አንተነህ ቸሬ
የመጀመሪያው የኦሮምኛ ቋንቋ ጋዜጣ፣ ‹‹በሪሳ (Bariisaa)››፣ መስራችና ዋና አዘጋጅ ነበሩ። የኦሮምኛ መዝገበ ቃላትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ መጽሐፍትንም ጽፈዋል። በሒሳብና በፊዚክስ ምሁርነታቸውም ይታወ ቃሉ።
የነፃነት ታጋይም ነበሩ … አንጋፋው ምሁር ፕሮፌሰር ማህዲ ሀሚድ ሙዴ! የፕሮፌሰሩን የ70 ዓመታት ጉዞና አበርክቶ በአጭሩ እንቃኛለን። በዚህ ጽሑፍ ላይ የተጠቀሱት አብዛኞቹ መረጃዎች የተገኙት ፕሮፌሰር ማህዲ ከበርካታ ዓመታት የስደት ቆይታቸው በኋላ በ2011 ዓ.ም ወደ አገራቸው ኢትዮጵያ ተመልሰው በነበረበት ወቅት ከ‹‹በሪሳ›› ጋዜጣ ጋር ካደረጉት ቃለ ምልልስ ነው።
ልጅነትና ትምህርት
ማህዲ የተወለደው በ1943 ዓ.ም ጪሮ ከተማ ውስጥ ነው። መደበኛ (ዘመናዊ) ትምህርት ቤት ከመግባቱ በፊት ሐይማኖታዊ ትምህርት ተምሯል። ወደ መደበኛው ትምህርት ቤት ሲገባ በቀጥታ የገባው ሦስተኛ ክፍል ሲሆን፣ በወቅቱም ዕድሜው ዘጠኝ ዓመት ነበር። ማህዲ የአንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተማረው ጪሮ ከተማ፣ ደጃዝማች ወልደገብርኤል ትምህርት ቤት ሲሆን ትምህርቱን ለማጠናቀቅ ያስፈለጉት ስድስት ዓመታት ብቻ ነበሩ። ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ በግማሽ ዓመት (በሴሚስተር) ከአንድ ክፍል ወደ ቀጣዩ ክፍል (ደረጃ) ማለፍ በመቻሉ ነው።
በመቀጠልም ወጣቱ ማህዲ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት ፊዚክስ ማጥናት ጀመረ። የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ሳለ ወደ ጎጃም በመሄድ በደብረ ማርቆስ፣ ንጉስ ተክለኃይማኖት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሁለት ወራት ያህል በመምህርነት አገልግሏል። ከዚያም ወደ ባሕር ዳር ተዛውሮ ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል አስተማረ። ከመምህርነት ሥራው በተጨማሪ ልጆች የሚማሩባቸው መጽሐፍትን ጨምሮ ሌሎች ጽሑፎችን በኦሮምኛ ቋንቋ ያዘጋጅ ነበር።
«እድገት በኅብረት» ዘመቻ
ማህዲ ባሕር ዳር መምህር ሆኖ እየሰራ ሳለ የ1966 ዓ.ም ሕዝባዊ አብዮት ተቀጣጠለ። አብዮቱ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን ከዙፋናቸው አውርዶ ወታደራዊ ቡድን ስልጣኑን ሲጨብጥ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ከመሃይምነት ጨለማ ያላቅቃል ተብሎ የታቀደው ‹‹የእድገት በኅብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ›› ታወጀ። ማህዲም የማስተማር ሥራውን አቋርጦ ዘመቻውን ተቀላቀለ።
ዘመቻው ሲጀመር ‹‹የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ወደ ዘመቻው ይሂዱ›› በመባሉ ማህዲ በኦሮምኛ ቋንቋ ያዘጋጃቸውን ጽሑፎች በወቅቱ የዘመቻው አስተባባሪ ለነበሩት የሥራ ኃላፊዎች አቀረበ። ጥረቱ መሰናክሎች ባያጡትም ጽሑፎቹ አገልግሎት ላይ መዋል ችለዋል።
በዘመቻው ላይ በኦሮምኛ ቋንቋ ለሚፃፈው የክፍለ ትምህርት ኃላፊም ማህዲ ነበር። በወቅቱ ማህዲና ሌሎች የክፍለ ትምህርት ኃላፊዎች የሒሳብ ትምህርትን ጨምሮ ወደ ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚነበቡ መፅሐፍት አሳትመው እንደ አገር መማሪያ እንዲሆን አድርገዋል።
በሪሳ (Bariisaa)
ፕሮፌሰር ማህዲ ከ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ‹‹በሪሳ (Bariisaa)›› ጋዜጣን የማቋቋም ጅምራቸውን ሲያስረዱ እንዲህ ብለው ነበር፡-
‹‹ … በተፈጥሮዬ አንድ ሰው መልካም ነገር እንዲገጥመው ሁሌም እመኛለሁ። እኔም ደግሞ መልካም ነገር ማግኘትን እሻለሁ። ሌላው ብሔር ያገኘውን መልካም ነገር የእኔም ብሔር እንዲያገኝ እመኛለሁ። በዚያን ወቅት በእንግሊዝኛና በአማርኛ የሚታተሙ ‹‹የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ››፣ ‹‹አዲስ ዘመን››፣ ‹‹ፖሊስና እርምጃው››፣ ‹‹ወታደርና ዓላማው›› የሚባሉ የተለያዩ ጋዜጦች ነበሩ።
በመሆኑም ‹‹ለምን በኦሮምኛ ቋንቋ የሚታተም ጋዜጣ አይኖረንም›› የሚል ሐሳብ ውስጤን ይሞግተኝ ነበር። ስለዚህም ሐሳቡ ሐሳብ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር በተግባር እውን ለማድረግ አጥብቄ አሰብኩበት።
በወቅቱ ጉዳዩ ከእኔ አቅም በላይ ይሆናል የሚል ነገር በውስጤ አልነበረም። እንዲያውም ነገሮች አልጋ በአልጋ የሚሆኑ ሁሉ መስለውኝ ነበር። ይሁንና ወደ እንቅስቃሴው ስዘልቅ ጠጠር ያለ መሆኑን ተረዳሁ።
ይህ ጊዜ 1963 እና 1964 አካባቢ ነበር። በዚያ ጊዜ የማስታወቂያ ሚኒስትር የኤርትራ ተወላጅ የሆኑ ዶክተር ተስፋዬ ገብረእግዚ ይባሉ ነበር። አቡነ ጴጥሮስ አካባቢ ወደነበረው ቢሯቸው በመሄድ ‹‹በአፋን ኦሮሞ ጋዜጣ ማሳተም እፈልጋለሁ›› አልኳቸው።
እርሳቸውም «ምን ያህል ብትንቀኝ ነው በዚህ ቋንቋ ጋዜጣ አወጣለሁ ብለህ ቢሮዬ የመጣኸው!? ውጣ!» ሲሉኝ በጣም ተናደድኩ። ነገር ግን በመምህርነት ባህር ዳር እሰራ ነበርና ያንኑ ቀጠልኩበት።
በ1966 ዓ.ም ወታደሩ «የወር ደመወዝ ይጨመርልን» በሚል በአስመራ፣ በኦጋዴንና በሌሎችም አካባቢዎችም ሲነሳሳ አክሊሉ ሀብተወልድ ወርደው እንዳልካቸው መኮንን የሚባሉ ቦታውን ያዙ። እንዳልካቸው የሚባሉ ደግሞ አሃዱ ሳቡሬን ሚኒስትር አደርገው አመጧቸው። እኔም ተስፋ ሳልቆርጥ የጀመርኩትን ሐሳብ ይዤ ወደ አሃዱ ስሄድ እንደ ሚኒስትሩ (ዶክተር ተስፋዬ) አይስደቡኝ እንጂ ተመሳሳይ ምላሽ ተሰጠኝ።
በ1967 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ ጃንሆይ ከሥልጣን ለቀቁ፤ ደርግ ደግሞ ቦታውን ተቆናጠጠ። በወቅቱ ‹‹ሁሉም ወደ ጦር ሜዳ ይሂድ ተብሎ›› ተወሰነ። እኔ ደግሞ በዚያ ጊዜ ማስተማሩን ትቼ እድገት በህብረትን ጀመርኩ። እዚያው እያለሁ ወደ ሦስት ያህል መጽሐፍትን ከፃፍኩ በኋላ አለቃዬ ግን «በቃህ እዚህ ላይ አቁም» ሲለኝ፣ ‹‹ምነው እኔ አልደከምኩ፤ እናንተ ስለምን ደከማችሁ?›› አልኳቸው። «አይሆንም በቃ» አለኝ።
አክሎም «እንድትጽፍ የተደረገው ለመሸጋገሪያ ነበር» አለኝ። ‹‹ምን ማለት ነው?›› ስል ሌላ ሰው ስጠይቅ ‹‹በሳብኛ ፊደል ተጠቅመው በኋላ ላይ አማርኛን በደንብ እንዲያነቡ ታስቦ ነው›› የሚል ምላሽ በተሰጠኝ ጊዜ በጣም ተቆጨሁ።
እንዲያም ሆኖ የእኛ ሰዎች ማንበብ ለመዱ። በመሆኑም ‹‹አሁን ይህን ያህል ፊደሉን አውቀው ማንበብ ከቻሉ በይበልጥ ደግሞ ጋዜጣ በማንበብ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርናል›› በማለት ቀደም ሲል የተኮላሸውን ሐሳብ እንደገና ነፍስ እንዲዘራ በማንሳት ደግሜ ሻለቃ ግርማ ይልማ ወደሚባሉ ሰው ዘንድ ሄድኩ። በኦሮምኛ ቋንቋ ጋዜጣ ማዘጋጀት እንደምፈልግ ስጠይቃቸው «ተቀመጥ» አሉኝ። ማኪያቶም አዘውልኝ ጠጣሁ። «ስማ» አሉኝ፤ «ሁለት የሚያስቸግሩ ነገሮችን ነው የጠየቅከኝ።
የመጀመሪያው ‹ጋዜጣ ላሳትም› የሚለው ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ጭራሽ የማይሆን ሐሳብ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት ጋዜጣ ካልሆነ በስተቀር ሰው በግሉ ጋዜጣ ማሳተም አይችልም» አሉኝ።
‹‹እንዴ! ጎህ፣ ፀደይ መጽሔት፣ ቁም ነገር የመሳሰሉ አሉ አይደል እንዴ!? ምነው የእኔ ብቻ መከልከሉ? ›› ስላቸው እነዚያ ሕትመቶች መጽሔቶች መሆናቸውን ነገሩኝ። ‹ወታደርና ዓላማው› እንዲሁም ‹ፖሊስና እርምጃውስ› አሉ አይደል›› ስላቸው እነሱም የመንግሥት ድርጅት ጋዜጣዎች መሆናቸውን ነገሩኝ። ስለዚህም «በግል ከሆነ መጽሔት እንጂ ጋዜጣ የለም» አሉኝ።
ቀጥለውም «ሁለተኛው ጥያቄህ ደግሞ በኦሮምኛ ቋንቋ ማለትህ ነው፤ በዚህ ቋንቋ ደግሞ የመንግሥት ፖሊሲ የለም» ሲሉ ተናገሩ። «በአማርኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በአረብኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተም መጽሔት ካልከኝ ግን ዛሬውኑ ታገኛለህ። በኦሮምኛ ቋንቋ ግን አይቻልም። ጋዜጣም አይቻልምና የማይሆኑ ሁለት ነገሮችን ነው የጠየቅከኝ» ሲሉኝ፤ ‹‹እሺ ምን ላድርግ?›› አልኳቸው «ልምከርህ፤ የምታውቅ ከሆነ ወደ ደርግ ሰዎች ሂድና አስፈቅድ፤ ሊፈቅዱ የሚችሉ እነሱ ብቻ ናቸው» አሉኝ።
ከአቶ ሌንጮ ለታና ከሌሎችም አካላት ጋር ተመካከርንና አንድ በደርግ ውስጥ ኦሮሞ የሆነና ኦሮሞን የሚወድ ሰው እንዳለ አጣራን፤ ልናነጋግረውም ወስነን በሄድንበት ጊዜ «ለምን ማስታወቂያ ሚኒስቴር አትጠይቁም?» ሲሉ ኮሎኔል ተካ ቱሉ ጠየቁን። እኛም ጠይቀን እንደነበርና ደርግን ጠይቁ ስለተባለን ወደእነርሱ መምጣታችንን በአስር ሳንቲም ሒሳብ ሸጥን። የቀረውን ደግሞ የሚገዛን ስናጣ በወቅቱ ሌንጮ ቀጠን፣ አጠር ያለና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪም ስለሚመስል ኮፍያ ቢጤ አናቱ ላይ ጣል አድርጎ ወደ አብዮት አደባባይ ብቅ በማለት ይሸጥ ነበር።
በድጋሜ አርቲክሎቻችንን ፅፈን ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በምንሄድበት ጊዜ «በቃ ከዚህ በኋላ እንዲህ ዓይነት ነገር አይኖርም» ተባልን። ‹‹ምክንያት?›› ስንላቸው ደግሞ «በቃ ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው የተፈቀደው» አሉን።
ወደ ላይ ከፍ ብለን የደርግ ሰዎችን ስንጠይቃቸው «አይ እናንተ ጭራሽ ሕዝብን አሳስታችሁ የኦሮሞን ሕዝብ ከደርግ ጋር ለማጣላት መንግሥት ያልፈቀደውን ተፈቀደ እያላችሁ ነውና ወንጀለኞች ናችሁ፤ በመሆኑም በወንጀል ትፈለጋላችሁ» በማለት ጭራሽ እኔኑ ይዘው ወደ ማዕከላዊ ወሰዱኝ።
ለአራትና ለአምስት ወር ገደማ ጋዜጣውን ከለከሉ። በዚህ መሃል አንድ ነገር ሆነ። እሱም ኮሎኔል አስራት ደስታ የሚባል የደርግ የማስታወቂያና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ስለዘመናዊ ፕሮፓጋንዳ ለመማር ከፕሬስ መምሪያ ሰዎችንም ጨምሮ ሌሎች ኃላፊዎችን በመያዝ ወደ ውጭ አገር ለጉብኝት ሄደ። በዚህ ጊዜ በእርሳቸው ቦታ ተተክተው ተጠባባቂ የሆኑ ሰው ዘንድ ሄደን ስናናግር «ኮሎኔል አስራት ያልፈታውንና አይሆንም ያለውን ነገር አልሰራም። ሲመለስ እኔንም ያስረኛል።
ግን አንድ መላ የምንግራችሁ ነገር ቢኖር ከኮሎኔል አስራት ይልቅ ከበድ ወዳለውና ኮሎኔል አስራትም የሚፈራው ሰው ዘንድ ወስጄ እንዲፈቀድላችሁ አደርጋለሁ» አሉና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ዘንድ ወስደው አስፈረሙልን። እናም እርሳቸው «ይፈቀድ» ሲሉ በመፈቀዱ ‹በሪሳ› በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም (በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት) ፊርማ ተጀመረ ማለት ነው። ይህ እንግዲህ በ1968 ዓ.ም መሆኑ ነው። እርሳቸው በወቅቱ ‹በየሳምንቱ ይታተም› ሲሉም ነው የፈቀዱት።
ይህን ተከትሎ በብስራተ ወንጌል ሬድዮ ጣቢያ በኦሮምኛ ቋንቋ ስርጭት ተጀመረ። በመሆኑም ብስራተ ወንጌልና ‹በሪሳ› በአንድ ላይ በመስራት ለአንድ ወር ከግማሽ ያህል ከተማውን ማንቀሳቀስ ቻልን። በዚህ ጊዜ ወደ ውጭ አገር የሄደው ኮሎኔል አስራት በመምጣቱ የተደረገውን ሁሉ አየና «ምነው በጎዶሎ ቀን ከአገሬ ባልወጣሁ፤ እግሬ በተቆመጠ» ሲል መናገሩን አልረሳውም።
በዚያ ጊዜ እኛ ከእርሱ የሚበልጡት ኮሎኔል መንግሥቱ ፈርመውልን ነው ወደ ሥራ መግባት የቻልነው። ነገር ግን ነገሮችን ሊያበላሽብን ተጋ። የብስራተ ወንጌል የሬድዮ አገልግሎቱን «ለፕሮፓጋንዳ እንፈልገዋለን» በሚል ወረሰ። የእኛንም ጋዜጣ ብዙ ሳይቆይ በ1969 ዓ.ም ወሰዱት … ››
‹‹በሪሳ›› በወታደራዊው መንግሥት ከተወረሰች በኋላ ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ ስለምን በኦሮምኛ ቋንቋ ጋዜጣ አይኖረውም? በአስመራ በትግርኛም ሆነ በጣሊያንኛ የሚታተም ጋዜጣ አለ፤ እንዲሁም በአረብኛ የሚታም አለ። እንዲያ ሆኖ ሳለ ስለምን በኦሮሚኛ የሚታተመው የዚህን ያህል መቆየት አቃተው? የሚል ጫና ከሕዝቡ መምጣት ጀመረ። ጋዜጣዋ በፕሬስ ስር የመንግሥት ሆና እንድትቀጥል ተወሰነ፤ ማህዲን ጨምሮ የጋዜጣዋ ሠራተኞችም የወር ደመወዝ ተከፋይ እንዲሆኑ ተደረገ።
በወቅቱ መንግሥት ለጋዜጣዋ 500 ሺ ብር መድቦ ነበር። ጫልቺሳ ጪብሳ፣ ዋቅጋሪ ጉንጆ፣ መሀመድ ሀሰን፣ ቡሎ ሲባ፣ ኢብራሂም ሐጂ እና ሌሎች ባለሙያዎች ደግሞ የጋዜጣዋ ሪፖርተሮችና የእርም ባለሙያዎች ሆነው ተቀጠሩ። አንዳንዶቹ ባለሙያዎች ያለምንም ክፍያ ሰርተዋል።
[በእርግጥ ማህዲም ቢሆኑ ለ‹‹በሪሳ›› ቢሰሩም ደመወዝ የሚከፈላቸው ግን በ‹‹እድገት በኅብረት›› ዘመቻ እንደነበር ገልጸዋል።] በፍሪላንስ ጸሐፊነት የሚሳተፉ ግለሰቦችም ነበሩ። ባለሙያዎቹ ለሥራ የሚገለገሉበት አንድ መኪናም ተገዛላቸው። ከፕሬስ እስከሚለቁ ድረስ የጋዜጣዋ ዋና አዘጋጅ (Editor-in-Chief) ማህዲ ነበሩ።
ስለጋዜጣዋ ስያሜ፣ ይዘት፣ የመረጃ ምንጭና በወቅቱ ያጋጥሟቸው ስለነበሩት ጫናዎች በተመለከተ ‹‹ … የጋዜጣዋ ስያሜ ‹‹በሪሳ (Bariisaa)›› የተባለበት ምክንያት ልክ የጨለማው ጊዜ የሚያበቃበትና የብርሃን ጊዜ የሚጠበቅበት ሆኖ፤ ነገር ግን ብርሃን ነው እንዳይባል ፀሐይ ያልፈነጠቀችበት፤ ጨለማ ነው እንዳይባል ደግሞ ሊነጋ የተዘጋጀበትና ጨለማው ገፎ የብርሃን ወጋገን በሚታይበት መካከል በመሆኑ ነው ‹በሪሳ› የመባሏ ምስጢር።
በወቅቱ ጋዜጣዋ ፖለቲካዊ የሆኑ ይዘቶችንም ይዛ ትወጣ ነበር። እኛ መረጃ ማስተላለፍ የምንፈልገው የሕዝብን ፍላጎት እንጂ የመንግሥትን አልነበረም። በዚህም የተነሳ የሕዝብን ጉዳይ ነው ለመንግሥት የምናስተላልፈው። በዚህም ምክንያት ለእኛ መንግሥት ማለት የመረጃ ኢላማችን እንጂ የመረጃ ምንጫችን አልነበረም። እነሱ ይሰሩ የነበረውን እናውቅ ስለነበር እነሱን የመረጃ ምንጭ አናደርግም።
እኛ በወቅቱ የምንሰራው ሕዝቡ መጨቆኑን፣ ንብረቱ መቀማቱ፣ ቋንቋውን መናገር አለመቻሉን፣ ባህሉ መጥፋቱን ማሳወቅ፣ ሕዝቡ በኦሮሚኛ ቋንቋ መማር አለበት የሚል ሲሆን፣ ሕዝባችን ራሱን በራሱ ማስተዳደር አለበት የሚለውን ነበር የምንዘግበው …
‹በመጀመሪያ እስኪ ሕዝቡ እርስ በእርሱ ይግባባ› ወደማለት አዘነበልን፤ ለዚህም ምክንያታችን ሕዝቡ ሸዋ፣ አርሲ፣ ሐረር … እየተባለ ተነጣጥሎ ነበርና ነው። ስለዚህ ‹በመጀመሪያ ሕዝቡ አንድ ሊሆን ይገባል› ብለን በመሆኑም አንድነቱን ለማሳየት እና እርስ በእርሱ እንዲተዋወቅ ጥረት አደረግን … ‹ለእኛ ብሎ የሚሰራ አይኖርምና እኛው ለእኛ መስራት አለብን› የሚል ተነሳሽነት በውስጣችን ተለኩሶ ወደ ትግል ገባን። በእርግጥም ዋና ግባችንም ባህላችንን ለማሳደግና የኦሮሞ ሕዝብ እርስ በእርሱ እንዲተዋወቅ በማድረግ የኦሮሚያን አንድነት ለማጠናከር ነበርና ነው በጋራ የተነሳነው … ። በወቅቱ የበሪሳ ዋና አዘጋጅ ልሁን እንጂ ኦነግ ነበርኩ።
ኦሮሞዎች ሁሉ ሪፖርተሮቻችን ነበሩ ማለት ይቻላል። በወቅቱ ይመጡልን የነበሩ ደብዳቤዎች በአሁኑ ሰዓት በበሪሳ ዝግጅት ክፍል ውስጥ ቢፈለጉ የሚጠፉ አይመስለኝም። እነዚህን በአስተያየት መልክ የሚመጡ ደብዳቤዎችን በምናስተውልበት ወቅት ሕዝቡ ሁሉ ሪፖርተራችን እንደሆነ እምነት ያድርብናል።
እኛ በወቅቱ ‹አንደኛው ሪፖርተር ጅማ፣ ቦረና፤ አንደኛው ደግሞ ነቀምቴ … ሂድ› ብለን የምንልክበት ሁኔታ አልነበረም። በሪሳን መንግሥት ከወሰደው በኋላ ደግሞ ቀደም ሲል የነበረው 500 ሺ ብር በጀት ስላለው ሪፖርተሩ አጀንዳ ቀርፆ አበል ተከፍሎት በወጣው ደንብ መሠረት ወደፈለገበት ቦታ ሄዶ እንዲሰራ ይላካል። በመሆኑም መንግሥት ጋዜጣውን ከወሰደው በኋላ የገንዘብ ችግር አልነበረም … ››
‹‹በሪሳ››ን በመመስረትና በማዘጋጀት ሂደት ብዙ ፈተናዎችን እንዳሳለፉ የተናገሩት ፕሮፌሰር ማህዲ ‹‹ … ሁኔታው ገደል ጠርዝ ላይ እንደሚሄድ ዓይነት ሰው ስጋት የሞላበት ነበር … በወቅቱ ግን የቱንም ያህል ጫና ቢያሳድሩብኝ ‹ያስሩኝ ይሆን? ሥራ አጣ ይሆን? ይገድሉኝ ይሆን?› የሚል ነገር አያሳስበኝም ነበር … ›› በማለት ተናግረው ነበር።
ማህዲ በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ወቅት በምሥራቅ ኢትዮጵያ የነበረውን የፕሮፓጋንዳ እንቅስቃሴ ውጤታማ ለማድረግ ወደ ኦጋዴን አቅንተው ባለሙያዎችን አሰልጥነዋል። ከሌሎች የበሪሳ ባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው በአማርኛና በሌሎች ቋንቋዎች ተጽፈው የነበሩ የማስተማሪያ መጻሕፍትን ወደ ኦሮምኛ ተርጉመዋል።
ከ‹‹በሪሳ›› ከለቀቁ በኋላ በኦነግ ሥራ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተመድበው ለአራት ዓመታት ያህል ቆይተዋል። በመቀጠልም ወደ አሜሪካ ሄደው ትምህርታቸውን ቀጥለው እስከ ፕሮፌሰርነት ደረጃ መድረስ ችለዋል።
የኦሮምኛ መዝገበ ቃላትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ መጻሕፍትንም ጽፈው አሳትመዋል። ‹‹አባ በሪሳ›› (የበሪሳ አባት/መስራች) እና ‹‹አባ ዲክሽነሪ›› የሚሉ መጠሪያዎችንም አግኝተዋል። በ1990 ዓ.ም ‹‹ቁቤ ኦሮሞ ሶፍትዌር›› የሚባል ቴክኖሎጂ ሰርተው አበርክተዋል።
ፕሮፌሰር ማህዲ ሐሚድ ባደረባቸው የልብ ህመም የሕክምና እርዳታ ሲደረግላቸው ቆይተው ጥር 15 ቀን 2013 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 26/2013