በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እንጀራ ከጄሶና ሰጋቱራ ጋር ተቀላቅሎ ለገበያ ሲቀርብ ተያዘ፣ በርበሬ ከሸክላ ጋር ተደባልቆ ሲቸበቸብ በቁጥጥር ስር ዋለ ፣ቅቤ ከሙዝ ፣ማር ከስኳር ጋር ተደባልቆ ሲሸጥ ተደረሰበት የሚሉና መሰል የወንጀል ዜናዎችን መስማት ተለምዷል፡፡
ከዚህ ባለፈም ከባእድ ነገሮች ጋር ተቀላቅለው ለገበያ የሚቀርቡ ምግቦች ተጠቃሚው ዘንድ በመድረሳቸው በሰዎች ጤና ላይ ጉዳት አስከተሉ ሲባልም ይደመጣል፡፡ ጊዜያቸው ያለፈባቸው፣ የመፈወስ አቅማቸው ደካማ የሆኑና ተመሳስለው በተመረቱ ህገወጥ መድሃኒቶች ምክንያትም በርካታ ሰዎች ለከፋ የጤና ጉዳት ሲጋለጡና አልፍ ሲልም ለሞት ሲዳረጉም ይሰማል፡፡
ህገወጥ ምግቦችና መድሃኒቶች ለገበያ ከመቅረባቸው እና በህብረተሰቡ ላይ የጤና ጉዳት ከማስከተላቸው በፊት ጥብቅ ቁጥጥር ሲደርግባቸውና በህገወጥ ንግዱ ተሳተፊ በሆኑ ግለሰቦች ላይ ዕርምጃዎች ሲወሰዱም አይታይም፡፡ በዚህም ምክንያት ባእድ ነገሮችን በምግቦች ውስጥ በመደባለቅ ለተጠቃሚዎች ማቅረብና ጊዜያቸው ያለፈባቸውንና የመፈወስ አቅማቸው ደካማ የሆኑ መድሃኒቶችን በህገወጥ መልኩ የመሸጡ ተግባር ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይታይም፡፡
ለህገወጥ የምግብና የመድሃኒት ንግድ እየተስፋፋ መምጣት የተለያዩ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ቢሆንም፣ በተለይም የቁጥጥር ስርዓቱ የላላ መሆኑና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ቅንጅታዊ አሠራር ደካማ መሆን የችግሩ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን በርካታ ወገኖች ይስማማሉ፡፡
ህገወጥ የምግብና የመድሃኒት ንግድን ለመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው የመንግሥት ተቋም የኢትዮጵያ ምግብ፣መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ሲሆን፤ ተቋሙ አስከአሁን ህገወጥ የምግብና የመድሃኒት ንግድን ለመቆጣጠር የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይሁንና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች የመንግሥት ተቋማት ጋር ጠንካራ ቅንጅት ፈጥሮ እየሠራ ባለመሆኑ ችግሩ በዘላቂነት ሊፈታ እንዳልተቻለ ይገለጻል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቋሙ ህገወጥ የምግብና የመድሃኒት ንግድ የቁጥጥር ስርዓትን ለማጠናከር ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ /flagship/ አቅዶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምሯል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥም ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉ ጠቋሚ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ የቁጥጥር ሥራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር እንዲያስችለውም ለመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ሰጥቷል፡፡
በኢትዮጵያ ምግብ፣መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የመድሃኒት ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዛኽኝ እንዳለው እንደሚገልጹት፤ የመድሃኒት ንግድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ 380 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይንቀሳቀስበታል፡፡ በኢትዮጵያም የመድሃኒት ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ በርካታ ገንዘብ ለመድሃኒት ግዢ ይውላል፡፡ ሆኖም ያዛኑ ያህል የህገወጥ መድሃኒት ንግዱም እየተባባሰ መጥቷል፡፡
ዳይሬክተሩ ባቋራጭ ለመክብር የሚደርግ ፍላጎት መጨመር፣ ተቆጣጣሪውና ህግ አስፈፃሚው አካል በኪራይ ሰብሳቢነት ውስጥ መግባት፣ ቀልጣፋና ዘመናዊ የቁጥጥር አገልግሎት አለመኖር፣ አብዛኛው የመድሃኒት አቅርቦት በውጭ ሃገር ተመርተው በሚገቡ መድሃኒቶች ላይ የተንጠለጠለ መሆንና የቁጥጥር ሥራው ወጥ በሆነ መንገድ በሰው ኃይል አደረጃጀትና በአሠራር የተጠናከረ አለመሆን ለህገ ወጥ የመድሃኒት ንግድ እየተባባሰ መምጣት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡
በየደረጃው ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ የቁጥጥር ስርዓትን ማጠናከር አለመቻልና የህብረተሰቡ ግንዛቤ በሚፈለገው ደረጃ አለማደጉም ለህገወጥ ንግዱ መበራከት የራሳቸውን አስተዋፅኦ አብርክተዋል ይላሉ፡፡
አቶ ገዛኸኝ እንደሚሉት፤ ከህገወጥ የመድሃኒት ንግድ ጋር በተያያዘ ወንጀሎችን የሚፈጽሙ ግለሰቦችን ለማስቀጣት የሚያስችል የመረጃ አያያዝ ክፍተት መኖር፣ በህግ የሚሰጡ ውሳኔዎች ከተፈፀሙ ወንጀሎች ጋር አለመመጣጠን ፣ በቂ መረጃ እያለ በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ አለመቻል የህገወጥ የመድሃኒት ንግድ ቁጥጥሩ ሳንካ ሆነዋል፡፡
በተለይም ህብረተሰቡ ችግሩን ተረድቶ ከተቆጣጣሪ አካላት ጋር አለመተባበሩ እና የህግ አካሉ የሚወስደው የቅጣት ዕርምጃ በቂ አለመሆኑ ችግሩ እየተባባሰ እንዲሄድ ሚና ተጫውተዋል፡፡
ህገወጥ የመድሃኒት ንግድን ለመከላከል በዋናነት ከፌዴራል አስከ ክልል ድረስ በቅንጅት የቁጥጥር ሥራውን ማጠንከር እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በተለይም በዘርፉ የሚታዩ ብልሹ አሠራሮችን ማስተካከልና ህብረተሰቡንም በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
ከህገወጥ የመድሃኒት ንግድ ጋር በተያያዘ በፍርድ ቤቶች ከሚቀርቡ ጉዳዮች ጥቂቶቹ ብቻ ውሳኔ እንደሚያገኙ ጠቅሰው፣ በዳኝነት በኩል የሚታዩ ውሳኔዎችን ማስተካከልና ጠበቅ ያሉ ዕርምጃዎችን በአጥፊዎች ላይ መውሰድ እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡ በህገወጥ የመድሃኒት ንግድ ላይ ሰፊ ጥናቶች ማካሄድ የሚቻል ከሆነ የችግሩን ምንጭ በማወቅ ተገቢውን መፍትሔ ማምጣት እንደሚቻልም ያመለክታሉ፡፡
የኢትዮጵያ ምግብ፣መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አማካሪ አቶ ወንድአፍራሽ አበራ በበኩላቸው እንደሚናገሩት ፤ በእንጀራ፣ በቅቤ፣ በማርና በበርበሬ ውስጥ ባእድ ነገሮች ተቀላቅሎባቸው የሚቀርቡ ምግቦች በህብረተሰቡ ጤና ላይ ክፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ፡፡
በአሁኑ ወቅትም በነዚህ የምግብ ዓይነቶች ውስጥ ባእድ ነገሮችን ቀላቅሎ ለተጠቃሚዎች የማቅረቡ ዝንባሌ እየጨመረ መጥቷል የሚሉት አማካሪው፣ ለዚህም ዋናውና ተጠቃሹ ምክንያት ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት አለመዘርጋቱና ይህን ተግባር በሚፈፅሙ ግለሰቦች ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ አነስተኛ መሆኑ ነው ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አማካሪው ገለጻ፤ በእንጀራ፣በቅቤ፣በማርና በበርበሬ ምግቦች ውስጥ ባእድ ነገሮች እየተቀላቀሉ ለገበያ የሚቀርቡ በመሆኑ በእነዚህ የምግብ ዓይነቶች ላይ ትኩረት በማድረግ መቆጣጠር አስፈልጓል፡፡ በቀጣይም በሌሎች የምግብ ዓይነቶች ላይም በማተኮር ቁጥጥሩ ይካሄዳል፡፡
የቁጥጥር ሥራው ኃላፊነት መውሰድን የሚጠይቅና ማበረታቻና ድጋፎችም የሌሉት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም በቀጣይ ሊስተካከልና ሊታሰብበት እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡ ከፖሊስ፣ ከደምብ ማስከበር እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋርም በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
አቶ ወንድአፍራሽ እንደሚሉት ፤ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ የመድሃኒት ምርቶች አንዴ የተመዘገቡና ከመካከለኛው ምሥራቅና ከእስያ ሃገራት የሚመጡ ከሆነ በቀጥታ መድሃኒቶቹ የሚመረቱባቸው ፋብሪካዎች ድረስ በመሄድ መድሃኒቶቹ በትክክለኛው መንገድ እየተመረቱ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ሆኖም የመድሃኒቶቹን አመራረት ለአምስት ዓመታት የማየትና የመከታተል ዕድል ላይኖር ስለሚችል ፤መድሃኒቶቹ ወደ ሃገር ውስጥ ሲገቡ በአየር ማረፊያ የመድሃኒት ናሙና በመውሰድ /consignment/ ምርመራ ይካሄዳል፡፡ ይህም መድሃኒቶች ጥቅም ላይ ከመዋላቸው በፊት ደህንነታቸውንና ጥራታቸውን ለማረጋገጥ ያስችላል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብ፣መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ ፤ ህገወጥ የምግብና የመድሃኒት ንግድን በአብዛኛው ለማስተካከልና ቁጥጥር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ያለውና የፍትሕ አካላትም እየደረሱ ያሉት ጉዳት ከደረሰ በኋላ ነው ይላሉ፡፡ ህብረተሰቡም በአብዛኛው ቅሬታዎችን የሚያቀርበው በማወቅም ሆነ ባለመወቅ ህገወጥ ምግቦችንና መድሃኒቶችን ከተጠቀመና በጤናው ላይ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
የዘመናዊ ቁጥጥር ስርዓት አንዱና ዋነኛው መንገድ ህብረተሰቡ የቁጥጥር ስርዓቱ ባለቤት እንዲሆን ማድረግ ነው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ባለቤትነቱንና ተሳታፊነቱን ለማረጋገጥ በህገወጥ የምግብና የመድሃኒት ንግድ እንቅስቃሴ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን በስፋት መስጠት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡ ይህንንም ለማሳካት የመገናኛ ብዙሃንን መጠቀም እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፤የተሻሻለው የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አዋጅ ሲፀድቅ የተቋሙም አደረጃጀት አብሮ የሚስተካከል ይሆናል፡፡ ህብረተሰቡም በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ የሃገር ውስጥ አምራቾችን የበለጠ ያበረታታል፡፡ በተለይም የንግዱ ህብረተሰብ ህገወጥ የምግብና የመድሃኒት ንግድን በመቆጣጠርና የህብረተሰቡን ጤና በመጠበቅ ረገድ ኃላፊነት እንዲሰማው ያደርጋል፡፡
ህብረሰተቡ ጥቆማዎችን በማቅረብ ዕርምጃ እንዲወሰድ ካልተባበረ በቀር ህገወጥ የምግብና የመድሃኒት ንግድን እንዲሁም ምግቦችን ከባእድ ነገሮች ጋር ቀላቅሎ የማቅረብ ተግባርን መግታት አይቻልም ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፣ የቁጥጥር ሥራውን ለማጠንከር ህብረተሰቡን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ፡፡ በተለይም ከፖሊስ ፣ ከንግድ ውድድርና ሸማቾች ባለስልጣንና ከደንብ ማስከበር ፅህፈት ቤት ጋር አብሮ መሥራት እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡ ህብረተሰቡ ለጉዳዩ ትኩረት እየሰጠ እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃንም ጉዳዩን እያቀጣጠሉት በሄዱ ቁጥር ችግሩን በዘለቄታው መፍታት እንደሚቻል ያስገነዝባሉ፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ እንደሚናገሩት፤ የህገወጥ መድሃኒትና ምግብ ቁጥጥር ስርዓቱ ለኪራይ ሰብሳቢነት በከፍተኛ ደረጃ የተጋለጠ ሲሆን፣ ከዚህ አኳያ በተለይ ስጋቱን ለመቀነስ ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋትና ስርዓቱን ማዘመን ያስፈልጋል፡፡ ስነምግባር በታከለበት መንገድና ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን መሥራትም ይገባል፡፡
ህብረተሰቡ የተቋሙን የቁጥጥር ሥራ በሚገባ እንደማያውቅ ጠቅሰው፣ ህገወጥ የምግብና መድሃኒት ግኝቶች ምን እንደሆኑና ምን ያህል የጤና ጉዳት ሊያስክትሉ እንደሚችሉ ማስገንዘብ እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ፡፡ ይህም ህብረተሰቡ በተቆጣጣሪዎች ላይ አመኔታ እንዲያሳድር በማድረግ ህገወጥነትን እንዲከላከል ማድረግ ያስችላል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 28/2011
አስናቀ ፀጋዬ