
ሰላም የነገሮች ሁሉ ማጽኛ መሠረት ናት:: መሠረት ደግሞ በጠንካራ አለት ላይ ሊገነባ ይገባል:: ይሄ ጠንካራ አለት ደግሞ አንደበት አይደለም፤ የሚሸነግል ምላስም አይደለም፤ ከሚኖር ማንነት የሚመነጭ፣ ከሰላማዊ ሠብዕና የሚወለድ እንጂ::
በኢትዮጵያም ዛሬ ላይ ስለ ሰላም የሚናገሩ አንደበቶች፤ ስለ ሰላም የሚያነበንቡ ምላሶች እልፍ ናቸው:: ስላምን ለማዋለድ፤ ሰላምን ተንከባክቦ ለማሳደግ፤ ሰላምን አሳድጎ ለማጽናት የሚተጉ ቅን እና ይቅር ባይ ልቦች፤ ሰላምን ሆነው የሚኖሩ እና ሌሎችም እንዲኖሩ የሚፈቀውዱ ሠብዓዊ ስሪቶች ግን የሚፈለገውን ያህል መገለጥ አልቻሉም::
ዛሬ ላይ እንደ ሀገር የሰላምና ደህንነት ሁኔታዎች በየአካባቢው በአንጻራዊነት እንዲገለጥ እየሆነ ያለውም ለዚህ ነው:: ሰላም አንጻራዊ ሆኖ እንዲገለጥ ያደረጉትም በየአደባባዩ እነዚህ ሰላምን ሰባኪ አንደበቶች፤ ስለ ሰላም ያለ ማቋረጥ በሚመስል መልኩ የሚያነበብቡ ምላሶች በቃላቸው ልክ መገለጥ፤ ግዘፍ ነስተው መታየት ባለመቻላቸው ነው::
በሁሉም አካባቢዎች፤ በሁሉም መደቦች፤ በሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች፤ በሁሉም አደረጃጀቶች ሰላም ዜና ናት:: ይህች ዜማ ግን ሕይወት ሆና የምትገኘው በጥቂቶች ሠብዕና ውስጥ ነው:: ለዚህም ነው እዚህም እዚያም ያልተቆራረጡ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች አልላቀቅ ያሉን:: ለዚህም ነው መንግሥት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ እናቶች፣… በየፊናቸው ስለ ሰላም ደጋግመው ቢናገሩም በሚፈለገው ልክ ውጤታማ ሊሆን ያልቻለው::
ለዚህም ነው ምክንያት እየፈለጉ ነፍጥ አንግተው ጫካ የገቡ አንጃዎች፤ ጫካም ገብተው በዘረፋና ሕዝብን በማወክ የተሰማሩ ጽንፈኞች፤ በከተማም ሆነው ሕዝቡ እንዳይረጋጋ የሚሠሩ የሃሳብ ልዕልና ድንኮች፤ ከሀገር ውጭም ሆነው የሌሎችን አጀንዳ በመቀበል ሀገርና ሕዝብን ለማመስ የሚተጉ የከሰሩ ፖለቲከኞች ጊዜ እየጠበቁ የሰላምን ካባ በምላሳቸው ለብሰው ከሰላም የተፋታ ሠብዕናቸው በገሃድ ሲገለጥ የሚታየው::
ዛሬም ሕዝብ ሰላምን አብዝቶ ይሻል፤ ስለ ሰላሙ ሲልም ዋጋ እየከፈለ ይገኛል:: የኃይማኖት አባቶች ሰላምን አብዝተው ይሰብካሉ:: የሀገር ሽማግሌዎች፣ ዑጋዞች፣ እናቶች፣ አባ ገዳዎች፣… ስለ ሰላም ያለመታከት ሲደክሙ ይስተዋላል:: መንግሥትም እነዚህ አካላት ከሁከት ይልቅ ስክነትን፤ ከግጭት ይልቅ ተነጋግሮ ችግሮችን መፍታትል፤ ከጦርነት ይልቅ ሰላማዊ አማራጭን እንዲመርጡ ሳይሰለች በሩን ከፍቶ መጠበቁም ለዚሁ ነው::
ነገር ግን ስለ ሰላም ከማውራት የዘለለ፣ የሰላም መንገድን የማይሹ አካላት ይሄን ሁሉ የሰላም ቃል ማድመጥ አይችሉም:: ምክንያቱም፣ ለእነርሱ ሰላም የሚነገር እንጂ የሚኖር እውነት አይደለም:: ሰላም እነርሱ ለሚፈልጉት ዓላማ መዳረሻ የቃላት ድርድር እንጂ ከሠብዕናቸው አልተዋሃደም:: ሰላም ለሰፊው ሕዝብ የሚጠቅም እንጂ ለእነርሱ ልብስም፣ ጉርስም የሚሆን አይደለም::
ስለዚህ እነዚህ ኃይሎች በጫካም ሆነው ሰላም ሲሉ፤ በከተማም ሆነው ሰላም ሲሉ፤ በውጪ ሀገርም ሆነው ሰላም ሲሉ፣ ስለ ሰላም በመናገራቸው ብቻ ሊያተርፉ የሚችሉትን አልያም ሊያገኙ የሚችሉትን ድጋፍ ታሳቢ በማድረግ እንጂ፣ ለሕዝቡ ሰላም ወጥቶ መግባት ያለውን ፋይዳ ከግምት አስገብተው አይደለም::
ለዚህም ነው ጠዋት ስለ ሰላም ባወራ አንደበታቸው፣ ማታ ላይ ስለ ቂምና ቁርሾ፤ ስለ ግጭትና መፈናቀል፤ ስለ ታጣቂ አንጃዎች ጀብዱና ለሀገር ሰላም ሲል ለሀገርና ሕዝቡ ዋጋ ስለሚከፍለው የፀጥታ ኃይል ውድቀት ቅዠትና ምኞታቸውን ሲያስተጋቡ የሚደመጡት::
ይሄ ደግሞ እነዚህ የከሰሩ የፖለቲካም ሆኑ የታጠቁ ኃይሎችና አንጃዎቻቸው፣ ሰላምን የሚጠሯት ለእነርሱ ፍላጎት መሸጋገሪያ መስላ ከታየቻቸው ብቻ እንጂ፤ ሰላም ለእነርሱ ትርፍ ያላት መሆኗን በመገንዘብ አይደለም:: ምክንያቱም ኪሳቸውን ቢሞሉም፤ ሥልጣን እናገኛለን ብለው ቢመኙም በሰላም አውድ ውስጥ ሳይሆን በሁከትና ግጭት ውስጥ ነው:: ምክንያቱም እነርሱ የግጭት ጠማቂ ሆነው የተከሰቱ የግጭት ነጋዴዎች፤ የሰላም አውድ ከሳሪዎች መሆናቸውን በደንብ ይገነዘባሉና ነው::
ሰላም ካለ ዘረፋ የለም፤ ሰላም ካለ ኮትሮባንድ የለም፤… እናም በዘረፋ እና ኮትሮባንድ ሰንሰለት ውስጥ ሆኖ ስለ ሰላም ከመናገር የዘለለ እንዴት በተግባር እንድትገለጥ መሥራት ይቻላል:: ከዚህ ባሻገር ሰላም ሠርቶ መክበርን ታበረታታለች፤ ሰላም በሃሳብ አሸንፎ ወደ ሥልጣን መሸጋገርን ሀብቷ አድርጋለች፤ ለመዝረፍ እንጂ ለመሥራት ያልተፈጠረ እጅ ይዞ፤ ስለ ጦርነት ከማወጅ ያለፈ ረብ ባለው ሃሳብ ያልተቃኘ አንደበትን ገንዘቡ ያደረገ ሰው እንዴት ሰላማዊ ሠብዕናን በውስጡ ሊያኖር ይችላል::
ሊሆን የሚገባው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው:: ሰው በሰውነቱ ብቻ ሰላማዊ ነው:: የሚኖረው፣ ሠርቶ የሚያተርፈው፤ የሃሳብ ልዕልናውን ወደ ሕዝብ አድርሶ ቅቡልነትን የሚያገኘው፤… ሰላማዊ አውድ ሲፈጠር ነው:: በሁከትና ግጭት ውስጥ የሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ አይሳኩም እንጂ ለጊዜው የተሳኩ ቢመስሉ እንኳን የአጭር ጊዜ ናቸው::
በመሆኑም፣ ከግለሰብ ጀምሮ እንደ ሕዝብ፤ ከመንደር ተነስቶም እንደ ሀገር የሚበጀውም፤ የሚያሻግረውም ይሄው ሰላማዊ መንገድ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል:: በተለይም ይሄን እውነት ተገንዝበው ስለ ሰላም ከሚለፉ ግለሰቦችና ተቋማት ጀምሮ፤ እንደ መንግሥትም የተያዘውን የሰላም አማራጭ ሁሉ ከግምት በማስገባት ከራስ ይልቅ ለሀገርና ሕዝብ ሲባል ስለ ሰላም ራስን ማዘጋጀት ይገባል:: ለዚህ ደግሞ ሰላምን ከመናገር የተሻገረ በተግባር መግለጥ የሚያስችል ሠብዓዊ ልዕልናን መላበስ የተገባ ነው::
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም