ውልደትና እድገታቸው እዚሁ አዲስ አበባ ቢሆንም አብዛኛውን ህይወታቸውን ያሳለፉት በአሜሪካ ነው፡፡ የከፍተኛ ትምህርታቸውንም በዛው አሜሪካ ተከታትለዋል። ገና በለጋ እድሜያቸው የራሳቸውን አነስተኛ የሪል እስቴት ኩባንያ አቋቁመው ወደ ቢዘነሱ ዓለም ተቀላቅለዋል፡፡ ከሪልእስቴትና ፋይናንስ አገልግሎት ጋር በተገናኘም በርካታ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡ በዚሁ ቢዝነስም በሀገረ አሜሪካ ከሃያ ዓመት በላይ ቆይተዋል፡፡
ካለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በአዲስ አበባ በመጀመሪያ የአፓርትመንት ሆቴል ግንባታ ለመጀመር ተንደርድረው፤ በመቀጠል ደግሞ ከሁለት አሜሪካውያን ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የመኖሪያ ቤት አልሚ ኩባንያ አቋቁመው የመኖሪያ ቤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኢትዮጵያውያን ገንብተው ለማቅረብ እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜም በሀዋሳ ኢንዱስቴሪ ፓርክ ውስጥ ለሰራተኞች የማደሪያ ህንፃዎችን ገንብተው ለማስረከብ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ውል የፈፀሙ የመጀመሪያው አልሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡ በቀጣይም ይህንኑ ግንባታ በሌሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለማስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ የመኖሪያ ቤት ግንባታዎችን ለዜጎች የማቅረብ ውጥን ይዘው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ- የኮርነር ስቶን ዴቨሎፕመንት ግሩፕ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሲራክ አምባዬ፡፡
አቶ ሲራክ ውልደትና አድገታቸው እዚሁ አዲስ አበባ ወሎ ሰፈር ፒኮክ አካባቢ ነው፡፡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚሁ አዲስ አበባ ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ አሜሪካ አቅንተው በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከሳውዘርን ኤሊኖይስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ ቀጥሎም በኤክስኪዩቲቭ ማኔጅመንት ፕሮግራም የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከ ዩ ሲ ኤል ኤ ዩኒቨርሲቲ ተቀብለዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለው ካጠናቀቁ በኋላ የራሳቸውን አነስተኛ ኩባንያ በአሜሪካ አቋቁመው ያረጁ ቤቶችን ገዝቶ ከማደስ ጀምሮ ሌሎችንም ከሪል እስቴት ጋር የተያያዙ ቢዝነሶችን ሲሰሩ ቆዩ፡፡ ከፋይናንስ አገልግሎት ጋር በተያያዘም በተለይ በካሊፎርኒያ የተለያዩ የፋይናንስና የታክስ ማማከር ስራዎችን ሰሩ፡፡ ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታትም አብዛኛውን ጊዜያቸውን በሪልእስቴትና በፋይናንስ አገልግሎት ዘርፎች ላይ አሳለፉ፡፡
ካለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ቦሌ ፒኮክ አካባቢ አፓርተመንት ሆቴል ለመገንባት 1 ሺ 100 ካሬ መሬት ቦታ ገዝተው የግንባታ ፍቃድ አውጥተው የዲዛይን ስራውን እንዳጠናቀቁ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከሰተ፡፡ ይህንንም ተከትሎ የሆቴል ዘርፉ ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ በመግባቱ ግንባታውን ለጊዜው አቆሙት፡፡
በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለዜጎች ማቅረብና በተለይ ደግሞ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሰራተኞች መኖሪያ ቤት እጦት ዋነኛ ችግር መሆኑን የተረዱት አቶ ሲራክ ‹‹ኮርነር ስቶን ዴቨሎፕመንት ግሩፕ›› የተሰኘና በተመጣጣኝ ወጋ የመኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለዜጎች ለማቅረብ የተዘጋጀ ኩባንያ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ካላቸው አሜሪካውያን ጓደኞቻቸው ጋር አቋቋሙ፡፡
በቅድሚያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተከሰተ ሰሞን ተቀማጭነቱን ፍራንክፈርት ካደረገው የጀርመን ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በማግኘት ፕሮፖዛል ቀርፀው ወደ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስገቡ፡፡ ኮሚሽኑም ፕሮፖዛሉን አይቶ ወደደው፡፡ የመሬት ሊዝ ውል ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ተፈራረሙ። በአሁኑ ጊዜም በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሰራተኞች ማደሪያ ህንፃ ለመገንባት እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡
ኩባንያው በኢንዱስትሪ ፓርኩ በ 21 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚገነባው የሰራተኞች ማደሪያ ህንፃ የመጀመሪያ ፕሮጀክት ሲሆን 600 ሚሊዮን ብር ተመድቦለታል፡፡ በዚህ የግንባታ ፕሮጀክትም 13 ህንፃዎች ይገነባሉ፡፡ ከነዚህ ህንጻዎች ውስጥ አስሩ ባለ አስር ወለል እንዲሁም ሶስቱ ባለ አራት ወለል ናቸው፡፡
የግንባታው ፕሮጀክት ሲጠናቀቅም ለ6 ሺ 500 የፓርኩ ሰራተኞች የማደሪያ ህንፃ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከግንባታው በኋላም የማደሪያ ህንፃውከፓርኩ ተለይቶ የራሱ አጥር ይኖረዋል፡፡ በውስጡም የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የአረንጓዴ ስፍራ፣ ስቶር፣ ካፍቴሪያ፣ ባንክና ሌሎችም ፋሲሊቲዎችን ያቅፋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የግንባታው ዲዛይን የተጠናቀቀ ሲሆን ግንባታውን ለማስጀመር የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ለግንባታው አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን ከውጭ ሀገር ለማስገባትም የቀረጥ ነፃ ፍቃድ ከገንዘብ ሚኒስቴር በኩል እየተጠበቀ ነው፡፡ ከመሰረተ ልማት አቅርቦት ጋር በተያያዘም ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነቶች በዚህ ወር ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። በመጪው ወርም የቁፋሮ ስራ ይጀመራል ተብሎ ይታሰባል፡፡
በኮርነር ስቶን ዴቨሎፕመንት ግሩፕ፣ በጀርመን ልማት ባንክና በዘመን ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወነው የሰራተኞች ማደሪያ ህንፃ ግንባታ ፕሮጀክት እ.ኤ.አ በ2023 አጋማሽ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በግንባታው ሂደትም በመጀመሪያው ምእራፍ በተለያየ መልኩ ከ450 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሰራ አድል ይፈጠራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በሁለተኛው ምእራፍ ደግሞ እስከ 130 ለሚጠጉ ሰዎች ተጨማሪ የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአሁኑ ጊዜም 10 ያህል ሰራተኞች በኩባንያው ውስጥ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተቀጥረው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
የማደሪያ ህንፃው መገንባት የሰራተኞችን ድካምናእንግልት እንዲሁም በየጊዜው የሚታየውን የሰራተኞች መልቀቅ ይቀንሳል፡፡ ሙሉ ጊዜያቸውን በስራ ላይ በማሳለፍ ውጤታማ ስራ እንዲያከናውኑና የኩባንያዎችን ምርታማነት እንዲያሳድጉ ይረዳል፡፡ ይህንንም ተክትሎ የኩባንያዎቹ የወጪ ንግድ ስለሚያድግ ሀገሪቱ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬም ከፍ ይላል፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ያሉ ኩባንያዎች ለሰራተኞቻቸው ትራንስፖርት የሚያወጡትን ወጪም ይቀንሳል፡፡ በተመሳሳይ ሰራተኞች ለቤት ኪራይ የሚያወጡትንም ወጪ ይቀንሳል፤ ገቢያቸውም ያድጋል፡፡
ከዚህ በሻገር ኩባንያው /education for ethiopia.org/ ጋር በመሆን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች በእንግሊዝኛ፣ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሲዳምኛና በሌሎችም የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች የተለያዩ ትምህርቶችን ኦን ላይን እንዲከታተሉ የሚያስችላቸው አንድሮይድ መተግበሪያ እያዘጋጀ ይገኛል፡፡ ይህ መተግበሪያም ሰራተኞች ስለ ዲጂታልና ፋይናንስ፣ ስነ ተዋልዶ ጤና፣ ቋንቋና እና ቁጠባ ትምህርቶችን እንዲማሩ ያስችላቸዋል፡፡ ለዚህም 500 የሚሆኑ ታብሌቶች በሙከራ ደረጃ በኩባንያው በኩል ተዘጋጅተዋል፡፡ ይህም በኢንዱስትሪ ፓርኩ ለሚገኙ አምራቾች የሚቀርብ ተጨማሪ አገልግሎት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ሰፊ የመኖሪያ ቤት ችግር እንዳለና ፍላጎቱና አቅርቦቱም የተመጣጠነ እንዳልሆነ የሚናገሩት አቶ ሲራክ፤ ወደዚህ የቤት ልማት ፕሮጀክት የገቡት በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች በመኖሪያ ቤት እጦት ሲቸገሩ በማየታቸው መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
ዜጎች የመኖሪያ ቤትን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ የግንባታ ዋጋን መቆጣጠር እንደሚያስፈልግም ይጠቁማሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የግንባታ ግብዓቶቹ ከቀረጥ ነፃ መግባት እንዳለባቸውና ኩባንያቸው ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመነት ኮሚሽን ጋር ያለው ስምምነት በዚሁ መሰረት መሆኑንም ይናገራሉ፡፡
የግንባታ ተክኖሎጂን በሚመለከት ደግሞ ኩባንያው ቀላል የኮንክሪት ሙሌት የኮንስትራክሽን ቴክኖሊጂን ለመጠቀም ማሰቡንም ይጠቅሳሉ፡፡ ይህም የህንፃውን ስትራክቸር ቀላል ስለሚያደርገው የግንባታ ዋነኛ ግብዓት የሆኑትን የሲሚንቶ፣ ብረት፣ ጠጠርና አሸዋ ወጪዎችን እንደሚቀንስ ይገልፃሉ፡፡
በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የሚኖረው ስምምነትም ሰራተኞች በዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት ደምብ መሰረት ከሚያገኙት ገቢ ከ30 ከመቶ በላይ ለኪራይ እንደማያወጡ መሆኑንም አቶ ሲራክ ገልፀው፤ የኩባንያው እቅድም ይህንኑ መሰረት ያደረገ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ይሁን እንጂ ኩባንያው በአንድ የኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ የሰራተኞች ማደሪያ ህንፃዎችን ብቻ መስራት የማያዋጣው በመሆኑ ግንባታውን በሌሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥም የማሳደግ ሃሳብ እንዳለውም ያመለክታሉ፡፡
በቀጣይም ኩባንያው ይህንኑ የሰራተኞች ማደሪያ ህንፃ ግንባታዎችን የማከናወን እቅድ እንዳለው አቶ ሲራክ ይናገራሉ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም ለኢትዮጵያውያን በሁሉም ከተሞች በተመጣጣኝ ዋጋ ቤቶችን በስፋት ገንብቶ የማቅረብ ውጥን እንዳለው ይገልፃሉ፡፡ ለዚህም የባንክ ብድር መመቻቸት ስለሚኖርበት ከመንግስት አካላት ጋር፣ ከባንክና ከውጭ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ለመስራት ውጥን እንዳለው ይጠቁማሉ፡፡
ሰዎች ከኮቪድ ጋር ራሳቸውን አለማምደው የመኖር ሁኔታ ውስጥ እየገቡ በመሆናቸው፣ የሆቴል ዘርፉም ቀስ በቀስ እየተነቃቃ በመምጣቱና የጎብኚዎች እንቅስቃሴም እያደገ በመሄዱ ኩባንያው ቀደም ሲል የጀመረውን የሆቴል አፓርትመንት ግንባታ እንደሚያስቀጥልም አቶ ሲራክ ይናገራሉ፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ለቤት ፈላጊዎች በተመጣጣኝ ዋጋ የመኖሪያ ቤት ማቅረብ ቀላል ባይሆንም የሰዎች ቤት የመግዛት አቅም መታየት እንዳለበትና የሞርጌጅ መሰረተ ልማቱም አብሮ መስተካከል እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ የብድር ሥርዓቱም በረጅም ዓመትና በአነስተኛ የወለድ መጠን ሊሆን እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡ ከዚህ አኳያም ኩባንያው ከወዲሁ መፍትሄ ለማበጀት ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ሰፋ ያለ ውይይትና ምክክር እንደሚያደርግ ይገልፃሉ፡፡ ኩባንያው ግንባታውን አስቀድሞ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የጀመረው ይህንኑ ታሳቢ አድርጎ መሆኑንም ይጠቅሳሉ፡፡
‹‹በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሰራተኞች ማደሪያ ህንፃ ግባታ ላይ ትኩረት አድርገን ስንሰራ ራሳችንን የምናየው በዚሁ ስራ ላይ ብቻ የተሰማራን አድርገን አይደለም›› የሚሉት አቶ ሲራክ፤ ራሳችንን የምናየው እንደ ሙሉ አገልግሎት ሰጪ ነው ሲሉ ይገልፃሉ፡፡ ደምበኞቻችንም በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞችና አልሚዎች ናቸው ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ኩባንያው ከውጭ ድርጅቶች ገንዘብ የማሰባሰብ አቅሙም ትስስሩም ያለው በመሆኑ በተለይ በተመጣጣኝ ዋጋ የመኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለፈላጊዎች የማቅረብ አቅም መገንባቱንም ይናገራሉ፡፡
በኢትዮጵያ ጎልተው ከሚታዩ ችግሮች ውስጥ አንዱ የመኖሪያ ቤት እጦት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በከተሞች አካባቢ የመኖሪያ ቤት በመንግስትም ሆነ በግል አልሚዎች በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እጅግ አዳጋች እየሆነ መጥቷል፡፡ የዜጎች የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና አቅርቦትም የሚመጣጠን አልሆነም፡፡
ከዚህ አኳያ እንደ ኮርነር ስቶን ዴቬሎፕመንት ግሩፕ የመሰሉና በተመጣጣኝ ዋጋ የመኖሪያ ቤቶችን ለዜጎች ለማቅረብ የመጡ ኩባንያዎች አሁን ላይ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት ችግር ከመቅረፍ አኳያ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በመንግስት በኩል ማበረታቻ ሊደረግላቸው ይገባል የእለቱ መልእክታችን ነው፡፡ ሰላም! ይሁን
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2014