አስቴር ኤልያስ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛው አገራዊ ምርጫ ከግንቦት መጨረሻ እስከ ሰኔ አጋማሽ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚካሄድ ይታወቃል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ ዝግጅቶች እያደረገ ነው። ምርጫው በሀገሪቱ የምርጫ ታሪክ አዲስ ምእራፍ ከፋች እንደሚሆን ይታመናል ።
በምርጫው አጠቃላይ ዝግጅትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ እንዲሁም ከፓርቲዎች እውቅና ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎችና በቅርቡ ከፓርቲነት የተሰረዘው ህወሓት ጉዳይ አዲስ ዘመን ከቦርዱ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ወይዘሪት ሶሊያና ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ አጠናቅሮ እንደሚከተለው አሰናድቶታል፡፡
አዲስ ዘመን፡– ምርጫው ሊካሄድ የቀረው አራት ወር ያህል ጊዜ ነው። ቦርዱ ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን እያደረገ ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል ?
ወይዘሪት ሶሊያና፡– ዝግጅቶቹ የተለያዩ ናቸው፤ አሁን ከዝግጅት ምዕራፍ አልፈን ምርጫን ለማስጀመርና የማስፈጸም ስራ ውስጥ ገብተናል። በጊዜ ሰሌዳው ላይ ካሉ ተግባራት መካከል አንደኛው ቢሮዎችን መክፈት ነው፣ እሱን ተከትሎ ያለው የእጩዎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች መረጣ ነው። ስለዚህ እዚህ ላይ ደርሰናል፤ እንዲህ ሲባል ከዝግጅት ጋር የተያያዙ ስራዎቹን አጠናቀናል ማለት ነው፡፡
በኦፕሬሽን በኩል ስናደርጋቸው የነበሩ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል። ማለትም የቁሳቁስ ግዥ፣ የቁሳቁስ እሸጋ፣ የተለያዩ ስራዎችን የሚያከናውኑ አስፈጻሚዎችን የመመልመል ስራና የመሳሰሉ ተግባራትን ማለት ነው።
ምርጫውን የማስፈጸም ስራ ስንጀምር ከክልሎች ጋር በመሆን በአንድ ክልል ውስጥ ምን ያህል የምርጫ ክልል ቢሮ ያስፈልጋል? ምን ያህልስ የዞን ቢሮዎች ያስፈልጋሉ? በሚለው ላይ ተወያያተናል ፤ ምክንያቱም እነዚህ ቢሮዎች በቋሚነት ለሌላ ስራ የሚውሉ ናቸው፤ ለምርጫ ጊዜ ሲሆን ለምርጫው ይሆናሉ፤ ይህም ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው የሚቆየው። አገልግሎታቸውን ሲያጠናቅቁ ወደመደበኛ አገልግሎታቸው ይመለሳሉ። በእነዚህ ጉዳዮች አብረን ከክልሎች ጋር ለመስራት ጥያቄዎችን ማቅረብ፣ መረጃዎቹን ማደራጀት እና መሰል ስራዎችን ስናከናውን ቆይተናል።
በሌላ በኩል ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምዝገባ ማጠናቀቅ ሌላው ተግባር ነበር። ለሲቪክ ማህበራት የተለያዩ ጥሪዎችን ማድረግ እንዲሁ ፣ ይህም ምርጫ ለመታዘብ ሊሆን ይችላል አሊያም ደግሞ መራጮችን ትምህርት ለማስተማር ሊሆን ይችላል፤ የራሳችንን የመራጮች ትምህርት ደግሞ ዝግጅት ማድረግም ሌላው ተግባር ነው፤ ምክንያቱም ምርጫው ሲጀመር መራጮች በተከታታይ መረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ ቀድሞ መዘጋጀት ያስፈልጋል፣ በዚህ ጉዳዩ የተለያዩ ስራዎችን ስንተገብር ቆይተናል።
አሁን የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን የሚያስተ ዋውቁበትና የምርጫ ምልክቶቻቸውን የሚመርጡበት የጊዜ ሰሌዳ ላይ ነን፣ ከዚህ ቀጥሎ ያለው ትልቁ ስራ በጊዜ ሰሌዳ መሰረት ያለው እንቅስቃሴ ነው ፡፡
አዲስ ዘመን፡– ከፖለቲካ ፓርቲዎች ሕጋዊ እውቅና ጋር ተያይዞ የነበረው ሂደት ምን ይመስል ነበር?
ወይዘሪት ሶሊያና፡– የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ተያያዥ የሥነ ምግባር ሕግን አንድ ላይ አጣምሮ የያዘ አዲስ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ወጥቷል። ከዚህ በፊት የነበሩትን ሕጎች አንድ ላይ አቅፎ የያዘ ሕግ እንደማለት ነው፤ በዛ ሕግ ላይ አዳዲስ መስፈርቶች አሉ። በተጨማሪም ከዚህ በፊት ከነበሩትም ሕጎች ውስጥ የተቀነሱ አሉ። በዚህ መሰረት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ከዚህ በፊት የነበሩትን አስተካክለን መጨመር ያለባቸው እንዲጨምሩ አስፈላጊ ያልሆኑትን ደግሞ በሕጉ መሰረት እንዲቀንሱ ተደርገዋል።
ከዚህ በፊት የነበረው የፓርቲዎች ሕገ ደንብ ስታንዳርድ አልነበረው። ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ማንኛውንም ሕገ ደንብ ይጽፋል፤ በኋላ ግጭቶች ሲፈጠሩ ሕገ ደንቡ ሕገ ደንባቸውን አያውቀውም፤ አይቆጣጠረውምና ሕገ ደንቡ ውስጥ ያልተካተተ ጉዳይ ይሆናል። ስለዚህ እንዲህ አይነቶቹን ክፍተት አይተናል፡፡
የጠቅላላ ጉባኤ፣ የእጩ አመራረጥ የመሳሰሉ ጉዳዮችን ፓርቲዎች ሕገ ደንባቸው ውስጥ የሚያካትቱ እንደመኖራቸው የማያካትቱም ይኖራሉ። ስለዚህ አዲሱ ሕግ ለሕገ ደንቦቹ ግዴታ ማሟላት ያለባቸውን ስታንዳርድ አውጥቷል። ይህን ሲያደርግ ከልምድም በመነሳት ሲሆን፣ ፓርቲዎች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችንም በማየት ነው። ስለዚህ ያንን መሰረት በማድረግ ሕገ ደንቦቻቸውን እንዲያሻሽሉ ተደርጓል፡፡
ሌላው የመስራቾች ፊርማ ከዚህ በፊት ከነበረው ቁጥር ጨምሯል። እሱን ማሟላት ያለባቸው መቼ ነው፤ ምን ያህልስ ቁጥር ነው የሚሉም በሕጉ ውስጥ የተቀመጡ መስፈርቶች አሉ። እነርሱን መስፈርቶች እንዲያሟላ መጀመሪያ ላይ ወጥቷል፤ ቀጥሎም የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት አድርገውበታል። ጊዜው ደግሞ ይበቃል ወይስ አይበቃም የሚለው ላይም ውይይት ተደርጎ ወደተግባር ተገብቷል፡፡
ከዚህ በፊት ክልላዊ ፓርቲ ለመመስረት 700 ፊርማ ማሰባሰብ በቂ ነበር። አገራዊ ፓርቲ ለመመስረት ደግሞ አንድ ሺ 500 ፊርማ ነበር የሚያስፈልገው። አሁን የክልላዊ ፓርቲ ወደ አራት ሺህ ከፍ ሲል አገራዊ ፓርቲ ደግሞ አስር ሺህ ሆኗል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ደግሞ ስብጥር የሚባል ነገር አለ፤ አገራዊ ፓርቲ ከሆነ ቢያንስ ከአምስት ክልሎች መስራችን ማግኘት አለበት። ከእያንዳንዱ ክልል ደግሞ የየራሱ ውጤት በመቶ የሚሰላ ነገር አለው። ከ15 በመቶ ጀምሮ ከፍተኛው 40 በመቶ ድረስ መስፈርቶች አሉት። በዚህ መሰረት ፊርማቸውን ሰብስበው አስገብተው ባሉበት ጊዜ የኮቪድ ወረርሽኝ መጣ፡፡
በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት ቦርዱ ተሰብስበው የመጡትን ፊርማዎች ተቀበለ እንጂ ለማጣራት አልተንቀሳቀሰም። በወረርሽኙ ምክንያት የተጣሉ ክልከላዎች ተነስተው በመጠኑም ቢሆን እንቅስቃሴዎች በተጀመሩበት ጊዜ የሰራነው የመጀመሪያ ስራ ቢኖር በእያንዳንዱ ክልል ላይ የሚገኙና መጣራት ያለባቸውን ፊርማዎች ቆጥረን ለይተናል።
በአንድ ክልል እንደ አማራ ኦሮሚያ ያሉ ክልሎች ላይ ወደ 2 ሺ 700 አካባቢ ድረስ መስራች ፊርማ ሲሆን፣ የቆዳ ስፋታቸው አነስ ባሉ ክልሎች ላይ እስከ 700 አካባቢ ነው ፊርማዎችንም የማጣራት ስራ መስራት ነበረብን። ይህን ስናደርግ ከገቡት ፊርማዎች በአጠቃላይ ከሶስት እስከ አምስት በመቶ ናሙና ይወሰዳል።
የፊርማ እውነተኛነትን የማረጋገጥ ስራ ሲሰራ የፓርቲው ማንነት እንዲነገር አናደርግም፤ ምክንያቱም አድልዎ የሚባል እድል እንዳይኖረው ነው። ስለዚህ ጉዳዩን የለየነው በፓርቲ ሳይሆን በየወረዳው ነው። ቦርዱ በሁሉም ቦታ ባሉት የክልል ጽሕፈት ቤቶች ጉዳዩ ይጣራል። እንዲህ ሲደረግ ግን የየትኛው ፓርቲ አባል ነው የሚለውን የምናወቀው እኛ ብቻ ነን እንጂ ሌሎቹ አያውቁም። ፊርማው የተፈረመበት ዞን፣ ወረዳ ይሁን ቀበሌ ድረስ በመሄድ ፈራሚው አካል በትክክል አለ ወይስ የለም የሚለውን ነገር ያጣራሉ።
አዲስ ዘመን፡– በማጣራቱ ስራ ያጋጠመ ችግር የለም?
ወይዘሪት ሶሊያና፡- እውነቱን ለመናገር የተለያዩ ችግሮች አጋጥመዋል። ለምሳሌ አንደኛው ችግር በአብዛኛዎቹ ወረዳዎች ውስጥ የተደራጀ መረጃ አለመኖር ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ፊርማውን የፈረመ አካል በዚህ ወረዳ የለም ይባላል። እንዲህ አይነቱ አካሄድ ሂደቱን ያጓትተዋል። ወይ ደግሞ ስም በትክከል ሳይጻፍ ይቀራል።
ሂደቱ ወራትንም ያህል ፈጅቶ ጨርሰን ስንመጣ ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት ከግምት ውስጥ የገቡ ነገሮች ለምሳሌ የስም አጻጻፉ የተሳሳተ ነው ተብሎ በቦታው ያለ አካል ደግሞ የማጣራት ሂደቱን ቶሎ ካላከናወነ እንደሕጋዊ ፊርማ ሆኖ ለፓርቲው ይቆጠርለታል፡፡
በተለይ እንደዚህ አይነት ችግር ያለባቸው አዲስ አበባ ከተማ ላይ ለምሳሌ መታወቂያው ላይ የቤት ቁጥር ተብሎ አዲስ የሚባል አለ፤ ይህ እንግዲህ በመንግስት በኩል የቤት ቁጥር ሊሰጠው አልቻለም ስለሚባል ለፓርቲው እንደ ሕጋዊ ፊርማ የሚቆጠርለት እንዲሆን አድርገናል፤ ምክንያቱም ፓርቲዎቹ የራሳቸውን ጥረት አድርገዋልና ነው።
ሌላው ደግሞ በክልል፣በዞንና በወረዳ አካባቢ አንተባበርም፤ ፊርማውን አናረጋግጥም የሚሉ ከሆነ እነርሱ ባለመተባበራቸው የተነሳ ፓርቲው ትክክለኛ ያልሆነ ፊርማ ነው ያቀረበው የሚሉ ድምዳሜ ላይ እንዳይደርስ ተብሎ ለፓርቲዎቹ እንዲቆጠር ተደርጓል።
ከዛ በተጨማሪ ደግሞ ግጭት ያለባቸው አካባቢዎች ለምሳሌ የማጣራት ስራውን በምናከናውንበት ጊዜ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በሌሎች አንዳንድ ቦታዎችም ግጭቶች ስለነበሩ በቦታው ተገኝቶ ለማጣራት አልተቻለምና እሱም ለፓርቲዎቹ እንዲቆጠር ተደርጓል። ስለዚህ ምንም አይነት ምክንያት የፓርቲዎችን ጥረት እንዳያስተጓጉል አድርገናል፡፡
በእነዚህ ሁሉ የማጣራት ስራ ከእድሜ በታች የሆነ የ13 ዓመት ልጅ ተገኝቷል። ፈረሙ የተባሉ ሰዎች የሌሉ እንዲሁም አንድ ሙሉ ወረዳ የሌለበትና ብዙ ስም የተጻፈበት አይነት ነገሮች አጋጥመውናል። ይህ ሁሉ የማጣራት ስራ ተሰርቶ በመጨረሻ ከቀረቡት ፓርቲዎች 35 በመቶ ያሟሉ እንደ ሕጋዊ ፊርማ ይቆጠርላቸዋል፤ ከ35 በመቶ በታች ያቀረቡ ፓርቲዎች ግን በቂ ፊርማ እንዳልሰበሰቡ ፓርቲዎች ተቆጥረው ሊሰረዙ ችለዋል።
ከፓርቲዎች ስረዛ ውጭ ያጋጠመን ለምሳሌ አገራዊ ፓርቲ ነን ብለው ቁጥር ያላሟሉ አሉ፤ ቢያንስ ከአምስት ክልል መስራች የማያመጡ ሆነው የተገኙ አሉ። ከአንድ ክልል የሚያመጧቸው በትልቁ 40 በመቶ ሲሆን በትንሹ ደግሞ 15 በመቶ ነው፡፡አንዳንዶች ግን 15 በመቶ በታች ስላመጡ ይህ ለአገራዊ ፓርቲ ብቁ ስላልሆነ መርጣችሁ የክልል ፓርቲ መሆን ትችላላችሁ የሚል እድል ተሰጥቷቸዋል።
እድሉንም የተጠቀሙ ፓርቲዎች አሉ። እሱን ማድረግ አንችልም ብለው የተሰረዙም አሉ። በጥቅሉ መጨረሻ ላይ በመጀመሪያ ዙር ወደ 27 የሚጠጉ ፓርቲዎች ከነበሩ ፓርቲዎች ውስጥ ፊርማውን ማሟላት ስላልቻሉ ተሰርዘዋል።
አንዳንዱ ፊርማ ማምጣት አንችልም ያሉም አሉ። ሁለተኛ ዙር ባደረግነው የማጣራት ስራ ደግሞ ዝቅተኛውን 35 በመቶ ያላሟሉ ፓርቲዎች የነበሩ ሲሆን፣ የማጣራት ሂደት ያለፉ ወደ 53 የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- አገራዊ ሆነ ክልላዊ ፓርቲ ለመሆን ፈልገውም መስፈርቱን ሳያገኙ ቀርተው የተሰረዙ ፓርቲዎች የትኞቹ ናቸው? ስማቸውን ማወቅ ይቻላል?
ወይዘሪት ሶሊያና፡– ብዙ ስለሆኑ አሁን አላስታውሳቸውም። አገራዊ ፓርቲዎች በማጣራት ሂደቱ ማለፍ የተቸገሩበትን ሁኔታ ክልላዊ ፓርቲዎች ግን ፊርማ ለማግኘት ብዙ አልተቸገሩም። እስከ 99 በመቶ ድረስ አሟልተው ማምጣት ችለዋል።
አዲስ ዘመን፡– በአገራዊ ደረጃ ያሉ ፓርቲዎች ፊርማ በማሰባሰቡ ሂደት ስንት በመቶ ላይ ደርሰዋል? ከፍተኛው የቱ ነው?
ወይዘሪት ሶሊያና፡– ለምሳሌ ብልጽግና 78 በመቶ ያህል ነው። 60 በመቶም አሉ። ነገር ግን ደግሞ ወደክልል ፓርቲዎች ሲመጣ ለምሳሌ የወላይታ ፓርቲዎች 96
በመቶ፣ የቁጫ ሕዝብ መቶ በመቶ እንዲሁ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች አብዛኛው ያስፈረሙት ፊርማ ከፍ ያለ ነው። ለምሳሌ ባልደራስ ከአዲስ ከተማ አስተዳደር ለክልላዊ ፓርቲ ሲሆን፣ ቁጥሩም 90 በመቶ አካባቢ በመሆኑ ከፍተኛ ነው። አገራዊ ፓርቲ ላይ ያለውን እጥረት ቦርዱ በማስተዋሉ በኋላ ላይ አቅሙን ቦርዱ ሲገነባ በምን አይነት መልኩ አቅማቸውን ይገነባል በሚለው ላይ የሚሰራ ይሆናል፡፡
ሌላው በፊርማ ማሰባሰቡ ላይ ያስተዋልነው ጉዳዩን በትኩረት ያለማየት ነገር ነው። ለምሳሌ የሕዝብ ድጋፍ ያላቸው ፖርቲዎች እንዳሉ ቢታወቅም በወረቀት ላይ ግን የፊርማ ማሰባሰብ ሥርዓታቸው ዝቅተኛ ሊሆን ይችላል።
ይህ የሚመነጨው አንደኛ የውክልና ስራ እንዲሰሩ የሚልኳቸው ሰዎች ወይ አቅም የሌላቸው ወይም ደግሞ ጉዳዩን በትኩረት ያለማየት ችግር ስለሚኖራቸው በአግባቡ አያስፈርሙም። መረጃ ይሳሳታሉ። ከዚህ በፊት የፓርቲ ፊርማ ተጣርቶ አያውቅም። ስለዚህ አሁንም ቢሆን ፊርማ ላይጣራ ይችላል በሚል ቸልተኝነትን ያሳዩ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡– የፓርቲዎች አርማና ምልክትን በተመለከተ አንዱን ከሌላው ፓርቲ ጋር ሲያነካካ ነበርና ሂደቱ ምን ይመስል ነበር?
ወይዘሪት ሶሊያና፡- አርማ ማለት የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ቋሚ ምልክቱ ነው። የምርጫ ምልክት ግን ለምርጫ ጊዜ ሂደት ብቻ አንድ ፓርቲ የሚጠቀምበት የምረጡኝ ቅስቀሳ በሚያደርግበት ወቅት ምልክቴ ናት የሚላት እንዲሁም የድምጽ መስጫ ወረቀቱ ላይ የሚወጣው ነው።
አንዳንድ ፓርቲዎች ከአርማቸው ጋር ተመሳሳይ የሆነ ምልክት ለመምረጥ ይሞክራሉ። ነገር ግን ሁለቱ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ፓርቲዎች ምልክታቸውን በየምርጫ ዙር መቀየር ወይም ደግሞ ያንኑ ይዞ መጓዝ ይችላሉ። ከዚህ በፊት የተጠቀምኩበት ምልክቴ ነው ካሉ ሌላው ደግሞ የእነሱን ቢመርጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ከዚህ በፊት ለተጠቀመው ነው።
በአሁኑ ወቅት ምልክት መረጣው ላይ ያደረግነው ነገር ለምልክታቸው ይሆን ዘንድ የሚያስችላቸውን ናሙና ሰጥተናቸዋል። ነገር ግን ከሰጠናቸው ናሙናዎች ውስጥ እነሱ የሚፈልጉ አይነት ምልክት ከሌለ የራሳቸውን ንድፍ ማውጣት ስለሚችሉ ያንን ያደረጉም አሉ፤ ከሰጠናቸው ናሙና ውስጥም የመረጡ አሉ። የሚያስገቡት የራሳቸው ከሆነ በተቀመጠው ስታንዳርድ ነው፤ ሁሉም ምልክት በጥቁርና ነጭ ቀለም ብቻ ነው መሆን ያለባቸው ፣ ያደረግነውም ያንን ነው ፡፡
ምክንያቱም ባለቀለም የሚሆን ከሆነ ቀለም በራሱ የራሱ የሆነ አከራካሪ ነገር ይዞ ሊመጣ ስለሚችል ነው። ለምሳሌ ከአገር አቀፍም ከክልል ባንዲራም ጋር መመሳሰል የለበት። ከታወቁም ከመንግስትም ሆነ ሌሎች ተቋምት ከሚጠቀሟቸው ምልክቶች ጋር መመሳሰል የለበትምና አከራካሪ እንዳይሆን ተብሎ ነው በጥቁርና በነጭ ቀለም ብቻ እንዲሆን የተደረገው።
በዚህም አብዛኞቹ ፓርቲዎች ከሰጠናቸው የናሙና አልበም ላይ ነው ምልክታቸውን የመረጡት። የራሳቸውን ምልክት አዘጋጅተው ያመጡ በቁጥር ደረጃ አስር አይሆኑም። የተወሰኑት ደግሞ ከዚህ በፊት የነበራቸውን ምልክት መርጠዋል። ይህ ምልክት ቀደም ሲል ስጠቀምበት ነበርና ይልቀቁልኝ የሚሉ አቤቱታዎችም የቀረበባቸው ምልክቶች ነበሩ።
አንዳንዴ ደግሞ ሁለት ፓርቲዎች የሚወራረሱ ምልክቶችን ይዘው ይመጣሉና እንደዛ ሲሆን በምርጫ ወቅት መራጩን የሚያምታቱ ስለሚሆን አንደኛው እንዲያስተካክል ይነገረዋል። የምልክት መረጣው ደግሞ በቀደመ ነው። አንድ ፓርቲ ምልክት ሳይመረጥ ቆይቶ እጩዎቼን መዝግቡልኝ ማለት አይችልም። ምክንያቱም በአሁን ወቅት የትኞቹ ፓርቲዎች እንደሚወዳደሩ ተለይቷል ማለት ይቻላል። ምልክት የማስገባቱ ሂደት አብቅቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡– ፓርቲዎቹ ምልክታቸውን ካስገቡ ቀጥሎ የሚመጣው የሚዲያ አጠቃቀም ነውና መቼ ነው የሚጀመረው? የምረጡኝ ቅስቀሳው የሚካሄደውስ በመንግስት ሚዲያ ብቻ ነው?
ወይዘሪት ሶሊያና፡– የሚዲያ አጠቃቀምና የእጩዎች የምረጡኝ ዘመቻ አንድ ላይ የሚጀመሩ ተግባራት ናቸው። ይህ ሂደት የራሱ መመሪያ ያለው ነው ፣ ይህንን የሚገዛ መመሪያ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ጋር በመሆን ተዘጋጅቷል። ባለስልጣኑ ለሚዲያዎቹ ድጋፍ ያደርጋል፤ ይቆጣጠራል። እኛ ደግሞ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፋ እናደርጋለን፤ እንቆጣጠራለን። እነሱ የአየር ሰዓት የሚደለድሉበት የራሳቸው የሆነ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሲስተም አላቸው። ባለው መስፈርት መሰረት ብሮድካስት ባለስልጣን ድልድሉን ያደርጋል።
በዚህም መሰረት ከሚዲያዎችም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አንድ ሁለት የሚሆኑ ክርክሮችን አድርገናል። በመሆኑም ከዚህ ቀደም ከነበረው መስፈርት የተሻለ እንደሆነ ገልጸውልናል። እንዲያውም ከጥቂት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሙገሳ ካገኘንባቸው ነገሮች መካከል አንዱ የሚዲያው ጉዳይ ነው።
ለምሳሌ ከዚህ በፊት መቀመጫ የነበረው ፓርቲ 30 በመቶ አካባቢ የሚያገኝበት ሁኔታ ነበር፤ አሁን አምስት በመቶ ብቻ ነው የሚያገኙት። ሴት እጩዎችንና የአካል ጉዳተኞችን የተወሰነ ያህል ይጨመራል።
በእኩልነት የሚከፋፈለው ጊዜ በጣም ትልቅ ነው። ሁሉም በእኩል የሚከፋፈሉት ጊዜ አለ። የሴት እጩዎችን ላመጡ 20 በመቶ ያህል የሚሰጥ አለ። ከዚህ በፊት መቀመጫ የነበረው ደግሞ አንድ ፓርቲ ሲሆን፣ እሱም አምስት በመቶ ነው ያለው። እሱም ብልጽግና ፓርቲ ነው።
ነባር መቀመጫ ያለው ፓርቲ ከ30 በመቶ ወደ አምስት በመቶ ዝቅ ማለቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያስደሰተ ነው፣ ሴት እጩዎችን ላስመዘገቡ ፓርቲዎች ደግሞ 20 በመቶ መሆኑ ቅር ያሰኛቸው ነበሩ።
ይሁንና የአየር ሰዓት ቀርቶ የገንዘብም ድጋፍ ሴት እጩ ላስመዘገበ ከፍ ያለነው። እዚህ ላይ ግን ብዙ ጊዜ ፓርቲዎቹ ሴት እጩ ማምጣት አስቸጋሪ እንደሆነ ነው የተለያዩ አቤቱታዎችን የሚያቀርቡት። ለዚህም ነው ማበረታቻውን አይተው ሙከራ ለማድረግ የማይሆንላቸው፡፡
ከዛ ውጪ ግን በመስፈርቶቹ ላይ የተለየ ቅሬታ የለም። የመመሪያው ረቂቅም ይጸድቃል ብለን ነው የምንጠብቀው። የሚቀየር ብዙ ያለው አይመስለኝም። የአየር ሰዓት ድልድሉ በቀረበው እጩም ላይ ይመሰረታል። ምክንያቱም ብዙ እጩ ያለው ብዙ የአየር ሰዓት ያገኛል። በመሆኑም ባለስልጣኑ እኛ በምንሰጠው መረጃ መሰረት የአየር ሰዓት ድልድሉን ያደርጋል።
አዲስ ዘመን፡– የሰዓት ድልድሉ የግሉንም ሚዲያ የሚጨምር ነው?
ወይዘሪት ሶሊያና፡– የአየር ሰዓት ድልድሉ ብሮድካስትንም ሆነ የተወሰኑ የህትመት ሚዲያን ይጨምራል። ባለስልጣኑ የሚወስነው ይሆናል እንጂ በተወሰነ ደረጃ የግልና ሳተላይት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሉና የህዝቡ መስማት ግዴታ ነው፤ በህግም የተቀመጠ ስለሆነ የአየር ሰዓት ማከፋፈል አለበት። የግሎቹ ግን በምን አይነት ሁኔታ ነው በዚህ ውስጥ መሳተፍ የሚችሉት የሚለውን ባለስልጣኑ የግል ሚዲያዎቹ ያላቸውን ሰፊ ሸፋን አይቶ የተወሰኑትን የሚያካትት ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡– ይህ የሰዓት ድልድል የግሉን የሕትመት ሚዲያ ይጨምራል?
ወይዘሪት ሶሊያና፡– የግሉን የሕትመት ሚዲያ አይጨምርም፤ ምክንያቱም የግሉ የሕትመት ሚዲያ በጣም የተጎዳ ነው። በዚህ ላይ በነጻ አምድ ስጥ ማለቱ ያስቸግራል። ምክንያቱም የአብዛኛዎቹ ገቢ የተገደበ ነው። የኤሌክትሮኒክሱ ግን ገቢያቸው ደህና ነው፤ ሰፋ ያለ የአገሪቱ አካባቢ መድረስ ይችላሉ ተብሎ ይታሰባል። በዚህም መሰረት ከግሉ ሚዲያዎች ውስጥ ምን ያህሎቹ እዚህ ውስጥ መሳተፍ ይችላሉ የሚለውን ባለስልጣኑ አይቶ የሚለያቸውና ሰዓቱን የሚደለድል ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡– ታዛቢዎች ከአገር ውስጥና ከዓለምአቀፍ ተቋማት እንደሚሆኑ ይጠበቃልና እስካሁን የተመዘገቡ አሊያም እንመዝገብ ብለው የጠየቁ አሉ?
ወይዘሪት ሶሊያና፡– ታዛቢዎችን በተመለከተ ከዚህ በፊት ከነበረው አካሄድ በተወሰነ መልኩ ልዩነት አለው። ከዚህ ቀደም የሕዝብ ታዛቢ የሚል መዋቅር ነበር። የሕዝብ ታዛቢ ማለት ምርጫ ጣቢያው ካለበት ሰፈር የሚመረጡና ሰዎች ሲመርጡ ተቀምጠው የሚታዘቡ ማለት ነው።
በአዲሱ ሕግ የሕዝብ ታዛቢ የሚል ነገር የለም። ከዚህ በፊት የነበረው የሕዝብ ታዛቢዎች ሲኖሩ የሲቪክ ማህበራት ግን የሉም፤ አይታዘቡም። በወቅቱ የነበረው ከፍተኛ አቤቱታ የሕዝብ ታዛቢዎቹ ሲመረጡ ካለው የመንግስት መዋቅር ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው የሚል ነው።
አሁን ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት የሕዝብ ታዛቢ የሚባለው ነገር ወጥቷል። በአዲሱ ሕግ መሰረት ሲቪክ ማህበራት ምርጫ መሳተፍ፣ መታዘብና ትምህርት መስጠት ይችላል። ይህን ለማድረግ ግን አገር በቀልነት መስፈርት ነው። ይህን ካሟላ ታዛቢ ለመሆን መመዝገብ ይችላል። ለዚህም ጥሪ አቅርበን ብዙ ታዛቢዎች ወደ20ሺ የሚጠጉ የታዛቢዎችን ስም ዝርዝር ድርጅቶች አስገብተዋል።
ይህን የመታዘብ ስራ ለመስራት ወጪ ያስፈልገዋልና ይህን የሚሸፍነው ራሱ ታዛቢዎችን የሚያሰማራው ድርጅት ነው። እንዲህ ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ እውቅናውን የሰጠናቸው ታዛቢ ድርጅቶች የሉም።
ገና በሂደት ላይ ነው። ቦርዱ ታዛቢዎች ናቸው ለሚላቸው ድርጅቶች እውቅና እንደሚሰጠው ሁሉ ድርጅቱ ደግሞ እነዚህ እንዲታዘቡ የማሰማራቸው የእኔ አባላት ናቸው ብሎ እውቅና መስጠት አለበት። እስካሁን 20 ሺ አባላትን ያስመዘገቡ አገር በቀል ድርጅቶች ይኑሩ እንጂ ሂደቱ ገና ይቀጥላል።
ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችን የሚጋብዘው የኢትዮጵያ መንግስት እንጂ ቦርዱ አይደለም። እንዲህም ሲባል በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት ምርጫ ልናካሄድ ነውና መጥታችሁ ታዘቡልን በሚል የተለያዩ ተቋማት ይጋበዛሉ።
እነርሱ የኢፌዴሪ መንግሥት የጋበዘበትን ደብዳቤ ይዘው መምጣት ይጠበቅባቸዋል። ያለደብዳቤ ልታዘብ ብሎ ቢመጣ እኛ እንመልሰዋለን። ሕጉም እንዲያ ነው የሚለው። ደብዳቤያቸውን ካስገቡ በኋላ የታዛቢዎቻቸውን ዝርዝር ያስገቡና እውቅና ይሰጣቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡– ከሰሞኑን የተሰረዘው ህወሓት ሂደቱ ምን ይመስል ነበር
ወይዘሪት ሶሊያና፡– የተወሳሰበ ሂደት የለውም፤ ምክንያቱም ሕገ ደንቡ ውስጡ የተቀመጠ ነገር ነው። አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በአመጻ ተግባር ላይ መሰማራት የለበትም። በዛ ተግባር ላይ ተሰማርቶ ከተገኘ ከፖለቲካ ፓርቲነት የሚያሰርዝ ጥፋት ነው ይላል ህጉ።
ቦርዱ ፓርቲው በዚህ ተግባር መሰማራቱን በተለያዩ መንገዶች ያስተዋለ መሆኑም ይታወቃል። በተጨማሪም አዲስ አበባ የሚገኘው ዋናው የህወሓት አባላት ጋር ሲሰሩ የነበሩትንና አባላቱን ለአንድ ፓርቲ ራሱን የመከላከል መብት ስላለው በዚህ ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጥ ለማድረግ ሙከራ ተደርጓል።
በዚህ ጉዳይ ያሉት ግን ከዚህ በኋላ ፓርቲውን አንወክልም፤ እዚህ አዲስ አበባ የሚወክልም አካል የለም ብለዋልና በዚህም ጭምር ነው በአመጻ ተግባር ላይ መሆኑ የተረጋገጠው።
ፓርቲው ከተሰረዘ በኋላ ደግሞ የፓርቲውን ንብረት አስመልክቶ አንድ ፓርቲ ከተሰረዘ በኋላ ንብረቱ ለሲቪክና ድምጽ ለሚሰጡ መራጮች ትምህርት መስጫ ሊሆን ይገባል የሚል ነገር ስላለ ፓርቲው ያለበት እዳ ተጣርቶና ተከፍሎ የሚቀረው ገንዘብ ለዚሁ ተግባር መዋል አለበት ብሎ ቦርዱ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አሳውቋል፡፡
አዲስ ዘመን፡– በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ወይዘሪት ሶሊያና፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ጥር 27/2013