ሴቶች የሚከብሩበት የጉራጌ ባሕል

የየካቲት ወር መጨረሻና የመጋቢት መጀመሪያዎቹ ቀናት በፈረንጆቹ ማርች 8 እያልን የምንጠራው ቀን ሴቶች በሥራዎቻቸው የሚወደሱበት፤ ታሪክ ሰርተው ያለፉት ደግሞ የሚዘከሩበት፤ ቀደም ሲል ያሳለፉትን ጭቆና በቁጭት የሚያወሱበትና አሁን ለተሻለ ነገ የሚሰሩበትን በሙሉ ልብና ጥንካሬ በመግለጽ ሴቶች መስራት እንደሚችሉ የሚያስመሰክሩበት ጊዜ ነው። በመሆኑም ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) በሀገር ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦና በየተቋማት ደረጃ ደግሞ ሴቶችን ከፍ በሚያደርጉ ዝግጅቶች ይከበራል።

የማርች 8 ትግል ውጤት ሴቶችን ማስከበር፤ መብትና ጥቅማቸውን ማስጠበቅ እንዲሁም የሴቶችን የትግል ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ነው። የሴቶችን እኩልነት ማረጋገጥ ነው። ይሄ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለ እሳቤ ይሁን እንጂ በባሕል ደረጃ ደግሞ የሴቶች መብቶች እንዲከበሩ እንቅስቃሴ የተጀመረው ቀደም ሲል እንደነበር ጥናቶች ያመለክታሉ። ለምሳሌ ያህል በጉራጌ ዞን የሴቶች እኩልነት ይከበር ስትል የመጀመሪያውን የዲሞክራሲ ጥያቄ በሀገር ደረጃ ያነሳች በማኅበረሰቡ ዘንድ ውግዘት ቢደርስባትም በእንቢተኝነት ስለሴቶች መብቶች የታገለችው ቃቄ ውርዶት ናት። ቃቄ ውርዶት በአሜሪካ የተነሳው የሴቶች መብት ይከበር ጥያቄ ከመጠየቁ በፊት አውቃና በቅታ ጥያቄ ያነሳች የመጀመሪያዋ ሴት ናት። ይሁን እንጂ ይሄ ጥያቄ ዓለም አቀፍ ሆኖ አደባባይ ባለመውጣቱ ዛሬ የራሳችንን ትተን ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን እናከብራለን። ያም ሆኖ ዛሬም ድረስ የሴቶች እኩልነት ተረጋግጧል ብሎ ለማለት አይቻልም። ዛሬም ገና ብዙ የሚቀሩ ያልተተገበሩ የሴቶች መብቶች አሉ። የሴቶች እኩልነት ባሕል መሆን ላይ አሁንም ክፍተቶች አሉ። የሴቶችን እኩልነት በማረጋገጥ ዙሪያ አሁንም የሚቀሩ ሥራዎች አሉ። ሌሎችም የሴቶችን ባሕል በማሳወቅና ባሕሎችን ወደፊት በማምጣት ረገድ በርካታ ሥራዎች ቢኖሩም ለአደባባይ የቀረቡት ግን ጥቂቶች ናቸው። ያልተነገረላቸውን ሀገርኛ ባሕሎቻችንን ወደፊት በማውጣት ማስተዋወቅ ደግሞ ከመገናኛ ብዙሀን የሚጠበቅ ነውና ለዛሬው የ‹‹ሀገርኛ›› ዓምዳችን ከ300 ዓመት በላይ ታሪክ ያለውን ሴቶችን የማክበር የጉራጌ ባሕል ለንባብ አብቅተናል።

በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለውን ማብራረያ የሰጡን የጉራጌ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋን ናቸው።

አንትሮሽት

አንትሮሽት (የእናቶች ቀን) በጉራጌ ማኅበረሰብ ዘንድ ለሴቶች ክብር፤ እንክብካቤ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሚነገርበት ከ300 ዓመት በፊት ጀምሮ ሲጠቀምበት የነበረ ባሕል ነው። አንትሮሽት ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን ብቻ አይደለም የቀደመው። ከኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ድንጋጌ አስቀድሞ የጾታ እኩልነትን ያረጋገጠ ባሕል ነው። ከዚህ አንጻርም ሕገ መንግሥቱ ጭምር ለሴቶች መብት ሳይሰጥ ባሕላችን ሴቶች መብት እንዳላቸው ያረጋገጠ ነው። በዚህ ደግሞ የጉራጌ ማኅበረሰብ ይህንን ልዩ ባሕል በአማርኛው የተለየ ትርጓሜ ሰጥቶት እናገኘዋለን። በማኅበረሰቡ ዘንድ አንትሮሽት ማለት በአማርኛው ሲተነተን የተለየ፤ ያልተለመደ የሚል ትርጓሜን ይይዛል። ይህንን ያለበት ምክንያት ደግሞ ሴቶች ረጅሙን ዓመት ሲያሳልፉ በጭቆና፤ የመብት ባለቤትነት ሳይረጋገጥላቸው ነው። የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፤ ተሳትፎ እና ሌሎች መብቶች አልነበሯቸውም። በዚህም ነጻነትን እየናፈቁ በችግር ውስጥ ሆነውም ስለ መብትና ተጠቃሚነታቸው ይሰሩ ነበር። ይህ የውስጥ ፍልሚያቸው ደግሞ አንድ ቀን ልዩ እድልን እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። ፍሬያቸው ስለራሳቸው የሚጨነቁበትንና የሚመክሩበትን እንዲሁም እረፍት የሚያደርጉበትን ልዩ በዓል አጎናጽፏቸዋል። ይህም በዓመት አንድ ጊዜ የሚከበረው ‹‹አንትሮሽት›› የተሰኘውን በዓል ነው።

በዚህ ባሕል እናቶች ከወትሮው ባለፈ ከሥራና ድካም እንዲያርፉና እንዲደሰቱ ይደረጋል። ልጆቻቸው የተለያዩ ስጦታዎች ያበረክቱላቸዋል። ሴቶች የባለቤት መብት እንዲሰማቸው፤ ነጻ ሆነው ተግባራትን ማከናወን እንዲችሉ እድል የሚያገኙበትም ነው። የገንዘብ ቁጠባ ያለውን ዋጋ እንዲያዳብሩ፤ በባለቤታቸውና በአካባቢያቸው ያላቸውን ቦታ እንዲያውቁ የሚሆኑበትም ነው።

አንትሮሽት የተጣላ የሚታረቅበት፤ ባል ሚስቱን የሚያከብርበትና በተራው ምግብ ሰርቶ የሚመግብበት ልዩ እለት ነው። እንዲሁም ለእናቶች የሚታረድ በሬ እንዳቅሙ የሚገዛበት፤ የጎረቤት እናቶችና ሴቶች ተሰባስበው የተለየዩ የባሕል ምግቦችን አዘጋጅተው በድምቀት የሚያከብሩበት በዓል ነው። ከምንም በላይ አንትሮሽን ለየት የሚያደርገው ባል ለሚስቱ የተለየ ግጥም ጭምር ይገጥማል።

በአንትሮሸት በዓል እናቶች ታጥበው ያልተነጠረ ቅቤ በአናታቸው እንዲሁም ሙሉ ሰውነታቸውን ተቀብተው በዘመናዊው የሴቶች መዋቢያ አጠራር« ስቲም ገብተው» ውስጣቸው ጭምር እንዲዋብ የሚደረግበት፤ በልዩ የበዓል ልብስና ጌጣጌጥ አሸብርቀው የሚታዩበት ልዩ ቀን ነው።

በአንትሮሽት በዓል የቅቤ አቀባብ ስርዓት በእናቲቱ የበኩር ልጅ ጾታ ይወሰናል። ለምሳሌ ሴት የበኩር ልጅ ያላት አንዲት እናት ቅቤ የምትቀባው በበኩር ልጇ አማካኝነት ነው። የበኩር ልጇ ወንድ ከሆነ ደግሞ በልጇ ሚስት እንድትቀባ ትደረጋለች።

በአንትሮሽት በዓል ልጅ የሌላቸው ሴቶችም ቢሆኑ ክብር ያገኛሉ። ምክንያቱም እነርሱ የአካባቢውን ልጆች በሙሉ የተንከባከቡ በመልካም ስነምግባር ያሳደጉ ባለውለታዎች ናቸው ተብሎ ነው የሚታሰበው። በመሆኑም በዕለቱ እነዚህ እናቶችም የሥራ እረፍት ያደርጋሉ፤ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በዓሉን በድምቀት ያከብራሉ። ከተለያዩ አካላት ስጦታ ይበረከትላቸዋል። ልጅ ላላቸው እናቶች እንደሚደረገው ሁሉ ለእነርሱም ማድረግ ግድ ነውና የሚቀርባቸው ነገር አይኖርም።

በዚህ በዓል ሌላው የሚደረገው ነገር አርአያ የሆኑ እናቶችም የተለየ ትኩረት ተሰጥቷቸው መከበራቸው ነው። ይህ በዓል እናቶች ዘወትር እንደሚያደርጉት 12 ሰዓት ተነስተው እስከ ምሽት ድረስ እንጨት እየለቀሙ፤ ውኃ እየቀዱ፤ ቆጮ ሲጋግሩ፤ አካባቢያቸውን ሲያጸዱና መሰል ተግባራትን ሲያከናውኑ የሚያሳልፉ አይሆንም። ይልቁንም ‹‹አንድ ቀን ልናርፍና ልንከበር ይገባል›› በማለት እንክብካቤ ያገኛሉ። የተለያዩ ባሕላዊ መጠጥና ምግቦችን አቅርበው ከመመገብ ባሻገር ልዩ ጣዕመ ዜማ እንዲሰሙም ይደረጋሉ። ይህም የሚሆነው በቀዬው ውብ ድምጽ ያላት ሴት ትመረጥና ለተከበሩት እናቶች እንድትዘፍን ይደረጋል። ድምጻዊዋ የምታዜመው ግጥም በዋናነት ይዘቱ እናቶች ከቤተሰቦቻቸው ባሻገር ለሕብረተሰቡ ያበረከቱት ውለታ ከፍ የሚያደርግ ነው። ግጥሙን ባለቤቶቻቸው፤ ልጆቻቸው፤ ራሳቸው እናቶችና ሌሎች በዓሉን የሚታደሙ ሰዎች ሊሰጡት ይችላሉ። በስፋት ግን ድምጻዊቷና ባሎች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ።

በአንትሮሽት በዓል ልጆች ለእናታቸው እንዲሁም ባል ለሚስቱ ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት የሚገልፁበት፣ ምስጋናቸውን የሚያቀርቡበትና ስለራሳቸው የሚወያዩበት ቀን ነው። ከዚያ ባሻገርም በአስትሮሽት በዓል የሴቶች የቁጠባ ባሕል በስፋት የሚታይበት ነው። ይህ ሁኔታ የሚከናወነው ደግሞ ገና በዓሉ ከመቃረቡ በፊት ሲሆን፤ የበዓሉ ድምቀት የሆነው እናቶች ሰውነታቸውን የሚያረሰርሱበት ቅቤ ሳይቀር የሚጠራቀመው በቁጠባ መልክ ነው። ለሚጠጣው፤ ለሚበላው የምግብ ዝግጅት የሚሆኑ እህሎች ቡናን ጨምሮ የሚዘጋጀውም በቁጠባ በተቀመጠው ገንዘብ ነው።

አልፎ ተርፎ ለሌሎች ወጪዎች የሚሆነው ገንዘብም በቁጠባ ለአንትሮሽት ተብሎ ይቀመጣል። ማንም ለምንም ጉዳይ የመቀነስ መብት የለውም። ምክንያቱም የአንትሮሽት ዋና ዓላማ በማንም የማትተካውን እናትን ማክበር ነው። ሌላው የጉራጌ ባሕል የገንየ ይባላል።

የ”ገንየ’’

ሁለተኛው በጉራጌ ማኅበረሰብ ዘንድ ለሴቶች ትኩረት ተሰጥቶ የሚከበረው በዓል የልጃገረዶች የክብር መገለጫ የሆነው በማኅበረሰቡ ዘንድ የ”ገንየ’’ ተብሎ የሚጠራው በዓል ነው።

በዓሉ ለሴት ልጅ ታላቅ ክብርና ፍቅር የሚሰጥበት ሲሆን፤ በጉራጌዎች ዘንድ አንዲት ሴት ወግ ማዕረግ ደርሷት ልትዳር ስትቃረብ የትዳር አጋሯ ወዳለበት ቦታ ስታቀና በእለቱ የሚከናወነው ሰርግ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ያምናል። ስለሆነም የትዳሩ ፍጥጥም ተጠናቆ ሰርጓ ከመድረሷ በፊት የተለያዩ ስርዓቶች እንዲከናወንላት ይደረጋል። አንዱ ደግሞ የወገን መንሰፍሰፍን እንድትመለከት፤ ከጓደኞቿ ጋር ዘና እንድትል የሚደረግበት ስርዓት ነው።

የገንየ ስርዓትን የሚያከናውኑት ወላጅ፤ ወንድምና እህት፣ አክስትና አጎት እንዲሁም ወዳጅ የሆኑ አካላት በሙሉ ናቸው። እስከ ሰርጓ ዋዜማ ድረስ ጥሪ እያደረጉ ይንከባከቧታል፤ እያበሉ እያጠጡ ቂቤ እየቀቡ ፍቅር እና ክብርን ይሰጧታል። ለነገ ሕይወቷ መሰረት የሚሆን ስጦታም ይበረከትላታል።

ይህ ባሕል በሁለት መልኩ ተከፍሎ የሚከናወን ሲሆን፤ የመጀመሪያው ከላይ እንዳልነው ከጋብቻ በፊት በሙሽሪቷ ቤተሰብና ዘመድ አዝማድ እንዲሁም ወዳጅ የሚከናወነው ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከጋብቻ በኋላ ወደ ባሏ ጋር ስትሄድ የጫጉላ ሽር ሽር አይነት በባሏ ቤተሰቦች ዘንድ የሚዘጋጀው ነው። ይህ ክብር ደግሞ ለሴቶች የተለየ ትርጉም አለው። አንዱ በባሕሉ ሴትን ልጅ ማሕበረሰቡ በክፉም ሆነ በደጉ ጊዜያት ለአባት ለእናቷ፤ ለወንድም ለእህቶቿ፤ ለጉረቤትና ለወገኗ ተቆርቋሪ ነች ብሎ ምን ያህል እንደሚያምን የሚረዱበት ነው።

አለኝታ እና ረዳት፣ ድርና ማግ ሆና ቤተሰብ ስታቀና፥ ቤት ስታደምቅ ኖራ የራሷ ጎጆ መቀለሷ አይቀሬ ነውና ለእርሷ ክብር ምን ያህል ቦታ እንደተሰጠው የምትረዳበትም ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ክብርን መጠበቅ ያለውን ዋጋ እንድታውቅ የሚያደርገ ነው። ምክንያቱም ይህ ልዩ ዝግጅት የሚደረግላቸው ሴቶች ከብራቸውን የጠበቁ፤ ማንነታቸውን ያልሸጡና ኩሩ ሴቶች ናቸው ተብሎ በብሄረሰቡ ዘንድ ይታመናል። በወግ ማዕረግ ከቤት ሳትወጣ ያገባች፤ ያረገዘችና የወለደች ሴት በዚህ ስርዓት ውስጥ እንድታልፍ አትደረግም። ስለሆነም ይህ በዓል ለሴት ልጅ ራሷን፤ ቤተሰቧንና የአካባቢውን ሰው የምታስከብርበትና ማንነቷን የምትነግርበት ተደርጎም ይወሰዳልና ለእሷ ልዩ ቀኗ እንደሆነ ታስባለች።

ነቐ (ረቆ)

የጉራጌ ማኅበረሰብ ሴቶችን በየፈርጁ ከፍሎ ክብርም፤ ነጻነትም የሚሰጥ ነው ስንል በምክንያት ነው። ከላይ ያሉት እንዳሉ ሆኖ ለልጃገረዶችም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ያከብራቸዋል። ይህ የልጃገረዶች የክብር ቀን በማኅበረሰቡ አጠራር ነቐ (ረቆ) እየተባለ ይጠራል። በባሕሪው ከእንቁጣጣሽ ጋር ይመሳሰላል። ከዝግጅቱ ስንጀምርም ከሦስት ወር ቀደም ብሎ እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ ማኅበረሰቡን በሚገባ እንድታገለግል ትደረጋለች። የመኸሩ ወቅት ሲጠናቀቅ ነጻነቷን ታውጃለች። የምትፈልገውን እንድታገኝም ትሆናለች።

ጥር እንደ መስከረም ሁሉ ለጉራጌ ልጃገረዶች የተለየ ነው። አሸብርቀውና ደምቀው በነጻነት ወጥተው ይጫወታሉ። እየዘፈኑ በየቤቱ በመሄድ የሚሰጣቸውን ይቀበላሉ። በዘፈኖቻቸው አወድሰው አለያም ቀልደውባቸው ወደ ጨዋታና ውይይት የሚገቡበት ልዩ እለት ነው። በእርግጥ ሁሉም ሰው በቂ ምርት የሚሰበስብበት ጊዜ ስለሆነ ከአመረተው ለመስጠት አይነፍግም። በቂ ድግስ የሚደግሱበትን ምርት ይሰጣቸዋል። ከስጦታቸው መካከልም ቡናም ይታከላል። ስለዚህም ልጃገረዶቹ በነገር ከመሸንቆጥ ይልቅ በውዳሴ ሁሉንም ሰው መርቀው ወደ ጨዋታቸው እንዲገቡ እድል ይፈጥርላቸዋል።

‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› እንደሚባል ሁሉ በረቆምም ልጃገረዶችን እንዳይጫወቱ የሚከለክል ሰው የለም። ከዚያ ይልቅ አንዳንድ እናቶች ልጆቻችን መድከም የለባቸውም በማለት የተዘጋጀ ምግብና መጠጥ ሊሰጧቸው ይችላሉ። በዚህም ልጃገረዶቹ ነጻነታቸውን አውጀው የተለያዩ ምግቦች ተዘጋጅተውና አዘጋጅተው ደስታቸውን እየገለጡ ያሳልፋሉ። ሀሳባቸውን ይገላለጣሉ፤ የተለየ ልምድም ከእናቶች ይቀስማሉ። በወቅቱ ልዩ ውበት የሚሰጠውን እንሾሽላ ጭምር በመሞቅ፤ አለኝ የሚሉትን ልብስ ለብሰው አሸብርቀው ይውላሉ።

በዓሉ ለልጃገረዶች ልዩ የሴትነት ትምህርት የሚሰጥበትም ነው፤ ማኅበራዊ መስተጋብራቸውን አጠናክረው በሴትነታቸው ዙሪያ ይወያዩበታል። መብታቸውን የሚያስከብሩበት፤ ስለ ሴትነታቸውና ችግሮቻቸው የሚመክሩበት ልዩ ቀንም ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህ ባሕላቸው ደግሞ ከብዙ ነገሮች ይጠበቁበታል። በተለይም ከመጤ ባሕሎች ራሳቸውን በብዙ መልኩ ይታደጋሉ።

ወይዘሮ መሰረት በመጨረሻ ለማኅበረሰቡ የሚሉት አላቸው። እንደ እነዚህ አይነት ባሕሎቻችን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አላቸው። የአትዮጵያን ማሕጸን ለምለምነት በሚገባ የሚያሳዩ ናቸው። ስለሆነም እነርሱን መነሻዎቻችን አድርገን ከመጤ ባሕል ልንጠበቅባቸው ያስፈልጋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ሞዴል የመሆን አቅም ያላቸውን ባሕሎች በዓለም ዓቀፍ ቅርስነት አስመዝግበን የቱሪዝም ሀብትና የገቢ ምንጫችን ልናደርጋቸውም ይገባል። ለዚህ ደግሞ መጀመሪያ ራሳችን ጠንቅቀን ማወቅና ማሳወቅ አለብን ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You