በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
መንገድ ላይ እየሄድን ሳያቋርጥ እያወራ የሚሄድ ሰው ብንመለከት ምን ይሰማናል? ወደ ስብሰባ ክፍል ገብተን ለስብሰባ ዘወትር የሚሰበሰቡ የቡድን አባላችን መካከል አንዱ ሰው ሁሌም በዝምታ ተውጦ አንዳች የማይናገር ቢሆን ምን ይሰማናል? ሌላው ተሰብሳቢ ደግሞ የሌሎችን ንግግር እያቋረጠ ሳይቀር ብዙ የሚናገር ቢሆንስ? አብሮን የሚሰራ የሥራ ባለደረባ እንደወትሮው ከመናገር ተቆጥቦ በዝምታ ተውጦ ብናይስ?
እኒህ መነሻ ጥያቄዎች በተጨባጩ አለም ውስጥ በየእለቱ የሚገጥሙ ናቸው። በፍጹም ዝምታም ሆነ ገደብ የለሽ ተናጋሪነትም ሁለቱም ከአዕምሮ እክል ጋር የሚያያዙም ናቸው። መናገር እና ማድመጥ የሰው ልጅ የማንነቱ አካላት ናቸው።
በንግግር ውስጥ ሃሳብ ይተላለፋል፣ በንግግር ውስጥ ስሜታችንን ለሌሎች እናጋራለን፣ በንግግር ውስጥ የሌሎችን ሃሳብ እንሰማለን እንዲሁም ስሜታቸውን እንካፍላለን።
በንግግር ግድፈት እንዲሁም በማድመጥ ሚዛን መሳት ምክንያት አብረውን ሊሆኑ የሚገባቸውን ልናጣ እንዲሁም በቀላሉ ልናከናውን የሚገባውን ነገር አላስፈላጊ ዋጋ እንዲሆን ልንገደድ እንችላለን። በምላስ ወለምታ ትዳር ይፈርሳል፤ ወዳጅነት ይቋረጣል፤ የሥራ ገበታ ይዘጋል እስከ ህይወትን ማጣት ሊያደርስ የሚችል ምስቅልቅል ምክንያት ይሆናል። መናገር እና ማድመጥ!
ፈንጂም …!
አንድ ታሪክ እናስቀድም። የተሰማትን ሁሉ ከመናገር ወደ ኋላ የማትል የአንዲት ሴት ታሪክ ነው። የተሰማትን ስሜት በሙሉ እንደወረደ ትዘረግፈዋለች። ይህ ለእርሷ እንደ ችግር የማይታይ መገለጫዋ ነው። በዚህ ሁኔታዋ የተጎዱ ሰዎች ቢመክሩ ቢዘክሯት አሁንም የተሰማትን ዶፍ በማውረድ ታሸማቅቃቸዋለች።
በዙሪያዋ ያሉ ሰዎች በምክራቸው ለውጥ ማምጣት ስላልቻሉ ጉዳዩን ግለሰቧ ለምታመልክበት ቤተክርስቲያን መጋቢ ያቀርባሉ። መጋቢው ቅሬታ የቀረበባትን ሴት ቢሯቸው አስጠርተው እየቀረበባት ያለውን ስሞታያቀርቡላታል። ሴቲቱም አንዳች አስገራሚ እውነት ለመናገር እንደጓጓ ሰው ፊቷን አፍክታ “ፓስተር እኔ እኮ አንዴ ከተናገርኩ በኋላ የምተው ሰው ነኝ፤ በፍጹም ቂም አልይዝም።
ሰዎቹ ያልተረዱት ነገር ቢኖር ይህን ነው።” በማለት ማስተባበያ ታቀርባለች። መጋቢዎም ምላሿን በጥሞና ካደመጡ በኋላ “አይ እህቴ እርሱማ ፈንጅም ቢሆን አንዴ ፈንድቶ ዝም ይላል፤ ጉዳዩ የሚያደርሰው ጥፋት ነው እንጂ።”
በማለት ምላሽ ሰጧት። ዛሬም እርስ በርስ በሚኖረን ተግባቦት የሚሆነው ጉዳትን ማሰብ አስፈላጊ ነው። ጉዳት እንዳይኖር ብሎ ከመናገር መተው ሳይሆን የመናገርና የማድመጥን ሚዛን መፈለግ ይገባል። ማድመጥን አስቀድመን ስለ መናገር እናስከትላለን። ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቁጣም የዘገየ ይሁን እንደሚል መጽሐፉ።
ማድመጥ
የምንናገረው የተገኘው በማድመጥ ነው። ማድመጥ ውስጥ መማር አለ። ማድመጥ ውስጥ የሌሎችን ሁኔታ መረዳት መቻል አለ። ማድመጥ ውስጥ መደመጥም አለ። ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ቢሆን ምድር በአስተውሎት የተሞሉ ሰዎች መገኛ በብዙ በሆነች ነበር። ያለንበት የቴክኖሎጂ፣ የኢንተርኔት እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያ ዘመን የበረከቱ ድምጾች በዙሪያችን የሚያደርግ ነው። የበረከቱ ድምጾች በዙሪያችን ሲመጡ መደመጥን ፈልገው ነው።
የበረከቱት ድምጾች አድማጭን ፍለጋ እየባዘኑ ነው። ምን ያህል ላይክ አገኘሁ፤ ምን ያህል ተከታይ አፈራሁ የሚለው መዋቅራዊ የሆነው የማህበራዊ ሚዲያው ቀመር የመደመጥ መሻትን ወደ አደባባይ ይዞ ወጥቶ የንግድ ቀመር ማድረግ የቻለም ነው። የንግድ ቀመሩም ውጤታማ ሆኖ በየጎዳናው ተደብቆ የቆየውን ሁሉ ወደ አደባባይ ይዞት ወጥቷል።
በዚህ ሁሉ ውስጥ ትልቅ ትርጉም ተሰጥቶት እየታየ ያለው መናገር መቻል እንጂ ማድመጥ መቻል አይደለም። ማድመጥ መቻል ቦታውን ይይዘው ዘንድ ሁላችንም ቆም ብለን ማሰብ አለብን። ዓላማ ተኮር ያልሆኑት የበረከቱት ድምጾች የፍጥረትን ሩጫ እየገቱ ምድራችን ሞት የረከሰባት እንድትሆን እያደረገ ስለሆነ።
ለማድመጥ ጊዜና ቦታ መስጠት መቻል እርሱ አስተውሎት ነው። ማድመጥ መቻል ሰነፉን ሰው እንደ ጠቢብ ሊያስቆጥር ጭምር የሚችል መሆኑን የጠቢቡ ሰለሞን ምሣሌ ይነግረናል እንዲህ በማለት ሰነፍ ዝም ቢል ጠቢብ ሆኖ ይቆጠራል፥ ከንፈሩንም የሚቈልፍ ባለ አእምሮ ነው ይባላል።
ውጤታማ አድማጭነት የሕይወት ገንቢ መንገድ ነውና እነሆ ጠቃሚ ነጥቦች፣
1. ማድመጥን በፍላጎት ማድረግ
ማድመጥ ልክ እንደ መናገርና መጻፍ እውነተኛ የሆነ የውስጥ ፍላጎት እና ትኩረት ማድረግን ይጠይቃል። በማድመጥ ላይ ትኩረት ማድረግ ካልቻልክ መማር ያለብህን ልትማር አትችልም፤ እንዲሁም የተማርከውንም ማስተዋል። ብዙዎቻችን ከሰማነው ነገር ውስጥ 25 ከመቶ የሚሆነውን የማስቀረት አቅም እንዳለን ይታመናል።
ትኩረትን መጨመር በቻልን ቁጥር የተሻለ ከምናደምጠው ማስቀረት እንችላለን። በማድመጥ ውስጥ ትምህርት መኖሩን፤ በመናገር ውስጥ ደግሞ መስጠት ብቻ መሆኑን መረዳት ይገባል።
ለዚህም ነው 36ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሌይነደን ቢ. ጆንሰን በምትናገርበት ጊዜ ምንም ነገር እየተማርክ አይደለም በማለት የተናገሩት። በምናደምጥበት ጊዜ ግን እየተማርን ነው፤ በትኩረት ሲሆን ደግሞ የበለጠ እየተማርን ነው።
2. ማድመጥን በአይንም ማድረግ
መስማትም ሆነ ማድመጥ ሲታሰብ ጆሮ መታሰቡ ግድ ነው። ነገር ግን በምትሰማበት ጊዜ ጆሮህን ብቻ የምትጠቀም ከሆነ የመልእክቱን አብዛኛውን ነገር አጥተኸዋል ማለት ነው። ጥሩ አድማጮች ከጆሮቸው ባሻገር አይናቸውንም ይጠቀማሉ። ጆሯቸውን ከፍተው እንደሚያደምጡት፤ አይናቸውንም ይከፍታሉ። ይህ ሲሆን ቃላትን ብቻም ሳይሆን በቃላት ውስጥ የሚተላለፈውን መልዕክት ሙሉ የሚያደርገውን የተናጋሪውን ስሜትንም ጭምር ማድመጥ ይቻላል።
3. አካላዊ እንቅስቃሴንም ማድመጥ
አንድ ተናጋሪ በድምጽ ከሚያወጣው ንግግር ባሻገር በአካላዊ እንቅስቃሴው ጠንካራ መልእክቶችንም ያስተላልፋል። ስለሚናገረው ነገር ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነ፤ በንግግሩ ውስጥ ቀልድ ካለበት፣ በሚናገረው እውነታ ውስጥ ያለው ህመም ይሆን ደስታ ወዘተ ጎልተው የሚሰሙት ከድምጽ ባሻገር በአካላዊ እንቅስቃሴ ነው።
ይህ ሁሉ በንግግሩ ውስጥ ብቻም ሳይሆን በአካላዊ እንቅስቃሴው ውስጥም ይተላለፋል። አካላዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚተላለፈውን መልእክትም ለማግኘት ጥረት ማድረግ ውጤታማ አድማጭ ያደርጋል። ውጤታማ አድማጭነት ማለት ውጤታማ ተማሪነት መሆኑን ደግመን እያሰብን።
በአካላዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ቃላት የማይገልጡት መልእክት የሚተላለፈው ታስቦበትም ሆነ ሳይታሰብበት ሊሆን ይችላል፤ ብዙ ጊዜ ሳይታስብበት ነው። አድማጩ ተናጋሪው ሊደብቀው የሚፈልግ መልዕትን እንኳን ሳይቀር በአካላዊ እንቅስቃሴው ውስጥ ማግኘት ያስችለዋል። በቃላት ውስጥ ያልተሸፈኑ ወሳኝ የሆኑ መልእክቶችን ማግኘቱ እንዳለ ሆኖ።
በቃላት በሚደረግ ንግግር ውስጥ ብቻ ሆኖ አቋም መያዝ እጅግ የተሳሳተ ውሳኔ ላይ ሊጥል ይችላል፤ በመሆኑም አካላዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያለውን መልእክትም ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይበረታታል። ጥረቱም እንዲሳካ የአንድን ሰው ንግግር ስንሰማ ትኩረታችንን ሰብስበን ጆሮችንንም አይናችንንም እንዲሁም አካላዊ እንቅስቃሴን ማንበብን መጨመር ተገቢ ነው።
4. የአድማጭነት ፍላጎትን ማሳየት
ያለንበት ዘመን የመረጃ ዘመን ነው። በመረጃ ዘመን መረጃ ወደ እኛ መድረስ እንዲችል መረጃ ሰጪ የሆኑ ሰዎች በቀላሉ ሃሳባቸውን ለመስጠት የሚፈልጉት አይነት ሰው መሆን ይገባል። ልጆች እንዲናገሩ ስናበረታታቸው በውሏቸው የገጠማቸውን ነገር ለመናገር ሳይፈሩ እንደሚነግሩን በዙሪያችን ያሉ ሰዎችም እንደዚያው ናቸው። ሰዎች ወደ ሚያደምጣቸው ሰው ጠቃሚ የሚባል መረጃን ይዘው ለመሄድ ይበረታታሉ።
ለእኛ የሚጠቅመን መረጃን ሰዎች በቀላሉ የሚነረግሩን እንዲሆኑ የሚያበረታታቸው ሌሎችን የማድመጥ ፍላጎታችን ነው።በመሆኑም ለመናገር የሚፈልጉ ሰዎችን ማበረታታት መቻል የማድመጥ አቅማችንን የሚያሳይ እንዲሆም እኛም ስንናገር እንድንሰማ የሚያደርግ በዋናነት ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎች በጊዜው ከእኛ ዘንድ እንዲደርሱ ማድረግ ነው።
መናገር
በመነሻችን ላይ ያነሳናት ሴት ታሪክ በንግግር ውስጥ የሚፈጠረውን አደጋ የሚያሳይ ነው። አደጋው መጋቢው እንዳሉት እንደ ፈንጅ ጉዳት የሚያደርስ ሊሆን ይችላል። በንግግር ውስጥ ሰዎችን መጉዳት እንደሚቻለው ሰዎችን ማቆም እንደሚቻልም ማሰብ ያስፈልጋል። በማንኛውም ነገር ውስጥ ከሚሆነው ጉዳይ በላይ ሰውን ነጥሎ አውጥቶ ሰውን ሁልጊዜ በመጥቀም ውስጥ ማድረግ መልካም ነው።
እንደ መርህ ንግግር አድርጎ ከመራቅ የንግግራችንን ጥራት መጨመር ላይ አተኩረን መናገር ባለብን ቦታና ጊዜ ላይ መናገር የተሻለው ነው። አለመናገርን እንደ መፍትሄ መውሰድ ሳይሆን ማድመጥንም መናገርንም በልኩ ማድረግ ነው የሚሻለው።
ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል የሚለው ሀገራዊ ብሄል ውስጥ ያለው መልእክት እዚህ ጋር ይሰራል። የንግግራችን ይዘት ሰዎችን ማነጽ እንጂ ማፍረስ፤ ማበረታታት እንጂ ተስፋ እንዲቆርጡ ማድረግ፤ ከዛሬ ነገ የተሻሉ እንዲሆኑ እንጂ ከዛሬ ወደ ኋላ እንዲመለሱ በማድረግ እንዳይሆን መጠንቀቅ እንጂ ከመናገር ልንርቅ አንችልም።
የንግግር ዓላማው ንግግራችንን በሚሰማው ሰው ውስጥ አዎንታዊ ተጽእኖን መፍጠር ከሆነ የንግግራችን ጥራትን ስናስብ የሚከተሉትን ነጥቦች ማሰብ ጠቃሚ ይሆናል።
1. ጥራት ያለው አስተሳሰብን መያዝ፣
መናገርን ስናስብ የምንናገረው ነገርን ማወቅ እጅግ አሰፈላጊ መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም። የምንናገረው ስለተረዳነው ነገር ሲሆን በልበ ሙሉነት ለሌሎች በሚጠቅምም ሁኔታ ማቅረብ ያስፈልጋል። በሰዎች ፊት ንግግር ማድረግን ጨምሮ አንድ ለአንድ በሚኖር ንግግር ውስጥ ስለምንናገረው ነገር ተገቢውን እውቀት ይዞ መገኘት ያለው ፋይዳ ሳይታለም የተፈታ ነው።
በሀገራችን ያሉ የራዲዮ እንዲሁም የቴሌቪዥን መርሃግብሮች መብዛት አማራጭ ሃሳቦችን የመስማት እድሉ ቢኖርም የአየር ሰዓት ወስደው የሚያስተላልፉ አካላት ስለሚናገሩት ነገር የሚያደርጉት የእውቀት ዝግጅትን ግን በብዙ የሚያስተች ሆኖ እናገኘዋለን።
ያለ እውቀት እንዴት ለንግግር አንደበት ይከፈታል? በድፍረት በማናውቀው ጉዳይ ላይ ለመናገር ስንነሳ ችግሩ አድማጩን በተሳሳተ አቅጣጫ መምራት ነው የሚሆነው። በመሆኑም ጥራት ያለው አስተሳሰብ ስለምንናገረው ነገር መያዝ የንግግር ውጤታማነት የመጀመሪያው ቁልፍ ነጥብ ነው።
2. መናገር ያሰቡትን ብቻ መናገር፣
በሰዎች ፊት ለመናገር ሲቆም ከሚደረጉ ዝግጅቶች መካከል ምን መናገር አለብኝ፣ በምን ጀምሬ በምንስ መጨረስ አለብኝ፣ ምን አይነት ምሳሌያዊ አገላለጾችን መጠቀም አለብኝ፣ ለምን ያህል ጊዜ ውስጥ ምንን ርእስ መናገር አለብኝ ወዘተ በሚል ሁኔታ መዘጋጀት ያስፈልጋል። ከመናገራችን በፊት መናገር ያለብንን መምረጥ መቻል ውጤታማ የሆነ ንግግር ማድረግ ያስችለናል።
ባልተዘጋጀንበት ንግግር ውስጥ የማይሆን ተስፋን መፍጠር፤ ያልታሰበበት እቅድ ማስተላለፍ ወዘተ ነገዎቻችን ውስጥ ዛሬ አሉታዊ ተጽእኖን መፍጠር ነው የሚሆነው። አድማጭ በንግግራችን ተነሳስቶ በሚያሳየው ስሜታዊነት ውስጥ ገብተን የንግግራችንን ይዘትም ሆነ የንግግራችንን ሰዓት አቅጣጫ ከማስቀየር መቆጠብ ይገባል።
በንግግር ወቅት ምን መናገር እንዳለብን እንዳሰብነው እንደዚያ ብቻ መናገር ይገባል። በንግግር ሂደት ውስጥ የሚፈጠሩ ሃሳቦችን በተቻለው መጠን ቀድመን ለመናገር ባሰብነው መንገድ እየቃኘን መሄድ ውጤታማ ንግግር ለማድረግ ያግዛል።
አድማጭ የሚኖረው ግብረ-መልስ የንግግራችንን አቅጣጫ ፈጽሞ በተቃራኒው መንገድ እንዳይሄድ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው። መናገር ያሰቡትን ብቻ የመናገር ጥበብ በዋናነት ከአንድ ሰው በላይ በሆኑ ሰዎች ፊት በምናደርገው መደበኛም ሆነ ኢ-መደበኛ ስብስቦች ላይ መጠቀም ይገባል።
3. ዋናው ነጥብ ላይ ማተኮር
ውጤታማ ተናጋሪዎች በንግግራቸው ውስጥ ተራራን አይዞሩም። በቀጥታ መናገር የሚፈልጉትን ነጥብ ይናገራሉ። የምንፈልገው ነገር ካለ ዙሪያ ጥምጥም ከመሄድ በቀጥታ እንጠይቅ። አንድን ሰው በሆነ ጉዳይ ላይ ማዘዝ ካለብን በቀጥታ እንዘዘው። ዋናው ነጥብ ላይ ከማተኮር በዘወርዋራ መንገድ እንድንሄድ የሚያደርገንን ነገር በመፈለግ መፍትሄ መስጠት ይገባል።
4. ንግግርን ቅልብጭ ማድረግ መቻል
በንግግር ውስጥ ቃላትን ላለማባከን ማሰብ ያስፈልጋል። ብዙ ባወራን ቁጥር በንግግር መካከል ግድፈት የመፍጠር እድላችንም እንዲሁ ይሰፋል። በመሆኑም በንግግር ጊዜ በግልጽነት መናገር፣ በተቻለው መጠን አጭር ማድረግ እንዲሁም የሚታወቁ ቃላትን መጠቀም ይመከራል።
5. ራስን መሆን
እያንዳንዳችን የራሳችን ማንነት አለን። ፈጣሪ ሲፈጥረን ሁላችንንም ውብና ድንቅ አድርጎ ፈጥሮናል። በዚህ ሳምንት ውስጥ በሸገር 102.1 የሸገር ማለዳ የጤና ፕሮግራም ላይ የቀረቡ የህክምና ባለሙያ ስለ አፍንጫ ጥቅም ይናገራሉ። አፍንጫችን የሚቀበለውን አየር እንዴት እያሞቀ ወደ ውስጥ እንዲገባ ሲተርኩ በፈጣሪ በመደነቅ በፈጣሪ መደነቃቸውን ይገልጻሉ።
አፍንጫችን ብቻ ብዙ ጥበብ ያለበት አካላችን ነው። ሌላውን ሁሉንም ስናስብ እያንዳንዱ ሰው ምን ያህል ውድ መሆኑን እንረዳለን። በመሆኑም በአጠቃላይ በህይወታችን ውስጥ ለራሳችን ከፍተኛ ዋጋ መስጠት ተገቢ ነው። በንግግር ውስጥም ለራሳችን ሃሳቦች ቦታን መስጠት፤ ላለን እውቀት ቦታን መስጠት እንዲሁም ለመናገር አቅማችን ቦታን መስጠት ይገባል።
በንግግር ውስጥ ራሳችንን እንጂ ሌሎችን ለመመስል መሞከር የለብንም። ከሌሎች መማር ያለብን ነገር ቢኖርም፤ ራሳችንን መሆን መቻል ግን አስፈላጊ ነው። የራሳችን የአነጋገር ዘዬ፣ ድምጽ አወጣጥ፣ ቃላት አደራደር ወዘተ አለን፤ እርሱን ማወቅና መሆን ለውጤታማ ንግግር አስፈላጊ ነው። ሌሎች ሰዎችን ለመምሰል በጣርን ቁጥር አድማጭን ለእኛ ያለውን ግምት ስለምናጠፋበት በተግባቦት መካከል ክፍተትን እንፈጥራለን፤ ተገቢም አይደለም።
ማጠቃለያ
ዛሬ በልባችን ውስጥ ሃዘንን የፈጠረ ነገር አለ? ያ ነገር የመጣው በሰዎች ንግግር ወይንም እኛ ሌሎችን በተናገርነው ያልተገባ ነገርስ ይሆን? ይህን ለማስተካከል ምን ማድረግ እንዳለብን ዛሬ ተማርን?
ማድመጥም ሆነ መናገር በህይወት ያለ ሰው የህይወቱ የዘውትር ተግባሩ ነው። ይህን ተግባር ከማሻሻል አንጻር መስራት ውጤቱ በብዙ አቅጣጫ የሚመነዘር መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል።
መርዶም ሆነ የምስራች በንግግር ውስጥ ይተላለፋሉ፤ ብላቴኖችን ማጀገንም ሆነ ማንኳሰስ በንግግር ውስጥ ይሆናል። ሀገርን መገንባትም ሆነ ማፍረስም እንዲሁ። ስለሆነም ማድመጥም ሆነ መናገር በማስተዋል ይሁን።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2013