ጌትነት ምህረቴ
በአዲስ አበባ ከተማ ከ21 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ 322 ባለቤት አልባ ህንጻዎችና ከአንድ ሺህ 338 ሄክታር በላይ መሬት በህግ ወጥ መልኩ መያዛቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፤ህገ ወጥነትና ጥፋት እንዳይቀጥል ፈትሾ ማስተካከል፣ ኢ-ፍትሃዊነትን ወይንም በአቋራጭ መንገድ ለመበልጸግ የሚደረግን አካሄድ መከላከል ይገባል።
ስለዚህ ተጠያቂነትን በማስፈን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል። በመሬት ወረራ፣ በህገ ወጥ መንገድ በተያዙ የጋራ መኖሪያና የቀበሌ ቤቶች ዙሪያ ፖሊስና የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ምርመራ በማካሄድ ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚሰሩ ምክትል ከንቲባዋ አስታውቀዋል።
በተለይ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ህገ ወጦች እንዲለቋቸውና በህጋዊ መንገድ በዕጣ እንዲተላለፉ ካቢኔው ውሳኔ ማስተላለፉን አስታውቀዋል። የጋራ መኖሪያ ቤትን በተመለከተም 21 ሺ 695 በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ ሲሆን እነዚህ ቤቶች ግለሰቦቹ ህጋዊ መንገድን ተከትለው ያገኟቸው አይደሉም።አንዳንዶቹ መብት ተፈጥሮላቸው ካርታ ተሰጥቷቸው ቤቱን ይዘው መገኘታቸውን ይፋ አድርገዋል።
ከእነዚህ ውስጥ 15 ሺ 891 ቤቶች ምንም አይነት መረጃ ያልቀረበባቸው ናቸው። አራት ሺ 530 ቤቶች ሰዎች ገብተውባቸው የነበሩ ግን ረጅም ጊዜ ዝግ ሆነው የቆዩ፣ 850 ቤቶች ተዘግተው የቆዩና ያልተላለፉ መሆናቸው ተጠቅሷል።እንዲሁም 424 ቤቶች ሰዎች ሰብረው ገብተው ተይዘው የተገኙ መሆኑን የጥናቱ ግኝት ማመልከቱን አስታውቀዋል።
በዕጣ ሳይሆን በተለያዩ አግባቦች ወደ ተጠቃሚው ግለሰቦች የተላለፉ ደግሞ 51 ሺ 64 ቤቶች ሆነው ተገኝተዋል። ቤቶቹ በድጎማና መካከለኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እስከተገነቡ ድረስ ለታለመለት ዓላማ መዋል ይገባው እንደነበር አንስተዋል። ከዚህ አኳያ በጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በህገ ወጥ መልኩ የሚኖሩባቸው ሰዎች ላይ ምን ህጋዊ ተጠያቂነት ያስከትላል የሚለው ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ በፌዴራል ማናቸውም ፍርድ ቤት ጠበቃና የህግ አማካሪ አቶ ቁምላቸው ባልቻ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተውናል።
እሳቸው እንደሚሉት፤እነዚህ ሰዎች ቤቱ ያገኙት በዘፈቀደ አይደለም፤ሆን ብለው አስበው ተዘጋጅተውበት፣ጉቦ ሰጥተው ወይም ከሀላፊዎች ጋራ ተመሳጥረው ወይንም የተዘጋውን ቤት ሰብረው ገብተው ነው ቤቱን ያገኙት። እናም የራሳቸው ያልሆነን ቤት ነው ሲኖሩበት የቆዩት። እንዲህ አይነት ተግባር ደግሞ የፍትሃብሄር ሀላፊነት ብቻ ሳይሆን የወንጀል ሀላፊነትን ያመጣል።
የጋራ መኖሪያ ቤቱ የሚተላለፈው በፕሮግራሙ መጀመሪያውኑ ተመዝግበው ሲቆጥቡ ቆይተው መንግስት ደግሞ የተወሰነ ድጎማ አድርጎ ቤት ለሌላቸው በዝቅተኛ ኑሮ ለሚኖሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ነው። ከዚህ አኳያ ቤቱን እንዴት አገኙት የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት አለበት። ምክንያቱም በምዝገባው ወቅት ያልተመዘገቡ፣ዕጣው ያልደረሳቸው ሰዎች በጋራ ቤቱ በህገ ወጥ ገብተው መኖቸራው ህገወጥ ተግባር ከመሆኑም ባሻገርየወንጀል ተባባሪ ሆነዋል።
ስለዚህ አሉ አቶ ቁምላቸው የወንጀልና የፍትሀብሄር ሀላፊነት ያመጣባቸዋል። በወንጀል ህጉ ቁጥር 402 ንዑስ ቁጥር 2 በግልጽ እንደተቀመጠው የመንግስት ሰራተኛና ሀላፊ የሚለውን በዝርዝር አስቀምጧል። በዚህ መሰረት በወንጀል ህጉ ቁጥር 404 ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛና ሀላፊ የመንግስትን ሀላፊነት ተጠቅሞ ያለ አግባብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለራሱ ሆነ ለሌሎች ጥቅም ያስገኘ እንደሆነ በሙስና ወንጀል ያስጠይቀዋል።
እንዲሁም በወንጀል ህጉ ቁጥር 405 ደግሞ በአስተዳደርና በፍትሀብሄር ሀላፊነት በተደራራቢ የሚያስጠይቅ መሆኑን ጠቅስዋል።እንዲሁም ለአብነት አለአግባብ መበልጸግ ተጠያቂ ይሆናሉ።
የራስ ያልሆነን ሀብት እንደራስ አድርጎ መጠቀምም የወንጀል ሀላፊነት ያስከትላል።ቤቱን ለማግኘት የሄዱበት መንገድ የወንጀል ሀላፊነትን ሊያስከትል ይችላል።እናም ከላይ በተጠቀሱት የፍትሀብሄርና የወንጀል ህጎች የሚጠየቁበት አግባብ መኖሩን ጠቅሰዋል።
ሆኖም በህግ ወጥ መልኩ በጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ከሚኖሩት ሰዎች ይልቅ ይበልጥ ተጠያቂነቱ የሚኖረው ይህን ቤት ለመስጠት ሀላፊነቱ ያላቸው የመንግስት ባለስልጣናት ላይ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ቁምላቸው፤እነዚህ የመንግስት ባለስልጣናት የህዝብና የመንግስት ንብረት ለሌላ ሰው አሳልፎ መስጠት በሙስና ወንጀልና የመንግስትን ስልጣን አላግባብ በመጠቀም ያስጠይቃቸዋል።
የህግ የበላይነት የሚረጋገጠው ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ሲሆን ነው። ከዚህ አኳያ ህግ በእነዚህ ሰዎች ላይ መስራቱን ማሳየት ሲቻል ሌሎች ሰዎች ከእነዚህ ይማራሉ። የቅጣት አንዱ ዓላማ ማስተማር ነው። ሌላውም በስልጣን ላይ ያለው ሆነ ወደፊት ስልጣን የሚያገኘው ሰው እነዚህ ሰዎች በህግ መጠየቃቸውን አይቶ ከእነዚህ አይነት ሰዎች ሊማር ይችላል።
ስለዚህ የፈጸሙት ድርጊት የወንጀል ሀላፊነትን የሚያመጣ ነው ። አቃቤ ህግ ጉዳዩን አጣርቶ ለፍርድ ቤት ማቅረብ አለበት።በዚህን ጊዜ ህብረተሰቡ ህግ መስራቱን በተጨባጭ ያያል ሲሉ አስረድተዋል። ለእነዚህ ሰዎች ውሳኔ ካልተሰጠ፣ፍርድ ቤት ቆመው ተገቢውን ቅጣት ካላገኙ ሌላው ወደ ስልጣን የሚመጣውም ሰው ትምህርት ሊያገኘ አይችልም። እነዚህን ሰዎች ወደ ፍርድ ለማቅረብ ፖሊስና አቃቤ ህግ ጊዜ ሳይሰጡ ርብርብ ማድረግ አለባቸው።
በመዲናችን የሚታየው የመኖሪያ ቤት እጥረት ነዋሪዎችን እያማረረ ይገኛል። ይኸው ችግር ቤት ፈላጊዎች ሰማይ የነካ ኪራይ ከፍለው እንዲኖሩም እያስገደደ ነው። መንግስት የነዋሪዎችን የቤት እጥረት ለመቅረፍ በቀረፃቸው የቤቶች ልማት መርሀ ግብሮች ለመፍታት ጥረት እያደረገ ቢገኝም የግንባታ ሂደቱ መጓተት የነዋሪውን የቤት ጥያቄ መመለስ አልቻለም።
በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ ረጅም ዓመታት ፈጅተው ተገንብተው ከተጠናቀቁት ቤቶች ደግሞ 21 ሺህ በላይ የሚሆኑት በህገ ወጥ መልኩ መያዛቸው ችግሩን ይበልጥ ያወሳስበዋል። ስለዚህ ከተማ አስተዳደሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በህገ ወጥ መንገድ እንዲያዙና ለዚህ ድርጊት ተባባሪ የሆኑ ሰዎችን የህግ ተጠያቂ ለማድረግ የጀመረውን እንቅስቃሴ ከፍጻሜ ማድረስ ይጠበቅበታል እንላለን።
አዲስ ዘመን ጥር 28/2013