የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 14ተኛ ሳምንት መርሐግብር በሳምንቱ የእረፍት ቀናትም በተለያዩ ከተሞች ተካሂደዋል።በመርሃ ግብሩ ውጤት መሰረትም መቀሌ ሰባ እንድርታ መከላከያን አምስት ለሁለት ያሸነፈበት ጨዋታ ብዙ ግቦች የተቆጠሩበት ሆኗል።
መቀሌዎች አምስተኛ ተከታታይ ጨዋታቸውን ባሸነፉበት የመከላከያው ጨዋታ አማኑኤል ገብረሚካኤል ነግሶ አራት ግቦችን በማስቆጠር ነግሶ ታይቷል።ተጫዋቹ በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ ስምንት ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱ ሰንጠረዥ ስሙን በሶስት ደረጃ ላይ እንዲያስቀምጥ አስችሎታል።
መከላከያ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች አስራአምስት ግቦችን ያስተናገደ ሲሆን በሜዳው አዲስ አበባ ስታዲየም በአዳማ፣በቅዱስ ጊዮርጊስ፣ አምስት ግቦች እንደተቆጠሩበት ይታወሳል።ውጤቱን ተከትሎም ውጤታቸውን ማሻሻል ሊጉን መምራት የሚያስችለውን ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል።
መቀሌ ሰባ እንድርታ 23 ነጥቦችን ይዞ ቀሪ ሶስት ጨዋታ እየቀረው ቅዱስ ጊዮርጊስን በሁለተኝነት ይከተላል።ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስና በመቀሌ ሰባ እንደርታ መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት ሁለት ብቻ መሆኑን ተከትሎም መቀሌዎች ተስተካካይ ጨዋታቸውን የሚያሸንፉ ከሆነ የሊጉ መሪ መሆን ይቻላቸዋል።
በሊጉ የተፍረከረከ የተከላካይ ክፍል የገነባው መከላከያ በውጤት ማጣት ሲሸበር የፊት መስመር ተሰላፊው ምን ይሉህ ወንድሙ በአንፃሩ የፊት መስመሩ ላይ ድንቅ ብቃት እያሳየ ይገኛል።ተጫዋቹ መቀሌ ላይ ያስቆጠራቸውን ሁለት ግቦችም የሊጉ ኮከብ ግብ አግቢነት በስሙ እንዲጻፍ አድርገውታል።
በሌላ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በሜዳውና በደጋፊው ፊት ሽንፈትን አስተናግዷል።ቡናማዎቹ በደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ በተቀመጠው ደቡብ ፖሊሶች 2 ለ 1 የተሸነፈበት ጨዋታ ያልተጠበቀ ውጤት የተመዘገበበት ሆኗል።
ባሳለፍነው ሳምንት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን በማሰናበት በቀድሞ ተጫዋቹ አላዛር መለሰ እየተመራ ወደ ሜዳ የገባው ደቡብ ፖሊስ ያልተጠበቀ ድል ተቀዳጅቷል፤ነጥቡንም ከአምስት ውደ ስምንት ከማሸጋገር ባለፈ ለክለቡ ከወራጅ ቀጣና መውጣት መነቃቃትን የሚፈጥር መሆኑ ታምኖበታል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ጨዋታዎች ነጥብ እስኪጥል ድረስ የሊጉ መሪ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና በአስራ ሶስተኛ ሳምንት በጅማ አባጅፋር አሁን ደግሞ በደቡብ ፖሊስ በመሸነፉ ውጤት ርቆታል።ቡናማዎቹ በተለይ በሜዳቸው የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች ነጥብ ማግኘት አለመቻላቸው በዘንድሮው የሊጉ ሻምፒዮንነት ጉዟቸው ላይ ቀዝቃዛ ውሃን የሚቸልስ ሆኗል። ውጤቱን በ22 ነጥብ ወደ አራተኝነት ዝቅ እንዲሉ አስገድዷቸዋል።
በርካታ ደጋፊዎችም በቡድኑ ወቅታዊ አቋምና በአሰልጣኝ ዲዴ ጎሜዝ የጨዋታ ፍልስፍና ላይ ቅሬታቸውን ማስደመጥ ጀምረዋል። ከውጤት ባሻገር በተለይ ክለቡ የሚታወቅበት መልካም የሆነ የጨዋታ ዘይቤ አጥፍተውታል በሚል እንዲሰናበቱ የሚጠየቁም በርክተዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 14ተኛ ሳምንት መርሐግብር ደማቅ በነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አሸናፊነቱ በኋላ በፋሲል ከተማ ሁለት ነጥብ የተነጠቀበትን ውጤት አስመዝግቧል። አንድ አቻ ተጠናቋል።
በሊጉ መክፈቻ መርሃ ግብሮች ደካማ አቋም ቢያሳይም ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻል በማሳየት አሸናፊነቱን የመለሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ ምንም እንኳን ሶስት ነጥብ ማግኘት ባይችልም የሊጉን መሪነት አስቀጥሏል።አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ25 ነጥብ የሊጉን የደረጃ አናት ተቀምጧል። ከሜዳቸው ውጪ ከፈረሰኞቹ ሁለት ነጥብ መውሰድ የቻሉት ፋሲሎች ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ አንድ ነጥብ በማግኘት በነበሩበት ስድስተኛ ደረጃ ላይ ረግተዋል።
በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄዱት ሌሎች ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና ደደቢትን ሶስት ለባዶ አሸንፏል።ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ያሉት ሲዳማ ቡና በተመሳሳይ 23 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
ጅማ አባጅፋርና ባህርዳር ከተማ፤አዳማ ከተማና ከወላይታ ድቻ አንድ አቻ ሲለያዩ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሜዳው ውጪ ስሁል ሽረን አንድ ለዜሮ አሸነፏል።ውጤቱም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲም በስሁል ሽረ ሜዳ ሶስት ነጥብ ይዞ የተመለሰ የመጀመሪያው ክለብ ሆኗል። ሀዋሳ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ሃዋሳ ከተማን 1ለ ዜሮ አሸንፏል።
በአጠቃላይ ውጤት መከላከያ ከደቡብ ፖሊስና ደደቢት በሊጉ ሰንጠረዥ የደረጃ ግርጌ እንደቅደም ተከተላቸው ከ16 እስከ 14 ያለውን ቦታ ይዘዋል።የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የመከላከያው ምን ይሉ ወንድሙ በዘጠኝ ግብ ሲመራ፤ የሃዋሳ ከተማው ታፈሰ ሰለሞንና የመቀሌው አማኑኤል ግብረሚካኤል በስምንት ግብ ይከተሉታል።
አዲስ ዘመን ጥር 28/2011
ታምራት ተስፋዬ