ትምህርት የሰው ልጆች ስብዕና የሚቀረፅበትና ሁለንተናዊ አስተዋፅዖ ያላቸው ዜጎች ማፍሪያ መሣሪያ ነው። ከድህነት የመውጫ ቁልፍ መሳሪያ በመሆኑም ተመራመሪ ልሂቃንን ማፍራት የምትችል ሀገር ተግዳሮቶቿን አስወግዳ ከድህነት መውጣት ትችላለች።
ዶክተር ዕጓለ ገብረዮሃንስ በ1953 ዓ.ም «የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ» በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው ትምህርት አዲስ ነገር ከማወቅ ከመመራመር የእስከአሁኑን ዕውቀት አልፎ ለመሄድ ከመጣጣር ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ። የምጣኔ ሀብት ሊቁ ካርል ማርክስም ትምህርትን ዓለምን የምንለውጥበት መሣርያ ሲል ገልጾታል።
የትምህርት ሚኒስቴር «የትምህርት ሥልጠና ችግሮችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች » በሚል ርዕስ ባለፈው ሐምሌ ለውይይት ያሳተመው ፍኖተ ካርታ ሀገር ማደግና ዜጎቿን ማሳደግ የምትችለው የተማረ የሰው ኃይል ዕምቅ ዐቅም ሲኖራት ነው ይላል።
ዜጎቻቸውን አስተምረው፣ በቴክኖሎጂ በልፅገው የሕዝባቸውን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የቻሉ የጎለበቱ ሀገሮች ልምድ የሚያሳየንም ይህንኑ ነው። እንደ ደቡብ ኮርያ፣ ሲንጋፖር፣ ቻይና፣ ቬየትናም እና ማሌዥያን የመሳሰሉት ሀገሮች ከፍተኛ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ የደረሱት በትምህርት መሆኑን በምሳሌነት በመጥቀስ ይሄው ፍኖተ ካርታ ያስረዳል። ያደጉት ሀገሮች አሁን ላሉበት ደረጃ የደረሱት በሰለጠኑት ዜጎቻቸው ጥናትና ምርምር ታግዘው መሆኑን ስናይ የትምህርት አስተዋፅዖ የረቀቀ እና የመጠቀ መሆኑን እንረዳለን።
በሀገራችን ዘመናዊ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት በእምነት ቦታዎች የሚማሩ ወጣቶች ከቤተሰቦቻቸው ርቀው ስለሚማሩ ምግብ ለማግኝት ይቸገሩ ነበር። ለእዚህም የኦሮቶዶክስ እምነት ተከታይ የአብነት ተማሪዎች ከዚህ አንጻር ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ የቆሎ ተማሪዎች በመባል ይታወቁ የነበሩ ተማሪዎች ምግባቸውን የሚያገኙት በየመንደሩ እየዞሩ ህብረተሰቡን በመጠየቅ ነበር።
ዘመናዊ ትምህርት ከተጀመረ ወዲህም ትምህርት ቤቶች በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ይገኙ ስለነበር በርካታ ተማሪዎች ዘመድ ወዳጅ ዘንድ ተቀምጠው ይማሩ ስለነበር የምግብ ጉዳይ ብዙም የሚያሳስባቸው አልነበሩም፡፡ አንዳንዶች ግን ቤት ተከራይተው ትምህርታቸውን ይከታተሉ ስለነበር የምግብ ጉዳይ ብዙም ባያሳስባቸውም ምግብ አዘጋጅቶ መመገብ ግድ ይላቸው ስለነበር የትምህርት ጊዜያቸውን የሚሻማ ሥራ ይሆንባቸው ነበር፡፡
ይህ ግን ሀገሪቱ ትምህርት ቤቶች ለማስፋፋት ባደረገችው ርብርብ እየተፈታ መጥቷል፡፡ የአንደኛ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በገጠር አካባቢዎች ጭምር ተከፍተዋል፡፡ ይህም ተማሪዎች ብዙም ርቀት ሳይጓዙ የሚማሩበት ሁኔታ እንዲፈጠር አስችሏል፡፡
ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚዘጋጁባ ቸው የመሰናዶ ትምህርት ቤቶችና የቴክኒክ ሙያና ስልጠና ኮሌጆች በብዛት ተከፍተው መሥራት ከጀመሩ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በከፍተኝ ትምህርት ደረጃም ሲታይ ከ50 የማያንሱ ዩኑቨርሲቲዎች በመላ ሀገሪቱ ይገኛሉ፡፡
በሀገሪቱ ከ20 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች በዲግሪ እየተመረቁም ናቸው፡፡ በዲፕሎማ የሚመረቁትም ከዚህ የሚተናነሱ አይደሉም፡፡ እነዚሀ አሀዞች በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ እንደሚደርሱም ይጠበቃል፡፡
የትምህርት ዕድሉ ለሁሉም ተማሪዎች የተመቻቸ ሁኔታን ቢፈጥርም፣ይህን መልካም ዕድል የሚገዳደሩ ሁኔታዎች ግን ይስተዋላሉ። ከእነዚህም መካከል አንዱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆች ልጆች እያጋጠማቸው ያለው የምግብ ችግር ነው፡፡
ከምግብ አቅርቦት አለመኖር ጋር በተያያዘ አንዳንድ ተማሪዎች በትምህርት ሰዓት መዳካም፣ መቆዘም፣ መዝለፍለፍ፣ መውደቅ እያገጠማቸው መሆኑን መምህራን ይጠቁማሉ፡፡ ተማሪዎቹ በትምህርታቸውም ቸልተኛ እንደሚሆኑ ፣ አቋርጠው እንደሚወጡ ፣ እንደሚቀሩ እና በአጠቃላይ እንደሚያቋርጡም ነው እየተገለጸ ያለው፡፡
ችግሩን የተረዱ የአንዳንድ ትምህርት ቤት መምህራን ከደመወዛቸው እየቀነሱ በማዋጣት እነዚህን ሕፃናት ተማሪዎች ለመደገፍ ጥረት ሲያደርጉም ቆይተዋል። ይህ ችግር በስፋት የሚስተዋለው በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን፣ መምህራኑ ለእነዚህ ተማሪዎች ዕውቀት ከመመገብ አልፈው ምግብ በማቅረብ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ጥረት ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡
መምህራንና ሠራተኞች ሲያደርጉ የቆዩት የምገባ ፕሮግራም ቀስ በቀስ የባለሀብቶችን ድጋፍ እያገኘም መጥቷል፡፡ አንዳንድ ባለሀብቶች በየአካባቢው በትምህርት ቤቶች ምግብ እንዲዘጋጅ በማድረግ ለችግረኛ ተማሪዎች ቁርስና ምሳ ያቀርቡም ነበር። በአዲስ አበባ ከተማ መሳለሚያ አካባቢ ወደ አበበ ቢቂላ ስታዲየም መታጠፊያ ላይ የሚገኙ አንድ ባለሀብት በራሳቸው ተነሳሽነት ለስምንት ዓመታት ያህል ለችግረኛ ተማሪዎች ቁርስና ምሳ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን በሕንፃው አቅራቢያ የሚገኘው የእሸት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንና ሠራተኞች ይናገራሉ።
የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማኅበርም ከአራት ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በየአካባቢው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ምግብ አብሳይ ሠራተኞችን ቀጥሮ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወላጆች ተማሪዎች የምግብ ዕደላ እያደረገ ይገኛል። በዚህም በርካታ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከትምህርታቸው እንዳይስተጓጎሉ ብሎም እንዳያቋርጡ፣ በትኩረት ስለትምህርታቸው ብቻ እንዲያስቡ ማድረግ መቻሉን ነው መምህራን የሚገልጹት።
በምገባ ፕሮግራሙ ለተማሪዎቹ ቁርስና ምሳ ይቀርብላቸዋል፡፡ ተማሪዎቹ በስነልቦና እንዳይጎዱ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የመመገቢያ ዕቃ ከቤታቸው ይዘው እንዲመጡ ተደርጎ ምግቡ ይከተትላቸውና ምሳ ላይ ከሌላው ተማሪ እኩል እንዲመገቡ ይደረጋል፡፡ ቁርሳቸውን ግን ከሌላው ተማሪ ቀደም ብለው በትምህርት ቤታቸው እንዲገኙ ተደርጎ በመመገቢያ አዳራሽ እንዲመገቡ እንደሚደረግ መምህራን ይገልጻሉ።
የምገባ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሚሆኑ ተማሪዎች በኮሚቴ እንደሚጣራም ከመምህራን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ተማሪዎቹ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆች ልጆች መሆናቸውን ከወረዳ አስተዳደር መረጃ በመውሰድ ይጣራል፡፡
ልጆቻቸው በምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ ከሆኑ ወላጆች አብዛኞቹ የዕለት ጉርስ ፍለጋ ሲባዝኑ የሚውሉ ናቸው፡፡ ቆሎ የሚሸጡ ፣ለታክሲዎች ሳንቲም የሚዘረዝሩ ፣የቀን ሥራ የሚሠሩ ናቸው፡፡አንዳንዶቹም በዕድሜና በህመም ምክንያት የተጎሳቆሉና ዘላቂ መተዳደሪያ የሌላቸው ሲሆኑ፤ ጥቂት የማይባሉት ደግሞ በሴተኛ አዳሪነት የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ በተለይ በአዲስ ከተማ እና በቂርቆስ አካባቢ የተጠቀሱት ችግሮች በስፋት የሚስተዋሉ አንደመሆኑ ለእነዚህ አካባቢዎች የምገባ መርሀግብር መዘጋጀቱ ተማሪዎቹንና ወላጆችንም በመታደግ የህብረተሰቡን ጫና በከፍተኝ ደረጃ እንደሚቀንሰውም ይታመናል፡፡
መንግሥትም ይህን ችግር በሚገባ ተረድቶታል፡፡ የመምህራኑ ችግረኛ ተማሪዎችን በምግብ የመደገፍ አርአያነት ያለው ተግባር ቀድሞውንም እውቅና የተቸረው ቢሆንም ይበልጥ ተቀባይነት ማግኘቱም መንግሥት ከወሰደው ዕርምጃም መረዳት ይቻላል፡፡
በያዝነው ዓመት በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ገንዘብ ተመድቦ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የችግረኛ ወላጆች ሕፃናት ተማሪዎች ምገባ ለማካሄድ ዝግጅቱ ተጠናቋል። ገንዘቡ ለተመረጡ ትምህርት ቤቶች ካለፈው ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ የተለቀቀ ሲሆን፣ቀደም ሲል በመምህራን፣ በባለሀብቶችና በእናት ወግ የበጎ አድራጎት ማኅበር በመሳሰሉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሚካሄደውን የመጀመሪያ ደረጃ ችግረኛ ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም የበለጠ ለማስፋት የሚያስችል ነው፡፡
መምህራን ከወርሃዊ ደመወዛቸው ላይ ገንዘብ በማዋጣት የሚረዱት ለተወሰኑ ተማሪዎች ብቻ ነው። ግብረሰናይ ድርጅቶችም ምገባውን ማካሄድ የሚችሉት ሊተባበሯቸው የሚችሉ ባለሀብቶች፣ ድርጅቶችና የውጭ ረጂዎችን ሲያገኙ ብቻ ነው። ገንዘቡ በተቋረጠ ልክ የምግብ ድጋፍ የሚደረግላቸው ተማሪዎች ቁጥር እየቀነሰ የሚሄድም ይሆናል።
የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማኅበር በያዘነው ዓመት በምገባ ሲደግፋቸው የነበሩ ሕፃናት ተማሪዎች ቁጥር መቀነሱም የሚያመለክተውም ይህንኑ ነው፡፡ በሚድሮክ ድርጅት ለበጎአድራጎት ድርጅቱ ሲደረግ የነበረው ድጋፍ መቋረጡና የመሳሰሉ ችግሮች ለምገባው መቀዛቀዝ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡ የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማኅበር በያዝነው ዓመት በአዲስ አበባ ብቻ በ22 ሚሊዮን ብር ለ9ሺህ ተማሪዎች ቁርስና ምሳ እንደሚያቀርብ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያስረዳል።
ካለፈው ታኅሣሥ ወር መገባደጃ ጀምሮ ትምህርት ሚኒስቴር ለአዲስ አበባ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 66ነጥብ 5ሚለዮን ብር በጀት ለቋል፡፡ በዚህም 50ሺህ 733 በትምህርት ምገባ የሚታቀፉ ይሆናል፡፡
ይህ የመንግሥት ዕርምጃ ተማሪዎች ለትምህርታቸው ትኩረት እንዲሰጡ በመምህራን፣ በባለሀብቶችና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሲከናወን የቆየው ተግባር በአስተማማኝ መልኩ በመንግሥት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያስችላል፡፡ ተማሪዎች ትኩረት ሰጥተው እንዲማሩ ያደርጋል፡፡
የምገባ ፕሮግራሙ በአዲስ አበባ መስተዳድር እና በስምንት ክልሎች የሚገኙ ችግረኛ ተማሪዎችን የሚያካትት ሲሆን፣ ለዚህም ማስፈጸሚያ 268 ሚሊዮን 746ሺህ 443 ብር ተመድቧል፡፡ በዚህም 853 ሺህ 146 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ችግረኛ ተማሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የጃፓን መንግሥት ለምገባ ፕሮግራሙ ድጋፍ አርገዋል።
ችግረኛ ተማሪዎች ትምህርት ቤት ሲሄዱ በሁለት ነገር የሚጠቀሙበት ሁኔታ በአስተማማኝ መልኩ ተመቻችቷል፤ ተማሪዎቹ በአፍም በመፃፍም ይመገባሉ። መንግሥት በመምህራን የተጀመረውን አርአያነት ያለው የተማሪዎች ምገባ ተግባር ይህን ይህል ገንዘብ መድቦ ማጠናከሩ ምንም እንኳ ኃላፊነቱ ቢሆንም ሊያስመሰግነው ይገባል፡፡
መንግሥት በተማሪዎች ምገባ ላይ ጠንካራ አቋም መያዙን በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአውሮፓ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆሴፔ ኮንቴ ጋር በተወያዩበት ወቅትም ተረጋግጧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምግብ እጦት ምክንያት ትምህርት መከታተል ለተቸገሩ ተማሪዎች መንግሥት ለተማሪዎቹ ምግብ ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ የሥራ ሂደት ለተማሪዎቹ ዳቦ ለማቅረብ የዳቦ መጋገሪያ ችግር እንዳለ ጠቅሰው፣ የጣልያን መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ የጣልያን መንግሥትም ጥያቄውን በመቀበል ዝግጁነቱን ማረጋገጡን መገለጹ ይታወሳል፡፡
መንግሥት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለሚማሩ ተማሪዎች ምግብና መኝታ እንደሚያቀርብ ይታወቃል፡፡ይህም ተማሪዎች ስለትምህርታቸው ብቻ እንዲያስቡ ያስችላል፡፡ አሁን ደግሞ ለአፀደ ሕፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ችግረኛ ተማሪዎች የቁርስና ምሳ ምገባ ለማካሄድ እንቅስቃሴ መጀመሩ የሰበሰባቸው ተማሪዎች እንዳይበተኑ ያስችላል፡፡ እንደሚታወቀው መንግሥት ትምህርት ቤቶችን እያስፋፋ ዜጎች እንዲማሩ ከሚፈጥረው ምቹ ሁኔታ በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ተማሪዎች በሙሉ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ጥሪ እያስተላለፈ ነው፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ትምህርት ቤት ከመጡ በኋላ በምግብ ችግር ሳቢያ ከትምህርት ቢስተጓጎሉ ወይም ቢያቋርጡ ይህ ሁሉ ድካም መና ይቀራል፡፡
ይህ የምገባ ፕሮግራም ይህን ዓይነቱን ችግር በሚገባ ይፈታል፡፡ ተማሪዎች ስለትምህርታቸው ብቻ እንዲያስቡም ያደርጋል፡፡ መጠነ ማቋረጥንም ሆነ በውጤት ላይ የሚስተዋል ችግርን ያስቀራል፡፡የወላጆችን ጫናም በማስቀረት ደስተኛ ሕይወት እንዲመሩ ይረዳል፡፡ የመምህራን የበጎ አድራጎት ተግባር ወደ አስተማማኝ እጅ መሸጋገሩንም ያመለክታል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 28/2011
ይቤ ከደጃች. ውቤ