
አዲስ አበባ፤ ማዕድ ማጋራትን ባህል አድርጎ ማስቀጠል ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መጪውን የትንሣዔ በዓል ምክንያት በማድረግ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች እና ጽሕፈት ቤቱ ለሚያሳድጋቸው ሕጻናት ማዕድ አጋርተዋል።
በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክትም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ሠራተኞች በዓመት ለኢድ፣ ለትንሣዔና ለዘመን መለወጫ የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብር እንደሚካሄድ አውስተዋል።
የማዕድ ማጋራትን አቅልሎ ማየት እንደማይገባ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ባህል አድርጎ ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
የአቅመ ደካሞችን ጓዳ ለመሙላት የሚደክሙ ብዙ ሰዎች እንዳሉ መገንዘብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በዓል በመጣ ቁጥር እጅ አጠር ሰዎች ለልጆቻቸው ምን አበላቸዋለሁ በሚል ይጨነቃሉ፤ በአንጻሩ ሀብታሞች ምግብ ይደፋሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን ማስተካከል ይገባል ብለዋል።
ለዚህም የተረፈውን ከመድፋት ተሳስቦ፣ ተደጋግፎና ተካፍሎ መኖርን ልማድ ማድረግ፣ ማዕድ ማጋራትንም በየመሥሪያ ቤቱና በየጎረቤቱ ባህል እንዲሆን መሥራት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ለራሷ በቂ ታመርታለች፤ በብዙ መልኩ ለራሷ አታንስም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ያላቸው ለሌላቸው በማካፈል የዕለት ጉርስን ማሟላት እንደሚቻል ተናግረዋል።
ማዕድ ማጋራት በጣም ጠቃሚ ሥራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የማዕድ ድጋፍ የተደረገላቸው ሰዎችም ከጎረቤቶቻቸው ጋር ምሳ በመብላት በኢትዮጵያዊነት ባህል በዓሉን እንዲያክብሩ አደራ ብለዋል።
በማዕድ ማጋራቱ ለተገኙ ልጆች ባስተላለፉት መልዕክትም የእናንተ ኢትዮጵያ በጣም ተስፈኛ ናት፡፡ የበለፀገች የተሻለች ኢትዮጵያን ትወርሳላችሁ ሲሉ ተደምጠዋል።
በልባችሁ መልካምነትንና ድሆችን መደገፍን፣ ማዕድ ማጋራትን እያሰባችሁ ስታድጉ የእናንተ ዘመን ከእኛ የተሻለ ይሆናል ነው ያሉት።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እጅ አጠር ሰዎችን በማሰብ በአብሮነት ቀኑን እንድናከብር ላደረጋችሁ ሁሉ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም