ምስጋናው ታረቀኝ(ስሙ የተቀየረ) አዲስ አበባ ውስጥ በአንድ የግል ትምህርት ቤት የሚያስተምር የቅርብ ጓደኛዬ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ የሳምንቷን የመጨረሻ የዕረፍት ቀናችንን በአንደኛችን ቤት ሆነን እናሳልፋልን፡፡ በአንዱ ቀን ታዲያ እንደተለመደው ስለ ሥራ እየተጨዋወትን ሳለ፤ የነበረበትን ለቆ አዲስ ትምህርት ቤት ውስጥ መቀጠሩን ነግሮኝ ስለነበር «አዲሱ ትምህርት ቤት እንዴት ይዞሃል፤ ክፍያውስ?» ስል ጠየኩት፡፡
እርሱም «ክፍያው እንኳን ከዚያኛው ትንሽ ይሻላል፤ ግን እባክህ እዚህም ሌላ ያልተመቸኝ ነገር አለ፣ ደስተኛ አይደለሁም» በማለት የሃዘን ቅላጼ ባለው ድምፅ መለሰልኝ፡፡ እኔም ሁኔታው የፈጠረብኝን የሃዘንና የመከፋት ስሜት እንደምንም ያዝ አድርጌ ፊቱን ትኩር ብዬ እየተመለከትኩ «ደመወዙ የተሻለ ከሆነ ደስተኛ ያልሆንከው ለምንድነው፤ ምን ገጠመህ?» ስለው ከኋላው ወዳለው ጠረጴዛ ዞረና አራት የሚሆኑ የ«ኤ4» መጠን ያላቸው ትልልቅ መጽሐፎችን አንስቶ ሰጠኝ፡፡
መፅሐፍቱን ተቀብዬ በጉጉት ማገላበጥ ጀመርኩ፡፡ ሁሉም የአራተኛ ክፍል ማስተማሪያ መፅሕፍት ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ ሞጁል ላይ የተጻፈው የትምህርት ዓይነት ስም እንደ ወረደ አንደኛው «ኢንግሊሽ»፣ ሁለተኛው «ስፖክን»፣ ሦስተኛው «ሪዲንግ ስኪል» አራተኛው ደግሞ «ጀኔራል ሳይንስ» ይላል፡፡
እኔ ራሴ የተመረቅኩበት የትምህርት ዘርፍ እንግሊዝኛ ቋንቋ በመሆኑ ትኩረቴን እንግሊዝኛ ሞጁሎቹ ላይ አድርጌ ምልከታየን ቀጠልኩ፡፡ «ኢንግሊሽ» የሚለውን ሞጁል አንስቼ የመጀመሪያውን ገፅ ገልበጥ አድርጌ ማውጫውን ስመለከት በመጀመሪ ያው ምዕራፍ ላይ «ፕሩፍ ሪዲንግ» የሚል ርዕስ ሳይ ክው ብዬ ደነገጥኩ፡፡ ራሴን ማመን ስላቃተኝ በፍጥነት ሞጁሉን ዘጋሁትና እንደገና ጀርባውን አፍጥጬ ሳይ መጽሐፉ እውነትም ለአራተኛ ክፍል ተማሪዎች የተዘጋጀ ነው፡፡
አሁን አዲስ ሥራ በጀመረበት ትምህርት ቤት ውስጥ ጓደኛዬን ያላስደሰተው ነገር ምን እንደሆነ ገባኝ፡፡ ቀና ብዬ ጓደኛዬን በግርምት ተመለከትኩትና «እውነት ይሄን ለአራተኛ ክፍሎች ነው የምታስተምሯ ቸው?» በማለት ስጠይቀው «እኔንስ ያሳዘነኝና እዚህ መምጣቴ ያስጠላኝ ነገር ምን ሆነና፤ አየኸው አይደል የሚሠራውን ጉድ» አለኝ፡፡ «እኔ ራሴ ፕሩፍ ሪዲንግ የሚባል ነገር አስራ ሁለተኛ ክፍል ላይም አልተማርኩም፤ እዚህ ግን ማንበብና መጻፍ እንኳን በደንብ ያልለመዱ የአራተኛ ክፍል ጨቅላ ሕፃናት ያለ አቅማችሁ ተማሩ ተብለው ሲጨነቁ ይውላሉ፡፡» እባክህ ገና የተወሰነ ብር ይጨመርልኛል ብዬ ህሊናዬን አልጎዳም፤ እዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ መሥራት አልፈልግም፣ ልለቀው ነው» በማለት የተከፋበትን ምክንያት አጫወተኝ፡፡
መምህሩ ሊመሰገን የሚገባው ነው፡፡ ምክንያቱም የአራተኛ ክፍል ጨቅላ ሕፃናትን «ፕሩፍ ሪዲንግ» የሚያስተምር ትምህርት ቤት እንደ እውነታው «የዕውቀት ቤት» ሳይሆን «የውድቀት ቤት» በመሆኑ እዚያ አስተማሪ መሆን መምህሩ እንዳለው የሚጎዳው ትውልድን ብቻ ሳይሆን የራስን ህሊናም ጭምር በመሆኑ ነው፡፡
ምክንያቱም «ፕሩፍ ሪዲንግ» ማለት የንባብ የመጨረሻው ደረጃ ሲሆን፤ ከፍተኛ የአዕምሮ ብስለትንና የማሰብ ችሎታን የሚጠይቅ ለአዋቂዎች ሳይቀር የሚከብድ ክህሎት ነው፡፡ እኔ በእንግሊዝኛ የተመረቅሁት እንኳን ፕሩፍ ሪዲንግን የተማርኩት ዩኒቨርሲቲ ከገባሁ በኋላ ያውም መጨረሻ ዓመት ላይ ነው፡፡ ለአዋቂዎችም የሚከብድ ነው የሚባልበት ምክንያትም ሥራው በእጅጉ አስተዋይነትንና ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ ነው፡፡
ለአብነትም «kill him not, leave him» በሚለው ለቅጣት አስፈጻሚ ፖሊስ የተጻፈ የእንግሊዝኛ ዐረፍተ ነገር ውስጥ ኮማ የምትባለውን ሥርዓተ ነጥብ «not» ከሚለው ቃል በፊት ተሳስቶ ቢያስቀምጣት እንደማንኛውም ስህተት በይቅርታ ወይም በእርማት የሚታለፍ አይደለም፣ በመሳሳታችን ምክንያት ክቡር የሆነውን የሰው ህይወት አጥፍተናልና! እንግዲህ እንዲህ ዓይነት ስህተቶችን የማስቀረት ክህሎት ነው «ፕሩፍ ሪዲንግ» የሚባለው፡፡
ታዲያ ማንበብ በደንብ የማይችል አንድ የአራተኛ ክፍል ጨቅላ ሕፃን ማንበብ እንኳን ሳይችል በምን ተዓምር ነው ከማንኛውም ዓይነት ስህተት በፀዳ መንገድ ማንበብን እንዲማር የሚደረገው?
ይህን በማሳያነት አነሳን እንጅ ሌላም ብዙ ብዙ ነገር አለ፡፡ ከላይ እንደቀረበው አንዱ የእንግሊዝኛ ቋንቋ የትምህርት ዓይነት «ኢንግሊሽ»፣ «ስፖክን» «ሪዲንግ ስኪል» አንዳንዶቹ የግል ትምህርት ቤቶች አካባቢ ደግሞ «ራይቲንግ» ተብሎ አንዱን አራት ጊዜ ያስተምሯቸዋል፡፡
ስፖክን፣ ሪዲንግና ራይቲንግ በቋንቋው ውስጥ የሚገኙ ክህሎቶች ሆነው እያለ የተለያየ የትምህርት ዓይነት ሆነው ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾላቸው መጽሐፍ ተዘጋጅቶላቸው ተማሪዎች እንዲማሩ ይደረጋል፡፡ እናማ እንግዲህ በእንግሊዝኛ ጻፍ ስትለው «በራይቲንግ ነው እንጅ በእንግሊዝኛ መጻፍ ይቻላል እንዴ?» የሚል ትውልድን ቀርጸው እስከሚያስረክቡን በትዕግስት መጠበቅ ነው እንጅ ምን እንላለን፡፡
ሌላም አለ «ጀኔራል ሳይንስ» የትምህርት ዓይነታቸው ደግሞ እነዚህን የአራተኛ ክፍል ሕፃናት ልጆቻችንን ማወቅ ስለሚገባቸው ስለ አምስቱ የስሜት ህዋሳትና ስለ ዋና ዋና የአካል ክፍሎቻችን አገልግሎት ትተው ለሕፃናቱ ቀርቶ ለዘርፉ ባለሙያዎች እንኳን በስንት ድካም የሚረዱትን ውስብስቡን የሥርዓተ ነርቭ ሳይንስ ያስተምሯቸዋል፡፡ ስለ ሥርዓተ ነርቭ የተማርኩት አስረኛ ክፍል ላይ መሆኑን በሚገባ አስታውሳለሁ፣ ከሥነ ህይዎት ትምህርት ብዙዎቻችን የሚከብደንም ይኼ እንደነበርም እንደዚሁ፡፡
እናም አንድ አንድ ዜጋ በዚህ አካሄድ የትውልዱ ዕጣ ፋንታ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ሁሌም የሚያሳስበኝን ጥያቄ ይዤ ጉዳዩ በቀጥታ ወደሚመለከተው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ደወልኩ፡፡ ምክትል ኃላፊው አቶ ኤልያስ ገብረሥላሴ፣ በመዲናዋ በሚገኙ አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች የሥርዓተ ትምህርት ጥሰት እየተስተዋለ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ካሳተማቸው የማስተማሪ መጽሐፍት ውጪ የራሳቸውን መጽሐፍት አሳትመው የሚጠቀሙ የግል ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ህብረተሰቡ መደበኛ ባልሆነ መንገድ በስፋት የሚያነሳው ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ችግሩ መኖሩን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ቢሮውም የሚያውቀው ጉዳይ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ችግሩን ለመቅረፍ በሱፐርቪዥን ባለሙያዎች አማካኝነት ቢሮው በራሱ መንገድ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም የባለ ድርሻ አካላት በተለይም የወላጆች እገዛ ችግሩን በመፍታት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ኃላፊው ይናገራሉ፡፡ «ከማንም በላይ ልጆቻቸው ምን ሲማሩ ውለው እንደመጡ የሚያውቁት ወላጆች ናቸው» ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ከመደበኛው ሥርዓተ ትምህርት ውጪ የሆኑ ማስተማሪያ መጽሐፍትን የሚጠቀሙ ትምህርት ቤቶችን ለይቶ ተገቢውን የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ ረገድ የወላጆች ድርሻ ወሳኝ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡
ስለሆነም በአንድ አገር ላይ ኢፍትሐዊ ሰብዓዊ ልማት እንዲኖርና ሁለት ዓይነት ዜጎች እንዲፈጠሩ በማድረግ የነገ ሃገር ተረካቢ በሆኑ ሕፃናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትለውን የሥርዓተ ትምህርት ልዩነት ለማስቀረት ሚናቸው የማይተካ መሆኑን ተገንዝበው ወላጆች ሊተባበሩን ይገባል የሚል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ይህ አካሄድ ትውልዱን በተገቢው መልኩ ቀርጾ ከማብቃት አኳያ ተጽዕኖ የሚፈጥር እንደመሆኑ፤ ዝግጅት ክፍላችንም፣ «በአንድ አገር ላይ የግል ትምህርት ቤት እንጅ የግል የትምህርት ሥርዓት ሊኖር አይገባምና የሚመለከተው አካል ትኩረት ሰጥቶሊያርመው ይገባል» የሚል መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 17/2011
በይበል ካሳ