በትግራይ ክልል የተካሄደውን ህግን የማስከበር እርምጃ ተከትሎ የትግራይ ክልል ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው እየተመለሰ ነው፡፡ ይሄንን መንግስትም ገልጿል፤ የተለያ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ወደ ስፍራው በማቅናት ማረጋገጥ ችለዋል። የህዝቡን ማህበራዊ እና አኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የመመለስ እና መሰረተ ልማቶችን መልሶ የመገንባት ስራ እየተከናወነም ይገኛል፡፡
ይሄን ተከትሎም በርካታ የውጭና የሀገር ውስጥ ድርጅቶች ለትግራይ ህዝብ ሰብአዊ ድጋፍ በማድረስ ረገድ አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ያሳዩት አጋርነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ትክክለኛውን ቁጥር ከማቅረብ ይልቅ አጋኖ የማቅረብ ሁኔታ ይስተዋላል።
በእርግጥ ከህግ ማስከበሩ በፊት በሰፍትኔት ፕሮግራም ታቅፈው የነበሩ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎች በክልሉ ውስጥ እንደነበሩ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ህግን የማስከበር እርምጃውን ተከትሎ ለችግር የተጋለጡ ወገኖች መኖራቸውም ይታወቃል፡፡ ከህግ ማስከበሩ ጋር ተያይዞ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ቁጥር ግን ከ700 ሺህ በላይ እንደማይበልጡ ተገልጿል። ይህ ደግሞ ቀደም ሲል በሴፍቲኔት ድጋፍ የሚደገፉ በክልሉ የሚኖሩ ዜጎች ቁጥር ሲጨመርበት ከፍ ያለ አሃዝ ሊያሳይ እንደሚችል ቢታመንም፤ ይሄን አሃዝ ግን በህግ ማስከበር እርምጃው የተፈጠረ አድርጎ ማቅረቡ መረጃውን ከእውነት የራቀ ያደርገዋል፡፡
ዋናው ጉዳይ ግን የክልሉና የፌዴራል መንግስት በጋራ በመሆን በትግራይ ክልል የሚገኙ 92 የማከፋፈያ ማዕከላትን በመጠቀም፤ በሴፍቲኔት ታቅፈው የነበሩትንና በህግ ማስከበሩ ለችግር የተጋለጡትን ጨምሮ ለ1 ሚሊዮን 46 ሺህ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንደደረሳቸው ለመገንዘብ ተችሏል።
በመቀሌ የሚገኘው የእህል ማከማቻ ውስጥ ብቻ ለቀጣይ ወራት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎቻችንን መመገብ የሚያስችል የምግብ ክምችት አለ፡፡ ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የራስን ችግር በራስ የመፍታት አቅም እንዳለው የሚያሳይ ከመሆኑ ባለፈ፤ ለዘመናት ሀገራችን ትታወቅበት የነበረውን የተመጽዋጭነት እሳቤ ታሪክ ያደረገ ነው።
በመሆኑም የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚመለከታቸው ዜጎች እየደረሰ መሆኑን በመረዳት ህዝብና መንግስት በጋራ በመሆን በቀጣይ ለሚከናወኑ የሰብአዊ ድጋፍ የማዳረስ ተግባራት የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። እስካሁን ባለው መረጃ በክልሉ የሚገኙ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው 1 ነጥብ 8 የሚሆኑ ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፤ የመንግስት ድርሻ 70 ከመቶ መድረሱ መንግስት ሃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን የሚያስረዳ ነው።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የእርዳታ ድርጅቶች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጉዳዩን ፖለቲካዊ የማድረግና በሃሰተኛ መረጃ የክልሉ ህዝብ በረሃብ እየተገረፈ እንደሆነ የማሳየት አካሄድ ግን ሊወገዝ የሚገባው ተግባር ነው። ይህም የማህበረሰቡን የመረዳዳት እሴቶች የማጠልሸት ተግባር ምንጩ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ማህበራዊ አንድነት ካለመረዳት የተነሳ በመሆኑ ከእንዲህ አይነት ተግባር እጃቸውን መሰብሰብ ይኖርባቸዋል።
ኢትዮጵያ የራሷን ችግር በራሷ የመፍታት አቅሟ የተፈተነው ከዚህ ቀደም በተፈጠሩ መፈናቀሎች ሲሆን፤ የጀመረቻቸው እንደ ህዳሴ ግድብና ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች ደግሞ የአንድነት መሰረቷን ያረጋገጡ መሆናቸው የማይካድ ሃቅ ነው። በቀጣይም ህዝቡ ቀድሞ የነበሩትን የአንድነትና አብሮ የመኖር እሴቶችን አጠናክሮ ከመንግስት ጋር በጋራ መሥራት ይኖርበታል።
እነዚህ የውጭ ሀገር ዲፕሎማቶች እና የመገናኛ ብዙሃን አካላትም በኢትዮጵያ በተለያየ መልክ ምድር ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች ለዘመናት ያቆዩትን የርስበርስ ድጋፍ የማይናቅ መሆኑንም ሊገነዘቡ ይገባል። ለዚህም ድብቅ ዓላማ እስከሌላቸው ድረስ የክልሉና የፌዴራል መንግሥት እያደረገ ያለውን የሰብአዊ ድጋፍ በቦታው ተገኝተው መመልከት እንደሚችሉም በተደጋጋሚ ተገልፆላቸዋል። በዚህ ረገድ የዓለም ምግብ ፕሮግራምም በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ ያደረገው አጋርነት ለሌሎች ሰብአዊ ድጋፍ አድራጊ ድርጅቶችም አርአያ የሚሆን ተግባር ነው።
በአጠቃላይ በትግራይ ሰፊ ረሃብ እና ችግር እንዳለ በማስወራት መጠቀም የሚፈልጉ አካላት ማወቅ የሚገባቸው ነገር ኢትዮጵያ የራሷን ችግር በራሷ ለመፍታት የማታንስ መሆኗን ነው። ከሁሉም በላይ በቂ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዳለም በተለያዩ የምግብ ማደራጃ ማዕከላት ውስጥ የተከማቸውን ምግብና የአቅርቦት ሁኔታ በቅርበት ሆኖ በመረዳት የሰብዓዊ ድጋፉና አቅርቦቱ የተመጽዋችነት እሳቤን ታሪክ ያደረገ መሆኑን ልብ ሊሉ ይገባል። በመንግሥት የድጋፍ አሰጣጥ ላይም እምነት ሊያሳድሩ ይገባቸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 02/2013