ዳንኤል ዘነበ
ሜኒንጃይቲስ ወይም ማጅራት ገትር ሜኒኢንጅስ የተባሉ አንጎልንና ሕብለ ሰረሰርን የሚሸፍኑ ሦስት የአንጎል ክፍሎች በመቆጣት ምክንያት የሚመጣ በሽታ ነው። የበሽታው ዋና መነሻ ተደርጎ የሚወሰደው እነዚህ በሜንኢንጀስ ዙሪያ ያሉ ፈሳሾች በቫይረስ ወይም በባክቴሪያ መጠቃት ነው።
ብዙውን ጊዜ ይህ በሽታ በአገራችን በወረርሽኝ መልክ በተለይም በክረምት ጊዜ የሚከሰት መንስኤው ቫይረስ፣ ባክቴሪያ፣ ፓራሳይት፣ ካንሰር፣ ኬሚካል፣ ፈንገስና የመድኃኒት አለርጂ ሊሆን ይችላል።
የበሽታው ምልክቶች በተለይ በቫይረስና በባክቴሪያ አማካኝነት የሚመጡ ናቸው። ሕመሙ በጀመረ አካባቢ ተመሳሳይ ሲሆኑ በባክቴሪያ አማካኝነት የሚመጣው በጣም ከባድ ነው። የምልክት አይነቶቹ በበሽታው አምጪ ተዋህስና እንደ ተጠቂው የዕድሜ መጠን በመጠኑ የሚለያይ ቢሆንም በአጠቃላይ ግን እነዚህ ምልክቶች ይታያሉ። ልብ ይበሉ ከ3 እስከ 7 ቀናት ውስጥ እነዚህ የበሽታው ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ።
1. ትኩሳትና ማንቀጥቀጥ
2. ከባድ የራስ ምታትና እንቅልፍ እንቅልፍ ማለት
3. የአንገት መገተርና መደናገር
4. የጀርባ ውጋትና የቆዳ ሽፍታ
5. የመገጣጠሚያና የሆድ ሕመም
6. ብርሃን ለማየት መቸገርና መልፈስፈስ
7. የምግብ ፍላጎት መቀነስ
8. ማቅለሽለሽና ትውኪያ ናቸው።
እነዚህን ምልክቶች እንዳዩ በፍጥነት የህክምና እርዳታ ማግኘት አለብዎት። ምክንያቱም በቫይረስና በባክቴሪያ አማካኝነት የሚመጣው ሜኒንጃይቲስ ሲበዛ ገዳይ ነው።
የመተላለፊያ መንገዶቹ
የተወሰኑ በቫይረስና በባክቴሪያ የሚመጡ
ሜኒንጃይቲስ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፉ ሲሆን በቫይረስ አማካኝነት የሚመጣው ሜኒንጃይቲስ የሚተላለፈው በሳል፣ በማስነጠስና በቅርብ ንክኪ በሆኑት (በንፍጥ፣ ምራቅና በአይነምድር) ነው። ትምህርት ቤቶች፣ የህፃናት ማቆያ፣ ወታደራዊ ካምፖች፣ ሆስፒታልና የዩኒቨርሲቲ ዶርምተሪዎች ደግሞ በባክቴሪያ ለሚመጣው ሜኒንጃይቲስ በስፋት የተጋለጡ ናቸው።
ሕክምናውና ምርመራው
1. የበሽታውን አምጪ ተህዋስ ለማወቅ የደም፣ የደረት ራጅና የሲቲ እስካን ምርመራ ይደረጋል።
2. ለትኩሳቱ አስፕሪንን የመሳሰሉ የሕመም ማስታጋሻ መድኃኒቶችን መውሰድ።
3. ምግብ በፈሳሽ መልክ መመገብ
4. ሴፍትሪአክሶን፣ ክሎራምፊኒኮል፣ ሳልፎናማይድ፣ ፔኒሲሊን ወይም አምፒሲሊን ወይም ኬሞ ፕሮፍላክሲስ የተሰኙ ፀረ-ተዋህሲያን መድኃኒቶች ይታዘዛሉ።
ቀድሞ መከላከል
በባክቴሪያ አማካኝነት የሚከሰተው ሜኒንጃይቲስ ክትባት ያለው ሲሆን ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚገቡ አዲስ ተማሪዎች፣ እድሜያቸው ከ11 እስከ 12 ዓመት የሆኑ ታዳጊ ልጆች፣ ሜኒንጃይቲስ በብዛት ወደሚገኙባቸው አገራት የሚሄዱ ተጓዦች እና ህፃናት እድሜያቸው 2 ወይም ከዚያ በላይ የሆኑና ጣፊያ የሌላቸው ወይም ዝቅተኛ የተፈጥሮ በሽታ የመከላከል አቅም ያላቸው ህፃናት ሊከተቡ ይገባል። በቂ እረፍት መውሰድ፣ ሲጋራ ማጭስ ማቆምና ከታመሙ ሰዎች መራቅ በሽታውን ለመከላከል ይመከራል።
ምንጭ- ከሀኪም ቤት ዶትኮም
አዲስ ዘመን ጥር 27/2013