የመጣ ሀገር ሆነ ማኅበረሰብ የለም። ይብዛም ይነስ የትኛውም ማኅበረሰብ አሁን ላይ ላለበት እድገት ፈቅዶም ይሁን በሁኔታዎች አስገዳጅነት ዋጋ ከፍሎ ያለፈ ትውልድ አለው።

የታሪክ መዛግብት እንደሚያስረዱን በትኛውም ዓለም ክፍል የተካሄዱ እና ስኬታማ የሆኑ የብልፅግና ጉዞዎች፤ በአንድም ይሁን በሌላ በወቅቱ የነበረውን ትውልድ ከፍተኛ መስዋዕትነት ጠይቀዋል። ትውልዱ ነገን ተስፋ በማድረግ፤ ጥርሱን ነክሶ፤ ፍላጎቶቹን ገድቦ፤ ተርቦ እና ተጠምቶ ሳይቀር ለመጪ ትውልዶች ነገን ሠርቶ አልፏል።

እንደ ደቡብ ኮሪያ እና ቻይና እስያ ሀገራት፤ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ብዙ ውድመት ያስተናገዱ ሀገራት፤ ከነበሩባቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች ወጥተው አሁን ያሉበት ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ አቅም ላይ የደረሱት፤ በወቅቱ የነበሩ ትውልዶች ነገን ተስፋ ባደረገ መነቃቃት ወቅቱ የጠየቃቸውን መስዋዕትነት መክፈል በመቻላቸው ነው። ያጋጠሟቸውን ችግሮች የሕልውና ጉዳይ አድርገው የሞት ሽረት ትግል አድርገዋል።

የሞት ሽረት ትግሉ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት በሁለንተናዊ መንገድ በመክፈል፤ እንደ ሀገር የጀመሩት ትግል በስኬት ከማጠናቀቅ ባለፈ፤ አሁን ላይ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ያስቻላቸውን መሠረት መጣል አስችሏቸዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚ ባለቤት እንዲሆኑም እረድቷቸዋል።

ትግሉ መጪ ትውልዶች ከቀደሙ የሕይወት ፈተናዎች፤ ከሕልውና ስጋት እና ፍርሐት ወጥተው፤ ሕይወትን በተሻለ መንገድ እና መልክ እንዲቀበሉ መልካም ዕድሎችን ፈጥሮላቸዋል። ቀጣይ ትውልዶችን ለበለጠ ልማት እና ብልፅግና የሚያነሳሳ፤ በራሱ ለትውልዶች የሥነ-ልቦና ከፍታ መፍጠር ያስቻለ የታሪክ ትርክት ባለቤቶች እንዲሆኑ ረድቷቸዋል።

ይህ ስኬታማ የሀገራት የለውጥ ተሞክሮ እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር ለጀመርነው እና አሁን ላይ ከትርክት ተስፋነት ወደሚጨበጥ ስኬት እየተሸጋገረ ላለው ሀገራዊ ለውጥ ትልቅ ተሞክሮ የሚሆን ነው። ለውጡን በሁለንተናዊ መልኩ በማስቀጠል ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የጀመርነው ሀገራዊ ትግል የሞት ሽረት ከመሆኑ አኳያ የእያንዳንዱ ዜጋ መስዋዕትነት የሚጠይቅ ነው።

የለውጡ ትውልድ ነገን ተስፋ አድርጎ፤ ጥርሱን ነክሶ፤ ፍላጎቶቹን ገድቦ ፤ ተርቦ እና ተጠምቶ ሳይቀር ለመጪ ትውልዶች የተሻለች ሀገር እና የተሻለ ነገን ሠርቶ ማለፍ ይጠበቅበታል። ባልተከፈለ መስዋዕትነት የሚፈጠር የተሻለ ነገ የለም። የለውጥ መነሳሳት በራሱ፤ እራስን ለተሻሉ ነገዎች መስዋዕት ለማድረግ የመነቃቃት አንዱ መገለጫ ነው።

ሕዝባችን አምጦ በራሱ ጊዜ የወለደው ለውጥ ስኬታማ እንዲሆን፤ ሕዝባችን ለውጡ ለሚጠይቀው መስዋዕትነት እራሱን በሁለንተናዊ መንገድ ማዘጋጀት ይጠበቅበታል። የሚከፍለው የትኛውም መስዋዕትነት ተስፋ ለሚያደርገው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ሕዝባዊ ጉዞ ትልቅ አቅም መሆኑን በአግባቡ ተረድቶ ግራ አጋቢ ከሆኑ ትርክቶች እራሱን መጠበቅ ይኖርበታል።

ብልፅግና በአነቃቂ የፖለቲካ ዲስኩሮች የሚፈጠር ሳይሆን፤ የመላ ሕዝቡን አቅም የሚጠይቅ፤ ነገን ለራስም ለመጪ ትውልዶችም የተሻለ ተስፋ አድርጎ ዛሬን በብዙ መስዋዕትነት ውስጥ ማለፍን የሚጠይቅ ነው። ይህ ደግሞ በባለፉት ስድስት የለውጥ ዓመታት በተጨባጭ የተስተዋለ ነው። በነዚህ የለውጥ ዓመታት ውስጥ ሕዝባችን በብዙ መልኩ ብዙ ዋጋ ከፍሏል።

ለውጡ አሁን ለደረሰበት ስኬት ለመድረስ፤ ሕዝባችን ብዙ መስዋዕትነት ከፍሏል። በለውጡ ዓመታት በለውጥ ውስጥ እንዳለ ሕዝብ ብዙ ኢኮኖሚው፤ ፖለቲካው እና ማኅበራዊ ፈተናዎች አጋጥመውታል። እያንዳንዱን ፈተና ለማለፍም፤ ፈተናው የጠየቀውን መስዋዕትነት ከፍሏል።

ይህ ዛሬ ላይ በቡዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ እየገነባቸው ያሉ ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ አቅሞች ከሁሉም በላይ ነገዎቻችንን ብሩህ እና ባለብዙ ተስፋ የሚያደርጉ፤ እንደ ሀገር አዲስ የልማት/ የብልፅግና ትርክት ባለቤት እንዲንሆን የሚያስችሉን፤ የመጪ ትውልዶችን ዕጣ ፈንታ የተሻለ የሚያደርጉ ዕድሎቻችን ናቸው።

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You