የትንሣዔ በዓል የዕርድ እንስሳት ገበያ ቅኝት

ከሰሜን ሆቴል ተነስተን ወደ ሸጎሌ የቁም እንስሳት ገበያ ማዕከል ስናመራ እዚህም እዛም በርከት ያሉ በጎችን ይዘው የቆሙ ነጋዴዎች ይታያሉ። በአስፋልቱ ከሚንቀሳቀሱት ተሽከርካሪዎች ለዓይን ቅድሚያ የሚታዩት በርካታ በሬዎችን በየተቃራኒ አቅጣጫ ጥቅጥቅ አድርገው የጫኑ አይሱዙ መኪናዎች ናቸው። ወደዋናው የቁም እንስሳት መገበያያ ማዕከል ከመድረሳችን በፊት በርካታ ክብ ክብ የሠሩ በየሜዳው የቆሙና መጠለያ የተሠራላቸው

ወደ ማዕከሉ ስንቃረብ እዚህም እዛም የሚታዩት በሬዎች ገበያ ነው ፡፡ በግንብ አጥር የተከለለው ሸጎሌ የቁም እንስሳት ገበያ ማዕከል የበሬ ንግድ ብቻ የሚስተናገድበት ነው። ወደ ውስጥ ስንገባ በአብዛኛው የማዕከሉ ቦታ በሬዎች ርስ በእርስ እየተገፋፉ የቆሙ ሲሆን በግቢው ገዥዎችና ሻጮች እዚህም እዚያም በዋጋ ሲከራከሩ ይታያል፡፡

የሸጎሌ የቁም እንስሳት ገበያ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተገኑ ቶሎሳ ይባላሉ። ያለፉትን ሦስት ቀናት በርካታ በሬ ወደ ገበያው ገብቷል፡፡ በተለምዶ ሰው ለበሬ ገበያ የሚወጣው ዓርብ የስቅለት እለት ማታ አካባቢና ቅዳሜ ሙሉ ቀን ነው። በእርግጥ ነጋዴው ከሚገዛበት ቦታ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ሰምተናል፡፡ ነገር ግን እስካሁን የተጋነነ የዋጋ ለውጥ አላየንም ይላሉ።

በእርግጥ የእኛ ሥራ ዋጋ መተመን አይደለም። ነገር ግን ሸማቾች በደላላና በሌባ ተዋክበው እንዳይዘረፉና እንዳይጭበረበሩ እንቆጣጠራለን። በግቢው ብቻ ሳይሆን ሸማቾች ተረጋግተው አማራጭ አይተው መስተናገድ ይችላሉ ብለዋል።

«በቁም እንስሳት ገበያው መጠነኛ የሚጠበቅ ጭማሪ አለ» ያሉን ደግሞ የበሬ ነጋዴና የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት የነጋዴዎች ተጠሪ የሆኑት አቶ ዳዊት አበበ ናቸው። አቶ ዳዊት በበሬ ንግድ ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ስሠራ ቆይቼአለሁ በየወቅቱ የሚኖር የዋጋ ልዩነት አለ። ብዙ ጊዜ የሚፈጠረው ልዩነት የመጨመር እንደሆነ ይገልጻሉ።

ዘንድሮ ከብት ለማምጣት ስንቀሳቀስ የገጠሙን ነገሮች እኛን ብቻ ሳይሆን ሁሉም ነጋዴ ዋጋ ለመጨመር የሚያስገድዱ ናቸው። ለምሳሌ ከነዳጅ ጋር በተያያዘ የትራንስፖርት ዋጋ ጨምሯል። የፀጥታው ጉዳይና የመኖ ዋጋ መጨመር ምክንያቶች እንደ ሁኔታው ከአስር ሺህ እስከ 20 ሺህ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል። ይህም ሆኖ አነስተኛ በሬ ከሃምሳ ሺህ ብር ጀምሮ የሚገኝ ሲሆን እንደ አቅም እስከ ሁለት መቶ ስልሳ ሺህ የሚሸጥ እንዳለ ነግረውናል።

“እኔ በጎችና ልየሎችም አስገብቻለሁ የእነሱም ገበያ ዋጋ ተቀራራቢ ነው። በግ ከስምንት ሺህ ብር ጀምሮ አለ። ፍየልም ከአስራ ሁለት ሺህ ብር ጀምሮ የሚገኝ ሲሆን ገዥው እንደየአቅሙ የሚገዛበት አማራጭ ዋጋ አለ” ሲሉ ገልጸውልናል።

እንስሳትን ቀድሞ መግዛት ማቆያ ስለሚፈልግ ብዙ ሰው ቀድሞ የመግዛት ልምድ የለውም የሚሉት ነጋዴው፤ ገዥው በአቅሙ ልክ እየገዛ እየሄደ መሆኑን ነግረውናል፡፡

በበግና የፍየል ገበያ ለመግዛት ሲዘዋወሩ ያገኘናቸው አቶ ግሩም አይቼው እንዳሉት፤ የመጣሁት የገበያውን ሁኔታ ለማጣራት እግረ መንገዴን ነው። ጥሩ ጥሩ በጎችና ፍየሎች ወደ ገበያው ገብተዋል፡፡ እስካሁን እየተጠራልን ያለውም ዋጋ እንደፈራነው አይደለም። ነገር ግን ዋጋው ካለፈው የገና በዓል ጭማሪ ማሳየቱን ይገልጻሉ።

እስካሁን መካከለኛ በግ ከአስራ ሁለት ሺህ በታች የጠራልኝ የለም የሚሉት ገዥው፤ ብዙ ነገር ጭማሪ ስላሳየ በዚህ ላይ በበዓል ገበያ የሚፈጠር ጭማሪ እንደሚኖር ስለሚገመት በበኩሌ በአምናው የገንዘብ መጠን እቅድ አልያዝኩም። ይህም ሆኖ ግን እዚህ ከመግዛቴ በፊት በአቅራቢያ ሌሎች ገበያዎችንም ለማየት እቅድ አለኝ ይላሉ።

በገበያ ቦታዎች የደንብ አስከባሪዎች፣ ፖሊሶችና የከብት ገበያ አስተናባሪዎች ከሌላው ጊዜ በተለየ ገበያው ሥርዓት እንዲይዝ ማድረጋቸው የሚያስደስት ሥራ ነው። ይህም በእዚህም ሊቀጥልና በሌሎች ቦታዎችም እንደ ተሞክሮ ሊተገበር የሚገባው ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You