ክፍለዮሐንስ አንበርብር
እንደ ጎጆ ቤት በየቦታው የሚታየው የጤፍ ክምር እይታን ይስባል። ቀልብን ይሰበስባል። የአርሶ አደሩ የወራት የልፋትና የድካም ውጤት ነውና ለተመልካች ያስደስታል፤ለለፋበት አርሶ አደር ደግሞ ያኮራል።
በተለይም ከደጀን እስከ ደብረማርቆስ ለጥ ባለው የእርሻ ማሳ ላይ ያለው የጤፍ ክምር ጎተራ ገብቶ የሚያልቅ አይመስለም። አርሶ አደሩ ወደ አውድማው እየወሰደ ከማበራየቱ በፊት የታጨደውን ጤፍ ከምሮ ንፋስ እንዲያገኘውና የውድማ ሥፍራ እስከሚያከማቸው በእርሻው ማሳ ላይ ያቆየዋል።
ይህን አይን የሚያጠግብ የእርሻ ውጤት እያየን ስራ ላይ ወዳሉት አርሶ አደር ቀረብን። አርሶ አደሩ አደራው ጎሹ ይባላሉ። የ53 ዓመት ጎልማሳ ናቸው፤ እስከ አምስተኛ ክፍል ፊደል ቆጥረዋል። ከውድማቸው ጎራ ብለን ትንሽ እንዳወጋን ከውድማው ካሉ የጤፍ ክምሮች ከአንዱ ጥግ ፀሐይ እንዳይነካው ተደብቆ በጀሪካን የተቀመጠ ጠላ ነበርና እስኪ የአርሶአደር ጠላ ቅመሱ ብለው ቀዱልን።
እንደ ዶሮ ዓይን የቀላውን ጠላ ግጥም አድርገን የሆድ ሆዳችን እናወጋ ዘንድ ፈቀዱልን። የከተሜ ሰው ወደ ውድማ ሲመጣ ጥሩ ነው። ችግራችንንም ደስታችንንም እንነግረዋለን። እነርሱ ደግሞ ለመንግስት ይነግሩልናል ብለን እናስባለን። ለዚህም ደስተኞች ነን ሲሉ ስሜታቸውን ያለመሰሰት አጋሩን።
ከማዶ በጤፍ ጎጆ ብዛትና ውበት ተገርመን ወዲያ ማዶ እያማተርን፤ ከአውድማው ጥግ ላይ ከተዘረረው ጭድ አድርገን ከጭዱ ዙሪያ ከበው ከሚበሉት እንስሳት ላይ ዓይናችን ጣል አድርገን። በውድማው ላይ ከተበጠረው ማኛ ጤፍ አጠገብ ሆነን ከአርሶ አደሩ አደራው ጎሹ ስለ ኑሯቸው፤ ቤተሰባቸው፤ ውሏቸውና ምኞታቸው እንዲሁም ቀጣይ እቅዳቸው ትንሽ አወጋን። በእርግጥ ወደ ውድማው ከመግባታችን በፊት በሀገሬው ባህል መሰረት ‹‹ውድማው ይበርክት፤ ሃይማኖት ያውርድ›› ብለን በአፀፌታው አርሶ አደሩ አሜን! አሜን! ብለው ከተግባባን በኋላ ወደ ውድማው መግባታችን ትገዘነቡ ዘንድ እንወዳለን።
አርሶ አደር አደራው ጎሹ በማለዳው ተነስተው ወደ ስራቸው ከመሄዳቸው በፊት ስለቀን ውሎ ያወራሉ። ከትዳር አጋራቸው ጋር በመሆንም ስለቤታቸው ይመክራሉ። ልጆቻቸውም ቀን ምን መሥራት እንዳለባቸው ስራ ይከፋፈላሉ። የበዓላት ቀን ካልሆነ በቀር እርሳቸው በማለዳ ተነስተው ወደ አጨዳ ያመራሉ። ከእጃቸው የማይለየው ቁርበትና መጫኛ ነው። ሲያጭዱ ከዋሉት የተወሰነውን ማታ ላይ በቁርበት አስረውና በአህያ ጭነው ወደ ውድማቸው ያመጣሉ። በበዓላት ቀን ደግሞ በማለዳው የቤታቸውን ጉዳይ አጠናቀው ከሰዓት በሁዋላ ማህበራዊ ሕይወታቸውን ይከውናሉ።
በዚህ ጊዜ የትዳር አጋራቸውም በቤት ውስጥ ብዙ ይሰራሉ። የሴቶች የስራ ኃላፊነት በርካታ ነው። ከቤት ውስጥ እስከ እርሻ ድረስ የእነርሱ የስራ ድርሻ ሰፊ መሆኑን አርሶ አደሩ ይናገራሉ። ‹‹ ሴቶች በማለዳ ተነስተው ቁርስ ያዘጋጃሉ፤ ለምሳ በአገልግል ክርችም አድርገው ምግብ ይቋጥራሉ።
ረፈድ ሲል ደግሞ የከብቶች ቤት አጽድተውና ኩበት ጠፍጥፈው ለሌላ ሥራ ይዘጋጃሉ። ልጆቻቸውም የትምህርት ሰዓት እስኪደርስ ያግዟቸዋል። አስፈላጊ ሲሆንም እርሻ ቦታ በመሄድ ስራ ያግዛሉ››።በሌላ ጊዜ የአርሶ አደር አደራው ሚስት እንጀራ ሲጋግሩ እርሳቸው ውሃ ከምንጭ ይቀዳሉ። እርሳቸው ከብቶችን ሲያበሉ ባለቤታቸው ደግሞ ሌላው ሥራ በመስራት ይተጋገዛሉ።
አርሶ አደር አደራው በቤታቸው ውስጥ ስለሚከወኑ ነገሮች ሁሉ ከቤተሰባቸው ጋር ምክክር እያደረጉ ነው የሚሰሩት። በተለይም ደግሞ የቤታቸው ወጪ እና ገቢ ላይ ይነጋገራሉ። ልጆቻቸውን ሁኔታ ይከታተላሉ፤ አብረውም ይወያያሉ። ቀደም ሲል አባወራ ብቻ ፈላጭ ቆራጭ የነበረ ቢሆንም በዚህ ዘመን ይህን የሚቀበል ሰው የለም።
አባወራውም ሆነ እማወራዋ በቤት ውስጥ እኩል መብትና ጥቅም አላቸው። አንዱ ብቻ ወስኖ ሌላኛው ሳይቀበል ምንም ማድረግ አይቻልም። ‹‹ በእኔ ውሳኔ ብቻ አንድ ነገር ለማድረግ ባስብ እንኳን ልጆቼ አይፈቅዱም። ›› ሲሉ የቤተሰብ ምክክርና ውይይት የጋራ ውሳኔ መኖሩን ይናገራሉ።
‹‹እንብኝ ካልኩ ደግሞ ጉዳዩ ወደ ውጪ ይወጣል። በሰፈሩ ያሉ ሚሊሽያዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች አይፈቅዱም። ሕግም ወንድ እና ሴት እኩል ናቸው ስለሚል ይህን መጣስ ያስቀጣል። በመሆኑም ከባለቤቴ ጋር ተመካክረንና እና ተነጋግረን እንደ አንድ አካል አንድ አምሳል ሆነን ነው የምንወስነው።
በአሁኑ ወቅት ሁሉም መብት አለው። በዘመነ እኩልነት መተጋገዝና መረዳዳት ግድ ነው። ይህ ያስተምሩናል። ይህን ካላደረግን ትዳሩም አይሰምር፤ ልጅም ማስተማር ይከብዳል›› ይላሉ- አቶ አደራው።
ከተሜው ያለ እኛ
እኛ ከሌለን ከተሜው አይኖርም፤ ከተሜው ከሌለ ደግሞ እኛ አለን ብለን አናስብም የሚሉት አርሶ አደር አደራው፤ ጤፋችን ምርት እንዲሰጥ የአቅማችን እንሰራለን፤ ለፍሬው ፈጣሪን እንለምናን። በመቀጠል ምርታችን ወደ ገበያ ሲወጣ ደግሞ ከተሜው ይገዛናል።
እኛም የከተሜው ሰው የሚያመርታቸውን የፋብሪካ ምርቶች እንገዛለን። ልብስና ሸቀጣሸቀጥ የሚመጣልን ከከተማ ነው። ታዲያ አንዳችን ለሌላችን የምንሆን ሰዎች ነን። ስለዚህ ከተሜው ለእኛ እኛም ለከተሜው መድኃኒት ነን። ተደጋግፈን ተዋደንና ተሳስበን ነው የምንኖረው ሲሉ የአብሮነትና ትብብር ገመዱ የጠነከረ መሆኑን ይገልፃሉ።
ዘረኝነት ወዲያ
በዘመናችን አንድ ነገር አለ። የሚያውቀውም የማያውቀውም ተናጋሪ ሆኗል። ብድግ ብሎ አንዱ አዝምም፤ ሌላው አዚም ልሁን ይላል። አንዳንዱ ደግሞ ዘው ብሎ ከቤትህ ይመጣል። እንደ ዘመኑ አንዳንድ የዘመኑ ሰው ተንኮል ፈራን ይላሉ። ብዙ ሰዎች በዚህ ዘመን አስመሳይ ሆነው ይመጣሉ።
ታዲያ ይህ ነገር እየጎዳን ነው። በኢትዮጵያ ዘረኝነትም ከፍቷል፤ ያሳዝናል ሲሉ አንገታቸው አቀርቅረው በእግራቸው ምድሪቱን ተምተም …ተም ተም አደረጉ። ከተከዙበት ሀሳብ ወጣ ብለውም ቀጣዩን እንዲህ ሲሉ ተናገሩ።
‹‹በእኔ ሃሳብ በዚህ ዘመን ሞት በዝቷል። በየምክንያቱ የሰው ልጅ መገደል የለበትም።ማንም የፈጣሪ ፍጡር ሊሞት አይገባም።›› የሚሉት አርሶ አደር አደራው፤ እኛም የእነርሱ እነርሱም የእኛ ናቸው። እኛ እየሆነ ባለው ነገር እናዝናለን። አቅማችን ፀሎት ነው። እየፀለይን ነው። አቅማችን በፈቀደው የተቸገረ እናግዛለን።
እናንተ ከመንግስት የሚከፈላችሁን ደመወዝ ወስዳችሁ ጤፍ ልትሸምቱ ወደ እኛ ትመጣላችሁ። እኛም ጤፋችንን ለመሸጥ ወደ ከተሜው እንሄዳለን። እና በአሁኑ ወቅት በየቦታው የምንሰማቸው የሰዎች ሞት ያሳዝነናል።
ከምንም በላይ ደግሞ ምንም የማያውቀው ድሃ እና ለእንጀራ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀስ የሚገደለው አርሶ አደር ያሳዝናል። ልጆቹን ለማሳደግ፣ ቤት ንብረቱን ለመለወጥ፣ ሃብት ንብረት ሊያፈራ የሚለፋ ሰው እንዴት ይገደላል? ፈጣሪ ይህን ነገር ይቅር ይበለን እንጂ የምንሰማና የምናየው ነገር በጣም ከባድ ነው። ለዚህ ሁሉ እየዳረገ ያለው ዘረኝነቱ ነውና ዘረኝነት ኧረ! ወዲያ ሲሉ ይኮንናሉ።
ለፍቶ መብላት
መኪናችሁ ያለ ነዳጅ አትሄድም አይደል? እኛም ልክ እንደዛው በደንብ ካልበላንና ካልጠጣን ነገሩ አይሰምርም። ለዚህም ከጠላው ጎንጨት ከዳቦው ጎመጥ እያደረግን ሥራችንን እንከውናለን ይላሉ አርሶ አደሩ። ለዚህም ሲባል የትዳር አጋራቸው በወቅቱ አስበው ጥሩ ጠላ ይጠምቃሉ። አልፎ አልፎም አረቄ ያወጣሉ።
ታዲያ ይህን እየቀመሱ ሥራቸውን ያፋጥናሉ። ድንገት እግር ጥሎት ከአውድማቸው ጎራ ያለ ሰው ልክ እንደ እኛ ከጠላው ይጋራል፤ ከቤታቸው ለዘለቀ ደግሞ አረቄውንም ጠላውንም ይቋደሳል፤ ከገበታው ቀርቦ ከማይጠገብ ማዕድ ይጋራል። አርሶ አደር አደራውም፣ የእኛ ጎተራው ሞልቶ ገበታው ተርፎ ማየት ምኞታችን ነው ይላሉ።
የገበሬው ልጅ
የአርሶ አደር አደራው ልጅ መላኩ አደራው የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ነው። አባቱ ስለትምህርት ያላቸው አመለካከት ትልቅ ስለሆነ ዘወትር እንዲያጠና ይመክሩታል። ታዲያ አባትየው እስከ አምስተኛ ክፍል ፊደል ቆጥረው ስለነበር ነገሮችን በተሻለ መንገድ ይረዱታል። እርሱም የአባቱን ምክር ይሰማል። ትምህርቱን ይከታተላል፤ በትርፍ ሰዓቱ ደግሞ በስራ ቤተሰቡን ያግዛል።
በአሁኑ ወቅት እህል እየተወቃ ነው፤ ጭድ ተከማችቷል። ይሄንን ቅዳሜና እሁድ በአህያ ወደ መከመሪያው ስፍራ ያግዛል። አባቱ ደግሞ ክምሩን ያሳምሩታል። እንደ ዶሮ ዓይን ኮለል ያለውን ጠላ እየተጎነጩ ክረምት ለሚጠመደው በሬ ከወዲሁ ጭድ እየከመሩ መኖ ያከማቻሉ፤ ጭድና ገለባው በንፋስ ከመወሰድም ይታደጉታል። ተማሪ መላኩም ይህን ጭድ ከብክነት በመጠበቅና በመንከባከብ ረገድ ሚናው ትልቅ ነው።
የአርሶ አደሩ ምርት ለከተሜው
በአሁኑ ወቅት ማኛ ጤፍ 3ሺ600 ብር ነው። ክረምቱን 4ሺ100 ብር ይሸጥ ነበር። ታዲያ ጤፋችን ዋጋው ቢቀንስም ገበያ ላይ የምንገዛቸው ነገሮች ያው እንደነበሩ አልቀነሱም። በመሆኑም እኛም ሳንጎዳ ሌላውም ሳይጎዳ ገበያው ቢስተካከል ብለው ይመኛሉ- አርሶ አደር አደራው። ከዚህ በተረፈ ሰማይና መሬት ካለ በወቅቱ ዝናብ ከዘነበ ምንም አንሻም። እኔ በወቅቱ ዘርቼ፣ ጉልጓውን አሳምሬ ምርት ሲደርስ አጭዳዬን በወቅቱ ከውኜ እና በደንብ ከውድማው ካበራየሁ በኋላ ምንም አልፈልግም ባይ ናቸው።
የሰው ልጅ ሲሞት አንድ ሰሌንና አንድ ነጠላ ነው የሚከተለን። ግን ደግሞ እስክንሞት ድረስ መልፋት አለብን። ልጆቻችንም ወደተሻለ ቦታ እንዲደርሱ እንለፋለን። እኔም ባለቤቴም ቤታችን እንዲቃና ልጆቻችን ወደፊት እንዲያድጉ ሁሌ እንመኛለን። ገበሬ ዝናብ በወቅቱ ከዘነበለት ሁሉም ደስተኛ ነው። ፀሎታችን ዝናብ ይዝነብለን፤ አዝመራ ያብብልን፤ ሰላም ለሀገራችን ለሕዝባችን ይሁን ብለን ነው።
የኢትዮጵያን ነገር አደራ!
የ53 ዓመቱ ጎልማሳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በ1978 ዓ.ም አቋርጠው ከግብርና ስራው ጋር ተዛምደዋል።ሆኖም ግን በወቅቱ ትምህርት ማቋረጣቸው ዛሬም ድረስ ይቆጫቸዋል። በዚህ ቁጭት ነው ልጆቻቸውን የሚያስተምሩት። ሁሉም አርሶ አደር ልጆቹን እንዲያስተምርና ነገ በተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ይፈልጋሉ። ለዚህ ምክራቸውን ይለግሳሉ።
በአካባቢው ጤፍ፣ ጓያ እና ሽንብራ በብዛት ይመረታል። የአገሬው ነዋሪም ሰርቶ ለመለወጥና ለማደግ ደፋ ቀና የሚል ነው። ታዲያ ይህን ምርት ለማምረት፣ ለመሰብሰብና ለሚፈልገው ለማድረስ የሀገር ሰላም መሆን ወሳኝ ነው። ልጆችም ተምረው አሰቡት ደረጃ የሚደርሱት ሀገር ሲኖር ነው። ስለዚህ ልጆችም ወደ ጥፋት እንዳያመሩ ቤተሰብ መምከር አለበት። ሁሉም ነገር እንዳሰብነው መልካም የሚሆነው ሀገር ሰላም ሲሆን ነው።ስለዚህ ለኢትዮጵያ ሠላም መሆን አብዝተን እንመኛለን ይላሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 27/2013