አንዳንድ ጊዜ በራበን ወቅት በችኮላ አልያም ከአቻዎቻችን ጋር በሽሚያ ስንበላ ምግቡን ሳናላምጥ የምንውጥበት ጊዜ ሊከሰት ይችላል። በተለይ ስጋ ነክ የሆኑ ምግቦች አጥንትም ስለሚኖራቸው እያጣጣምንና እያላመጥን ስንበላ በጥርሳችን ወይም በምላሳችን ልንውጥ ስንል ትንንሽ አጥንቶችን ያጋጥሙናል።እንደ አሳ ዓይነት ምግቦች ደግሞ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልጉ ናቸው “አሳ መብላት በብልሃት” የተባለውን ምሳሌ የሚመክረን የአጥንቱን ስንጣሪን ሳንውጥ በመጠንቀቅ እንድንመገብ ለማሳሰብ ነው።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በምግብ አብሳዮች ችግር ውይም ጥንቃቄ ማነስ ምክንያት አላስፈላጊ ነገሮች ምግብ ውስጥ ተቀላቅለው የምናገኝበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።
ሰሞኑን በእንግሊዝ ሀገር አንድ ወጣት ፕሮፌሽናል አትሌት ለምግብ ማንሻ የተሰካን ስንጥር ከምግቡ ጋር መዋጡን አስንበቧል። የ18 ዓመቱ ወጣት አትሌት ህመሙ ካጋጠመው በኋላ ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን በዚያም የሆድ ህመምና የደመም መፍሰስ ምልክት ታይቶበት እንደነበር የእንግሊዝ የህክምና መፅሔት ዘግቧል።
ዶክተሮቹ ወደ አንጀት መመርመሪያ መሣርያ (colonscopy) ከተው ከቆዩ በኋላ ሁለት ኢንች የሚሆን የጥርስ መጎርጎሪያ ስንጥር በትልቅ አንጀቱ ውስጥ ተሰንቅሮ ተገኝቷል።
ስንጥሩ የደም ቧንቧ ውስጥ ዘልቆ ገብቶ ወደ ደምሥሮቹ ባክቴሪያ እንዲገባ አድርጓል የተባለ ሲሆን የህክምና ባለሙያዎች እንደሚገልፁት አትሌቱ ከፍተኛና አዳጋች የሆነ የጤና ችግር አጋጥሞት ለመሞት ተቃርቦ እንደነበር ግልፀዋል።
የጥርስ መጎርጎሪያ እንጨት ወይም ስንጥር መዋጥ እንግዳ የሆነ ክስተት ቢሆንም ብዙ ውስብስብ ነገሮችን የሚያስከትል ነው።በ2014 የታተመው የዓለም ቀዶጥገና ጥናታዊ ሕትመት ከላይ በተጠቀሰው አደጋ ዙሪያ ብቻ 136 ጉዳዮች መከሰታቸውተዘግበዋል።እንደ መረጃው ከሆነም ከእነዚህ ውስጥ ግማሹ የጥርስ መጎርጎሪያ እንጨቱን መዋጣቸውን አያውቁም። አስር በመቶዎቹ ደግሞ የጥርስ ስንጥር ውጠው ሞተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 28/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ