ባሕልን ከማስተዋወቅ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እየጎለበተ የመጣው ኢሬቻ

በኦሮሞ ብሔረሰብ ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል እሬቻ አንዱ ነው። የክረምት ወቅት አልፎ የበጋው ወቅት ሲገባ በአዲስ ዓመት መባቻ መስከረም ወር ላይ ይከበራል። እሬቻ በኦሮሞ ብሔረሰብ ዘንድ በድምቀት የሚከበር በዓል ሲሆን፤ ብሔረሰቡ ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበት ታላቅ ባሕላዊ እሴቱ ነው። በዚህም በዓል ብሔረሰቡ ፈጣሪውን ያመሰግንበታል፤ ዘመኑ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት እንዲሆን ይመኝበታል።

ከዓመት ዓመት በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ የመጣው የእሬቻ በዓል ዘንድሮም የፊታችን ቅዳሜና እሁድ በድምቀት ይከበራል። የ2017 ዓ.ም የእሬቻ በዓልን በደማቅ ሁኔታ ለማክበርም የተለያዩ ዝግጅቶች ተደርገዋል። ከዝግጅቶቹ መካከልም ‹‹እሬቻ ኤክስፖ 2017›› አንዱ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው ይህ ታላቅ ዓመታዊ ዓውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም የተከፈተ ሲሆን ለሰባት ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይም የኦሮሚያ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።

የኦሮሚያ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ከሀገሬ ኢቨንት እና ፕሮሞሽን ጋር ያዘጋጀው ይህ ኢግዚቢሽንና ባዛር የኦሮሞ ብሔረሰብን ባሕል ከማስተዋወቅ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ አበርክቶው የጎላ ስለመሆኑም የኤግዚቢሽኑ ተሳታፊዎችም ገልጸዋል። ተሳታፊዎቹ ድርጅቶች እንዲሁም ግለሰቦች የኦሮሞ ባሕልን ይገልጻሉ ያሏቸውን ባሕላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች እንዲሁም ባሕላዊ ምግቦችንና መጠጦችንም ይዘው ቀርበዋል።

የዝግጅት ክፍላችንም ኤግዚቢሽኑን በጎበኘበት ወቅት የኦሮሞ ብሔረሰብ ባሕላዊ ምግቦችና መጠጦችን ጨምሮ የተለያዩ አልባሳት፣ ጌጣጌጦችንና ቁሳቁስን በስፋት ተመልክቷል። የኦሮሞ ባሕላዊ የምግብ ዓይነቶችን እያስተዋወቁና እየሸጡ ካገኘናቸው መካከል ነጋ የኦሮሞ ባሕላዊ ምግብ አንዱ ነው። ድርጅቱ ባሕላዊ ምግቦችን እያዘጋጀ ለገበያ የሚያቀርበው በሁለት እህትማማቾች አማካኝነት መሆኑን ወይዘሮ ፀሐይ ለታ ትገልጻለች። ወይዘሮ ፀሐይ ከታናሽ እህቷ ጋር በመሆን በተለይ ተወልደው ያደጉበትን የወለጋ አካባቢ ባሕላዊ ምግቦችን እያዘጋጁ ለገበያ ያቀርባሉ፡፡

ወይዘሮ ፀሐይ እንዳብራራችው፤ እሷና እህቷ የሚያዘጋጇቸውንና የወለጋ አካባቢ መገለጫ ከሆኑት ባሕላዊ ምግቦች መካከል ጭኮ፣ አንጮቴ፣ ጮሮርሳ፣ ቆጭቆጫ፣ አካኢ ቆሪ፣ ጨጨብሳና ፉስፉሶን ይዘው በኢግዚቢሽኑ ቀርበዋል። ከባሕላዊ መጠጦቹም እንዲሁ የወለጋ ቡና እና ብርዝ ይገኝበታል። እነዚህን የኦሮሞ ባሕላዊ ምግቦችና መጠጦች በኤክስፖው ይዘው መቅረብ በመቻላቸው እጅግ ደስተኛ እንደሆኑም ገልጻለች፡፡

ወይዘሮ ፀሐይ እንዳለችው፤ የእሬቻ ኤክስፖ መዘጋጀቱ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው አለው። እሬቻ የሰላምና የአንድነት በዓል ነው። በተለይም የኦሮሞ ብሔረሰብ ከያለበት ተሰባስቦ ጨለማ ከሆነው የክረምት ወቅት ወደ ብርሃን ላሸጋገረው ፈጣሪው ታላቅና የከበረ ምስጋና የሚያቀርብበት እንደመሆኑ ማህበራዊ ግንኙነትን የሚያጠናክርና ከየአካባቢው የሚመጣውን ሕዝብ አንድ የሚያደርግ ነው።

ከማህበራዊ ጠቀሜታው ባለፈም ከዓመት ዓመት እየሰፋና እየደመቀ የመጣው የእሬቻ በዓል አከባበር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም ከፍተኛ እየሆነ መጥቷል። የእሬቻ በዓል መገለጫ የሆኑና በዓሉን ያደምቃሉ የተባሉ የማህበረሰቡ ባሕላዊ ምግቦች፣ ቁሳቁስና አልባሳት በዚህ ወቅት በስፋት ወደ ገበያ ይወጣሉ። ይህም ለኢኮኖሚው የሚኖረው አበርክቶ ጉልህ ነው። ባሕላዊ አልባሳቱን፣ ጌጣጌጦቹንና ባሕላዊ ምግቦቹን ከማስተዋወቅ ባለፈ በመሸጥ ለሚተዳደሩ ሰዎች አንድ የንግድ/ ቢዝነስ/ አማራጭ ሆኖ እያገለገለ ነው። ለበርካቶች የሥራ ዕድል እየፈጠረም ይገኛል። በተለይም ዘንድሮ የሚከበረው የእሬቻ በዓል ‹‹እሬቻ ኤክስፖ 2017›› በሚል ለመጀመሪያ ጊዜ ኤግዚቢሽንና ባዛር መዘጋጀቱ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል።

በዓሉ በዚህ መልክ እንዲከበር መደረጉ አንዱ ከሌላው ብዙ እንዲማርና የገበያ ትስስር እንዲፈጠር በማድረግ ኢኮኖሚያዊ አበርክቶው ጉልህ ነው የምትለው ወይዘሮ ፀሐይ፤ እሬቻ በኦሮሞ ብሔረሰብ በድምቀት የሚከበር የምስጋና በዓል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከባሕላዊ ምግቡ በተጨማሪ ወጣቶች በተለያዩ ጌጣጌጦች እንደሚያሸበርቁ ገልጻለች። ወቅቱ ባሕልን ለማስተዋወቅ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን በመጥቀስም ቀጣይነት ባለው መልኩ በዓሉን ማስተዋወቅና ወደ ቢዝነስ መቀየር እንደሚያስፈልግ አመላክታለች፡፡

ወይዘሮ ፀሐይ እንዳብራራችው፤ በኢሬቻ ኤክስፖው ላይ የተለያዩ የኦሮሞ ብሔረሰብ ባሕላዊ ምግቦች፣ ቁሳቁስ፣ አልባሳትና ጌጣጌጦች የቀረቡ ሲሆን፤ ነጋ የኦሮሞ ባሕላዊ ምግብም ባሕላዊ የሆኑ ምግቦችን ይዞ ቀርቧል። የኦሮሞ ባሕላዊ ምግቦች በአብዛኛው ከገብስና ከቀይ ጤፍ የሚዘጋጁ ናቸው። ጨጨብሳና ጮሮርሳ ከቀይ ጤፍ የሚዘጋጁ ናቸው፤ ጮሮርሳ በእርጎና በአይብ የሚበላ ምግብ ነው። ከገብስ የሚዘጋጀው ቆሪና ጩኮ የተባለው ባሕላዊ ምግብ በዋናነት በቅቤና ቅመማቅመም ታሽቶ ይዘጋጃል፡፡

እነዚህ የባሕል ምግቦች በማንኛውም ጊዜ ማህበረሰቡ የሚጠቀማቸው ቢሆኑም በተለየ ሁኔታ የሚዘጋጁት ግን ለእንግዳ፣ ለአራስና ለዘመድ ጥየቃ ነው። እነዚህን ልዩ ጣዕም ያላቸውን ባሕላዊ ምግቦች ከተማ ላለው ነዋሪ ተደራሽ ለማድረግ ማዘጋጀቱን በመኖሪያ አካባቢያቸው ቡራዩ አካባቢ እንደጀመሩት ያነሳችው ወይዘሮ ፀሐይ፤ ሰው በጣም እንደሚፈልጋቸውም ገልጻለች።

በተለያዩ ምክንያቶች ምግቦቹን በስፋት መሥራት ባይቻልም፣ ሰው በሰው በመጠቀም ገበያ ውስጥ መግባት እንደቻሉም ትናገራለች። በቀጣይም አስፍተው ለመሥራት ማቀዳቸውን ጠቅሳ፣ ለዚህም ኤክስፖው ላይ መሳተፋቸው ከበርካቶች ጋር ሊያስተዋውቃቸው እንደሚችል ተናግራለች። በአሁኑ ወቅት ከሀገር ውስጥ ባለፈ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባሕላዊ ምግቦቹን በትዕዛዝ እንደሚያሰሩና እስካሁን ካናዳ፣ አሜሪካና ኖርዌይ መላክ እንደቻሉም ገልጻለች፡፡

እሬቻ ማለት ከክረምቱ ጨለማ ብራ ወደ ሆነው መስከረም መሸጋገርን የሚያሳይና ይህን የጨለማ ጊዜ በመሻገሩ የኦሮሞ ሕዝብ በአንድነት ሆኖ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት በዓል ነው ስትል ያብራራችው ወይዘሮ ፀሐይ፤ የአንድነትና የምስጋና በዓል የሆነው እሬቻ በሰላምና በድምቀት መከበር እንዳለበትም አስታውቃለች። በዓሉን ለሚያከብሩና ለሀገሪቱም ሰላምና መልካሙን ተመኝታለች።

የአዳማው ፊራኦል ዲዛይንም በእሬቻ ኤክስፖው ላይ የኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳትን ይዞ ቀርቧል። በፊራኦል ዲዛይን የተለያዩ የኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳት እንደሚዘጋጁ የጠቀሰችው ወጣት ሳምራዊት በቀለ የድርጅቱ የሽያጭ ባለሙያ ናት። እሬቻ ኤክስፖ 2017 ለመጀመሪያ ጊዜ መዘጋጀቱን ጠቅሳ፣ ኤክስፖው መጀመሩን ጥሩ ብለዋለች። በቀጣይ እየሰፋና እየደመቀ እንደሚሄድ ዕምነቷ መሆኑንም ገልጻለች።

በኤግዚቢሽኑ የወንድ፣ የሴት፣ የአዋቂና የህጻናት የኦሮሞ ባሕልን የሚገልጹ ባሕላዊ አልባሳትን ይዘው መቅረባቸውን ወጣት ሳምራዊት ጠቅሳ፣ እንዲህ አይነቶቹ ባዛርና ኤግዚቢሽኖች የገበያ ትስስር ለመፍጠርና ልምድ ለመለዋወጥ ዕድል እንደሚሰጡም ተናግራለች። በተለይም በእሬቻ በዓል ላይ ሊለበሱ የሚገባቸው አልባሳትና ጌጣጌጦች በስፋት ወደ ገበያው እንደሚመጡ አስታወቋ፣ ይህም ባሕልን ከማስተዋወቅ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ሰፊ ነው ትላለች። ከበዓሉ ጋር ተያያዥ የሆኑ አልባሳት፣ ምግብና ጌጣጌጦችን በማዘጋጀት ቢዝነስ መሥራት የቻሉ በርካቶች መሆናቸውን ጠቅሳ፣ በቀጣይም ኤክስፖው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቃለች።

በኤግዚቢሽኑ ዝግጅት የተሳተፈው የሀገሬ ኢቨንት ምክትል ማናጀር አቶ ጥላሁን ጫላ እንዳሉት፤ የእሬቻ በዓል በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ የሚሳተፍበትና በባሕላዊ እሴቱ በስፋት የሚታወቅ በዓል ነው። ይህን ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ለማጉላት ታስቦ የተዘጋጀ ኤክስፖ ነው። ኤክስፖውን የሚጎበኙ በርካታ ሰዎች በኤግዚቢሽኑ ባሕላዊ ምግቦቹን፣ አልባሳቱንና ጌጣጌጡን እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁስን ጭምር ማግኘትና በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት እንዲችሉ ተደርጓል፡፡

የእሬቻ በዓል የኦሮሞ ባሕልን ከማስተዋወቅ ባለፈ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ድርሻ ለመጠቀም ታስቦ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው እሬቻ ኤክስፖ 2017 በታሰበው ልክ የተሳካ ነው ማለት ይቻላል ያሉት አቶ ጥላሁን፤ በኤግዚቢሽኑ የተለያዩ ባሕላዊ ምግቦችና አልባሳት እንዲሁም ጌጣጌጦችን የሚሰሩ ሰዎች ምርቶቻቸውን ይዘው ቀርበዋል። ሸማቹም እየጎበኘና እየሸመተ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም በአብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድ የማይታወቁና ጥሩ የሆነ ጣዕም ያላቸው የኦሮሞ ባሕላዊ ምግቦችን በማስተዋወቅ ረገድ ሰፊ ድርሻ አለው ሲሉ ጠቅሰው፣ ከባሕላዊ አልባሳትና ምግቦች በተጨማሪ የተለያዩ የምግብ ሸቀጦችም መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በእሬቻ ኤክስፖው በ250 ሺ ጎብኚዎች እንደሚጎበኝ ተገምቷል። 100 የሚደርሱ ጥሪ የተደረገላቸው አቅራቢዎችም ምርቶቻቸውን ይዘው ቀርበውበታል። ባንኮችና ኢንሹራንሶች ተገኝተውበታል።

ኢግዚቢሽኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው፤ በዚህ ዝግጅት ከዚህ በኋላ ሰዎች እሬቻን ሲያስቡ ኤግዚቢሽንና ባዛሩን ጭምር እንዲያስቡ ማድረግ ተችሏል ሲሉ አስታውቀዋል። ጎብኚዎች በኤግዚቢሽኑ የተመለከቷቸው የኦሮሞ ባሕላዊ ምግቦችን በስፋት ማድነቃቸውን አቶ ጥላሁን ገልጸዋል፡፡

በእሬቻ ኤክስፖ 2017 ተሳታፊዎች አብዛኞቹ ከአዲስ አበባ ከተማ የመጡ መሆናቸውን አመልክተው፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ያሉ ከተሞችም መሳተፋቸውን ተናግረዋል። ከአዳማ፣ ከሻሸመኔና ከሸገር ሲቲ የመጡ ስለመኖራቸው ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ኤክስፖው ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀ በመሆኑ ተሳታፊዎችን በተፈለገው መጠን ማስገባት አልተቻለም። ከዚህ ትምህርት በመውሰድ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲዘጋጅ ይደረጋል፤ በዚህም በርካቶችን ተደራሽ ማድረግ የሚቻልበት ዕድል ይፈጠራል። ይህም ባሕሉን ከማስተዋወቅ ባለፈ ኢኮኖሚውን በማነቃቃት ረገድ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።

‹‹እሬቻ ምስጋና የሚቀርብበት በዓል ነው፤ ኦሮሞ ክረምቱን የጨለማ ወቅት አድርጎ የሚያይ በመሆኑ መስከረም ሲጠባ ከጨለማው ዘመን ወደ ብርሃናማ ዘመን በሰላም ያሸጋገርከን ፈጣሪ እናመሰግንሃለን በማለት አምላኩን አብዝቶ የሚያመሰግንበት በዓል ነው›› ብለዋል። በእሬቻ በዓል በስፋት የሚንጸባረቀው ባሕላዊ እሴቱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ማንኛውም ሰው ወደ ኤግዚቢሽኑ በመምጣት የኦሮሞን ባሕል፣ እምነትና እሴቱን መማርና መረዳት ይችላል ብለዋል።

ከመስከረም 18 ቀን እስከ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የሚካሄደው “እሬቻ ኤክስፖ 2017” የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የሚያሳተፍ፣ በውጭ ሀገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ታዳሚ የሚሆኑበት መሆኑ ተገልጿል።

የኦሮሚያ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ደራራ ቱለማ ኤክስፖው በሚቀጥሉት ዓመታት በቋሚነት እንደሚዘጋጅ አመልክተዋል። እሬቻ ታላቅ የምስጋና በዓል እንደመሆኑ፤ ኤክስፖውም ይህንኑ ያሳያል ብለዋል። ባሕላዊ ኤግዚቢሽኖች እና ትርኢቶች የእደ ጥበብ ወርክሾፖች፣ አገልግሎትና ምርቶች የሚቀርቡበት ባዛር መሆኑን አብራርተው፣ የማህበረሰብ ተሳትፎ ክፍለ ጊዜዎችን በማካተት ጭምር በርካታ ተግባራት የሚቀርብበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ባሕሉን ከማስተዋወቅ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው አስታውቀዋል።

የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት የእሬቻ በዓል አከባበርን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ በዓሉ መስከረም 25 ቀን ሆራ ፊንፊኔ በአዲስ አበባና መስከረም 26 ቀን በቢሾፍቱ ሆራ ሀርሰዴ ይከበራል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You