
አዲስ አበባ፡- የኑሮ ውድነትን በሚያባብሱ እና በሕገ ወጥ መንገድ ምርት በሚያከማቹ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የአዲስ አበባ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አስታወቁ። በሕገ ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ የሰላም ሠራዊት አባላት ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚደክሳ ከበደ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ በሸገር ከተማ እና በአዲስ አበባ ከተማ የኑሮ ውድነትን በሚያባብሱ እና በሕገወጥ መንገድ ምርት የሚያከማቹ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥራዎች ተሠርተው ውጤት ማግኘት ተችሏል።
አዲስ አበባ ላይ የንግድ ሱቅ ኖሯቸው መጋዘኖቻቸውን በሸገር ከተማ በማድረግ ሕገወጥ የምርት ክምችት ሲያደርጉ በተገኙ እንዲሁም የንግድ ሱቆቻቸው ሸገር ከተማ ላይ ሆኖ መጋዘኖቻቸውን አዲስ አበባ ላይ በማድረግ የሸቀጦች እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል፡፡
ከገቢ ስወራ ጋርም በተያያዘ እቃዎቻቸውን ወደ ሸገር በማሸሽ ገቢ በሚሰውሩ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ከፍተኛ የኦፕሬሽን ሥራ መሠራቱን አስታውቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከ241ሺ በላይ የሰላም ሠራዊት አባላት በ4992 ብሎኮች ተደራጅተዋል፤ ከወንጀለኞች ጋራ በቅንጅት ሲሠሩ የነበሩ የሰላም ሠራዊት አባላትን በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ቢሮው የሰላም ሠራዊት አባላት ጥፋተኛ ሆነው ሲገኙ ተጠያቂ የሚደርግ አሠራር አለው የሚሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ከዚህ ቀደም ከጠላት ኃይሎች ጋር በቅንጅት ሲሠሩ የተገኙ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አራት በኮልፌ አምስት በድምሩ 9 አባላት ላይ ርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል፡፡
የሰላም ሠራዊት አባል መሆን ከወንጀል ተጠያቂነት ነፃ እንደማያደርግ የሚናገሩት አቶ ሚደቅሳ፤ ሕግ እና ሥርዓትን አክብሮ መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል። ከሕግ አግባብ ውጭ የሚሠሩ የሠራዊቱ አባላትም ሕግን አክብሮ የሚሠራውን ባለመልካም ስብዕና ባለቤት የሆነውን የሰላም ሠራዊት እንደማይወክልም አብራርተዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ የሰላም ሠራዊት አባላት በጎ ፈቃደኞች ናቸው፡፡ በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው በሰላም ሠራዊት አደረጃጀት ውስጥ ያሉ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ቀን እና ሌሊት ከተማቸውን በንቃት ይጠብቃሉ። ነገር ግን ቁጥራቸው ጥቂት የሚባሉ የሰላም ሠራዊት አባላት ሕግና ሥርዓትን ባለማክበር ከወንጀለኞች ጋር በጋራ ሲሠሩ ተይዘዋል፡፡ እነዚህ ጥፋተኞች የሠራዊቱን ስም ሊያጎድፉ አይገባም፡፡
ከ600ሺ በላይ የሚሆን የሰላም ሠራዊት አባል በሕልውና ዘመቻው ወቅት ወደ ክተቱ እንደገባ ያስታወሱት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፤ ከሱስ እና ከተለያዩ የሥነምግባር ችግሮች ጋር ተያይዞ ቁጥሩን በመቀነስ ወደ 241ሺ ማውረድ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በሁለቱ ከተሞች የፀጥታ ጥምር ኃይል እንዳለ አመልክተው፤ የሸገር ከተማ ምክትል ከንቲባ የአዲስ አበባ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ እና የሁለቱም ከተሞች ፖሊስ ኮሚሽኖች በተገኙበት በጋራ ሥራዎች እንደሚገመገሙ ገልጸዋል፡፡
ሸገር ላይ ጥፋት አጥፍቶ አዲስ አበባ ላይ መደበቅ እና አዲስ አበባ ላይ ጥፋት አጥፍቶ ሸገር ላይ መደበቅ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ወንጀለኞችንም አሳልፎ የመስጠት አካሄድም ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም