አስናቀ ፀጋዬ
እረፍት የሚባል ነገር አያውቁም። ዘወትር ማለዳ ተነስተው በሥራ ገበታቸው ላይ በመገኘት ሙሉ ጊዜያቸውን በሥራቸው ቀጥረው ከሚያሰሯቸው ሠራተኞቻቸው ጋር በሥራ ያሳልፋሉ። ያሰቡትን ሳይፈፅሙ ከዋሉም እንቅልፍ አይተኙም።
የተማሩት ትምህርትም አሁን ካሉበት የሙያ ዘርፍ ጋር ፈፅሞ የሚገናኝ ባይሆንም በአንድ ወቅት የተመለከቱት ነገር ወደዚህ ሞያ ገብተው እንዲሰሩ ገፋፍቷቸዋል- የሂልማር ጋርመንት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሰላማዊት ሆምና።
ወይዘሮ ሰላማዊት ውልደትና እድገታቸው በኦሮሚያ ክልል ሀገረማርያም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው ሀገረማርያም ተብሎ በሚጠራ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ያቤሎ ከተማ በያቤሎ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በ1992 ዓ.ም አምቦ ዩኒቨርሲቲ ገብተው የከፍተኛ ትምህርታቸውን በጄነራል አግሪካልቸር ትምህርት ዘርፍ ተከታትለው በ1994 ዓ.ም በዲፕሎም ተመርቀዋል።
ከምርቃት በኋላም ክርስቲያን ችልድረን ፈንድ በተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ በዴቨሎፕመንት ዎርከር የሞያ መስክ ተቀጥረው ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ሰርተዋል። የአግሪካልቸር ሞያን ፈልገው ያልተማሩ በመሆናቸውና የሞያውን ዘርፍ መቀየር በመፈለጋቸው እንደገና ትሮፒካል ኮሌጅ ኦፍ ሜዲስን በተሰኘ የግል ተቋም ገብተው በፋርማሲ ሞያ በዲፕሎም በ1997 ዓ.ም ተመርቀዋል። እንደገና በ1998 ዓ.ም አምስት ኪሎ ከሚገኘው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ትምህርት ቤት የቢ ኤስ ሲ ዲግሪያቸውን በፋርማሲ አግኝተዋል።
ወይዘሮ ሰላማዊት በተማሩበት የፋርማሲ ሞያ በግል ፋርማሲዎች ለሁለት ዓመት እንዲሁም በመንግሥት ፋርማሲዎች አንድ ዓመት ከስድስት ወር ከሰሩ በኋላ የራሳቸውን መድኃኒት ቤት አዲስ አበባ ላይ ከፍተው መስራት ጀመሩ። ሆኖም በፋርማሲው ሥራ ብቻ እርካታ ባለማግኘታቸው ተጨማሪ ሥራ መስራት እንዳለባቸው አእምሯቸው ዘወትር ያሰላስል ጀመር።
በአንድ ወቅትም ከጓደኛቸው ጋር ሆነው በመንገድ ሲሄዱ ቃሊቲ አካባቢ የልብስ ስፌት ፋብሪካ ይመለከታሉ። ልብስ ስፌት ፋብሪካው በያዛቸው የሠራተኞች ብዛትና አጠቃላይ ባለው አሠራርም ይደመማሉ። ይህንንም ተከትሎ የራሳቸውን የልብስ ስፌት ፋብሪካ የማቋቋም ፍላጎት በውስጣቸው አደረ።
በወቅቱ የልብስ ስፌት ፋብሪካ ኢንቨስትመንት በርካታ ገንዘብ የሚጠይቅ መስሏቸው የነበር ቢሆንም ሥራውን ለመጀመር የሚያስፈልገው አነስተኛ መነሻ ካፒታል ከ2 ሚሊዮን ብር የማይበልጥ መሆኑን ቢዝነሱን ጠንቅቀው ከሚያውቁ ሰዎች ጠይቀው ተረዱ። ቀደም ሲል ይሰሩት የነበረው የፋርማሲ ሥራ ትርፍ እንዳለው ቢያውቁም በዚህ የልብስ ስፌት ሥራ ሦስት ሰዎችን ብቻ ይዘው እኩል በሆነ ዋጋ በርካታ ሥራዎችን መስራት እንደሚችሉም ተገነዘቡ።
በዚህ አነስተኛ መነሻ ካፒታል ወደሥራው መግባት የሚያስችላቸው አቅም እንዳላቸው ስለተረዱም ወደ ልብስ ስፌት ሥራው ለመግባት ወሰኑ። የልብስ ስፌት ድርጅቱን ለማቋቋም ከወሰኑ በኋላም በልብስ ስፌት ዙሪያ እውቀቱ እንዲኖራቸው በማሰብ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኝ ብርሃን ፋሽን በተሰኘ የልብስ ስፌት ትምህርት ቤት ገብተው የልብስ ስፌት ኮርሶችን ወሰዱ። እግረመንገዳቸውንም የልብ ስፌት ቢዝነሱን ማጥናት ቀጠሉ።
ከዚያም በ2011 ዓ.ም ሁለት የልብስ መስፊያ ማሽኖችን በራሳቸው ገዝተውና አምስት ሠራተኞችን በሥራቸው ይዘው 100 ሺ ብር በማይበልጥ ካፒታል ሂልማር ጋርመንት የተሰኘ የልብስ ስፌት ድርጅት አቋቋሙ። ገርጂ መብራት ኃይል ኮንዶሚኒየም የንግድ ቤት ውስጥ ተከራይተውም የልብስ ስፌት ሥራውን ጀመሩ። በጊዜው ወደ ልብስ ስፌት ሥራው ሲገቡ ገና አዲስ ከመሆናቸው አኳያም አጠቃላይ የልብስ ስፌት ቴክኒካል ሥራውን የሚያግዝ ከፍተኛ ባለሞያም ቀጠሩ።
በባለሞያው ታግዘውም የልብስ ገበያ ፍላጎት የት አካባቢ እንዳለ መለየት ቻሉ። በተለይ ደግሞ ከመርካቶ ነጋዴዎች ጋር በመነጋገር እነርሱ በሚያመጧቸው ሳምፕሎች መሠረት ልብሶችን በመስፋት ለገበያ ማቅረብ ጀመሩ። በጊዜው ለመርካቶ ነጋዴዎቹ የሚያቀርቧቸው የልብስ ስፌት ምርቶችም በአብዛኛው የልጆች ልብሶችና በመጠኑ ደግሞ የአዋቂ ጃኬቶችና ቱታዎች ነበሩ።
ለመርካቶ ነጋዴዎች የሚያቀርቧቸውን ልብሶች በኤግዚቢሽኖች ላይ ማቅረብ ሲጀምሩ ደግሞ ከሸማቹ በኩል የነበረው ምላሽ አርኪ ሆኖ አገኙት። ‹‹ሌሎች ተጨማሪ የሕፃናት ልብሶች የላችሁም ወይ?›› የሚሉ ጥያቄዎችም ከሸማቾች በኩል ይቀርቡላቸው ጀመር። ይህም በአነስተኛ ካፒታል በትንሹ የጀመሩትን የልብስ ስፌት ሥራ ገበያ ለማወቅና መስተካከል የሚገባቸውን ነገሮች ለመረዳት አስቻላቸው። በሂደት ገበያውን እየለመዱት ሲመጡም ማሽኖችን እየጨመሩ ሥራውን ማስፋት ቀጠሉ።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ማሽኖችን በሊዝ ፋይናንሲንግ እንደሚያቀርብ ሲረዱ ደግሞ ሃያ ከመቶውን እርሳቸው ሰማንያ ከመቶውን ደግሞ ባንኩ እንደሚሸፍን ተስማምተው ተጨማሪ የልብስ ስፌት ማሽኖችን በመጨመር የተለያዩ የአዋቂና የሕፃናት ልብሶችን ሰፍተው ለገበያ ማቅረብ ቻሉ። በጊዜው ከልብስ ስፌት ድርጅቱ የሚያገኙት ትርፍ ከሚያወጡት ወጪ ጋር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ከፋርማሲያቸው በሚያገኙት ገቢ ድርጅቱን ደገፉ። ዋነኛ ትኩረታቸውንም ከትርፍ ይልቅ ድርጅታቸውን ማስፋት ላይ አደረጉ።
በአሁኑ ወቅት ሂልማር ጋርመንት 37 ቋሚ ሠራተኞችንና 53 የልብስ ስፌት ማሽኖችን በመያዝ ልዩ ልዩ የአዋቂና የልጆች ልብስ ስፌት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። የተመዘገበ ካፒታሉም 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ደርሷል። ከሚያመርታቸው ምርቶች ውስጥም የልጆች ፒጃማዎች፣ ቁምጣዎች፣ ቲርሸቶች፣ ሱሪዎች፣ ሸሚዞች፣ ከትምህርት ቤት መልስ የሚለበሱ ልብሶችና የተማሪ የደንብ ልብሶች ይገኙበታል።
የአዋቂ ሙሉ ልብስ፣ የመምህራን፣ የህክምና ባለሞያዎችንና የጥበቃ ሠራተኞች የደንብ ልብሶችንና ቱታዎችንም አምርቶ ለገበያ ያቀርባል። የምርት ጥሬ ዕቃዎችንም ከአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክና ከመርካቶ አከፋፋዮች ይረከባል። ኮፍያዎችንም በውጭ ሰዎች ያሰራል። የምርቶቹን ጥራት ለመቆጣጠርም የራሱን የጥራት ቁጥጥር ባለሞያ ቀጥሯል።
ድርጅቱ ለልብስ ስፌት ሥራው የሚያገለግሉ አብዛኛዎቹ ማሽኖች ያሉት ሲሆን ለዚሁ ሥራ የሚያግዙ ተጨማሪ ማሽኖችን በሊዝ ፋይናንሲንግ ከልማት ባንክ ለማግኘት ጥያቄ አቅርቧል። ጥያቄው ምላሽ የሚያገኝ ከሆነም ማሽኖቹን በእጅጉ አስገብቶ የልብስ ስፌት ሥራውን በስፋትና በጥራት የማከናወን ፍላጎት አለው። በአሁኑ ወቅት ያሉት አጠቃላይ የልብስ ስፌት ማሽኖችም የ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ዋጋ አላቸው።
የኮሮና ወረርሽኝ ያሳደረው ተፅእኖ እንዳለ ሆኖ ከተለያዩ የልብስ ስፌት ውጤቶች ድርጅቱ ከተመሰረተ ወዲህ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ የ2 ሚሊዮን 28 ሺ ብር ሽያጭ አካሂዷል። በአሁኑ ዓመት ከመስከረም ወር ጀምሮም ድርጅቱ የኮሮና ወረርሽኝ ካሳደረበት አሉታዊ ተፅእኖ እያገገመ መጥቶ አራት የማከፋፈያ ሱቆቹን በአዲስ አበባ ከፍቶ የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። ተከራይቶ ለሚያመርትበት ሕንፃም በየወሩ 80 ሺ ብር ወጪ ያደርጋል።
ሂልማር ጋርመንት በልብስ ስፌት ሥራ ሁለት ዓመት ያስቆጠረ ገና ታዳጊ ድርጅት መሆኑን የሚጠቅሱት ወይዘሮ ሰላማዊት በቀጣይ በርካታ እቅዶች እንዳሉት ይናገራሉ። በተለይ ደግሞ የልብስ ስፌት ማሽኖችን በመጨመርና የሠራተኞችንም ቁጥር በማሳደግ ትልልቅ የልብስ ስፌት ኩባንያዎች የሚሰሯቸውን ሥራዎች ሁሉንም ዓይነት የልብስ ስፌት ሥራዎች በስፋት፣ በጥራት፣ በብዛትና በዘመናዊ መንገድ የመስራት እቅድ እንዳለው ያብራራሉ።
በሂደትም ወደ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪው በመግባት አሁን ላይ ከውጭ በግዢ የሚጠቀምባቸውን ጥሬ ዕቃዎች በራሱ አምርቶ የመጠቀም የረጅም ጊዜ ውጥን እንዳለውም ይገልፃሉ። ትልቁ ችግሩ ቦታ ከመሆኑ አኳያም የራሱን ቦታ ማግኘትና በራሱ ቦታ ላይ የመስራት ፍላጎት እንዳለውም ይጠቅሳሉ። ለዚህም ለአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ቢሮ ጥያቄ ማቅረቡንና ይህ ደግሞ ረጅም ጊዜ የሚወስድ ከመሆኑ አኳያ የማምረቻ ሼድ እንዲሰጠው ክፍለከተማውን መጠየቁንም ይገልፃሉ።
ከዚህ ባሻገር ድርጅቱ የሚያመርታቸውን ምርቶች ወደ ውጪ የመላክ እቅድም እንዳለው ወይዘሮ ሰላማዊት ተናግረው፤ ለዚህም ከወዲሁ የተለያዩ ሂደቶች መጀመራቸውንም ይጠቁማሉ። ምርቶቹን ወደ አፍሪካ ሀገራት ለመላክም በተለይ ከሱዳንና ኡጋንዳ ጋር ግንኙነቶችን ለመፍጠር ሙከራ እየተደረገ እንደሚገኝም ይጠቅሳሉ።
‹‹የልብስ ስፌት ዘርፉ በሚገባ ከተሰራበት ሰፊ የሥራ ዕድልና ከፍተኛ ገቢ የሚያሰገባ ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ሰላማዊት ከዚህ አኳያ ዘርፉ የሚጠበቅበትን ያህል አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ከመንግሥት በኩል በቂ ድጋፍና ማበረታቻ ሊደረገለት እንደሚገባ ይጠቁማሉ። በተለይ ደግሞ በዘርፉ ገብተው መስራት ለሚፈልጉ አልሚዎች ከፋይናንስ ጀምሮ የመስሪያ ቦታዎችን በማመቻቸት በስፋት እንዲሰሩ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።
መንግሥት ብቻውን ይህን ማድረግ የማይችል ከመሆኑ አንፃርም የግሉ ዘርፍና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም ያሳስባሉ። ዘርፉን መቀላቀል ለሚፈልጉ አዳዲስ ሰዎችም የሊዝ ፋይናንስ ቢደረግና ለሚወስዱት ብድርም የወለድ መጠኑ ቢስተካከል ዘርፉን ይበልጥ ማሳደግና ማስፋት እንደሚቻልና በስሩ የሚይዘውን የሠራተኞች ቁጥር መጨመር እንደሚቻል ይጠቁማሉ።
ዘርፉ የጥሬ ዕቃዎች እጥረት የሚታይበት መሆኑንም ጠቅሰው፤ ዋጋውም በየዕለቱ እያሻቀበ በመሄዱ ጥሬ ዕቃው በሀገር ውስጥ በስፋት የሚመረትበትንና በተመጣጣኝ ዋጋ ለልብስ ስፌት አምራቾች የሚቀርብበት ሁኔታ ሊመቻች እንደሚገባም ያመለክታሉ።
‹‹በዚህ የልብስ ስፌት ሥራ ውጤታማ ነኝ›› የሚሉት ወይዘሮ ሰላማዊት 37 ቋሚ ሠራተኞችን በሥራቸው ቀጥረው ማሰራታቸው የውጤታቸው አንዱ ማሳያ መሆኑን ይናገራሉ። ይህም ለሀገራቸው የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ጠቋሚና የሞራል እርካታም ጭምር ያገኙበት ስለመሆኑ ይመሰክራሉ።
ድርጅታቸው አዲስ ከመሆኑ አኳያም ትርፍ በማምጣት ረገድ ገና ውጤት ያመጣ ባይሆንም እዚህ ውጤት ላይ ለመድረስ እየተንደረደረ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። በሂደት ግን የድርጅታቸውን አቅም በማሳደግና ምርቱን በመጨመር በዘርፉ ለሀገራቸው ትልቅ አስተዋፅኦ ለማበርከት ሌት ተቀን እንደሚሰሩም ይጠቁማሉ።
በዚህ የልብስ ስፌት ዘርፍ የመስራት ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ገብተው እንዲሰሩም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ሌሎችም ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ዘርፉን ተቀላቅለው እንዲሰሩና ትርፋማም እንዲሆኑ ተስፋ ሳይቆርጡ ጠንክረው እንዲሰሩ ይመክራሉ። ሥራው በርካታ ውጣውረዶች ያሉበት ከመሆኑ አኳያም ውጣውረዶቹ ወደ ኋላ ሳይጎትቷቸው በጥንካሬ ወደፊት መገስገስ እንዳለባቸውም ይጠቁማሉ። ከትርፍ ባሻገር ለሀገራቸው የተወሰነ አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለባቸው አምነው መስራት እንዳለባቸውም ያስገነዝባሉ።
ወይዘሮ ሰላማዊት የልብስ ስፌቱን ዘርፍ በትንሽ ካፒታል ተቀላቅለው ከፍ ወዳለው ደረጃ ለመድረስ እያደረጉ ያሉትን ጥረት እያደነቅን አሁን ካላቸው የሥራ ትጋት አኳያ በቀጣይ በዘርፉ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚደርሱ እንገምታለን። በተመሳሳይ ሌሎችም የእርሳቸውን ትጋትና ሥራ ወዳድነት እንደአርአያ ወስደው በዚህ ዘርፍ ተቀላቅለው ቢሰሩ ከራሳቸው አልፈው ሀገራቸውን የሚጠቅሙበት ዕድል እንዳለም ለመጠቆም እንወዳለን። ሰላም!!
አዲስ ዘመን ጥር 29/2013