አዲስ አበባ ከተማ የሚገኘውን የአበበ ቢቂላ ስታዲየም ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማደስና አስፈላጊውን ጥገና ለማካሄድ የሚደረገው እንቅስቃሴ እየተፋጠነና እየተጠናቀቀ መሆኑን የከተማው ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ዳይሬክተር አስታወቁ።
የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ዳይሬክተር አቶ ማቴዎስ ኦልቀባ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ጨረታ ወጥቶ በማሸነፍ ግንባታውን የተረከበው ዦንግም ኢንጅነሪንግ የቻይና ኩባንያ በየካቲት ወር መገባደጃ 2009 ዓ.ም ነው ሥራውን የጀመረው፡፡ በአሁኑ ወቅት የስታዲየሙ እድሳትና ጥገና ከ70 በመቶ በላይ ተጠናቋል።
ዳይሬክተሩ፣ የእግር ኳስ ሜዳው የተጠገነ መሆኑንና የሩጫ ሜዳው ዙሪያውን አስፋልት እንዲለብስ ተደርጓል፤ ከደረቀ በኋላም የመሮጫ ትራኩን የማልበስ ሥራ ይከናወናል ብለዋል፡፡ በስታዲየሙ ዙሪያ ሱቆች እየተገነቡ መሆናቸውን አስታውቀው፤ ስታዲየሙን ለማጠናቀቅ ጥቃቅን ሥራዎች መቅረታቸውን ገልጸዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ የስታዲየሙ እድሳትና ጥገና በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ይጠናቀቃል የተባለ ቢሆንም፤ በታሰበው ጊዜ ሊጠናቀቅ ባለመቻሉ ተጨማሪ ሦስት ወራት ተይዞለታል፡፡ ግንባታውም በሚቀጥለው መጋቢት ወር ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጀነር ታከለ ዑማም በተደጋጋሚ የግንባታውን ሁኔታ በቦታው ተገኝተው እየተከታተሉ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ ይህም የግንባታውን ሂደት በፍጥነት ለማጠናቀቅ እንደሚረዳ ተናግረዋል፤ በከተማው አስተዳደር ለወጣቶችና ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የተሰጠውን ትኩረት እንደሚያመለክትም ገልጸዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በስታዲየሙ የሚገነባው የአትሌቲክስ መሮጫ ትራክ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን እና ለአትሌቲክስ መሮጫ፣ መለማመጃና ማወዳደሪያ ተደርጎ ጥቅም ላይ የሚውል ነው፡፡ ለሩጫ፣ ለዱላ ቅብብል፣ ለዝላይ እንዲሁም ለከፍታ ዝላይ ማወዳደር የሚያስችልም ነው። የአካባቢው ነዋሪዎችና ወጣቶች በትርፍ ሰዓታቸው በጤና ቡድን ተደራጅተው ስፖርታዊ ውድድሮች ሊያደርጉበት የሚያስችል በመሆኑ ዜጎችን በስፖርታዊ እንቅስቃሴ፣ በአካልም ሆነ በአዕምሮም እንዲነቃቁ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
ስታዲየሙ ቀደም ሲል ከነበረው ይዞታ በላቀ መልኩ ስለሚታደስ የአካባቢው ነዋሪዎችና ወጣቶች በተለያዩ መልኩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይታመንበ ታል፡፡ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች የሚደረጉበት ሁኔታ የበለጠ ይመቻቻል፡፡ በስታዲየሙ ዙሪያ ያሉትን አካባቢዎች በአረንጓዴ ተክሎች በማሰማመር፣ አቧራማ ቦታዎችን አስፋልት በማልበስ እንዲሁም ለተሽከርካ ሪዎች ማቆሚያ አድርጎ ለመሥራት የሚመለከታቸው አካላት ከወዲሁ መረባረብ እንዳለባቸውም ዳይሬክተሩ አቶ ማቲዎስ ተናግረዋል።
ለስታዲየሙ ተመልካቾች መቀመጫዎች ሙሉ ለሙሉ የተገጠሙ ሲሆን፣ የስታዲየሙን ዙሪያ ለተመልካቾች አመቺ በሚሆን መልኩ ዙሪያውን ጣሪያውን ለማልበስ የሚያስችል የተሠሩ የዋልታና ማገር ተከላዎችን በስታዲየሙ በመገኘት ለመጎብኘት ተችሏል።
እስከ 30 ሺ ሕዝብ ለሚይዘው ለአበበ ቢቂላ ስታዲየም እድሳትና ጥገና ሥራ 105 ሚሊዮን ብር መመደቡን አመልክተው፣ ግንባታውም የተለያየ ሙያ ያላቸው 100 የሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 28/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ