በጋምቤላ ክልል አኙዋክ ብሄረሰብ ዞን የምትገኘው ዲማ ወረዳ በወርቅ ሃብቷ ትታወቃለች። ወረዳዋንም በደቡብ ምስራቅ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ በደቡብ ምእራብ የአኮቦ ወንዝ፣ በሰሜን የጎግ ወረዳ እንዲሁም በሰሜን ምስራቅ የመዠንግር ዞን ያዋስኗታል።
ወረዳዋ በክልሉ በማህበር ተደራጅተው በባህላዊ መንገድና በልዩ አነስተኛ ደረጃ ወርቅ በማምረት ለብሄራዊ ባንክ ከሚያቀርቡ ውስጥ አንዷ ናት።በዚሁ በጀት አመት ክልሉ ለብሄራዊ ባንክ ላቀረበው ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅና እንደ ሀገር ለተገኘው ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የወረዳዋ አስተዋፅኦ የጎላ ነው።
በወረዳዋ ወርቅን በልዩ አነስተኛ ደረጃ ከሚያመርቱት ውስጥ አንዱ የቶር ኡዳንግ ልዩ አነስተኛ ወርቅ አምራች ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ነው።አቶ ቶር ኡዳንግ ደግሞ የማህበሩ መስራችና ስራ አስኪያጅ ናቸው። በማህበራቸው በኩል ለብሄራዊ ባንክ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ በማቅረባቸውም በቅርቡ የመአድንና ነዳጅ ሚንስቴት በሸራተን ሆቴል ባዘጋጀው የእውቅናና ሽልማት መረሀግብር ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል።
አቶ ቶር ኡዳንግ ትውልደቸውም ሆነ እድገታቸውም በዲማ ወረዳ ነው። ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ወርቅ ሲመረት እያዩ ነው ያደጉት። ትምህርታቸውንም በዛው ጋምቤላ ተከታትለዋል። ነፍስ እያወቁ ሲመጡ እንደብዙዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች በባህላዊ መንገድ ወርቅ ለማውጣት ፍላጎቱ አልነበራቸውም። ከዚህ ይልቅ በአብዛኛው የሰሩት ስራ ከሆቴል ጋር በተያያዘ ነው። የኋላ ኋላ ግን ወደ ወርቅ ማምረት ስራ መግባታቸው ግን አልቀረም።
ከጥቂት አመታት በፊት መጀመሪያ ከሚኖሩበት ቀበሌ የድጋፍ ደብዳቤ አፃፉ። በመቀጠልም ባለሙያ ወደ ዲማ ወረዳ በመምጣት የወርቅ ማውጫ ቦታ ለካላቸው። እንደገና ወረዳው ሌላ የድጋፍ ደብዳቤ ለክልሉ የማእድን ቢሮ ፃፈላቸው። የክልሉ የማእድን ቢሮም ፍቃድ ሰጥቷቸው በሶስት ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ወደ አንደኛ ደረጃ የወርቅ ማምረት ስራ ተሰማሩ ።በዚህ ደረጃም ለጥቂት አመታት ሰሩ።
በሂደትም ከወርቅ ምርት የተሻለ ገቢ ለማግኘት በማሰብ መቆፈሪያ ስካቫተሮችንና ማጠቢያ ማሽኖችን በመከራየት፣ ትልቅ ጄኔሬተር፣ የውሃ ፓምፕና የኤሌክትሪክ መብራት በማሟላት ፍቃድ አግኝተው በ2012 ዓ.ም ወደ ልዩ አነስተኛ ወርቅ አምራችነት ተሸጋገሩ።
በስራቸውም ማሽን ኦፕሬተሮችን ጨምሮ ሃያ የሚሆኑ በጉልበትና በሌሎች የስራ ዘርፎች የሚሰሩ ሰራተኞችን ቀጥረው ማሰራት ጀመሩ ። ወርቅ ማምረት በጀመሩ የመጀመሪያው አመትም በአስር ወራት ውስጥ ብቻ ለብሄራዊ ባንክ 50 ኪሎ ግራም ወርቅ ማቅረብ ቻሉ።ይህም በፌዴራል ማአድንና ነዳጅ ሚንስቴር አማካኝነት ለሽልማት አበቃቸው።
በአሁኑ ግዜ ማህበራቸው በተፈቀደለት ቦታ ላይ ጉድጓዶችን በጉልበት ሰራተኞችና በተካራያቸው ማሽኖች እያስቆፈረና አፈሩን በማሽን እያሳጠበ ወርቅ እያመረተ ይገኛል።ወርቅ የማምረት አቅሙም ከግዜ ወደግዜ እየተሻሻለ መጥቷል። ቀጥሮ ለሚያሰራቸው የጉልበት ሰራተኞችም የላባቸውን ያህል በቂ ክፍያ ይከፍላል።በእየለቱ የሚያገኘውን ወርቅም በተከታታይ ለብሄራዊ ባንክ ያቀርባል። በእለቱ የወርቅ ገበያ ዋጋ መሰረትም ባቀረበው የወርቅ መጠን ልክ ሂሳቡን ይቀበላል።
ማህበሩ ወርቅ የሚያመርተው ቀድመው በባህላዊ መንገድ ወርቅ ይመረትባቸው በነበሩ ቦታዎች ውስጥ በመግባት ነው።ወርቅ ይገኝባቸዋል ተብለው በሚታሰቡ በሌሎች አካባቢዎች ላይ በቂ ጥናት ባለመደረጉም እስካሁን ድረስ አልገባም።በእነዚህ ቦታዎች ላይ መንግስት ጥናት የሚያካሂድ ከሆነና በልዩ አነስተኛ ደረጃ ወርቅ ለሚያመርቱ ማህበራት ፍቃድ የሚሰጥ ከሆነ ማህበሩ ወደዚህ ገብቶ የመስራት እቅድ አለው።
በሶስት ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል የተጀመረው የማህበሩ ወርቅ ማምረት ሥራ ዛሬ ላይ እያደገ መጥቷል።ወርቅን ለብሄራዊ ባንክ በከፍተኛ ደረጃ እያቀረቡ ከሚገኙ ልዩ አነስተኛ ወርቅ አምራች ማህበራት መካከልም አንዱ ለመሆን በቅቷል።
የማህበሩ ካፒታል እያደገ በመምጣቱም አቶ ቶር ከወርቅ ማምረት ስራው ጎን ለጎን በዛው አካባቢ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴልና የእንግዳ ማረፊያ ግንባታ እያከናወኑ ይገኛሉ።የማህበሩን ሙሉ ካፒታልም ወደዚህ ግንባታ አዙረዋል።
እስካሁን ድረስም ለሆቴሉ ግንባታ አስር ሚሊዮን ብር ወጪ አድርገዋል።በቀጣይ የሆቴሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለበርካታ የአካባቢው ሰዎች የስራ እድል ከመፈጠር በዘለለ በአካባቢው ከወርቅ ጋር በተገናኘና በሌሎች የተለያዩ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ሰዎች እንደማረፊያ ሆኖ እንደሚያገለግል ይጠበቃል ።
ቀደም ሲልም በሆቴል ስራ ውስጥ እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ ቶር ዛሬ ላይ ወደዚሁ የሆቴል ኢንቨስትመንት የገቡት ከዚህ የሆቴል ስራ ጋር በተገናኘ ረጅም ግዜ ስለቆዩና በዚሁ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎቱ ስላደረባቸው መሆኑን ይናገራሉ።ገንዘብ በመጣ ቁጥር ሀሳቦችም አብረው የሚመጡ በመሆናቸው በወርቅ ማምረት ስራ ባገኙት ገቢ ወደ ሆቴል ኢንቨስትመንት እንደገቡም ይገልፃሉ ።
በቀጣይም አቶ ቶር የወርቅ ማምረት ስራውን በዘመናዊ መልኩ ከማከናወን በዘለለ በአስመጪና ላኪነት የስራ ዘርፍ ላይ ገብተው የመስራት እቅድ አላቸው።የበቆሎ ማቀነባበሪያ ፋብሪካም የማቋቋም ሃሳብ ያላቸው ሲሆን ለዚህም ገቢያቸውን ለማሳደግ ከወዲሁ በርትተው እየሰሩ እንደሚገኙ ይናገራሉ።
በሂደት ደግሞ ገቢያቸውን በማሳደግ በአዲስ አበባ ከተማ መዋእለ ነዋያቸውን በማፍስስ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ውስጥ ገብተው የመስራት ውጥን እንዳላቸውም ይጠቁማሉ።በቅድሚያ ግን በአሁኑ ግዜ በአካባቢያቸው የጀመሯቸውን ስራዎች በተለይ ደግሞ የሆቴል ግንባታቸው ማጠናቀቅ እንደሚፈልጉ ይገልፃሉ።
ማህበሩ በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው ወርቅ እያመረተ የሚገኘው ማሽን በመከራየት እንደሆነ የሚገልፁት አቶ ቶር፣ ይሁንና ወርቅ የማምረት ስራው ተጨማሪ ውሃና የውሃ ፓምፕ እንዲሁም የማጠቢያና መቆፈሪያ ማሽኖችን ጭምር የሚጠይቅ በመሆኑ እነዚህን ለማሟላት በመንግስት በኩል የፋይናነንስ ድጋፍ በተለይ ደግሞ ብድር እንደሚያስፈልግም ያመላክታሉ።
ማህበሩ በተለይ የማሽነሪ ድጋፍ ከመንግስት ቢያገኝ ወርቅን በዘመናዊ መንገድ አምርቶና መጠኑንም ጨምሮ ለብሄራዊ ባንክ በማቅረብ ሀገሪቱ የውጪ ምንዛሬ እንድታገኝ የራሱን አስታዋፅኦ እንደሚያደርግም ይጠቁማሉ።
በ2014 ዓ.ም ከዚህ ቀደም በአስር ወር ብቻ ካቀረበው 50 ኪሎግራም ወርቅ በላይ ለብሄራዊ ባንክ የማቅረብ እቅድ እንዳለውም የሚገልፁት አቶ ቶር፣ ይሁንና የወርቅ ምርት መጠን ከአመት አመት የሚለዋወጥ በመሆኑ በአመት ለብሄራዊ ባንክ የሚያቀርበው የወርቅ መጠን ከ50 ኪሎግራም ሊያንስ ወይም ከፍ ሊል እንደሚችልም ይጠቁማሉ።
ወደወርቅ ማምረት ሥራ ከገቡ ጥቂት አመታት እንደሆናቸው የሚናገሩት አቶ ቶር እስካሁን ባለው ሂደት ከስራቸው ለበርካቶች የስራ አስድል በመፍጠር፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ በማቅረብ ሀገሪቱ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እንድታገኝ በማድረግና የራሳቸውንም ገቢ በማሳደግ ረገድ ውጤታማ ስለመሆናቸውም ይመሰክራሉ።በተለይ ደግሞ ከዚህ በፊት በሆቴል ስራ ውስጥ መስራታቸው ከዛም በኋላ ወደ ወርቅ ማምረት ስራ ገብተው የተሻለ ገቢ በማግኘታቸው ወደ ሆቴል ኢንቨስትመንት ለመሸጋገር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳደረገላቸውም ይጠቅሳሉ።
እንደ አቶ ቶር ገለጻ፣ በወርቅ ማምረት ስራ ጨምሮ በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች ውስጥ ገብተው ለመስራትና ውጤታማ ለመሆን እቅድ ያስፈልጋል።እቅዱን ለማሳካት ሌት ተቀን ጠንክሮ መስራት የግድ ይላል።በተለይ ደግሞ ወጣቶች ገና በለጋ እድሜያቸው ተሯሩጠው መስራት ይኖርባቸዋል።ይህም በመጦሪያ እድሚያቸው ያለስጋት ሊኖሩ የሚችሉበትን መንገድ ይቀይሳል።በሞራልና በተነሳሽነት የሚሰሩ ከሆነ ደግሞ ከራሳቸው አልፈው ሀገርን መለወጥ ይቻላቸዋል።
በአሁን ወቅት ወጣቶች ወደ ስራ ያለመግባትና የመዘናጋት ባህሪ እንደሚታይባቸውም የሚጠቆሙት አቶ ቶር፣ብዙዎቹም ለሱስ ተገዢ በመሆናቸው ከዚህ መጥፎ ነገር በመውጣት ስራ ላይ ብቻ ማተኮር እንደሚኖርባቸውም ያሳስባሉ።በተናጥል መስራት እንኳን ባይችሉ በማህበር ተደራጅተው የሚሰሩበትን መንገድ መፈለግ እንደሚኖርባቸውም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
በተለይ በወርቅ ማምረት ስራ ለተሰማሩ ወጣቶች የግላቸው ጥረት ብቻውን በቂ ባለመሆኑ በመንግስት በኩል ለወጣቶቹ ብድር ቢመቻችላቸው ተገቢ መሆኑንም ያመለክታሉ።ወርቅ ካመረቱ በኋላም ወደ ብሄራዊ ባንክ እንዲያቀርቡ ሁኔታዎች ቢመቻቸቹ ተገቢውን የወርቅ መጠን ከማግኘት በዘለለ ሀገሪቷ ከምርቱ የምታገኘውን የውጪ ምንዛሬ ማሳደግ እንደሚቻልም ይገልፃሉ።
ከዚህ በተረፈ እርሳቸው በሚገኙበት የዲማ ወረዳ የመሰረተ ልማት ችግር በተለይ የመንገድ አቅርቦት ችግር እንደሌለና የፋይናንስ ድጋፍ ከተገኘ ወጣቶቹ በአካባቢው ላይ ተደራጅተው በበቂ ሁኔታ ወርቅ ማምረት እንደሚችሉም ይጠቁማሉ።ይህ ሲባል ግን የመንገድ መሰረተ ልማቱ በቂ ነው ማለት ሰላልሆነ ተጨማሪ የመንገድ መሰረተ ልማቶች በመንግስት በኩል መከናወን እንደሚገባቸውም ያመለክታሉ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2013