ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ሊካሄድ የቀረው የአራት ወራት እድሜ ነው። በአሁኑ ወቅት ለሀገራችን ምርጫ ትልቁ አጀንዳ እንደመሆኑም፤ ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ተአማኒ ከሁሉም በላይ ደግሞ ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ሁሉ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። መንግስት የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ከምንግዜውም በላይ ቆራጥነቱን በተደጋጋሚ በገባው ቃል አሳይቷል ፤ ይሄንኑም በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሀገራት የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በህጋዊ መንገድ እና በሰላማዊ የውድድር መንፈስ በምርጫው እንዲሳተፉ እድል ሲፈጠርም፤ የተመቻቸ የውድድር ሜዳ እንዲኖር አስቀድሞ ምህዳሩን የማስፋት ስራ ተሰርቷል።
ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለምርጫው ብቁ ሆኖ ለመቅረብ እና ለመወዳደር የሚያስፈልጋቸውን ዝግጅቶች ከወዲሁ እያሟሉ ይገኛሉ። ብሄራዊ የምርጫ ቦርድም በምርጫው ለመወዳደር ካመለከቱ ፓርቲዎች መካከል መስፈርቱን አሟልተው በህጋዊ መንገድ ተመዝግበዋል ያላቸውን 49 ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክት ይፋ አድርጓል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ የዲሞክራሲ ተቋማት በአዲስ መልኩ ራሳቸውን እንዲገነቡ እና በእውቀት እንዲመሩ ተደርጓል። በዚህ ረገድ በዋነኛነት የሚጠቀሱት የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የፍትህ ተቋማትን የማደራጀትና ማጠናከር ስራ መከናወኑ ለአብነት ተጠቃሽ ነው።
የዲሞክራሲ ተቋማት ነጻ ሆነው በሁለት እግራቸው ቆመው የሚጠበቅባቸውን በመወጣት የተሳካ ምርጫ እንዲካሄድ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሀገራዊ ሀላፊነት አለባቸው። አሁን ባለው አቋማቸውም ይሄንን ኃላፊነት ይወጣሉ የሚል ተስፋ ተጥሎባቸዋል።
በዚህ ረገድ በሀገራችን ባለፉት ዓመታት በተካሄዱት አምስት ሀገር አቀፍ ምርጫዎች፤ ምርጫው ተአማኒ፣ ነጻ እና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ቢታሰብም በተግባር የታየው ውጤት ግን በተቃራኒው ነበር። በዚህም የዲሞክራሲ ተቋማቱና የአስፈጻሚው አካላት ብቃትና ተአማኒነት ጭምር ጥያቄ ውስጥ ወድቆ ቆይቷል። ይሄ ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ ዲሞክራሲ እንዲያብብ ሳይሆን እንዲቀጭጭ ምክንያት ሆኗል።
በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ይሄን በማይደግም መልኩ እንዲካሄድ ሰፊና የተጠናከረ ስራ እየተሰራ ይገኛል። ሙሉ ለሙሉ ዲሞክራሲ የሆነ ምርጫ ማካሄድ ባይቻል እንኳን ለዲሞክራሲ ምህዳሩ መሰረት የሚጣልበት ዘመን እንዲሆን በሁሉም ወገን ጥረት መደረግ አለበት። ውድድሩ በእውቀትና በአዋቂዎች የተመራ፣ በጥላቻ ላይ ሳይሆን በፖሊሲዎች የተቃኘ እና በተሻለ መልኩ የሀገርና የህዝብን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ሊሆን ይገባል።
በዚህ ምርጫ በአገር አቀፍ ደረጃ 55 ሺህ 220 ያህል የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚኖሩ ይጠበቃል። በእነዚህ ጣቢያዎች ሰላማዊ የሆነ ምርጫ ለማካሄድ እንዲቻልም በፌዴራልና በክልል ፖሊስ የሚመራ የምርመራ ዴስክ መቋቋሙ ተገልጿል። የሰለጠኑና ስልጠናውን መውሰዳቸውን የሚያረጋግጥ መታወቂያ የያዙ ፖሊሶች እና ነጻ ፍርድ ቤት የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ ይገኛል።
ፀጥታን በማስጠበቅ ለሚሳተፉ የፀጥታ ሃይሎች የሚለብሷቸው የደንብ ልብሶችና መታወቂያዎች እየተዘጋጀ ነው። ይሄ የሚያሳየው ምርጫው ነጻና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግስት ያለውን ቁርጠኝነትና ብቃት ነው።
በመሆኑም ምርጫው ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ ዲሞክራሲያዊ ሰላማዊና ያለምንም የፀጥታ ችግርና ሥጋት እንዲጠናቀቅ ሁሉም ፓርቲዎች የራሳቸውን ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ምርጫው የሚካሄደው በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንገዶች የስልጣን ሽግግር ለማድረግ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
መሸነፍና ማሸነፍ መኖሩን ማመንና መቀበል ይገባል። ይሄ እንዲሆን ደግሞ ሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በምርጫ ስነምግባር ደንቡና በህግ መመራት አለባቸው። ከጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ይልቅ የወደፊቱን የህዝብ አብሮነትና የአገር ሰላምን ማስቀደም ይጠበቅባቸዋል።
የፀጥታ ሃይሉ ከማንም ወገንተኛ ሳይሆን ምርጫው ነፃ እንዲሆን አቋም ይዞ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት መወጣት አለበት። ምርጫው ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅም ሁሉም ሀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2013