ከተመሰረተ አስራ ሦስት ዓመታትን አስቆሯል። በባዮ-ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከኢትዮጵያም ሆነ ከምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ነው። ኢትዮጵያ በዚሁ ዘርፍ ራሷን እንድትችል ትልቅ ራእይና ግብ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰም ይገኛል። ከምስረታው ጀምሮም አባላቶቹን ወደተለያዩ ሀገራት በመላክ በዚሁ ቴክኖሎጂ ዘርፍ አስፈላጊውን እውቀት እንዲገበዩና የእውቀት ሽግግር እንዲኖራቸው በማድረግ ሥራው በኢትዮጵያውያን ባለሞያዎች ብቻ እንዲከናወን ታላቅ ጥረት ሲያደርግም ቆይቷል።
ቀደም ሲል የባዮ-ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በተለይ ደግሞ ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ ግብአቶችን ከውጭ ሀገር በማስመጣት ሥራ ላይ ብቻ ተሰማርቶ የቆየ ሲሆን፤ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ደግሞ እነዚህኑ ግብአቶች ወደማምረት ተሸጋግሯል። በአሁኑ ጊዜም ሙሉ ትኩረቱን በዚሁ ግብአት ማምረት ሥራ ላይ አተኩሮና የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጥሬ ዕቃዎችን ተጠቅሞ ምርቱን በማምረት ለገበያ እያቀረበ ይገኛል።
ምርቶቹንም ለመንግሥት በተለይ ደግሞ ለኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ፣ ለግል ድርጅቶች እንዲሁም ለንግድ ድርጅቶች በተለይ ደግሞ ለአስመጪዎችና ቸርቻሪዎች እያቀረበ ሲሆን፤ በአምስት ዓመት እቅዱ ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ ግብአቶችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎች ለማዘጋጀት እየሠራ ነው።
በዚሁ እቅድ መሰረትም የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በማሟላት መንግሥት ለዘርፉ የሚያወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት ብሎም ምርቶቹን ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዘሬ ለማስገኘት ጥረት እያደረገም ይገኛል። ከሰሞኑም በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምርቶቹን በስፋት ለማምረት የሚያስችለውን የሕንፃ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጧል – ዘ ኒው ሚሊኒየም ወርልድ ሜዲካል ዲቫይስ ማኒዩፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ።
አቶ ተሾመ በየነ የ ዘ ኒው ሚሊኒየም ወርልድ ሜዲካል ዲቫይስ ማኒዩፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ናቸው። ውልደታቸውም ሆነ እድገታቸው እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ መነን አካባቢ ነው። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በእየሩሳሌም፣ በአምሃ ደስታ፣ ድል በትግልና ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል። ከዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸው ጎን ለጎንም ለአምስት ዓመታት ያህል የሃይማኖት ትምህርት ወስደዋል።
ባለፉት አስራ አምስት ዓመታትም ከህክምና መሳሪያዎችና ከነዚሁ ጋር በተያያዙ ሥራዎች ውስጥ ቆይተዋል። በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪም በተለይ በዚህ ቴክኖሎጂ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት ቻይናና ደቡብ ኮሪያ ጋርም በስፋት ሠርተዋል። ከዘርፉ ጋር በተያያዘም የተለያዩ ትምህርቶችንና ኮርሶችን ወስደዋል። በተለይም የተማሩት የማስተርስ ትምህርት ፕሮግራሞች ከዚሁ የባዮ-ቴክኖሎጂ ዘርፍ ጋር የተዛመዱ ነበሩ።
ከዛሬ አስራ ሦስት ዓመት በፊት ዘኒው ሚሊኒየም ወርልድ ኢምፖርት ኤንድ ኤክስፖርት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርን ከአስር በዘርፉ ከሚሠሩ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን አቋቋሙ። ኩባንያውም አባላቶቹን ወደተለያዩ ሀገራት በመላክ በባዮ- ቴክኖሎጂ ዘርፍ አስፈላጊውንና ጊዜው የሚጠይቀውን እውቀት እንዲገበዩ ብሎም የእውቀት ሽግግር በማድረግ ሥራው በኢትዮጵያውን ባለሙያዎች ብቻ እንዲሠራ ጥረት ማድረግ ጀመረ።
በመቀጠልም የባዮ-ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በተለይ ደግሞ ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ ግብአቶችን ከውጭ ሀገር በማስመጣት ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ ቀጠለ። በተለይ ደግሞ ከውጭ የሚያስገባቸውን ምርቶች ለኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲና ለተለያዩ የግልና የንግድ ድርጅቶች ማቅረቡን አጠናከረ። በነዚህ ጊዜያትም ኩባንያው ከምርቶቹ ጋር በተያያዘ ያለውን የገበያ ሁኔታና የማምረት ሂደት በሚገባ ማጥናት ቻለ።
ይሁንና ከውጭ የማስመጣቱን ተግባር ብቻ የፈለጉ የኩባንያው አባላት መንጠባጠብ በመጀመራቸው አቶ ተሾመን ጨምሮ የተቀሩት የማህበሩ አባላት ባሳዩት ፅናት ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ ግብአቶችን የማምረቱን ዘርፍ መሰረት አድርገው ቀጠሉ። ኩባንያውም በጥናትና ምርመር ሥራ ውስጥ ያሉና በማምረት ሥራው ላይ ሊሠሩ የሚችሉ አዳዲስ ሰዎችን በማካተት በአስመጪና ላኪነት የነበረውን ፍቃድ በመተው የማምረት ሥራው እንዲቀጥል አደረገ።
በአሁኑ ጊዜም በተለይ ደግሞ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ኩባንያው በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ቦታ ተሰጥቶት ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ ግብአቶችን ማምረት ላይ አተኩሮ እየሠራ ይገኛል። ሙሉ በሙሉ ከውጭ ሀገር የሚገቡትን ጥሬ እቃዎች ወደ 60 ከመቶ ዝቅ በማድረግና የሀገር ውስጥ ግብአቶችን 40 ከመቶ በመጠቀም ምርቶቹን አምርቶ ለገበያ እያቀረበ ነው።
ከአንድ ዓመት በፊትም የተወሰኑ ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ ግብአቶች አካላት በማምረት ውጤታማ መሆን ችሏል። ይሁንና መጀመሪያ ላይ እነዚህ ምርቶች በአብዛኛው ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸውና በትስስርም የሚሠሩ እንደመሆኑ ምርቶቹን አምርቶ ለገበያ በማቅረብ ሂደት ከፍተኛ ችግር አጋጥሞት አንደነበር ያስታውሳል።
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጊዜም ለጤና ሚኒስቴር ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ የእርግዝና መመርመሪያ መሳሪያዎችን በነፃ ለግሷል።
በ46 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ሥራውን የጀመረው ኩባንያው በአሁኑ ወቅት 50 ሠራተኞችን ቀጥሮ እያሠራ የሚገኝ ሲሆን፤ በዚህ የሰው ኃይሉ በዓመት 137 ሚሊዮን 800 ሺ ቴስት ኪት የማምረት አቅም አለው። ይህም መንግሥት የሚፈልገውን ምርት በበቂ ሁኔታ ለማሟላት ያስችለዋል። እያመረታቸው የሚገኙ ምርቶችም አራት ሲሆኑ፤ እነዚህም UCG /የእርግዝና መመርመሪያ መሳሪያ/፣ URS/ አስር የተለያዩ በሽታዎችን የሚገልጽ/፣H.payroly/ የጨጓራ መመርመሪያ /፣ እና H.payroia Ab /በደም የሚወሰድ ምርመራ/ ናቸው። በሂደት ላይ የሚገኙ የተለያዩ በሽታዎች መመርመሪያ መሳሪያ ምርቶችም አሉት። ምርቶቹንም ከውጭ ከሚገባው ምርት ባነሰ ዋጋ ለገበያ ያቀርባል። እነዚህኑ ምርቶች አሁን በበቂ ሁኔታ ለመንግሥትም ሆነ ለግል ተቋማት የማቅረብ አቅም ገንብቷል።
ኩባንያው የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ሲሆን፤ በእቅዱ መሰረት በአምስት ዓመት ውስጥ ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ ግብአቶችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎች ለማዘጋጀት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል። ይህ እቅዱ ሲሳካም የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በማሟላት መንግሥት ለዘርፉ የሚያወጣውን የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስቀርም ተስፋ አሳድሯል። ምርቶቹንም ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት ውጥን ይዟል።
ምርቶቹን በስፋት ለማምረትና በተለይ ደግሞ የሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎችን ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ለማምረትና ወደ ውጭም ለመላክ የሚያስችለውን ሕንፃ ለመገንባት ዝግጅት በማድረግ ላይ ነው። ግንባታውንም በሁለት ደረጃ ለማከናወን ከ509 ሚሊዮን ብር በላይ መድቧል። ግንባታውን አጠናቆ ወደማምረት ሲሸጋገርም 495 ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በዚሁ የሰው ኃይል ከ500 ሚሊዮን በላይ የመመርመሪያ ኪቶችን የማምረት አቅም እንዳለው በጥናት አረጋግጧል።
‹አጋፔ›› ወይም የፍቅር መአድ በሚል የንግድ ምልክት እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ኩባንያው አምስት ዶክተሮችንና አንድ ከፍተኛ አማካሪ ፕሮፌሰር እንዲሁም በዘርፉ ረጅም ዓመት የሠሩና ልምድ ያላቸው አባላቶች ያሉት ሲሆን፤ በቀጣይም በዚህ ዘርፍ ጠንካራ ሥራ የሠሩ ባለሞያዎችን አካቶ በመሥራት ለሀገርም ሆነ ለምሥራቅ አፍሪካ ብሎም ለተቀሩት አፍሪካ ሀገራት ፋና ወጊ የሆነ የባዮ ቴክኖሎጂ ኩባንያ በመመስረትና ለኢትዮጵያም ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ማዕከል የማድረግ ዓላማ ይዟል።
ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት በተለይ ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ስምምቶችን የማድረግ ሂደት ላይ ይገኛል። የሀገር ውስጥ ባለሞያዎችን በማበረታታትና በማጠናከርም የሚሠራ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
ኩባንያው ይህን ሥራ ሲሠራ በቀጣይ በዓለም ገበያ በመግባትና የባዮቴክ ገበያን መሰረት አድርጎ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ተሾመ፤ እንደሀገር ትልቅ የገቢ ምንጭ እንደሚሆን ይገልጻሉ። ማህበሩ በዚህ ዘርፍ ቀዳሚ እንደመሆኑ መጠን መንግሥትም በተለይ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ በዓለም መድረክ ጎልታ እንድትታይ አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን ያቀርባሉ። በተለይ ደግሞ እነዚህ ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ መሳሪያዎች በጣም አስፈላጊና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚወጣባቸው እንደመሆኑ መጠን መንግሥት እነዚህ መሳሪያዎች በስፋት በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ኩባንያውንም ሆነ በቀጣይ በዚሁ መሳሪያ ማምረት ላይ ለሚሰማሩ ድርጅቶች ሰፊ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባውም ያመለክታሉ።
‹‹ዘ ኒው ሚሊኒየም›› በባዮ-ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማራ በኢትዮጵያም ሆነ በምሥራቅ አፍሪካ ብቸኛውና የመጀመሪያው ኩባንያ ነው የሚሉት አቶ ተሾመ፤ በአፍሪካ ደረጃም የተወሰኑ ሀገራት ብቻ እንዲህ ዓይነቱ ኩባንያ እንዳላቸው ይጠቁማሉ። ኩባንያው ያለውጭ ሀገር ዜጎች በኢትዮጵያውያን ብቻ እየተሠራ ያለ በመሆኑና ለሀገሪቱ የሚያሰገኘው ጥቅምም ከፍተኛ እንደመሆኑ እንደትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት መታየት እንዳለበት ያመለክታሉ። ከዚህ አኳያ ፕሮጀክቱን መሬት አውርዶ ከመፈፀም አንፃር ከመንግሥት በኩል ትልቅ ድጋፍ እንደሚያስፈልገውም ይጠቁማሉ።
ኩባንያው ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ የዘርፉ ባለሞያዎች በሩ ክፍት ነው። በጋራ አብሮ በመሥራት እንደሀገር ትልቅ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ይጠቁማሉ። በተለይ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን በሀገሪቱ ህግና በማህበሩ ፖሊሲ መሰረት በጋራ በመሥራት ኢትዮጵያ በባዮቴክ ቴክኖሎጂ ከዓለም አቀፍ ተርታ እንድትመደብ የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ እንዲችሉ ይጋብዛሉ። ከዚህ አኳያም ኩባንያው ረዥም ጉዞ ለመሄድ ማሰቡንም ይጠቅሳሉ። ኩባንያው በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልልቅ ስም ካላቸው የባዮቴክ ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ የማድረግ ግብ ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንዳለም ያመለክታሉ። ከዚህ አኳያ ኩባንያው ሁሉን አቅፎ የሚሄድ ሀገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን ይጠቁማሉ። አሁን ባለው ሂደት ኩባንያው ውጤታማ ነው የሚሉት አቶ ተሾመ ለዚህ ውጤት መምጣት የሁሉም አባላት ጥረት ከፍተኛ እንደነበር ይጠቁማሉ። የእርሳቸው መንፈሳዊ ህይወትም ለኩባንያው ውጤታማነት የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከቱን ይገልጻሉ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም