ወጥቶ ለመግባት፣ ወልዶ ለመሳምም ሆነ ዘርቶ ለመቃም ከምንም በላይ የሰላም መኖር የግድ ይላል፡፡ ሰላም በሌለበት ስለ ልማት ሊታሰብ አይችልም፡፡ የሰላም አለመኖር እስከ ህይወት መነጠቅ ያደርሳል፤ የአካል መጉደልና የንብረት መውደምም ያስከትላል፡፡እንደ ሀገር የሚደርሰው ቀውስ ደግሞ ሌላው አስከፊ ገጽታው ነው፡፡
እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ በኢትዮጵያ ምዕራቡ ክፍል ያጋጠመውን የሰላም መናጋት ተከትሎ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ወለጋ ዞን እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማሺ ዞን ችግሮች መከሰታቸው ይታወቃል፡፡ ይህን ተከትሎም በርካታ ሰዎች ቀዬቸውን ለቀው ሰላም አለ ብለው ወዳሰቡት አካባቢም መሰደዳቸው ይታወሳል፡፡
በአሁኑ ወቅት ግን በመንግስት፣ ችግሩ በተከሰተባቸው ክልሎች፣ በአባ ገዳዎችና በአገር ሽማግሌዎች ርብርብ በአካባቢዎቹ የሰላም አየር መንፈስ ጀምሯል፡፡ ይህንንና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘሪሁን ተክሌን አነጋግረናቸው እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡፡
ቀደም ሲል ዞኑ የነበረበት ሁኔታ
ከጥቂት ወራት በፊት በተፈጠረው የሰላም መናጋት ምክንያት በዞኑ በሰላም ወጥቶ መግባት አይታሰብም ነበር፡፡የመንግስት ተሽከርካሪዎችም ሆኑ ህብረተሰቡ የሚንቀሳቀስባቸው ተሽከርካሪዎች እንደ ልብ መዘዋወር አይችሉም ነበር፡፡ በዞን ደረጃ ያለው አመራር ወደ ወረዳና ቀበሌ ወርዶ ከህዝቡ ጋር የሚያደርገው ግንኙነትም ተገድቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በህሊና ደረጃ ሰው ይኖር የነበረው በስጋት ነው፡፡ በሰላም በቤቱ እንኳን መተኛት አይችልም፡፡ ማን ማንን እንደሚያስፈራራ እንኳ በቅጡ አይታወቅም፡፡ የማይታወቁ ሰዎች መንገድ ዘግተው ተሽከርካሪም ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ አድርገዋል፡፡ የፈለጉትን ነገር ከመኪና አስወርደው ይወስዳሉ፡፡
የመንግስት መስሪያ ቤቶች እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻሉም፡፡ በተለይ ደግሞ በወረዳ ደረጃ ያለው መዋቅርም ወደ መፍረስ ደርሶ ነበር፡፡ሰው ከቤቱ በማይታወቅ ኃይል ተወስዶ ይደበደብና ይዘረፍ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በዞኑ ከፍተኛ ስጋት ተከስቶ ነበር፡፡
በመጨረሻው አካባቢ ደግሞ ባንኮች ተዘርፈዋል፡፡ የመንግስት መስሪያ ቤቶችም ተቃጥለዋል፡፡ በተለይ ወደ ሰባትና ስምንት በሚሆኑ ወረዳዎች የሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ የወደሙበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ሰነዶች ተቃጥለዋል፡፡ ሌሎቹ እንዲወገዱና እንዲጠፉ ተደርጓል፡፡
ድርጊቱ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሶም ህብረተሰቡን አስደንግጧል፡፡ ከዚህም የተነሳ ህብረተሰቡ በመረበሹ ምክንያት የዕለት እንቅስቃሴውን ማድረግ ወደማይችልበት ደረጃ ደርሶ ነበር፡፡
መንግስት እንዲደርስለት ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ የጸጥታ ኃይሉም እንዲደርስለት ጠይቋል፡፡ ለጥሪው መሰጠት የነበረበት ምላሽ ከመዘግየቱ የተነሳ ብዙ ጥፋቶች ደርሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በዞኑ የሚገኙ ባንኮች ስራ ላይ አይደሉም፡፡ በዞን ደረጃ እንቅስቃሴ እያደረገ ያለው በጊምቢ ከተማ የሚገኝ አንድ ባንክ ብቻ ነው፡፡ ወደ ስድስት የሆኑ ባንኮች ተዘርፈዋል፤ ይሰሩበት የነበረው ሲስተምም ተበላሽቷል፡፡ በመሆኑም እንቅስቃሴ መጀመር አልቻሉም፡፡
ሌሎች ባንኮች ደግሞ በጸጥታ ስጋት የተነሳ በአሁኑ ወቅት ዝግ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ የህብረተሰቡ የእለት ተዕለት እንዲሁም የንግድ እንቅስቃሴ ተገድቧል፤ የመንግስት ሰራተኛው የወር ደመወዙን የሚያገኝበት ሁኔታ የለም፡፡
አሁን የተፈጠረው ሰላም ማሳያ
በአሁኑ ወቅት በየወረዳው ተሽከርካሪዎች መግባት ችለዋል፡፡ ህብረተሰቡ የሚመላለስ ባቸው መኪናዎች በሰላም ወጥተው በሰላም ይገባሉ፡፡ አገር አቋራጭ ትራንስፖርቶችም ይመላለሳሉ፡፡ ህዝቡም የትራንስፖርት አገልግሎት በትክክለው መንገድ እያገኘ ነው፡፡
በዞኑ 20 የገጠር ወረዳዎችና ሶስት የከተማ ወረዳዎች አሉ፡፡ የጸጥታ ኃይሉ ሁሉም ዘንድ ገብቷል፡፡ ይህም በመሆኑ ህዝብ የሚረብሹ ሀይሎች አሁን የሉም፤ አንዳንዶቹም በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ በተለያየ አካባቢዎች ሽማግሌዎችን፣ አባገዳዎችን፣ ቄሮዎችን፣ የመንግስት ሰራተኞችንና ሴቶችን ያካተቱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚገኙባቸው ውይይቶች ተደርገዋል፡፡
በውይይቱ ህብረተሰቡ ሰላም ፈላጊ መሆኑን መረዳት ተችሏል፡፡ መንግስት የጸጥታውን ኃይል ባለማሳተፉ ችግሩ መድረሱን ህብረተሰቡ በመድረኮቹ ተናግሯል፡፡ የጸጥታው ኃይል ከደረሰላቸው በኋላ ግን ህብረተሰቡ ከመንግስትና ከጸጥታው ኃይል ጋር ሆኖ በየጊዜው ህዝቡን ሲረብሹና መንገድ ሲዘጉ የነበሩ አካላት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል፡፡ አንዳንዶቹ ጉዳዩ ተጣርቶባቸው ወደ ስልጠና እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ሌሎች ደግሞ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፤ በህግ ይጠየቃሉ፡፡
አሁን ላይ ያለው አሳሳቢው ችግር
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስራ አለመጀመሩ የዞኑ አሳሳቢ ችግር ሆኗል፡፡ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በዞናችን ደረጃ በየገጠር ወረዳ ያሉ ባንኮች ስራ ላይ ያለመሆናቸው ነው፡፡ ያልተዘረፉትም ቢሆኑ ሌሎቹ ስለተዘረፉ ብቻ ‹‹እኛ የእነሱ እጣ ፈንታ ያጋጥመናል ›› በማለት አልከፈቱም፡፡ የተዘረፉትም ደግሞ ኦዲት እስከሚደረግ ድረስ ስራ ማስጀመር አይቻልም እያሉ ናቸው፡፡
ያልተዘረፉትም ቢሆኑ ገንዘብ ጭነው ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ለመውሰድ ስጋቱ ስላለቀቃቸው ‹‹ገንዘብ ማስገባት አይቻልም›› ብለውናል፡፡ እኛም ይህ ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ ነቀምቴ ላለው ዲስትሪክት ማመልከቻ ጽፈን ጠይቀናቸዋል፡፡ በኛ ዞን አሁን ባንክ ያለው ጊምቢና ነጆ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ በሁለቱ ባንኮች ገንዘብ ገብቶ ህብረተሰቡ እንዲጠቀም ጠይቀናቸዋል፡፡
ይሁንና የነቀምት ዲስትሪክት የሚመለ ከታቸው ኃላፊዎች ‹‹እኔ ገንዘብ ጭኜ ወደ ጊምቢ ለመውሰድ ኃላፊነቱን አልረከብም›› ይላሉ፡፡ ጊምቢ ያለው ቅርንጫፍ ጽሀፈት ቤት ደግሞ ከዚህ ቀደምም ችግር ስለነበር ‹‹የጸጥታው ኃይል ቢያጅበኝም ኃላፊነቱን ተቀብዬ ከነቀምቴ ዲስትሪክት ገንዘቡን ማውጣት አልችልም›› ይላል፡፡
ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ለሰራተኛው የሚከፈለው የወር ደመወዝ የለም፡፡ በመሆኑም በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡ ሰራተኞች ምንም እንኳን የወር ደመወዛቸውን ወር ከገባ ከሃያ ቀን በኋላ ያገኙ የነበረ ቢሆንም እስካሁን የጥር ወር ደመወዝ አልተከ ፈላቸውም፡፡
መከፈሉ ብቻ ሳይሆን አሁን አሳሳቢው ነገር የትና ከየትኛው ቦታ እንደሚከፈልም እርግጠኛ መሆን አለመቻሉ ነው፡፡ ለምሳሌ የተዘረፉት ስድስት የመንግስት ባንኮች ናቸው፡፡ በመሆኑም እነሱ አሁን ስራ መጀመር አልቻሉም፤ ምክንያቱም የተዘረጋው ሲስተም ሁሉ ምስቅልቅሉ የወጣ ነው፡፡ ኦዲትም ይደረጋሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡
አሁን ያለው ችግር የተዘረፉ እንደተዘረፉ ሆነው እንኳ በሚሰሩ ባንኮች ውስጥ ምንም አይነት ገንዘብ አለመኖሩ ነው፡፡ ገንዘብ ከጠፋ ወደ ሁለት ወር በማስቆጠር ላይ ነው፡፡ ከዛ ቀደምም ቢሆን ሰራተኛው ገንዘብ እንዲወስድ የተፈቀደለት እስከ 500 ብር ብቻ ነበር፡፡ ወረዳ ባንኮች ከ500 ብር በላይ የማይከፍሉበት ምክንያት ደግሞ በመንገድ ላይ ሲደረግ የነበረው ዘረፋና ምዝበራ ስለነበር አሁንም ድረስ ከስጋት ባለመላቀቃቸው የተነሳ ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም ገንዘብ ተገቢውን ሂደት ተከትሎ ወደ ባንክ እየገባ አይደለም፡፡ ይህ በጣም አሳሳቢ ሆኖብናል፡፡
ዞኑ ያቀረበው የመፍትሄ ሐሳብ
እኛ መፍትሄ ነው ብለን ያልነው ነቀምት ዲስትሪክት ከዞኑ የፋይናንስ ኃላፊ ዘንድ ማመልከቻ አስገብተናል፡፡ ጊምቢ ካለው ቅርንጫፍ መስሪያ ቤትም ዘንድ ማመልከቻ አስገብተናል፡፡ ለጊምቢ ኮማንድ ፖስትም አሳውቀናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለጸጥታው ጉዳይ እንኳ የምንሰራበት ገንዘብ የለም፡፡ የመንግስት ሰራተኛውም ቢሆን ከጊምቢ መውሰድ የሚችለው ግፋ ቢል እስከ ሁለት ሺ ብር ብቻ ነው፡፡
ስለዚህ እኛ ያስቀመጥነው ጉዳይ ከስድስት ያህል ወረዳዎች ባንኮች ተዘርፈዋል፡፡ በዛ አካባቢ ፔሮል አዘጋጅተው የነቀምቴ ዲስትሪክት ደግሞ ገንዘብ ወደ ጊምቢ ቅርንጫፍ አስገብቶ ከጊምቢ ደግሞ የጸጥታ ኃይሉ አጅቦ ወደየወረዳዎቹ በመውሰድ በፔሮል እንዲከፍሉ መንገድ እየቀየስን ነው፡፡
ይሁንና የጊምቢ ቅርንጫፍ የሚሰጠው ሃሳብ ግን ከነቀምቴ ይወሰድ የሚል ነው፡፡ የዞኑ ፋይናንስ ጽህፈት ቤት ደግሞ ‹‹ይህ አሳማኝ አይደለም፤ እንዴት ብዬ ነው ሰራተኛውን ወደ ሁለት መቶና ከዛ በላይ ኪሎ ሜትር ተጉዞ ገንዘብ ይዘህ ግባ የምለው›› ሲል ስጋቱን ያጋራል፡፡ የዞናችን ኮማንድ ፖስት በጸጥታው ዘርፍ ለማጀብ ዝግጁ መሆኑን ግን ገልጾልናል፡፡
ሰላም ሰፍኗል እየተባለ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ያስቸገረበት ምክንያት
በአሁኑ ወቅት ከቦታ ቦታ መዘዋወር ይቻላል፤ ምንም ችግር የለም፡፡ ባንኮች የሰጉበት ምክንያት ከዚህ ቀደም በቄለም ወለጋ ውስጥ የሞቱና በመንገድ ላይ የተዘረፉ የባንክ ሰራተኞች መኖራቸውን ነው፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ በዞናችን ውስጥ ወደ ስድስት የሚሆኑ ባንኮች መክፈል የሚያስችላቸው ስርዓት በመበላሸቱ እንዲሁም ያለው ሰነድ በመጥፋቱ ሂደቱን ማስቀጠል አልተቻለም የሚል ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ዘረፋና የሲስተም መበላሸት ከዚህ በፊት የተፈጠረ መሆኑ ቢታወቅም ባንኮቹ አሁንም ስጋቱ እንዳላቸው ነው ኃላፊው የሚናገሩት፡፡ ለሰራተኛውም ህይወት ኃላፊነትን እንደማይወ ስዱም አስረድተዋል፡፡
አሁን ያለው የጸጥታ ሁኔታ መሻሻሉንና በሰላም ወጥቶ መግባት እንደሚቻል እንዲሁም በመንገድ ላይ የሚያጋጥም ፈተናም እንደሌለ እና የጸጥታው ኃይል ሁሌም ዝግጁ ነው ብለን ብናሳውቃቸውም አሁንም ስጋት እንዳላቸው ነው ምላሽ የሚሰጡን፡፡
በዞኑ የተረጋጋ ሁኔታ በመኖሩ ባንኮች ከስጋት ቢወጡ
አሁን በዞኑ የተረጋጋ ሁኔታ አለ፡፡ መንገዱ ሰላማዊ ነው፤ የመንገድ ላይ ዝርፊያም ሆነ የግለሰብ ንብረት ሲዘረፍ አይስተዋልም፡፡ የአገር ሽማግሌዎችም ጉዳዩን በመፍታቱ ረገድ ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፡፡ ከምንም በላይ ዋናው ነገር መንገዱ ነጻ መሆኑ ነው፡፡
በዞናችን ውስጥ ባሉ ሃያ የገጠር ወረዳዎችና ሶስት የከተማ ወረዳዎች ሁሉ የኦሮሚያ ፖሊስና ልዩ ኃይል አለ፡፡ አንዳንድ በሚያሰጉ አካባቢዎች ደግሞ መከላከያም አለ፡፡ በተለያዩ የገጠር ቀበሌዎችም ሆነ ከተማ አካባቢ የጸጥታ ኃይሉ በአግባቡ እየተንቀሳቀሰና ፍተሻ እያደረገ ይገኛል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል እና ከዞናችንም የተውጣጡ አመራሮች በአንዳንድ ወረዳዎች በመገኘት እስካሁንም ህብረተሰቡን እያወያዩ ናቸው፡፡ ይህም ከተጀመረ ወደ ሶስት ሳምንታት ያህል አስቆጥሯል፡፡ ስለዚህም የባንክ እንቅስቃሴ ለማድረግ በዞናችን ውስጥ አስተማማኝ ሰላም በመኖሩ ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም፡፡የንግድ ባንክ ያለምንም ስጋት የገንዘብ እንቅስቃሴውን ቢያደርግ መልካም ነው፡፡
በተረፈ ሁሉም ነገር ተስተካክሎ በአግባቡ እየሄደ ይገኛል፡፡ የመንግስት ሰራተኛውም በአሁኑ ወቅት የሚገኘው በስራ ገበታው ላይ ሆኖ ነው፡፡ ህብረተሰቡም በሰላም ወጥቶ እየገባ ይገኛል፡፡ አዳዲስ አመራሮችም በዞንና በወረዳ ደረጃ ተመድበው እየሰሩ ናቸው፡፡
ሌሎች እንደ አዋሽና መሰል ባንኮች ስራ ላይ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ስራ ላይ የሌለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ነው፡፡ ስጋቱን ወደ ጎን በመተው በተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት በመጠቀም ገንዘብ ወደ ባንክ በማስገባት ህብረተሰቡ እንዲጠቀም ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ የግል ባንኮችም እንዲሁ ቢያደርጉ ተመራጭ ነው፡፡
በየትኛውም የዓለም ክፍል ጦርነትም ሆነ የጸጥታ ችግር ቢኖርም የባንክ እንቅስቃሴ የዚህን ያህል አይቆምም፤ የባንክ እንቀስቃሴ ቆመ ማለት ግን የመንግስት ስራም ቆመ ማለት ነው፡፡ እኛ በአሁኑ ሰዓት ሙሉ ለሙሉ ወደ ልማት ለመግባት ተዘጋጅተናል፡፡ በሙሉ አቅማችን ወደ ልማት እንዳንገባ ገንዘብ በባንክ ውስጥ የለም፡፡ይህንን ችግራችንን አይቶ መንግስት መላ ይበለን እንላለን፡፡
በዞኑ የሚገኙ የተፈናቃዮች ሁኔታ
በዞናችን ውስጥ ወደ 102 ሺ የሚሆኑ ተፈናቃዮች አሁንም 33 በሚሆኑ መጠለያዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እርዳታ እየቀረበላቸው ነው፡፡ ተፈናቃዮቹ ወደ ዞናችን ለመጠለል የመጡት ከኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ድንበር አካባቢ ነው፡፡
እነዚህ ተፈናቃዮች ቀደም ሲል የጸጥታው ጉዳይ አሳሳቢ በመሆኑ እርዳታ ለማግኘት ይቸገሩ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የሰላሙ ሁኔታ መልካም በመሆኑ ማንኛውም መኪና እርዳታ ይዞ መግባት ይችላል፡፡ ይሁንና እርዳታ መግባት ቢችልም ዛሬም ድረስ ስጋት ያለ የሚመስላቸው አካላት በመኖራቸው ሰላም መስፈኑን ላረጋግጥ እወዳለሁ፡፡
አንድ ችግር ነው ብዬ መናገር የምፈል ገው ነገር ቢኖር በተለይ ከካማሼ ዞን ተፈናቅለው በዞናችን የተጠለሉ የመንግስት ሰራኞች ደመወዝ ሳያገኙ ወደ አምስት ያህል ወር ማስቆጠራቸውን ነው፡፡፡ በአሁኑ ወቅት እኛን እያስቸገረ ያለው የመንግስት ሰራተኛው ጥያቄ ነው፡፡ ደመወዝ ሳይከፈላቸው የቆዩ የመንግስት ሰራተኞች በየጊዜው እየመጡ ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ስለ እነሱ ጉዳይ የመንግስትን ምላሽ እየጠበቁ ናቸው፡፡
ተፈናቅሎ የመጣው የመንግስት ሰራተኛውም ሆነ አርሶ አደሩ ወደየመጣበት እንዳይመለስ ሰላም እንደሌለ ተፈናቃዮች የሚናገሩ ሲሆን፣ አርሶ አደሩም ምርቱን በአግባቡ በማምረት ተጠቃሚ ይሆን ዘንድ ‹‹መከላከያ ይደግፈንና እንመለስ እያለ ነው ›› የሚል ጥያቄ እያነሱ ናቸው፡፡ እኛም ድጋፍ ማድረግ ጀምረናል፡፡
ተፈናቃይ አርሶ አደሮች በሰላም መታጣቱ ምክንያት ወደመጡበት ቀዬ ተመልሰው ሰብላቸውን መሰብሰብ ባለመቻላቸው ሳቢያ ሰብሉ እየተበላሸና እየረገፈ መሆኑን በመጥቀስ ያለቀው አልቆ ማሽላውንና ዳጉሳውን መሰብሰብ ያስችላቸው ዘንድ መመለስ እንደሚፈልጉ እየገለጹ ናቸው፡፡ለዚህም የመከላከያ ኃይሉ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው እኛን አጥብቀው በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ተሽከርካሪዎች ከእኛ ዞን ወደ ካማሺ ዞን እየገቡ ናቸው ናቸው፡፡ ይሁንና የዚያን ያህል አስተማማኝ ነው ብሎ መናገር አያስችልም፡፡
ለተፈናቃዮች ድጋፍ የሚያስፈልግ ስለመሆኑ
በአሁኑ ወቅት በዞናችን የተፈጠረውን መረጋጋት ተከትሎ በዞኑ ላሉ ተፈናቃዮች የሚያስፈልገውን እርዳታ በአግባቡ ማስገባት እንዲቻል እርዳታ ሰጪዎች የበኩላቸውን እንዲያደርጉ እንሻለን፡፡ ለክልሉ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ሁኔታውን አሳውቀናል፡፡ ተፈናቃዩ ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ ከዞኑ አዋሳኝ ቦታ የተፈናቀሉትም ወደ ቦታቸው ለመመለስ የተቃጠለባቸውን ቤት መስራትን ይጠይቃል፡፡ የጠፋባቸውንና የወደመባቸውን ንብረቶቻቸ ውንም መመለስ እና መተካት ያስፈልጋል፡፡ ይህን ሊያስፈጽምና ሊያስተባብር የሚችል መዋቅር ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ወረዳና ዞን ድረስ ሊቋቋም ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡
በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ውስጥ ያሉትን ለመመለስ የሚያዳግተን ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም የጸጥታው ሁኔታ መልካም ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ እንቅስቃሴ ግን መንግስት አቅጣጫውን ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡ ይህ ከሆነ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ውስጥ መመለስ የሚችሉት የትኞቹ ናቸው የሚለውን በመለየት ተፈናቃዮቹን የማቋቋም ስራ መጀመር ይቻላል፡፡
የዞኑ አመራሮች ተጠያቂነት
በየወረዳው ያሉ የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና ሌሎችም በጉዳዩ ላይ በመምከር ጥቂት በማይባሉ አካላት ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡ የተወሰደውም እርምጃ ለምሳሌ አመራሩን በመገምገም ስራቸውን በአግባቡ ባልተወጡና በትክክለኛው መንገድ መጓዝ ባልቻሉ ሰዎች ላይ ነው፡፡ እነሱንም ከአመራርነት በማንሳት በምትካቸው ከክልሉ በመጡ አመራሮች እንዲተኩ ተደርገዋል፡፡
በየዞኑ ተገምግመው በኦሮሚያ ከተመደቡ አመራሮች የዞን የጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ተመድበዋል፡፡ ወደ 15 የሚሆኑ የአመራር ቦታዎች በዞናችን ምደባ ተካሂዷል፡፡ በዞኑ ባሉት 20 የገጠር ወረዳዎችና በሶስት የከተማ ወረዳዎች ያለው አመራር በተለይ የላይኛው አመራር በአዲስ መዋቅር ተገንብቷል ማለት ይቻላል፡፡
የዞኑ አመራሮች ስልጠና እየወሰዱ ስለመሆናቸው
በዞኑ ያሉ ሌሎች አመራሮች ደግሞ በአሁኑ ወቅት ወደ ስልጠና ገብተዋል፡፡ ከስል ጠናው በኋላ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚታወቅ ነገር ባይኖርም በጥቅሉ ግን በዞኑና በወረዳው ያለው መዋቅር አዲስ ቁመና እንዲይዝ ከስልጠናው በኋላ ምደባ ይደረጋል ማለት ነው፡፡
ወደ ስልጠናው ከመገባቱ በፊት በስልጠናው ተሳታፊ እንዲሆኑ የተፈለገው ሁሉም አመራሮች ቢሆኑም ቆይቶ ግን የተወሰኑ በገጠር አካባቢ በውሃ፣ በትምህርት፣ በመንገድ፣ በጤናና በሌላውም ላይ ስራዎችን የሚያከናውኑ እንዲሁም በከተማው አካባቢ ደግሞ በንግድ ጽህፈት ቤት እና በጥቃቅንና አነስተኛ ላይ የተሰማሩ እንዲሁም የወረዳና የዞን አመራሮች ወደ ስልጠናው እንዲገቡ ተደርገዋል፡፡ በየወረዳው ያሉ አምስት ስራ አስፈጻሚዎችም እንዲሁ በስልጠናው የተካተቱ አካላት ሆነዋል፡፡
መልዕክት
ድጋሚ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በአሁኑ ወቅት በጣም አሳሳቢና አስቸጋሪ የሆነብን የገንዘብ ዝውውር ነው፡፡ የመንግስት የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዚህ አስከፊ በሆነ ችግር ወቅት ህብረተሰቡን ማገልገል ካልቻለ ወደፊት በህብረተ ሰቡ ዘንድ የሚኖረው አመኔታ ይቀንሳል፡፡ ህብረተሰቡ በባንኩ ላይ ያለውን አመኔታ እያጣ ይሄዳል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራሮች በአስቸኳይ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል እላለሁ፡፡ ለምሳሌ መምህራን አሁን የእረፍት ጊዜያቸው እንደመሆኑ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ወዳጅ ዘመዶቻቸውን መጠየቅ ይፈልጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ የጥር ወር ደመወዛቸውን ካላገኙ ወደየትም መንቀሳቀስ አይችሉም ፡፡
በተመሳሳይ ዞናችን ቡና አብቃይ ወረዳዎች አሉት፡፡ ዞኑ በቡናው በኦሮሚያ ክልልም ይታወቃል፡፡ ዞኑ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ከሚያቀርቡ ዞኖች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡
ወቅቱ የቡና ግብይት የሚካሄድበት ነው፡፡ ይሁንና ነጋዴው ከባንክ የሚያወጣው ገንዘብ የለም፡፡ በመሆኑም አርሶ አደሩ ደግሞ ቡናውን ወደ ገበያ አውጥቶ በተመጣጣኝ ዋጋ መሸጥ አይችልም ማለት ነው፡፡ በተመጣጣኝ ዋጋ ካልሸጠ ደግሞ ለመንግስት ግብር ለመክፈል ይቸገራልና ይህ ችግር ሊፈታ ይገባል፡፡ ስለዚህ መንግስት በተለይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ መፍትሄ ሊሰጠን ይገባል የሚል መልዕክት አለኝ፡፡ ህብረተሰቡ እንዳይቸገርና የንግድ እንቅስቃሴውም እንዳይቆም በጥቂት ቀናት ውስጥ ይስተካከልልን ስንል ጥሪ እናቀርባለን፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 28/2011
አስቴር ኤልያስ