ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አቶ በላይነህ ክንዴ ወደ ንግዱ ዓለም የገቡበት አጋጣሚ የሕይወትን አስቸጋሪ ገጽታ ለመሻገርና እና ከአልረታም ባይነት የመነጨ የሥራና ሀገር ወዳድነት ስሜት የመነጨ ነው።12ተኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በ1980 ዓ.ም ወደ ሁርሶ ጦር ትምህርት ቤት ሄደው የመኮንነት ስልጠና ወስደው በቀድሞ ጦር ውስጥ በመግባት እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ እስከ መቶ አለቃ ማዕረግ ድረስ አገልግለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕዴግ) የቀድሞ ጦር ሠራዊትን በ1983 ዓ.ም ሲበተን የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ከተበተኑት የሰራዊቱ አባላት አንዱ ናቸው።እንደማንኛውም የሰራዊት አባል የዕለት ጉርስ ስላልነበራቸው በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል።
ከ1983 ዓ.ም እስከ 1984 ዓ.ም ዓ.ም ሚያዚያ ድረስ ለአቶ በላይነህ ነገሮች እጅግ ፈታኝ ነበሩ።በዚህ ወቅት በአራት ብር የቀን ሥራ እየሰሩ ራሳቸውን ለማሸነፍ ጥረት አድርገዋል።ኮኮብ ዱቄት ፋብሪካ ውስጥ ደግሞ 75 ብር ወርሃዊ ደመወዝ እየተከፈላቸው ኑሮን ለመደጎም ሞክረዋል።ይህ የማይረሳ ትውስታቸው ግን ለዛሬ ማንነትና ጥንካሬ ምንጭ የሆናቸው የሕይወታቸው አይረሴ አካል ነው።
በወቅቱ እናታቸው የቡና ንግድ ፈቃድ ነበራቸው።ያኔ! ከጎጃም መጥተው በዕጣ አንድ መኪና ቡና ደርሷቸው 10ሺ ብር አትርፈው ሸጡ።በዚህ ጊዜ እናትየው ልጃቸው በላይነህን ከሚኖርበት ሳሪስ አካባቢ ፈልገው አገኙት።እናትየው ባተረፉት ብር ልጄ! እራስህን ደጉመህ፤ ቤተሰብም አግዝ ብለው መከሯቸው።ከዚያ ጉዞ ወደ አገር ቤት ሆነ።
10 ሺ ብር ከእናታቸው ወስደው ሚዛን እና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን ገዙ።ከ10ሺ ብር ውስጥ 4ሺ600 ብር ቀራቸው።በዚህ ሥራውን በሚገባ ጀመሩት።በዚህን ጊዜ ከጎጃም ማር እና ቅቤ እየገዙ ወደ አዲስ አበባ ይዘው ይመጡና በአንድ ኪሎ እና ሁለት ኪሎ አከፋፍለው ይሸጡ ነበር።በዚህም ሥራ በወቅቱ ብዙ ተፎካካሪ ስላልነበራቸው በጣም ትርፋማ ነበሩ።
በዚህ ወቅት ማር እና ቅቤውን ከፋፍሎ ለመሸጥ እንኳን አነስተኛ ሚዛን አልነበራቸውም።ታዲያ አንድ ሱቅ ያለው ግለሰብ ጠጋ ብለው ማታ ሥራውን ካጠናቀቀ በኋላ ሚዛኑን ለአቶ በላይነህ በነፃ ይመዝኑበት ዘንድ ይሰጣቸው ነበር።እርሳቸው ማታ መዝነው ጠዋት ሚዛኑን ለባለቤቱ ይመልሱ ነበር ።ከዚያ ያንን በዘንቢል እያዞሩ ለደንበኞቻቸው ያከፋፍሉ ነበር።ወደ ጎጃም ሲመለሱ ደግሞ ሸቀጣ ሸቀጦችንና ለአገሬው አስፈላጊ የሆኑ የኢንዱትሪ ምርቶችንና የእንስሳት መድኃኒቶችን ጭነው ወደ ጎጃም ይሄዳሉ።
አቅማቸው እየጠነከረ ሲሄድ ደግሞ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፍኖተ ሠላም ቅርንጫፍ 30ሺ ብር የእናታቸው ቤት እንደዋስትና ተይዞ ብድር አገኙ።በዚህ መሐል ከጎጃም አዲስ አበባ ብዙ ምልልሶች የነበሩ ሲሆን በጭነት መኪና ከላይ ሆነውም ይሄዱ ነበር።እስከ 1992 ዓ.ም ድረስ በዚህ ንግድ ላይ ቆዩ።በዚህ ሥራ ውስጥ እያሉ 300ሺ ብር የሚደርስ ሀብት ማፍራት ቻሉ።
በሂደት ደግሞ 45 ሰዎችን የመጫን አቅም ያለው አንድ የሕዝብ አውቶብስ 180ሺ ብር ገዝተው ወንድሞቻቸው እንዲሰሩበት አደረጉ።ግን መኪናው አትራፊ አልነበረም። በተደጋጋሚ ሞተር ሲነክስ ከገቢው ወጪው በዛ።ከዚያ መኪናውን ሸጠው በዚሁ ሰበብ ጠቅልለው ወደ አዲስ አበባ ገቡ።
በመቀጠል አዲስ አበባ መጋዘን ተከራይተው የማር እና ቅቤ ንግድ ማጧጧፍ ጀመሩ።ይህን እየሰሩ ሁለት ጓደኞቻቸው የቅባት ምርቶችን ወደ ውጭ የመላክ ሥራ እንስራ ብለዋቸው አብረው መሥራት ጀመሩ። በዚህ ጊዜ የአቶ በላይነህ ባለቤት ማር እና ቅቤውን መነገድ ጀመሩ።አቶ በላይነህ ደግሞ ከአራት ዓመት በኋላ ከጓደኞቻቸው ጋር የጀመሩትን ሥራ በየግላቸው ጀመሩ።
በሂደት በላይነህ ክንዴ ላኪ እና አስመጪ የሚል ድርጅት ተመሰረተ።የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም አቶ በላይነህ ክንዴን የሕይወት ተሞክሯቸውን፣ አጠቃላይ የቢዝነስ እንቅስቃሴና ቀጣይ ፕሮጀክቶች ላይ እንግዳ አድርጓቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- ድርጅታችሁ በበርካታ ሥራዎች ስኬታማ እየሆነ የመጣበት ምስጢር ምንድን ነው?
አቶ በላይነህ፡– የሰው ልጅ ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ ቦታ መድረስ ይችላል።ምስጢሩ ደግሞ ታታሪነት ነው።የእኛ መፈክር የታታሪዋ ኢትዮጵያ ምልክት ነን ብለን እናስባለን።ላለፉት 29 ዓመታት ያለመታከት ሰርተናል።የእኔ ባህል ድርጅቱና የማኔጅመንት አባላት ተላብሰውታል።
ታታሪ፣ መዝኖና ትጉህ ሆኖ በመስራት ስኬታማ ሆነናል። ክፍለሃገር ሆኜ ቅዳሜ ገበያን ላለማቋረጥ ዓርብ ሌሊት በጭነት መኪና ከላይ ሆኜ ስሄድ አድራለሁ።ስንመለስ ደግሞ ጥራት ያለው ማር እና ቅቤ ለከተሜው እናቀርብ ነበር።በዱቤ የወሰድኩትንም በእምነትና በፍጥነት እመለስ ነበር።ሌላው ምቀኛ አለመሆንና መልካም ምሳሌ መሆን ነው።ለራስ ተጠቅሞ ሌላውንም መጥቀም ነው።
አዲስ ዘመን፡- የድርጅታችሁን ስም በውጭና በሀገር ውስጥ ለማንገስ ምን አሰራር ትከተላላችሁ?
አቶ በላይነህ፡- እንግዲህ ተባብሮ መሥራት ሲባል ብዙ ነገር አለ። በግብይት ውስጥ ገዥና ሻጭ አለ።በዚህ ውስጥ መተማመን አለበት። እኛ ከአርሶ አደር እና መካከለኛ አርሶ አደር እንገዛለን። የምርት ግብይት ሳይኖር ቀጥታ ግብይት እናካሂድ ነበር። ብር እንኳ ቢያንሰን በእምነት ይሰጡን ነበር።ወለጋ ጉትን፣ ሁመራ ያሉ አርሶ አደሮችን እና መካከለኛ ነጋዴዎችን በመጠየቅ እውነታውን ማረጋገጥ ይቻላል።እህላቸው ሲረክስ ገበያ እንድንፈልግ የሚጠይቁ አርሶ አደሮችም ነበሩ።
መንግስትም በእኛ ላይ እምነት ነበረው።በኢትዮጵያ ታሪክ ወደ ውጭ የግብርና ምርት በብዛት የሸጥነው እኛ ነን።በ2005 ዓ.ም አንድ ሚሊዮን ኩንታል በቆሎ ለጣሊያን ገበያ አቅርበናል።
በአንድ ሳምንት 460ሺ ኩንታል በቆሎ መርከብ ላይ ሞልተን ልከናል።ይህ የሆነው የግዥ እና የሎጂስቲክስ ሥርዓታችን የተቀላጠፈ በመሆኑ፣ ለመንግስት፣ ለድርጅቶችና አርሶ አደሮች ታማኝ ሆነን በመሥራታችን ነው።ቻይና ስንሄድም በሰሊጥ ገበያው ላይ በላይነህ ክንዴ ምን አለ? እስከማለት ደርሰዋል።የምንሰራውም የሀገርን ገፅታና ክብር በጠበቀ መንገድ ነው ።አሁንም ይህን ማዕከል ባደረገ መንገድ እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቡሬ የተገነባው የዘይት ፋብሪካ ፈተናዎች የበዙበት ነበር ይባላል ።እንዴት ታለፈ?
አቶ በላይነህ፡- የእኔ፣ የድርጅቱ፣ የማኔጅመንቱ እና ሰራተኛው መለያ ታታሪ መሆን ነው።ሌላው ከባንኮች፣ መንግስትና ተቋማት ጋር ያለን ግንኙነት መልካም ነበር።ይህም ፕሮጀክቱን እንድናጠናቅቅ አግዞናል።መንግስት የዘይትን እጥረት ለመፍታት ቁርጠኛ ነው።እኛም ስንነሳ የበለጠ ቁርጠኞች ሆነን ነው።
የውጭ ሰዎች የሚመጡት ትርፍ ይዘው ለመሄድ እንጂ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስተዋፅዖ ለማድረግ አይደለም።ከዚህ አስተሳሰብ በመነሳት ሁላችንም ተደጋግፈን ፋብሪካው እንዲሰራ አድርገናል።
በእኛ በኩል ፈታኝ ሁኔታ ነበር።ያለፉት ስድስት ዓመታት ለእኛ እንደ ምጥ ነበር። ትልቅ ፕሮጀክት ነው።በሀገራችን ደግሞ ብዙ ችግሮች አሉ።ቢሆንም በፅናት ለማለፍ ችለናል።ከሚደግፈው በላይ የሚጠልፈውም ይበዛል።መልካም አስተሳሰብ የሌለው ቡድን አለ።ይህን ማሸነፍ በራሱ ቀላል አይደለም።ይህ ፕሮጀክት እንዴት ተጀመረ፣ እንዴት ተከናወነ፣ እንዴትስ ተጠናቀቀ የሚለው በራሱ ሰፊ ነው።
በኢትዮጵያ 110 ሚሊዮን ይዘን በቀን 50 ቶን ዘይት ብቻ የሚያጣራ ፋብሪካ ነበር ያለን።ከጎረቤት ሀገራት አኳያ ሲታይ ምንም እንደሌለን ነው።የምንጠቀመው 99 ከመቶ ከውጭ በሚመጣ ግብአት ነበር።በሀገር ውስጥ ያለው ደግሞ በአግባቡ አሲድ እና ስብ ሳይቀንስ ኑግ እና ጎመንዘር እየተፈጨ በደንብ ሳይጣራ ለገበያ ይቀርብ ነበር።እኛም ከ10 ዘይት አስመጪዎች መካከል ነበርንበት። በዚህ ሥራ ላይ ስለቆየን የሕዝብ ችግርም ይገባን ነበር።
ፕሮጀክቱ ሲጀመር ከውጭ ሀገር ካምፓኒ ጋር ‹‹ጆይንት ቬንቸር›› ነበር።ሁለት ዓመት አብረን ከሠራን በኋላ ወደ ተግባር እንዳንገባ መሰናክል ሆኖ ነበር።ከዚያ በተገቢው ዘዴ አስፈላጊውን ክፍያ ወስዶ ሥራውን ማቃናት ተችሏል።በመሐል ብዙ ፈተና ነበር።መብራት፣ ገንዘብ፣ መሰረት ልማትና የመሳሰሉት ችግሮች ነበሩ።ቢሆንም በቆራጥነት ገብተንበት እየሰራን ነው።ከውጭ የዘይት ድፍድፍ ማምጣቱ እንዲቀርም በሀገር ውስጥ ወደ እርሻ ገብተናል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ድርጅቱ የካፒታል መጠን ስንት ደርሷል?
አቶ በላነይህ፡– በቁጥር እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር ያስቸግራል።በሴክተር ሲታይ ግን በላኪና አስመጪ፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ በሆቴል፣ ትራንስፖርት፣ ኮንስትራክሽን፣ አግሪካልቸር እና ሌሎች ዘርፎችም አለንበት።
አሁን ወደ ኢንቨስትመንት እየገባን ስለሆነ ንግዱን እየቀነስን ነው።ለአብነት በአስመጪና ላኪ ከሁለት ዓመት በፊት ድርጅቱ ሦስት ቢሊዮን ዓመታዊ ሽያጭ ነበረው።የፈሳሽና እና የነዳጅ 110 ከባድ መኪናዎች አሉን።ፊቤላ የራሱ የሆኑ 160 ተሽርካሪዎች አሉት።በሕዝብ ትራንስፖርት ደግሞ ጎልደን ባስ 35 አውቶብሶች ያሉት ሲሆን አሁን ለመገጣጠም ስራዎች እየተጠናቀቁ ነው።የጎልደን ባስ አስመጪም ነን።
በኮንስትራክሽም በርካታ ማሽኖች አሉን።በእርሻ ይርት እና ጃዊ፣ ቤንሻንጉል እርሻዎች አሉን።ገላን ላይ የመኪና መገጣጠሚያ አለን።በሆቴል ዘርፍ አዳማ ራስ ሆቴል፣ በአዲስ አበባ ኢትዮጵያ ሆቴል፣ በባህርዳር ደግሞ ሂልተን ሆቴሎች አሉን ።በሼር ሆልደር የሚሰሩ የኤሌክትሪክ ምሰሶ ፋብሪካዎች በጎንደርና ባህርዳር አሉን ።በማኑፋክቸሪንግ ደግሞ ፊቤላ አለን።ድርጅቱ የከረጢት ፋብሪካም አለው።
አዲስ ዘመን፡- የአንድ ባለሃብት መለኪያው ሌላ ባለሃብት ማፍራት ነው።በዚህ ላይ እርስዎ ሚና ምንድን ነው?
አቶ በላይነህ፡– ቡሬ ላይ የሚሰራው የዘይት ፋብሪካ 4ነጥብ5 ቢሊዮን ብር ነው የጨረሰው።በዝርዝር ስንመለከተው ድፍድፍ የሚያመላልሱ 160 ቦቴ ተሽርካሪዎች አጠቃላይ ወጪያቸው አንድ ቢሊዮን ብር ነው።ማሽነሪውና የኤሌክትሪክ ኢንስታሌሽኑ 1ነጥብ6 ቢሊዮን ብር፣ ኮንስትራክሽኑ አንድ ቢሊዮን ብር የፈጀ ፕሮጀክት ነው።የመስሪያ ካፒታሉን ጨምሮ 4ነጥብ5 ቢሊዮን ደርሷል።
ይህ የውጭ ምንዛሪ አንድ ዶላር 30 ብር በነበረበት ጊዜ የተሰጠ ዋጋ ነው። ሚዛናዊ በሆነ ዋጋ ሰባት ፋብሪካዎችን በአንድ ስፍራ ገንብተናል።እስከ አንድ ክፍለ ዘመን የሚቆይ ግንባታ ነው ።160 ተሽርካሪዎችን በራሳችን መገጣጠሚያ የገጣጠምነው ።የሀገር ሃብት መሆኑን ስለምንገነዘብ በትልቅ ኃላፊነት ነው የሰራነው።
ሌሎች ባለሃብቶችን በተመለከተ ለሀገር ጠቃሚ ናቸው ብለን እናምናለን።ማኔጅመንታችንም የሚያስበው ተወዳዳሪዎች ቢሆኑም እኛን ያነቁናል ብሎ ነው።አብረን እናብባለን ብለን እናስባለን። እኛ ሞዴል ሆነን ብዙ ባለሃብቶች እንዲፈሩ ሰርተናል ብለን እናስባለን።ከእኛ ድርጅት ወጥተው 12 ግለሰቦች በርካታ ሰው ቀጥረው የሚሰሩ ተወዳዳሪ ሆነዋል።
አንዳንዶችም በየሴክተሩ ከእኛ ጋር ተወዳዳሪ የሆኑ አሉ።ከድርጅቴ ወጥቶ እኔን ቢወዳደረኝም እኔ ልጅ ወልጄ እንዳሳደኩ ነው የምቆጥረው ።ስችል ገንዘብ ሰጥቻለሁ፣ እውቀት ሰጥቻለሁ፣ የሥራ ዕድል ፈጥሬአለሁ።ዘመድም የሆነ ዘመድም ያልሆነ ከዚህ ወጥቶ ራሱን ችሎ የሚሰራ አለ። ይህ በጣም ደስ ይለኛል።በዚህ ሴክተር መልካም ሥራ እንዲሰራ ጥሩ ተፅዕኖ አለኝ ብዬ አስባለሁ። ይህ ሁልጊዜ የሚያረካኝና የሚያስደስተኝ ነው።ከእኔ ስኬት ጀርባ የእነዚህ ሰዎች ስኬት ያስደስተኛል።የእኔን መልካም ተሞክሮ ይዘው እንዲሄዱም መልም ምሳሌ በመሆን ሰርተናል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ድርጅታችሁ ቻይናን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት ሰብሮ ገበያውን ተቀላቅሏል።እንዴት ለዚህ በቃ ?
አቶ በላይነህ፡- መልካም ሥም ማለት ሀገር ውስጥ ብቻ አይቀርም።የውጭ ደንበኞቻችንም እኛ ታማኝ እንደሆንን፣ ከእኛ ሲገዙ በመጠን እና ጥራት ምንም ችግር እንዳይገጥማቸው በማሰብ ነው።ታማኝ በመሆን ገበያ ሲረክስና ሲወደድ ደንበኛን አለማስቀየም ያስፈልጋል።ለገበያ በጥራት ማቅረብ ትልቅ ጉዳይ ነው።እምነታችንም ጠብቀን ነው የምንሄደው።ሌላው ቀርቶ በስልክ የተደዋወልነውን ማፍረስ አንፈልግም። ለዚህም ቀድሞ የተከልነው የነበረውን ስምና ዝና ወሳኝ ነው።በዚህም ከውጭ ደንበኞች ጋር ገበያው ሰብረን ገብተናል።
አሁን ከንግድ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ገብተናል።ዱሮ መኪና አስመጥተን እንሸጥ ነበር። አሁን በኮንቴነር መጥቶ እዚህ እንገጣጥማለን።ሰሊጥ ጥሬ መላክ ትተን እየቆላን እንልካለን።ዘይት የታሸገ እናመጣ ነበር አሁን እዚሁ አምርተን አሽገን እንሸጣለን።
ፋብሪካው እዚህ በመገንባቱ የፓልም ዘይት ማሌዥያ በሚሸጥበት ዋጋ እዚህ እየሸጥን ነው።ፓልም ዘይት ጉዳት እንዳለው ተደርጎ ተጋኖ ተወርቶ ነበር።እኛ ግን የስብ መጠኑን በሚገባ መጥነን ለህብረተሰባችን ጤና በሚስማማ መንገድ እናቀርባለን።ከንግድ ወደ ማኑፋክቸሪንግ እየሄድን ስለሆነ የሥራ ዕድል መፍጠር እና የሕብረተሰቡን ችግር መፍታት ግዴታችን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ቡሬ ላይ ለተገነባው የዘይት ፋብሪካ ለአርሶ አደሮች መንግስት ከሰጠው ካሣ ተጨማሪ እርስዎ ተጨማሪ ካሣ ከፍለዋል።ይህን ያደረጉበት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ በላይነህ፡– የፋብሪካው ግንባታ 4ነጥብ5 ቢሊዮን ብር ወስዷል።በአሰራሩ መሰረት መሰል ፕሮጀክቶች ባንክ 70 ከመቶ ድርጅታችን ደግሞ 30 ከመቶ መሸፈን ነበረበት።እኛ ግን 70 ከመቶ ሸፍነን 30 ከመቶ ከባንክ ብድር ወስደናል ።
እዛ ያወጣነውን ገንዘብ ወደ ሕንፃ እንቀይረው ብለን ብናስብ ህንፃ ሰርቶ 60 ሰው ቀጥሮ ያለጭንቀት መኖር ይቻላል።ካምፓኒዎች ረጅም እድሜ እንዲኖራቸው ከተፈለገ ከህብረተሰቡ ጋር መኖ ርና መናበብ አለባቸው። እኔ እዛ ስሄድ ዋናው ዓላማዬ ፋብሪካ ከፍቼ ሰዎችን እጠቅማለሁ፣ እኔም እጠቀማለሁ ሀገሬንም እለውጣለሁ ብዬ ነው።ከአስተሳሰቡ ስትነሳ ይህ ነው መሆን ያለበት።
እኔ እዚያ አካባቢ ላይ መሬት ጠበብ አድርጌ ይህ ይበቃኛል ብዬ ነበር።ዲዛይኑ ሲመጣ አርሶ አደሩ ከዘሩት መሬት ውስጥ ገባ።ይህንን ነገር ምን ማድረግ ይሻላል ብለን ስንመካከር አርሶ አደሩ ምርት እስኪሰበስብ እንጠብቅ ብለን ተመካከርን።
ይህን ምስጢር የሰሙት አርሶ አደሮች ፕሮጀክቱ ከሚቀር ካሣውን በሚቀጥለው ዓመት እንወስዳለን አሉኝ።በጣም አዘንኩ፤ የሰዎቹ ሁኔታ ልቤን ነካኝ።ከዚያን ሰዎቹ ተመዝገቡ።19 ሰዎች ምርታቸውን ይነካ ነበር።
በአጠቃላይ መሬት የተነካባቸው 59 አርሶ አደሮች ነበሩ።ግን አዝመራቸው ለተነካቸው 19 አርሶ አደሮች መንግስት ከከፈለው ተጨማሪ 25 በመቶ ካሳ እንዲከፈል አድርገናል።ካሣው አነስተኛ ስለሆነ ለመቋቋም በቂ አይደለም የሚል እምነት ነበረን።
‹‹እኛ ኑሮ እናሻሽላለን ብለን አርሶ አደር አፈናቃዮች መሆን የለብንም›› የሚል እምነት ስላለኝ ነው። አሁን ልጆቻቸውን እየቀጠርን ነው።የምረቃ ዕለትም እነዚህ ሰዎች ልዩ ተሸላሚዎች ናቸው። አሁንም የቀን ሰራተኛ ሆነው በዚያ እየሰሩ ነው።በዚህ ብዙ የተለወጡ ሰዎች አሉ።
ለከተማዋ አስተዳደሩም ከሰራተኛ ግብር በየወሩ 500ሺ ብር እንከፍላለን።እነዚህ ሰዎች ለእኛ እጅግ አስፈላጊ ናቸው።በቀጣይም ከእነርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን፡- ፕሮጀክቱ ግዙፍ ከመሆኑ የተነሳ የጥሬ ምርት እጥረት ያገጥመናል የሚል ሥጋት የላችሁም?
አቶ በላይነህ፡– ፋብሪካው በቀን 1ሺ500 ቶን ወይንም 1ነጥብ5 ሚሊዮን ሊትር እና ከዚያ በላይ ዘይት ያመረታል።በዓመት 20 ሚሊዮን ኩንታል የቅባት እህሎች ይፈልጋል።ሀገሪቱ በዓመት የምታመርተው በአማካይ ከሦስት ሚሊዮን አይበልጥም።
ስለዚህ ከአርሶ አደሩ ጋር ሰርተን ፍላጎታችን የተሟላ እስኪሆን ከውጭ ድፍድፉን አምጥተን እንሰራለን።ቀደም ሲል ዘይቱ ማሌዥያና ዩክሬን ይታሸግ ነበር።አሁን ግን የበለፀጉ ሀገራት ያላቸውን ቴክኖሎጂ የታጠቀ ፋብሪካ እዚህ ስላለ ለህብረተሰባችን በሚጠቅምና በተመጣጣኝ ዋጋ እናመርታለን።ይህ ትልቅ ዕድገት ነው።
ሁለተኛ አርሶ አደሩን በማስተባበርና እራሳችን ምሳሌ በመሆን ምርጥ ዘር በመስጠት፣ የአፈር ማዳበሪያ በማቅረብና ከመንግስት ጋር በመሥራት በቀጣይ አምስት ዓመታት የፋብሪካ ግብዓታችንና ድፍድፋችን ከሀገር ውስጥ እንዲሆን እንሠራለን።ለዚህም ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 10ሺ ሄክታር መሬት ወስደን ባለፈው ዓመት ውጤት ያለው ሥራ አከናውነናል።
ችግሮች እያሉም እየሰራን ነው።ፋብሪካውን በስድስት ዓመት እንዳጠናቀቅነው በቀጣይ ስድስት ዓመታት ሀገሪቱ ምርቱ ከዚህ ተመርቶ ለሕዝባችን በወጪ ዝቅተኛ የሆነ፤ ተረፈ ምርቱ ለብዙዎች የሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሆን እንሰራለን።
ሀገር ያደገው የተወሰኑ ሰዎች ጠንክረው ከሰሩ ሌሎች ሲከተሉ ነው።እኛም ሞዴል ሆነን ሌሎች እንዲሰሩ ማድረግ ነው።ምርታማነትን ከፍ እናደርጋለን።ከመንግስት መዋቅር ጋር በመሥራት ዓለም ባደገበት መንገድ እንሄዳለን።ስድስት ወር በረዶ ሆነው ስድስት ወር ሰርተው ዓለም የሚመግቡ ሀገራት አሉ።
እኛ ተረት እየተረትን ድህነት ታቅፈን ነው ያለነው። ከመንግስት ጋር ሰርተን የሀገራችን ድህነት እናጠፋለን። ለዚህም ድርጅታችን በግንባር ቀደምትነትና በጥሩ አደረጃጀት በማንኛውም መንገድ ዝግጁ ነው። የሀገራችን ድህነት ምንጭ መድረቅ አለበት። ለዚህም ሕብረተሰቡና መንግስት ከጎናችን ነው። በቀጣይም አብረን እንሰራለን የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- የገበያ መዳረሻዎች የሚሆኑት የት ነው?
አቶ በላይነህ፡- የያዝነው ድሃ ህብረተሰብ ነው።የሚያናድደው ነገር ወርቅ መሬታችን ውስጥ እያለ አውጥተን እንዳንጠቀም የውጭ ተላላኪ የሆኑ ቡድኖች አሉ።ሀገር ውስጥ ሆነውም ራሳቸውን ብቻ የሚያዳምጡ አሉ።እነዚህን መታገል አለብን።የተወሰኑትን ታግለን እያሸነፍን ነው።የአስተሳሰብ እንጂ የሀገር ድህነት የለብንም።የተወሰኑ በቡድን ሀገር የሚያደኸዩም አሉ።እነርሱም በአግባቡ እንዲሰሩ ይደረጋል ብለን እናምናለን።ለእነዚህ መፍትሄ መበጀት አለበት።የተወሰኑ የፖሊሲ መዛባቶችም አሉ።እነርሱ እየተስተካከሉ ነው።
አሁን ጥሬ ዕቃ የምናገኘው ከዩክሬን፣ ኢንዶኔዥያ፣ ማሌዥያና ከመሳሰሉት ሀገራት ነው።ከእነዚህን ተሞ ክሮ መውሰድ ይገባል። ችግራችን ተሞክሮ ወስደን ወደ ተግባር መቀየር ላይ ነው።ወርቁን አውጥተን መጠቀም አለብን።
ውሃችንን ለመጠቀም ግድቡ ተጀምሯል።መሬታችንን ማረስ አለብን።መሬትና ጉልበታችንን ማገናኘት አለብን። ባለሃብቱ ቁርጠኛ ሆኖ ባያርስ እንኳ ጉልበት ይዘው 24 ሰዓት ሰርተው ማምረት የሚፈልጉ ሰዎች አሉ።እነዚህ ሰዎች አንድ ቦታ ታጭቀዋል።መሬቱ ደግሞ ያለስራ ተቀምጧል።ይህን ማገናኘት ያስፈልጋል።
መንግስት በፖሊሲው ጉልበትና መሬትን ማገናኘት አለበት።ቻይና እና ቱርክ በሀገራችን ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንለምናለን። እኛ ግን አንዱ ብሔር ሌላ ቦታ እንዳይሰራ እናግዳለን።
ይህ መቆም አለበት።እዚህ ሀገር ማንኛውም ሰው ተዘዋውሮ መሥራት አለበት።መሬት ላለማት ብቻ መሆን አለባት እንጂ ይህ የእኔ ክልል ነው የሚለው አስተሳሰብ አስቸጋሪ ነው ።የውጭ ባለሃብት ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ እንዲሰራ ሕጋችን፣ ሕገመንግስታችንና አስተሳሰባችን መፍቀድ አለበት።መሬት ላለማውና ለሰራው መሆን አለበት።የሚያለማ ሲመጣ አካባቢ ህብረተሰብ ተጠቃሚ ይሆናል።
አንድ ሰው የሚበላው የተወሰነ ግራም ነው።የሚጠጣውና የሚለብሰውም የተወሰነ ነው።ከሰራ ያንን ሰው መደገፍና ዕድል መስጠት ይገባል።ሁሉም ሰው ባለው ሃብት መጠቀም አለበት።ሀብታችን አንድ ክፍለ ዘመን ሙሉ ሳይሰራበት ተቀምጧል።እነዚህን ማልማትና መጠቀም ይገባል።
‹‹የሀገራችን ኢኮኖሚ ካደገ ፖለቲካችን እና ማህበራዊ ሕይወታችን የተረጋጋ ይሆናል›› ሰው ሲሠራ መመቅኘት መቆም አለበት።ትክክለኛ አስተሳሰብ መስረፅና ጎጠኝነትና ቀበልተኝት መቆም አለበት።የውጭ ተሞክሮውም የሚያሳያው ይህንን ነው።እኛ ያለንበት ቀጣና ለእርሻ፣ ማዕድን፣ ለቱሪዝምና ሌሎችም የተመቸ ነው።ከእኛ የሚጠበቀው ትዕግስትና መስተካከል ነው።
ከካፒታል እጥረት በስተቀር ሁሉም ነገር አለን።ካፒታል ደግሞ የተወሰነ ጊዜ ተቸግረን በታታሪነትና በሥነሥርዓት ከሰራን ሁሉም ይስተካከላል።ሃብት ስናገኝ በአግባቡ መጠቀም ይገባል።ባለፈው ሥርዓት የመጡ ብድሮችና ሃብቶች በአግባቡ ሳንጠቀም የተወሰኑ ግለሰቦችን በልፅገውበት አልፈዋል።አሁን ያለፈው ሁኔታ እንዲቀጥል መፍቀድ የለብንም።ሀገራችንን ማስቀደም አለብን።እኔ ራሴን ብቻ መውደድ የለብኝም የሚል ፍልስፍና አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- የባለሃብቱ ችግር መሬት በማግኘትና ማጣት ላይ ብቻ የተወሰነ ነው?
አቶ በላይነህ፡– ብልሽቱ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ይነካል። በተለይ ከባለሃብቱ፣ ምሁራንና ፖለቲከኞች ዘንድ አለ።ባለሃብቱ መሬት ወስዶ ብድር ካገኘ በኋላ አያለማም።አላግባብ መሬት ይዞ መቀመጥ አለ።በማህረሰቡ ዘንድ የዚህ ብሄር ነኝ ይህ መሬት የእኔ ነው የሚል አስተሳሰብ አለ።በእኔ አስተሳሰብ መሬት ለሚያለማ ሰው መሆን አለባት።አጭበርባሪዎችም ከጨዋታ ውጭ መሆን አለባቸው።
አንዳንዱ ለራሱና ለቤተሰቡ ከሠራ በኋላ ሌላው ገደል ይግባ የሚል አስተሳሰብ አለው፤ ይህም ስህተት በመሆኑ መቆም አለበት። ይህ በፖሊሲ መመለስ አለበት።አንዳንዱ ደግሞ ለብዙዎች ፋይዳ በሌለው ሴክተር ላይ ይሰማራል።ይህ እንደ ሀገር መስተካከል አለበት።ዛሬ ሕንፃ ቢገነባ ድሃው የሚበላውን ካጣ ያፈርሰዋል። እያየነው ነው፤ ብዙ ተሞክሮም አልፈናል።ስለዚህ ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል በሚፈጥረው ላይ ማተኮር አለበት የሚል ሃሳብ አለኝ።
የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተዛቡ አስተሳሰቦች መታረም አለባቸው።ከፖለቲካው ጀምሮ ባለሃብት፣ መንግስት እና ምሁራን በሙሉ ለሀገር የሚጠቅም ነገር ላይ ማተኮር አለብን።
የሁሉም ማሰሪያና ማጠንጠኛው የሀገር ዕድገት የሚመሰረተው በኢኮኖሚ ላይ ነው። ኢኮኖሚ ደግሞ ፍትሐዊ የሆነ አካሄድ መከተል አለበት።የውጭ ከመናፈቅ በራስ ሃብት፣ ጉልበትና መሬት ማገናኘት ይገባል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ወሰን መኖር የለበትም።ሕግ ከተከበረ በዓለም ላይ የትም ሄደህ የምትኖርበት ዘመን ላይ ነን። እኛ ሀገር ከክልል ክልል መሄድ ከሀገራት ሀገራት ከምትሄደው በላይ አስቸጋሪ የሆኑ አስተሳሰቦች አሉ።ይህ መቆም አለበት።ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ተንቀሳቅሶ መስራት አለበት።
በእርግጥ የኢንቨስትመንት ሕጋችን ይህን ይላል። ግን በተግባር መሬት ላይ መውረድ አለበት።ይህን ካደረግን ብዙ ዕድገት እናመጣለን።አንድ ሰው ብዙ የሥራ ዕድል ሲፈጠር መደነቅ አለበት።
ብዙ የሰራ ብዙ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለን ማሰብ አለብን። አሁን መንግስት የያዛቸው ነገሮች ጥሩ ናቸው። ሳንካዎችና ጎጠኝነት ከተፈታ፤ አስተሳሰባችን ሰፋ እያለ ከሄደ እና ተባብረን ከሰራን ሀገራችን ከድህነት ትወጣለች።የውጭ ምርቶችን የሚተኩ ምርቶች ከመጡና ወደ ውጭ የምንልከው ምርት ካለ ሀገራችን ትለወጣለች።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ባለሃብቶች ከባንክ ብድር ወስደው ከተፈቀደላቸው ኢንቨስትመንት ውጪ ለሌላ ዓላማ ያውላሉ።እርስዎ ደግሞ ሀገሬን አስቀድማለሁ ይላሉ። ይህን አስተሳሰብ እንዴት አመጡት?
አቶ በላይነህ፡– እኔ ብቻ ሳልሆን የተወሰኑ ባለሃብቶች ለሀገር ማሰብ የሚፈልጉ አሉ።እኔ ወታደርም ስለሆንኩ መሰለኝ ሀገሬ እንድትፈርስ አልፈልግም።ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ከሚፈልጉ ሰዎች አንዱ ነኝ።ስለዚህ ኢ-መደበኛ ነገር መሥራት አልፈልግም።አንዳንድ ቢሮክራሲው ሲያስቸግር ኢ-መደበኛ ነገር ሰርተህ ልታልፍ ትችላለህ።እኔ ግን ኢትዮጵያን፣ ቤተሰቤንና ድርጅቴን እወዳለሁ።እሰራለሁ ብዬ መሬት ወስጄ ሣልሰራ ያለፍኩትና አጥሬ ያስቀመጥኩት መሬት የለም።እኔ ብዙ ዕድሎች አሉኝ።
አዲስ አበባ ውስጥ ህንፃ ከሌላቸው ባለሃብቶች ውስጥ አንዱ ነኝ። ኢትዮጵያ ሆቴልን ብቻ በጨረታ ገዝቻለሁ።አንድ ፎቅ ብሰራ የሥራ ዕድል የምፈጥረው ለሁለት ሰው ነው።ለዚህ መሰል ነገር ዕድል አልሰጥም።እኔ ወጣ ብዬ ሀገሪቱን ሊያሳድግ የሚችልና ብዙ ሰዎችን ሊቀጥር የሚችል የሥራ ዕድል የሚፈጥር ዘርፍ ላይ ነው ኢንቨስት ማድረግ የምፈልገው።
ይህን ስናገር ፎቅ አያስፈልግም ለማለት ወይንም ሕንፃ ያላቸውን ለመቃወም ሳይሆን አስተሳሰቤ ይህ ስለሆነ ነው።አሁንም ከአዲስ አበባ ወጣ ብዬ ቡሬ ላይ 4ነጥብ5 ቢሊዮን ብር ኢንቨስት ያደረግኩት የዚሁ አስተሳሰብ ፍሬ ነው።ለቢሮ ግንባታ ብዬ አዲስ አበባ ውስጥ መሥሪያ ቦታ ጠይቄ ነበር ግን አልተሰጠኝም።
ግን ለምን አልተሰጠኝም ብዬ ቅር አልሰኝም።በሂደት ሊሰጠኝ ይችላል።የእኔ ትኩረት ሀገር የሚለውጡ ፕሮጀክቶች ላይ ነው።ፈተናዎችን አልፌ መሰል ፕሮጀክቶችን እውን ሳደርግና በሂደት ብዙ ሰዎች ሲጠቀሙ ማየት በጣም ያስደስተኛል።
እዚህ ላይ ግን ማስተዋል ያለብን አንድ ነገር ፣ ለሀገር የሚጠቅሙ እና ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ፕሮጀክቶችን፣ የፕሮጀክት አስተሳሰቦችን፤ ለመላው ሕዝብ ፋይዳ ያላቸው ኢንቨስትመንቶች ላይ መሰማራት ያስፈልጋል ።የተወሰኑ ቡድኖች ተጠቃሚነት ላይ መሰረት ያደረገ ኢንቨስትመንት እና ሀገራዊ ኃላፊነትን የዘነጋ አካሄድ ውጤቱ የከፋ እንደሚሆን ከህወሓት ውድቀት መረዳት ይቻላል ። ከዚህ በቂ ትምህርት ልንወስድ ይገባል ።
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ጊዜ ድጋፍ ሲያደርጉ ይሰማል። ይህ እሳቤ ከምን የመጣ ነው?
አቶ በላይነህ፡– እኔ ኢትዮጵያዊነትን የምደጋግመው ከመለያየት አንድነታችን ስለሚጠቅመን ነው።ይህ ሕዝብ አንድ ሕዝብ ነው።ገዥዎች በሚመቻቸው መንገድ ለመከፋፈል ይሞክራሉ።አንድ ሆኖ በመሥራት አገር ይለወጣል እንጂ መከፋፈል ጠቃሜታ የለውም የሚል ፍልስፍና አለኝ።ይህን ለመግለፅ በእኔ ተሞክሮ አሁን በስድስት ክልሎች ላይ እየሰራሁ ነው።በሌሎችም ክልሎች ለመድረስ ጥረት እያደረግን ነው።
ሀገሪቱ ትለውጣለች ብዬ በማስበው ላይ አሻራዬ እንዲኖር እፈልጋለሁ።ለአብነትም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 33 ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዝተናል በቀጣይም እንገዛለን።ኮሚቴ ሆኜ ባለሃብቶችን ሳስተባብር ነበር በቀጣይም አስተባብራለሁ።
ለሀገራችን ሞራል፣ አንድነትና ማንነት ወሳኝ ስለሆኑ ገና በስፋት እሳተፋለሁ።ለዚህ ፕሮጀክት የሕይወት መስዋዕትም ቢሆን ለመክፈል ዝግጁ ነኝ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቱሪዝም መስህብን ለማሳደግ በማሰብ በተዘጋጀው ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት እውን ለማድረግም 35 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርገናል።
ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችንም በማገዝ ረገድ ድርጅት ኃላፊነታችንን ተወጥተናል።በተጨማሪ የስፖርትና ጤና ተቋማትን በመደገፍ ላይ እንገኛለን።
በቀጣይም ለሀገር የሚጠቅሙ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ በስፋት እንሰራለን። በሀገር ላይ ጦርነት ሲታወጅም ቀድሞ መድረስ ችለናል።ተማሪዎችን እናስተምራለን እንረዳለን።የድርጅታችን አንዱ ክንፍና ባለቤቴ የምትመራው ፋውንዴሽን ተቋቁሟል።ለሕዝባችን ብዙ እንሰራለን ብዙ እንደግፋለን ብለን እናስባለን።
አዲስ ዘመን፡- ይህን በማድረግዎ ምን ይሰማዎታል?
አቶ በላይነህ፡- ለሀገሬ ምን አደረግሁላት ብዬ ሳስብ እደሰታለሁ።ለልጆቼ እነግራቸዋለሁ፤ እነርሱም ሚዲያ ላይ ያያሉ።ህብረተሰቡም ክብር ሲሰጠው ደስ ይለኛል። እኔም ማህበራዊ ኃላፊነቴን እንደተወጣሁ ያሳየኛል።ግን ብዙ እንደሚቀረኝ እገምታለሁ።ከዚህ በላይ ብዙ መሥራት አለብን።በአሁኑ ወቅት ትኩረታችንና አብዛኛውን ጊዜያችንን የምናጠፋው ድርጅቱን የማዋቀር እና ለድርጅቱ ቋሚ የሆኑ የገቢ ምንጭ በኢንቨስትመንት ካደራጀን በኋላ ከዚያ የሚመጡትን ገቢዎች ለማህበራዊ አገልግሎት ማድረግ አለብን የሚል ፅኑ እምነት አለን።ከዚህ አኳያ ብዙ አልሰራንም ገና ነን። አሁን ባለን አቅም ትንሽ ረድተናል ብለን እናስባለን።
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ሰርተው እራሳቸውን ያላስተዋወቁና ከሚዲያ የሚቆጠቡ ሰው እንደሆነ ይነገራል። እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ በላይነህ፡- እኔ አልናገርም ብልም ሚዲያው ይገፋኛል። አንዳንድ ሁነቶች ላይ እየገፉኝ እናገራለሁ።ብዙም ከሚዲያው ተደብቄያለሁ አልልም።ከሌላው ባለሃብት አኳያ ሲታይ ተደብቅሁ ማለት አይቻልም።ብዙ አንናገርም ብለው የሚሸሹ አሉ።አንዳንዶች ደግሞ ሚዲያ ከሚፈልጉትም አንፃር እኔ ሁልጊዜ ልናገር ብል በየቀኑ ጋዜጠኛ ይጠይቀኛል።ስለዚህ መካከል ላይ ነን።አልተናገርኩም ማለት አይቻልም።መሠረታዊ ነገር ላይ ከመጣ እናገራለሁ።ድርጅቱ ውጤት ካመጣ እናገራለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ድርጅታችሁ በሚያደርገው ጥረት ላይ የመንግስት ድጋፍ ምን ይመስላል?
አቶ በላይነህ፡- በእውነቱ ለመናገር የመንግስት ድጋፍ ጥሩ ነው።እንደ ዕድል ሆኖ በምሠራቸውን ሥራዎች መንግስት ይደግፈኛል።ለፍቶ አዳሪና በባህሪዬ ታትሬ የምሠራ ሰው ነኝ፤ እግዚአብሄርም ረድቶኛል።
የተሰማራሁትም ሀገሪቱ በምትፈልገው ዘርፍ ላይ ነው። በተቻለ መጠን መንግስት የውጭ ምንዛሪ አግዞኛል፤ መሬት ሰጥቶኛል፣ ከቀረጥ ነፃ ማሽኖችን አስገብቻለሁ።ጤናማ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉት ባለሃብቶች መካከል ስለሆንኩ መንግስት እየደገፈን ነው።
አዲስ ዘመን፡- የድርጅቱ ቀጣይ ዕቅዶች ምንድን ናቸው?
አቶ በላይነህ፡- የተጀመሩና መጠናቀቅ ያለባቸው ሥራዎች አሉት። የዘይት ፋብሪካው ተጀመረ እንጂ አልተጠናቀቀም። ድፍድፉን ከውጭ እያመጣን ነው። በሀገር ውስጥ ለመሸፈን በእርሻው ላይ በሰፊው መሥራት፣ ማዘመንና ለውጥ ማምጣት አለብን። ግብርናው ላይ ሲሠራ ብዙ ሰው ይጠቅማል።
በተረፈ ምርቱም ብዙ ሰው ይጠቀማል።በሆቴል ዘርፍ ኢትዮጵያ ሆቴል ፈርሶ መሠራት ያለበት ነገር አለ።አዳማ ራስ ሆቴል እና ባህርዳር ሂልተን ሆቴል የተጀመሩ ሥራዎች መጠናቀቅ አለባቸው።በአውቶሞቲቭ ዘርፍ በአፍሪካ ብዙ ሕዝብ ያላትና ግን ደግሞ ትንሽ ተሽከርካሪ ያላት ሀገር ናት።
የሕዝባችን ኑሮ እየተለወጠ ስለሚሄድ ከትልቅ እስከ ትንሽ ማሽነሪ የሚገጣጥምና ሞተሩንም እዚህ የሚፈበረክ ተሽከርካሪ መሥራት አለብን።የተጀመሩ ሥራዎችን አስፍተን ለቀጣይ ትውልድ አሻራ ማኖር አለብን።
በግሉ ሴክተር ሲታወቅ አንድ ትውልድም ይዞ አሸናፊ ሆኖ የሚቀጥል ካምፓኒ ባለቤት በመፍጠር ረገድ ኢትዮጵያ አልታደለችም።ሰውየው ከሞተ በኋላ ልጆች ተጣልተው ሃብት ይካፈላሉ።እሱን እንዳይሆንና ተቋም ሆኖ እንዲቀጥል በዙሪያው ያሰባሰባቸው ኃይሎች እንዳይጎዱ እኔም ሳልኖር ቢሆን ድርጅቶቹ ለረጅም ዓመታት እንዲኖሩ አደረጃጀቱን መሥራት ያስፈልጋል።አሁን በቦርድ እንዲተዳደር ሥራ ጀምረናል።
ቤተሰብ ተጠቃሚ መሆን አለበት እንጂ ድርጅቱን እንዳያፈርስ እና በመዋቅር እንዲመራ እንሠራለን። በአፍሪካ እና በዓለም ሥመ ጥር ድርጅት እንዲሆን እንሰራለን።በቡሬ ላይ ያለው ፕሮጀክት ሙሉ ለሙሉ ሥራ ሲጀምር ሠራተኞቻችን 5000 ይደርሳሉ። በሥራቸው ደግሞ ቤተሰብ አላቸው። በቀጣይ በ10ሺ እና 15ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በቀጥታ ቀጥረን እንሰራለን። ዕድሜ ከሰጠን ይህን እንሰራለን፤ ዕድሜ ባይሰጠኝ ሌላ ሰው ይዞት እንዲቀጥል አደረጃጀቱን እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ኢትዮጵያዊ እርስዎ ያዘኑበትና ባይሆን ብለው የሚያስቡት ነገር አለ?
አቶ በላይነህ፡- እኔ የማዝነው በዘረኝነት ነው። ዘረኝነት ለማናችንም አይጠቅምም።አንድ ሆኖ ተጋብቶና ተዋልዶ የኖረውን ሕዝብ ለመከፋፈል የሚሰሩ ሥራዎች ያሳዝኑኛል። በጣም አዝናለሁ፤ አስለቅሶኝም ያውቃል።ሚስኪኑና ምንም የማያውቀው ሕይወቱን መሥዋዕት እያደረገ ለወንበር ወይ ለገንዘብ መጠቀሚያ ሲሆን በጣም ያሳዝነኛል።
ሁለተኛው ሀገራችን ምንም እንደሌላት ድሃ ሆና በሌላ ስትመፀወት ነው። ስድስት ወር ሰርቶ ዓለምን የሚመግብ ማህበረሰብ አለ። እዚህ ሀገር 12 ወር ምቹ ሆኖ፣ የሚሰራ ሰውም እያለ በማይረባ ትርክት ሀገር እንዳይለማ መደረጉ ሁሌም ይቆረቁረኛል። ትንሽ እየሰራህና ዓለምን እየጎበኘህ ስትሄድ ሚስጥሩን ታውቃለህ።
አዲስ ዘመን፡- ልጆችዎን የሚያዝናኑት ወደ ሥራ ቦታ ይዘው እየሄዱ ነው ይባላል ፤ ይህን ማድረግ ለምን አስፈለገ?
አቶ በላይነህ፡– እውነት ነው።ብዙ ወደ ውጭ ይዤ አልሄድም።ታሪኩን እነግራቸዋለሁ።ፋብሪካ እና መጋዘን ይዣቸው እሄዳለሁ፤ እነርሱም ይጠይቁኛል ያውቁታልም። እኔም የምሰራውን ሥራ ያውቃሉ። የማታዝናናን ለምንድን ነው ብለው ይጠይቁኛል።ጠንከር ሲሉብኝ ከወንድሜ ጋር እልካቸዋሁ።እኔ ስራው ይይዘኛል፤ እነርሱም ይገባቸዋል።
ፋብሪካ እና ሥራ ቦታ የምወስዳቸው ነገ ድርጅቱን እንዲያስቀጥሉት ነው።እኔ የተፈጠርኩት ለቤተሰቤ ብቻ አይደለም። እግዚአብሄር ዕድል ሰጥቶኝ ብዙዎችን ዳቦ እንዳበላ ፈቅዷል።ለሀገር መሆን እኮ መታደል ነው።
አንድ ሰው እኮ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ሀገር የሚያገለግለው የተለየ ደመወዝ አግኝቶ አይደለም።ሀገር ለማገልገል ነው። ስለዚህ እኛ ጥሩ መኪና እና ቤት እያለን ለምን ሀገር አናገለግልም ብለን እናስባለን።ይህን ሃሳብም ይጋራሉ። ልጆቼም እንደማንኛው ኢትዮጵያዊ ነው የሚኖሩት። አባካኝ አይደሉም እነርሱም ብዙም አይፈልጉትም።
አዲስ ዘመን፡- የሚያስተላልፉት መልዕክት አለዎት?
አቶ በላይነህ፡- እንደ ባለሃብት ከተጠቀምንበት አሁን ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ ጥሩ ነው።በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ዘርፍ የልዩነት ፍልስፍና አሳልፈናል። ህብረተሰቡ ጭንቅላት ላይ ብዙ ጣጣ አምጥተዋል።አሁን የአንድነት ፍልስፍና አለ።ሁሉም ባህሉንና ኢኮኖሚውን እያሳደገ ግን በጋራ ሰርቶ መለወጥ ይችላል።
አንዱ ለአንዱ ገበያ እንጂ ሥጋት መሆን የለበትም የሚለው አስተሳሰብ እየጠነከረ መሄድ አለበት።አንዱ የጎደለውን ሌላው መሙላት አለበት፤ በዚህ ሁኔታ ሠርተን ለውጥ ማምጣት እንችላለን። ኢኮኖሚው የሚያድገውና ሁላችንም ስንተባበር ነው።
ሀገራችን ከችግር የምትወጣው በግብርና፣ ማዕድንና ቱሪዝም መሆኑን በመንግስት ተለይቶ ወጥቷል፤ የ10 ዓመት ዕቅድ ተብሎ የወጣውም ጥሩ ነው።ግን ወደ ተግባር መቀየር ይገባል።ሰነድ በማዘጋጀትና በመናገር ችግር የለብንም፤ ግን ወርዶ መሥራት የሚፈልግ የለም።ሁሉም ምቾትና የተለየ ነገር ይፈልጋል።
ሰው እኮ ይወለዳል፣ ይኖራል ይሞታል። አንድ ሰው ዕድል ከተሰጠው 60 እስከ 100 ዓመት ቢኖር ነው።በዚህ ጊዜ ሰርቶ ለውጥ አምጥቶ ማለፍ አለበት።ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ምሁሩም እውቀቱን፣ መንግስትም ፖለቲካው ላይ ጥሩ ፖሊሲ በመቅረፅና በመደገፍ፤ ባለሃብቱም ሕዝብና ሀገርን በሚለውጡና በሚጠቅሙ ፕሮጀክቶች ላይ ከተንቀሳቀሰ ኢትዮጵያ ለማደግ ረጅም ጊዜ አይወስድባትም።
በሃብታችን ምክንያት ብዙ ጠላቶች አሉን፤ ሀብታችንን ይፈልጋሉ።አንዳንዶቻችን አውቀን ይሁን ሳናውቅ የእነርሱ ሰለባ እንሆናለን። ስለዚህ ከዚህ ተጠንቅቀን ሀገራችን በሚጠቅም አቅጣጫ ሄደን ኢትዮጵያን መለወጥ፣ አንድነታችንን ማጠናከርና መመካከር አለብን። ተደጋግፈን መሥራት አለብን።
እውነትን ደግሞ መድፈርና የቲፎዞ አካሄድ ማቆም አለብን።ኢትዮጵያ ሕዝብ ከድህነት ለመውጣት አንድ ሆኖ ከሰራ ከአምስት እስከ 10 ዓመት ይበቃል።ድሃ ሀገር ስለሆንና ብዙ ያልሰራንበት ሃብት በመኖሩ ኢኮኖሚያችን በትንሹ መቀጣጠል ይችላል።ለዚህ እኔ ምስክር ነኝ።ከሠራን የሌለን ነገር የለም።
ግን አሁን ባለንበት ሁኔታ የምንቀጥል ከሆነ አደጋ ውስጥ እንገባለን።እየመጣ ያለው ወጣት ሥራና እንጀራ ይፈልጋል።ዛሬ ዘመናዊ መኪና እየነዳን እንሄዳለን፤ ነገ ፖለቲከኛውም ሆነ እኛ እንደዚህ መቀጠል አንችልም ።እኛ ስግብግብ ሆነን ሁለት እና ሦስት እንጀራ እየበላንና እያጋበስን ለራሳችን ምቾት የምንኖር ከሆነ እንዳልኖርን ይደረጋል።ሁልጊዜ መነጋገር፣ በመድረክ ችግሮችን የመፍታት ባህል ሊኖረን ይገባል።እራሳችን ስንወድ ደግሞ ለሌላውም እያሰብን መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን፡- የዝግጅት ክፍላችን ጥሪ አክብረው እንግዳችን ስለሆኑና ስለድርጅትዎ አጠቃላይ ሁኔታዎች ሐሳብዎትን ስላካፈሉን በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሥም እናመሰግናለን።
አቶ በላይነህ፡- እዚህ መጥታችሁና ጊዜ ወስዳችሁ ስለኢንቨስትመንቶቼና ፕሮጀክቶቼ እንድናገር ስለጋበዛች ሁኝ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ጥር 28/2013