በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ መፍትሄ አማራጭ እርምጃዎች ተወስደዋል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በደርግ ዘመነ መንግሥት ነዋሪዎች በማህበር ተደራጅተው መኖሪያ ቤቶችን እንዲገነቡ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ጀምሮ መንግሥት በራሱ ወጪ የመኖሪያ ቤቶችን እያስገነባ ችግሩን ለመቅረፍ ጥረቶች ተደርገዋል።
ከዚህም ጎን ለጎንም ነዋሪዎች በራሳቸው አቅም መኖሪያ ቤቶችን እንዲገነቡ በአነስተኛ ዋጋ የግንባታ መሬት የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት ችግሩን ለመቅረፍ ተሞክሯል። ይህም ሆኖ ግን ወደ ከተማዋ የሚደረገው ፍልሰት በየጊዜው ከፍ እያለ ከመሄዱ ጋር በተያያዘ ችግሩን መቅረፍ ሳይቻል ቀርቷል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ችግሩ ከመፍትሄው በላይ ሆኖ ቆይቷል።
ይህንን ከፍ ያለ ማህበራዊ ችግር ለመቅረፍ የዛሬ 15 ዓመት ገደማ የጋራ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት ተግባራዊ መሆን መጀመሩ ይታወሳል። ሃሳቡ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የከተማዋን ቤት አልባ ነዋሪዎች ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ደግሞ ብዙዎችን የቤት ተስፈኛ ማድረጉ የሚጠበቅ ነበር።
ፕሮጀክቱ ለሕዝብ ይፋ ከሆነበት ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች በቤት ፈላጊነት ከመመዝገብ አንስቶ በተቀመጡ መመሪያዎች መሰረት በዝግ የባንክ አካውንት የሚጠበቅባቸውን ገንዘብ የቤት ባለቤት እሆናለሁ በሚል ከፍ ያለ ተስፋ ሰንቀው ከዕለት ጉሮሯቸው እየቀነሱ ሲቆጥቡ ቆይተዋል። አሁንም እየቆጠቡ ይገኛሉ።
ይሁንና ፕሮጀክቱን በበላይነት በሚመራው የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ውስጥ ከነበረው ዘርፈ ብዙ የአሠራር፣ የሥነምግባር እና የከፋ የሙስና ችግር የተነሳ ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ ብዙ ተስፋ ሰንቆ የተጀመረው ይህ ፕሮ ጀክት የነዋሪዎች ቅሬታና ም ሬት ማ ዕከል ሆኗል።
በአንድ በኩል በግንባታዎች ወቅት በተጠና በተደራጀ መልኩ በተካሄዱ ዘረፋዎች ግንባታዎቹ በተቀመጠላቸው ጥራት መስፈርታቸውን አሟልተው አለመገንባታቸው፤ በተቀመጠ የአፈጻጸም መመሪያ መሠረትም ቤቶች ለባለ ዕጣዎች አለመተላለፋቸው ዕድለኞችን ለተጨማሪ ወጪ የዳረጉ መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።
ከዚህም ባለፈ እነዚሁኑ ከፍ ያለ የጥራት ችግር ያለባቸውን እና በብዙ ጣር «የተጠናቀቁ» የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ከተቀመጠው መመሪያ ውጪ ለማይገባቸው ግለሰቦች ከመስጠት ባለፈ የፖለቲካ ቁማር መቆመሪያ እንዲሆኑ ተደርገዋል።
በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የቆየውን ህገወጥነት መልክ ለማስያዝ የሄደበት መንገድ ይህንን እውነታ ከአሉባልታነት ወደ ተጨባጭ እውነታነት አውርዶታል፤ ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት ትልቅ አቅም እንደሚሆንም ታምኗል።
አስተዳደሩ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በኩል በጋራ መኖሪያ እና በቀበሌ ቤቶች ላይ ያስጠናው ጥናትና፣ የጥናቱ ግኝት በርግጥ በአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን የነበረውን የከፋ ችግር አደባባይ ማውጣት ያስቻለ ነው። ጥናቱ የፋይናንስ ጉዳዮችን ታሳቢ ያደረገ ቢሆን ደግሞ ችግሩ ምን ያህል የከፋ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አይከብድም።
የጥናት ግኝቶች በኮርፖሬሽኑ ህገወጥነት የቱን ያህል ባህል ሆኖ እንደነበር ብቻ ሳይሆን ህገወጥነት የቱን ያህል ሥርዓት ሆኖ እንደቆየ፤ ከኮርፖሬሽኑ ባለፈ የፖለቲካ ሥርዓቱ ለተጠያቂነት ምንም ያህል ቦታ እና ደንታ እንዳልነበረው ከአሉባለልታ ባለፈ በተጨባጭ ያሳየ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የችግሩን ደረጃ በተጨባጭ ለማየት፣ ከዚህም በላይ ጥናቱን በገለልተኛ አካል በማስጠናት እውነታውን አደባባይ ያወጣበት መንገድና ቁርጠኝነት የሚበረታታ ነው። የተጀመረው ለውጥ የበለጠ በሕዝብ ዘንድ ተአማኒነት እንዲኖረው ለማድረግ የሚኖረው አስተዋጽኦም ከፍ ያለ ነውና ምስጋና የሚቸረው ነው።
ይሁንና የጥናቱ ዓላማ ችግሩን በማሳየት ላይ ብቻ ያተኮረ እንደማይሆን ይገመታል። ከዚህ አንጻር መስተዳድሩ ከዚህ ሁሉ ጥፋት በስተጀርባ ያሉ አመራሮችን ባለሙያዎችንና ከጥፋቱ ጋር በአንድም ይሁን በሌላ እጃቸው ያለበትን ግለሰቦችን ለፍርድ በማቅረብ ተጠያቂነትን አስተማሪ በሆነ መልኩ ማስፈን ይጠበቅበታል። ይህን ማድረግ ሲችልም ነው ኃላፊነቱን ተወጥቷል የሚባለውና በቀጣይም በሕዝብ ዘንድ አመኔታ የሚኖረው!
አዲስ ዘመን ጥር 30/2013