ዳንኤል ዘነበ
ታይፈስ ሪኬቲሲያ (Rickettisia) በሚባሉ የባክቴሪያ አይነቶች የሚመጣ ድንገተኛ ትኩሳት የሚያስከትሉ በሽታዎች የሚጠሩበት የወል ስም ነው። በአለማችን ላይ ብዙ የታይፈስ አይነቶች አሉ። ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ በሚተላለፉበት መንገድ እና በሚያስከትሉት በሽታ አደገኛነት የሚለያዩ ሁለት የታይፈስ አይነቶች አሉ።
በቁንጫ አማካይነት ከአይጥ ወደ ሰው የሚተላለፍ ታይፈስ ይህ ብዙ ጊዜ የሚታየው የታይፈስ አይነት ነው። የሚተላለፈውም በባክቴሪያው የተያዙ አይጦች ወይንም ድመቶች ላይ የሚመገቡ ቁንጫዎች ወደ ሰው በማለፍ ሲናከሱ ነው። እነዚህ ቁንጫዎች ቆዳ ላይ ተጣብቀው ደም ከመጠጡ በኋላ በአይን የማይታይ ሰገራ ጥለው ያልፋሉ። የተነከሰው ሰው የተነከሰበትን ቦታ በሚያክበት ጊዜ በቁንጫ ሰገራ ውስጥ የነበረው ባክቴሪያ በተነከሰው ቀዳዳ በኩል ወደ ሰውነት ውስጥ ዘልቆ በመግባት እና በሰውነት ውስጥ በመራባት በሽታውን ያስከትላል። የበሽታው ምልክቶች የሚታዩት ታካሚው በቁንጫ ከተነከሰ በአማካይ ከ 2 ሳምንታት በኋላ ነው።
በሰውነት ተባይ አማካይነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ታይፈስ
ይህኛው አይነት ታይፈስ በወረርሺኝ መልክ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ አደገኛ እና ለሞት ሊያደርስ የሚችል በሽታ ነው። የሚተላለፈውም በሰውነት ተባይ ነው።
(የዚህን ተባይ ስም መጥራት ለአብዛኛው ሰው የሚከብድ በመሆኑ ነው እንጂ የሰውነት ተባይ በሚል የምጠራው ‘የልብስ ቅማል’ መሆኑ ይታወቅልኝ) አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰተው ንፅህናው ባልተጠበቀ ሁኔታ በአንድ ክፍል ውስጥ ብዙ ሰው በሚኖርበት እና ተጠጋግቶ በሚተኛበት ጊዜ ነው። ለምሳሌ ማረሚያ ቤቶች፣ የጎዳና ልጆች፣ ዶርሚተሪዎች፣ ሙአለ ህፃናቶች….የመሳሰሉት ናቸው።
ይህ የሰውነት ተባዮች ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው እንደልባቸው እንዲተላለፉ ምቹ አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል። ስለሆነም ከመካከል በአጋጣሚ አንድ በባክቴሪያው የተጠቃ ሰው ካለ በሽታውን በአንድ ጊዜ ለብዙ ሰዎች ሊያስተላልፍ ይችላል። በተባዩ የተነከሰው ሰው በሚያክበት ጊዜ በተባዩ ሰገራ ውስጥ ያሉ ባክቴሪያዎች ወደ ሰውነት በመግባት በሽታ ያስከትላሉ። የበሽታው ምልክቶች የሚከሰቱት በተባይ ከተነከሱ ከ 1-2 ሳምንት በኋላ ነው።
የታይፈስ ምልክቶች
የሁለቱም ታይፈስ አይነቶች ምልክቶች ከሞላ ጎደል አንድ አይነት ናቸው። ነገር ግን በቁንጫ የሚመጣው ታይፈስ ምልክቶች ቀላል የሆኑና አደገኛ ያልሆነ በሽታ ሲሆን በሰውነት ተባይ የሚተላለፈው ግን ህመሙ እጅግ አደገኛ እና ቶሎ ካልታከመ ለህይወት የሚያሰጋ ከመሆኑም በላይ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ በመሆኑ ለህብረተሰቡ አደጋ ነው። የሚከተሉት ምልክቶች አብዛኛው ታካሚ ላይ የሚታዩ ናቸው።
• ድንገተኛ የሆነ ሀይለኛ ትኩሳት
• ራሰ ምታት
• ብርድ ብርድ ማለት እና መገጣጠሚያን መቆረጣጠም
የሚከተሉት ደግሞ የተወሰኑ ታካሚዎች ላይ የሚታዩ ናቸው። (በተለይ በሰውነት ተባይ የሚተላለፈው)
• ቆዳ ላይ የሚወጣ ሽፍታ
• ደረቅ ሳል
• የአስተሳሰብ መዛባት (Confusion) እና ራስን መሳት (Coma)
ምርመራው
ልክ እንደ ታይፎይድ አሁን በየላብራቶሪው እየተሰራ ያለው የታይፈስ ምርመራ (Weil Felix የሚያየው የፀረ-ታይፈስ ኬሚካል (antibody) መኖር አለመኖሩን ነው። እነዚህ ኬሚካሎች ግን ከዚህ በፊት በነበረ መለስተኛ የታይፈስ ኢንፌክሽን (እንዲያውም ብዙ ጊዜ ምልክት ሳያሳይ ያለፈ) ወይንም በሌላ አይነት የባክቴሪያ ወይንም ቫይረስ የተነሳ በሰውታችን ውስጥ ሊገኙ ይችላሉ።
በመሆኑም ይህ ምርመራ ፖዘቲቭ ስለሆነ ብቻ አንድ ሰው ታይፈስ አለበት ብሎ ማረጋገጥ አይቻልም። ታዲያ አንድ የጤና ባለሙያ የአንድ ሰው በሽታው ታይፈስ ሊሆን ይችላል የሚለው እንዴት ነው?
1. ከላይ የተዘረዘሩት ምልክቶች በተለይ ድንገተኛ ትኩሳት ሲኖር
2. ታካሚው ለቁንጫ ወይንም ተባይ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ተጋላጭነት ከነበረው
3. ሌላ በሽታ ለምሳሌ ወባ፣ ኢንፍሉዌንዛ፣ ታይፎይድ፣ የሳንባ ወይንም የኩላሊት ኢንፌክሽን የመሳሰሉት አለመሆኑ ሲረጋገጥ፣ ታይፈስ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ስለሆነ እና ህክምናው ውጤታማ እና ቀላል ስለሆነ ህክምናውን መውሰድ ይመከራል።
ህክምናው
ሁለቱም የታይፈስ አይነቶች በተመሳሳይ አይነት መድሀኒት ይታከማሉ። አብዛኛውን ጊዜ የምንጠቀመው መድሀኒት በአፍ የሚወሰድ ዶክሲሳይክሊን (doxycycline) ነው። በተጀመረ በ2 ቀን ትኩሳቱ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠፋ ይጠበቃል። ይህ ካልሆነ ግን ታይፈስ ሳይሆን ሌላ በሽታ ሊሆን ይችላል እና ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል። ከ5-7 ቀን ህክምና በቂ ነው።
መከላከያ መንገዶቹ
1. በቁንጫ ለሚተላለፈው ቁንጫዎችን እና አይጦችን ማስወገድ
2. በተባይ ለሚተላለፈው አይነት የግል ንፅህናን መጠበቅ፣ የሰው ልብስ አለመልበስ፣ ከመካከል አንድ ሰው ላይም እንኳን ተባይ ከተገኘ የተለያዩ ኬሚካሎችን በመጠቀም የሁሉም ሰው ልብሶች እና አልጋ ላይ የተባይ ማጥፊያ ዘመቻ ማድረግ
ከላይ ያስተላለፍነው መረጃ ለጠቅላላ እውቀት እንጂ የሀኪምዎትን ምክር ሙሉ በሙሉ የሚተካ አይደለም። በተቻለ መጠን ሀኪምዎን ያማክሩ።
ምንጭ -ከዶ/ር ኤርሚያስ ሸንቁጤ ፌስቡክ ፔጅ
አዲስ ዘመን ጥር 27/2013