
አዲስ አበባ፡- እንደ ሀገር የምንመለከታቸውን ከባህል ያፈነገጡ ተግባራትን ለመግራት የሃይማኖት ተቋማት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባት የሆኑት መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል ገብረእየሱስ ቆሞስ አሳሰቡ፡፡
መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ያለፈው ትውልድ የራሱን በጎም ይሁን በጎ ያልሆነ ሥራ ሠርቶ አልፏል፡፡ አሁን ያለው ትውልድ ደግሞ የራሱን ሥራ መሥራትና እየተጓዘበት ያለውን መንገድ ማጤን ይገባዋል፤ ትውልድን በማነጽ ረገድም የሃይማኖት ተቋማት ትልቅ ሥራ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
ሀገር የምትኖረው ሰላም ሲሰፍን፣ መተባበር ሲኖር ነው ያሉት መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል፤ እውቀት አለን የሚሉ ግለሰቦችም ሕዝብን ከሕዝብ ከሚነጣጥል ንግግራቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባና መረጃን ከማጋራታቸው በፊት ቆም ብለው ሁለቴ ማሰብ ይገባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል ፡፡
እንደ ሀገር በርካታ የምንታወቅባቸው አብሮ የመኖር እሴቶች ያለን ቢሆንም በምንሰማቸው ዜናዎች ይህ ባህላችንና እሴታችን እየተዳከመ ነው ያስብላል፡፡ ለዚህም ትውልዱን ከመተሳሰብ፣ ከፍቅር፣ ከመቻቻልና ከመረዳዳት ከተማ ማነው ያስኮበለለው የሚለውን መጠየቅ ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አንድነትን የሚጠላ ሊኖር አይችልም ያሉት፤ መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል፤ አሁን ያለው ትውልድ ሀገሩን ለማሳደግ እና አንድነቱን አስቀጥሎ ለመቆየት የአባቶቹን ፈለግ በመከተል አብሮነትን እና አንድነትን የሚያጠናክርበት የፍቅር ካምፕ ያስፈልገዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት በኅቡዕም ሆነ በገሐድ የሚያስተምሩት ትምህርት ተመሳሳይ፣ ሀገርና ትውልድን የሚያንጽ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተው፤ የሃይማኖት አባቶች ዘረኝነትና ጎጠኝነትን የሚፀየፍ ትውልድ የሚገነባ መልዕክት ማስተላለፍ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡
ሰላምን በማጽናት ረገድ መንግሥትም ነገሮችን በትዕግስት በማየት ኃላፊነት አለበት በማለት የገለጹት መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል፤ እንደ ዜጋ እንዲሁ መብትና ግዴታችንን ለይተን ማወቅና ለትውልዱ ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡
መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል በአሁን ጊዜ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሰዎች የራሳቸውን ሃሳብ በቀላሉ እንዲያጋሩ አስችሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ምክንያት በእነዚህ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መረጃዎች እና የሚተላለፉ መልዕክቶች ጥላቻን የሚዘሩ እና የሕዝብን አንድነት የሚሸረሽሩ እንዳይሆኑ ቁጥጥር ማድረግ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩና እንደ ሕዝብ ያለንን አንድነት የሚሸረሽሩ መልዕክት በሚያስተላልፉ ላይም ርምጃ ሊወሰድ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል ፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በዚህ እና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የስብከተ ወንጌል ክፍል አገልግሎት አገልጋይ የሆኑት መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል ገብረእየሱስ ቆሞስ ጋር ያደረግነውን ቆይታ በዘመን እንግዳ ገጽ 6 ላይ ያገኙታል፡፡
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም