ከቤት አልባነት ወደ ቤት ባለቤትነት

አቶ ተስፋዬ አያሌው የሦስት ልጆች አባት ናቸው። ከልጆቻቸው ጋር በአነስተኛና እርጅና በተጫጫናት ቤት ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ይናገራሉ። በቤታቸው አጠገብ ከሚደፋው ቆሻሻ በሚመጣው ሽታም ጤናቸው ይታወክ እንደነበር ይናገራሉ።

በዚህ ምክንያትም ለ15 ቀናት ሆስፒታል ተኝተው ለመታከም መገደዳቸው ተናግረው፤ ከሆስፒታል በወጡ በሦስተኛው ቀን የተከራዩት ቤት እንደፈረሰ እና የሚሸሸጉበት መሄጃ እንዳጡ ነው የገለጹት። በዚህም ሳቢያም በድንጋጤ ደርቀው እንደቀሩ ከደቂቃዎች በኋላ እንደነቁ ያስታውሳሉ። በኋላም ጎዳና ላስቲክ አንጥፈው መኖር ተያያዙት፡፡ በዚህ ጊዜም ቀን ሐሩሩ፣ ማታ ብርዱ፣ ጠዋት ውርጩ ሲፈራረቅባቸው እንደቆዩ በምሬት ይገልጻሉ።

የሚላስና የሚቀመስ የሚሰጥ ዘመድና ወዳጅ የሌላቸው በመሆኑ ችግራቸውን ይበልጥ ከባድ እንዳደረገው የሚናገሩት አቶ ተስፋዬ፤ አሁን ይህን ችግሬን አምላክ አይቶልኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይኸው የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ዘመናዊ ቤት ባለቤት አድርገውኛል ሲሉ ነግረውናል፡፡

ደረጃውና ንፅሕናው በተጠበቀ መኖሪያ ቤት ለመኖር በመብቃታቸው እንደገና የመወለድ ያህል እንደሆነ በደስታ ይናገራሉ። የትንሣዔ በዓልን ሲያከብሩም ከተማ አስተዳደሩ በሰጣቸው አዲሱ ቤት በመሆኑ ደስታቸው ልዩ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሌላኛዋ ከከንቲባ አዳነች አቤቤ እጅ የቤት ቁልፍ የተረከቡት ወይዘሮ ዙፋን ገብረ መስቀል ልክ እንደአቶ ተስፋዬ ሁሉ በብዙ መከራ ውስጥ ያለፉ መሆናቸውን የአካባቢው ማኅበረሰብ ያውቅ ስለነበር “እንኳን ለዚህ አበቃሽ! ፈጣሪ የልብሽን መሻት ፈፅሞልሻል” እያሉ በታላቅ ድምፅ በእልልታ ደስታቸውን ገልጸዋል።

ወይዘሮ ዙፋን፤ ከዚህ በፊት ይኖሩበት የነበረው ቤት በልማት ፈርሶ የምትክ ቤት ባለቤት የሆኑት እህታቸው ብቻ በመሆናቸው ከሦስት ልጆቻቸው ጋር ለአራት ወራት በጎዳና ላይ ኑረዋል። በእነዚህ ቀናትና ወራትም ብዙ መከራና ፈተና አልፈው እዚህ መድረሳቸውን ይናገራሉ፡፡

ባለቤታቸው ተባራሪ ሥራ እየሠራ የልጆቻቸውን ጉርስ ለመሙላት እንደሚታትሩ ገልፀው፤ እሳቸው ደግሞ ጎዳና ላይ የሠሯት ቤት አጠገብ ቡናና ሻይ በመሸጥ በሚያገኟት ገቢ እንደሚተዳደሩ ተናግረዋል።

ልጆቻቸውን ይዘው አልጋ ላይ ጋደም እንዳሉ ንፋስ የጎጆቸውን የሸራ ጣሪያ ይዞባቸው እንደሚሄድ አስታውሰው፤ ተሠርቶ የተሰጣቸው የብሎኬት ቤት ችግራቸው ተቀርፎ ተረጋግተው መኖር እንዲችሉ ማድረጉን ደስታቸውን ገልፀዋል።

ለትንሣኤ በዓል የተበረከተላቸው የቤት ስጦታ ከሰቀቀን ኑሮ ዕረፍት እንደሚሰጣቸው፣ የዘመናዊ ቤት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸውና ልጆቻቸውን ለቁም ነገር ለማድረስ የነበረባቸውን ጫና ያቀለለላቸው መሆኑን ነው የገለፁት።

ከትናንት በስቲያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካሞች፣ ለሀገር ባለውለታዎች እና ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ለተጋለጡ የከተማዋ ነዋሪዎች በቦሌ ክፍለ ከተማ ጎላጎል አካባቢ የመኖሪያ ቤት በስጦታ አበርክቷል።

ከተማ አስተዳደሩ ለአቅመ ደካሞች ካስተላለፋቸው ቤቶች ውስጥ ጥቂቱን ተዘዋውረን ተመልክተናል። “ዋው” የሚገርም ነው፡፡ ቤቶቹ የተገነቡበት ጥራት፣ ወለሉ ላይ የተነጠፉት ሴራሚኮች፣ የቤቶቹ ስፋት፣ መፀዳጃ ቤቶቹ የተሠሩበት መንገድ ደረጃቸውን የጠበቁ እንደሆነ አይተናል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You