
ጎንደር ላይ ማክሰኝት ወደ ምትባል ከተማ ለተማሪዎች የዐይን ምርመራ ለማድረግ የሕክምና ቡድን ተሰማርቷል። ከእነዚህ ሀኪሞች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሕክምና ትምህርት ቤት በዐይን ሕክምና ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር እንዲሁም በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የአዋቂና የሕፃናት ዐይን ሕክምና ልዩ ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ሳዲቅ ታጁ አንዱ ሲሆኑ፤ የገጠማቸውን ታሪክ እንዲህ ሲሉ አጫውተውናል።
አካባቢው ላይ በዐይን ሕመም የሚሰቃዩ በርካቶች ቢሆኑም ምርጫቸውን ግን ተማሪዎች ላይ አድርገዋል። ምክንያቱም እነዚህ ልጆች የነገ የሀገር ተረካቢዎች ናቸው። በልጆቹ ላይ የሚከሰት የዐይን ጤና ችግር እንደ አዋቂዎች አይደለም። በጊዜው መፈታት ካልቻለ አደጋው በቀላሉ የሚመለስ አይደለም። እናም ቀድሞ የዕይታ ድክመት እንዳይከሰትባቸው ማከም ያስፈልጋል። ለዚህም ነው የዐይን ብርሃናቸውን ለመጠበቅ በዚያ ስፍራ ላይ የተገኙት። በዚህ ሕክምና ውስጥ መምህራኑ ችግሯን ያልተረዷት አንዲት ልጅ የገጠማትና መጨረሻ ላይ የተደረሰበት ችግር ትልቅ ትምህርት የሰጠ ነበር።
ልጅቷ ስትታይ ማንም ሰው የዐይን ጤና ችግር አለባት የሚላት አይነት አይደለችም። ግን በየቀኑ እየተሰቃየችም ቢሆን ትምህርቷን ትከታተላለች። ውጤታማ ባትሆንበትም ትምህርቷን ማቋረጥ አትሻም። መምህራኑ ሳይቀሩ ሲፈርዱባት ምንም አትላቸውም። የመጡት ሀኪሞች ሳይቀር መጀመሪያ ሲመረምሯት ችግሯን አልተረዱትም ነበር። ያለመነጽር የተለያዩ ምርመራዎች ካደረጉ በኋላ ውጤቱ የዐይን ጤና ችግር እንዳለባት ስለነገራቸው በቀጥታ የመነጽር ምርመራውን ወደማድረጉ ገቡ። ፊቷ ላይ ያዩት ፈገግታና የደስታ እንባ መቼም ከአዕምሮ የሚጠፋ እልነበረም።
በመነጽሩ እገዛ የተጠየቀችውን ሁሉ መልሳለች። ሕልሟን እውን ያደረጉላት አይነት ስሜት ስለተሰማትም ለምርመራ ያደረጉላትን መነጽር ለማውለቅ አልወደደችም። መነጽር እንደሚያስፈልጋት ከወሰኑ በኋላ ሌላ ተረኛ ሲጠሩ ሊወስዱባት እንደሆነ ስታስብ ያጠለቀችውን መነጽር ጠረጴዛ ላይ አስቀምጣ ፍሬሙን ብቻ ይዛ ሮጠች፤ ማንም አልተከተላትም። ምክንያቱም ምንም እንደማያደርግላት ያውቃሉ። ሆኖም ድርጊቷ ስለዚህች ልጅ የበለጠ እንዲጠይቁ አነሳሳቸው። ስለ ልጅቷ ማንነት ሲያጣሩም በትምህርቷ ሁልጊዜ ዝቅተኛ ውጤት እንደምታመጣ ሰሙ። የማየት ችግር ውስጥ እንዳለች መምህራኑ ሲነግሯቸው ግን እስከዛሬ በአደረጉት ነገር ተቆጩ፤ በጣሙንም አዘኑ። ችግሯ በመነጽር የሚስተካከል ከሆነ ራሳቸው ይህንን እንደሚያደርጉላት ቃል ገቡ። ልጅቷንም አስጠርተው መነጽር እንደሚሰጣት አስረድተዋት ደስተኛ እደረጓት።
ዶክተር ሳዲቅ በአንጸባራቂ ነገሮች (መስታወት፣ ውሃ ፣ አዲስ ቆርቆሮ፣ መነጽር …) የሚመጣ የዐይን ሕመም እንደ ተማሪዋ ሁሉ የሚታዩም የማይታዩም ሊሆን ይችላል ብለው፤ በአንጸባራቂ ነገሮች ምክንያት የሚከሰቱ የዐይን ጤና ችግሮች በሕክምናው Belair reflection ተብለው እንደሚጠሩ ይናገራሉ። ችግሩ የሚከሰተው ደግሞ ብርሃንን በውስጣቸው ማስተላለፍ በሚችሉ ወይም ደግሞ ማንጸባረቅ በሚችሉ ቁሶች አማካኝነት ብርሃን ዐይን ላይ በሚያርፍበት ጊዜ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
እነዚህ ችግሮች በርካታ ሲሆኑ፤ ዋና ዋናዎቹ የዐይን ድርቀት አንዱ ነው። ይህ ችግር የሚፈጠረው በተፈጥሮው በዐይናችን ሽፋሽፍትና በዐይናችን ኳስ መካከል ያለውን ቅባት ነጸብራቁ ዐይን ላይ በሚያርፍበት ወቅት ይበትነዋልና እንዲደርቅ ያደርገዋል። በዚህም ዐይን ይታመማል። የማቃጠል፤ ከፍተኛ የሆነ የመቆርቆር ስሜትና መሰል ያለመመቸት ስሜቶች እንዲፈጠሩም ምክንያት ይሆናል ብለውናል፡፡
ሌላው አሁን ላይ በተለይ ወጣቱና አምራች የምንለው የማኅበረሰብ ክፍል በዚህ ችግር በብዛት የሚጠቁበት የዐይን ሕመም ሲሆን፤ በተፈጥሮ አለርጂ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ላይ አንፀባራቂ ነገሮች ሲያርፉ የሚፈጠረው ነው። ረጅም ጊዜን ከኮንፒውተርና ስልክ መሰል የቴክኖሎጂ ውጤቶቸች ጋር ማሳለፍም አንዱ በአንጸባራቂ ነገሮች የሚከሰት የዐይን ጤና ችግር ነው። ይህ በሽታ ከኮምፒውተር ጋር በተገናኘ የሚመጣ የእይታ በሽታ (computer vision syndrome) እየተባለ የሚጠራ ሲሆን፤ የቴክኖሎጂ መሳሪያ አጠቃቀም አሁን እየሰፋ በመሄዱ ከትንሹ የሕመም ስሜት እስከ ከባዱ የዐይን ዝለት ድረስ አደጋን የሚያደርስ መሆኑንም ዶክተር ሳዲቅ ይናገራሉ።
ያደጉትና በቴክኖሎጂው የበለጸጉት የዐለም ሀገራት እነዚህን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ሲጠቀሙ በሕግ ነው፤ አንጸባራቂ ነገሮች ለዐይን ጤና ችግር ብቻ ሳይሆን ለቆዳ ካንሰርም ያጋልጣሉና ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ። ልዩ ክትትልና ድጋፍንም ከማኅበረሰባቸው አይለይም። የዐለም ጤና ድርጅት ያወጣውን ምክረ ሀሳብ ደግሞ አንዱ ከዚህ ጋር ተያይዞ እንደ ግዴታ ማኅበረሰቡ እንዲጠቀመው የሚሆንበት ነው። ይህም 20፤20 20 የሚባለው የኮምፒውተርና ሞባይል አጠቃቀም ስርዐት ነው። ይህም 20 ደቂቃ ስልክዎን ወይም ኮምፒውተሩን መመልከት ከዚያ ለ20 ደቂቃ 20 ጫማ ያህል ወይም ስድስት ሜትር አርቀው ፊት ለፊት ማየትን ተግባራዊ ማድረግ ነው። ተግባሩ የዐይን ጤና ችግርን ቀድሞ ለመከላከል ያግዛልና እኛም ሀገር ላይ ቢተገበር መልካም ነው ይላሉ።
ከአንጸባራቂ ቁሶች ነጸብራቅ ጋር በተያያዘ ሌላው ሊከሰት የሚችለው የዐይን ጤና ችግር ብርሃን ውሃ ላይ አርፎ ሲመለስ የሚፈጠረው ነው። በተለይ ማታ ላይ በሚያሽከረክሩ ሰዎች የመኪና መብራት ሳቢያ ውሃ ላይ ብርሃኑ ሲያርፍ ውሃው አንጸባርቆ ዐይንን እስከ ማጥፋት ይደርሳል። ይህ ችግር ከዐይን አለርጂ ጋርም ይያያዛልና ልብ ሊባል ይገባዋል። ብዙዎች የብርሃን እይታ ፍራቻ ያለበት የዐይን አለርጂ ኖሮባቸው በውሃ ነጸብራቅ ዐይነቴ ታመመ ይላሉ። ይህ ግን ትክክል አይደለም። ውሃ ሲያንጸባርቅ ዐይን መታመሙ እውነትነት ያለው ቢሆንም መነሻ ምክንያቱን መለየት ግን የግድ እንደሚል ያስገነዝባሉ፡፡
በአንጸባራቂ ነገሮች የሚመጣው ሌላው የዐይን ጤና ችግር የዕይታ መቀነስ ሲሆን፤ በተለይም ብርሃን የሚቀበለው የዐይን ክፍል በነጸብራቅ ምክንያት ችግር ከደረሰበት ዳግም ወደነበረበት በምንም አይነት ሕክምና ሊመለስ አይችልም። ይህ ደግሞ ዐይነስውርነትን ጭምር የሚያመጣ ነው። በእርግጥ የዐይነስውርነት ብያኔ ሁለት መልክ አለው። በሕክምና ተረድቶ የፊት ለፊት እይታ መጠኑ ሦስት ሜትርና ከዚያ በታች ከሆነ እና የዕይታ አድማሱ ድግሪ ከ10 ድግሪ በታች ከሆነ የሚፈጠረው ነው። ስለሆነም ብርሃን የሚቀበለው የዐይን ክፍል በነጸብራቅ ምክንያት ችግር ሲደርስበት የእይታ መጠናቸው በዚህ ልክ መሆን ይጠበቅበታል አንድ ሰው ዐይነስውር ሆኗል ለማለት ይላሉ።
ዶክተር ሳዲቅ፤ አንጸባራቂ የሚባሉት ቁሶች ስክሪኖች፤ ኮምፒውተርና ሞባይሎች፤ መስታዎቶች፤ ቀለማት፤ በጤና ባለሙያዎች ያልታዘዙ መነጽሮች ዋናዋናዎቹ መሆናቸውን ይዘረዝሩና እነዚህ አንጸባራቂ ነገሮች ከትንሹ የዐይን አለመመቸት ስሜት እስከ የዐይን ብርሃን ማሳጣት ድረስ የሚደርስ ጉዳት እንደሚያስከትሉ ይናገራሉ። እነዚህ አንጸባራቂ ቁሶች የሚፈጥሯቸው ጨረራዎች አልትራ ቫዮሌት ሬት ኤ እና ቢ የሚባሉ ሲሆኑ፤ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻችንን የሚጎዱ ናቸው። በተለይ ተጋላጮች የሆኑት የሰውነት ክፍላችን ቆዳና ዐይናችን በመሆናቸው እነርሱ ላይ ከፍተኛ አደጋ ይፈጥራሉም ሲሉ ያብራራሉ።
አንጸባራቂነትን በሁለት ከፍለው የሚያነሱት ዶክተር ሳዲቅ፤ አንዱ ብርሃኑ ሲለቀቅ ቁሱ ላይ አርፎ መልሶ ሳያንጸባርቅ ውጦ ማስቀረትና የምንፈልገውን ምስል መከሰት እንደሆነ፤ ሌላኛው ደግሞ ብርሃን ቁሱ ላይ ሲያርፍ አንጸባርቆ ወደ ዐይናችን መመለስ ሲሆን፤ ይህ የዐይን ጤና ችግር የሚፈጥረው አይነት ነጸብራቅ እንደሆነ ያስገነዝባሉ።
በአንጸባራቂ ቁሶች አማካኝነት ለሚመጡ የዐይን ጤና ችግሮች ተጋላጭ የሚሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሥራቸውን ውጪ ላይ ያደረጉ ሰዎች፤ ማለትም ጥበቃ፤ ፖሊስ፤ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች፤ ደንገዝገዝ ባለ ጨለማ ውስጥ የሚያሽከረክሩ ሰዎች ናቸው። ከዚህ አንጻርም አጠቃላይ ችግሩ በጾታ ሲታይ ወንዶች የበለጠ የችግሩ ሰለባ ይሆናሉ። በእድሜ ሲታይ ደግሞ በአማካኝ የእድሜ ደረጃ ላይ የሚገኙ ማለትም መስራት የሚችሉ ከ20 እስከ 50 የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ዜጎች የችግሩ ተጋላጭ ስለመሆናቸውም ዶክተር ሳዲቅ ይገልጻሉ።
በአንጸባራቂ ነገሮች ሳቢያ የሚከሰትን የዐይን ጤና ችግር ለማከም የተለያዩ ዘዴዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ። ተግባራዊነታቸውም እንደ ችግሩ አይነትና የጉዳት ወሰን የሚታይ ነው። ለምሳሌ- በአንጸባራቂ ነገሮች የሚፈጠረው የዐይን ጤና ችግር ድርቀት ከሆነ ለማከም ከምንጠቀማቸቸው ዘዴዎች አንዱ የአኗኗር ዘይቤያቸውን እንዲቀይሩ ማድረግ ነው። በዚህም በቂ የሆነ ውሃ እንዲጠጡ፤ የእንባ ምርቱን እንዲጨምር ለማድረግ ፊትን ለብ ባለ ውሃ ታጥቦ ለተወሰነ ደቂቃ በንጹህ ፎጣ እንዲይዙ ማድረግን የመሳሰሉ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ይመከራሉ። በሌላ በኩል መድሀኒቶችን በማዘዝ ሕክምናው ይደረጋልም። መድሀኒቶቹ ደግሞ በጠብታ መልክ የሚወሰዱ፤ የሚቀቡ አለያም የሚዋጡ ሊሆኑ ይችላሉ።
አለርጂ ላለባቸው ሰዎች ደግሞ ሕክምናው ብዙ ጊዜ የሚሰጠው አለርጂውን ሊቀንስ የሚችል መድሀኒት ነው። ሌላው የዐይን ሞራ ግርዶሽ ሲከሰት የሚሰጠው ሕክምና ሲሆን፤ በቀላል የቀዶ ሕክምና የሚከናወን ነው። ብርሃን የሚቀበለው የዐይናችን ክፍል ላይ አደጋ ሲደርስ ግን ከሌላው የተለየ ሕክምና ይሰጣል። ምክንያቱም ይህ ሕክምና ለውጥን የሚያሳይ ሳይሆን ችግሩ እንዳይሰፋ ለማድረግ የሚከናወን ነው። ስለዚህም በዚህ አይነት ችግር ውስጥ ያሉ ታማሚዎች የሚታከሙት የብርሃን መጠኑ በአለበት እንዲቆይ የሚያደርግ ቫይታሚን በመስጠት እንደሆነ ዶክተር ሳዲቅ ይናገራሉ።
ሌላው ዶክተር ሳዲቅ ያነሱት ጉዳይ ይህንን የዐይን ጤና ችግር ቀድሞ መከላከል የሚቻልባቸውን መንገዶች ነው። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ጅምሩ ከፖሊሲ ማውጣት የሚነሳ ነው። ዘመኑን የሚዋጁ ፤ የአካባቢን ገጽታ የሚቀይሩ ተግባራት ሲከናወኑ ከማኅበራዊ፤ ከኢኮኖሚያዊ አንጻር ታይተው፤ የሚመለከታቸው አካላት ተወያይተው የሚወሰኑ ሊሆኑ ይገባል። ለአብነት የከተሞቻችን ሕንጻዎች ሲሰሩ ከዐይን ጤና አንጻር ምንም አይነት ምክክከር የተደረገባቸው አይመስሉም። ምክንያቱም ዐይንን ሊጎዱ የሚችሉ አንጸባራቂ ነገሮች በስፋት በሕንጻዎች አካባቢ ታይተዋል።
እንደ መንግሥት የወጣ የመስታወት ደረጃ ቢኖርም አንዳንዶችጋ እየታየ ያለው ከዚህ የተለየና ለከፍተኛ ዐይን አደጋ የሚያጋልጥ ነው። የቀለማትም ጉዳይም ቢሆን በተለይ ነጩ ቀለም አንጸባርቆ የዐይን ጤና ችግርን ከጊዜ በኋላ መፍጠሩ አይቀርም። በተለይም ኢትዮጵያ የ13 ወር ጸጋ ባለቤት በመሆኗ የጸሐይ ብርሃን ዐመቱን ሙሉ ያለ በመሆኑ ይህንን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ ይናገራሉ። ከመስታወት ይልቅ ጠጣር ነገሮችን መጠቀም ለዐይን ጤና አዋጪነት አለውና ይህ ቢሆን መልካም ነው ካልተቻለ ግን ምን አይነት መስታወቶች ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው የሚለውን መንግሥት ከዐይን ጤና ባለሙያዎች ጋር ሊወያይባቸው ይገባል ይላሉ። ለአንጸባራቂ ነገሮች ተጋላጭ የሚሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሥራ ላይ ደህንነታቸው ከዐይን ጤናቸው አንጻር ታይቶ ሊጠበቅላቸው እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።
በአጠቃላይ የፊት ለፊት እይታ፤ የእይታ አድማስ፤ ቀለማትን የማየትና የመለየት እድል፤ የብርሃንና ጨለማን ምንነት መለየት፤ የጥልቅ እይታ መቀነስ ችግሮች እንዳይከሰቱ መንግሥት ባለሙያዎችን ማማከር፤ ተግባራዊ የሚያደርጉ አካላትን በአግባቡ መቆጣጠር፤ የጥራት ደረጃዎችን መለየትና ቅድሚያ ለሰዎች ጤና ሰጥቶ መስራት እንደሚገባውም አስተያየታቸውን ይለግሳሉ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም