በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አሊያም ሰብዓዊነት ተግባር ለምስጉን ስራችሁ፣ ለአዲስ ፈጠራችሁ፣ አሊያም ስለድንቅ ችሎታችሁ እናመሰግናለን፤ ጥሩ ሰርታችኋል፤ከጎበዞች መሀከል ተመርጣችኋል በሚል ግለሰቦች ሽልማት ይሸለማሉ።እውቅናም ይሰጣቸዋል።
ከታላቁ ኦስካር ሽልማት ከመሰጠቱ እንዲሁም አካዳሚ አዋርድ ከመካሄዱ አንድ ቀን በፊት የሚሰጥ አንድ ሽልማት ግን ከሌሎቹ ለየት ይላል።ራዚ የሚሰኘው ይህ የሽልማት አይነት የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1981 ጆን ዊልሰንና ሞ ምርፊ የተባሉ ግለሰቦች ሲሆን ስነስርዓቱ የሚካሄደው ደግሞ አሜሪካ ሎስአንጀለስ ውስጥ ነው።
በየዓመቱ በሚካሄደው በዚህ የሽልማት ስነስርዓት በዓመት ውስጥ ቀሽም ስራ የሰሩ ግለሰቦች አትችሉም፤ አትመጥኑም፤አሳፍራችሁናል፤የወረደ ተግባር ፈፅማችኋል፣ ሌላ ስራ ሞክሩ፤ ይቀራችኋል፤ ተብለው ይሸለሙበታል።
በዚህ ስነስርዓት እጩዎች ተዋዳድረው የበለጠ ቀሽም ስራ የሰራው አዳራሽ ተጠርቶ ይሸለማል። በተለይ በፊልሙ ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ቀሽም የፊልም ተዋናዮች፤ዳይሬክተሮች ውዳሴን ሳይሆን ትችትን በህዝብ ፊት ይወስዳሉ። ሰነፍ ናችሁ ተብለው ይጨበጨብላቸዋል።ስምንት ሚሊ ሜትር የሚረዝመውን ወርቅ ቅብ ሽልማት እየሳቁ ይረከባሉ።
በዚህ መድረክ በርካታ ስመ ጥር አርቲስቶች ቀሽም ተብለው መድረክ ላይ እየወጡ በህዝብ ፊት ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።በኮሜዲያኑ ቢል ኮዝቢ አሃዱ የተባለው ይህ ሽልማት በኋላም ቶም ክሩዝ፣ ቤን አፍሊክ፣ ሚል ጊብስን፣ ሃሌ ቤሪ ሳንድራ ብሎክ፣ ታይለር ፔሪ፣ የመሳሰሉ የፊልሙ ጠበብቶች ቅሽም መባላቸውን አመስግነው ተቀብለዋል።የአምናው የሽልማቱ አሸናፊ ሆኖ የተመረጠው ዳውየን ጆንሰንም «ባይ ዋች»bywatch በሚለው ፊልም ቀሽም ገፀ ባህሪን ተጫውተሃል ተበሎ ተመርጦ ሽልማቱን በጸጋ ተቀብሏል።
በአሁኑ ወቅት ሲ.ኤን.ኤንን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚያስተላልፉት ይህ የቀሽሞች ሽልማቱ ስነ ስርዓት ዘንድሮ ለ39 ጊዜ ይካሄዳል።መርሃ ግብሩም የፊታችን የካቲት 15 ቀነ ቀጠሮ ተይዞለታል።
በአገራችንም መሰል የሽልማት ስን ስርዓት ቢካሄድ ከእኔ በላይ ላሳር የሚሉ ካልሆኑም የሚቃወሙት የሚኖሩ አይመስለኝም። በእርግጥ ከመኮርኮም ማበረታታት ቀዳሚ ምርጫ ቢሆንም ቀሽም ሲገኝም መሸለም ትክክል ነው።ምክንያቱም ቀሽሞችንም እየወቀሱ ቁጥራቸውን መቀነስ ይቻላል። ቀሽም ነው ማለት ደግሞ ምንም አትችልም፤ዘላለም አትሰራም ማለት አይደለምና።
አዲስ ዘመን ጥር 28/2011
ታምራት ተስፋዬ