
ፓን አፍሪካኒዝም መድሎ በገጠማቸው በዓለም ዙሪያ በተበተኑ አፍሪካውያን የተነሳ ነው። አሜሪካ እና ካረቢያን አካባቢ ቀኝ ግዛትን እና የባሪያ ንግድን በመቃወም መቀንቀን የጀመረው ፓን አፍሪካኒዝም፤ በዋናነት መሪ ሆነው የተንቀሳቀሱት ‹‹ ዱ ቦይስ›› እና ‹‹ማርክስ ጋርቬይ›› መሆናቸውን የታሪክ መዛግብት ያትታሉ።
ከማኅበራዊ ንቅናቄነት ባሻገር ፖለቲካዊ ሆኖ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ሲነሳ፤ በ1900 በእንግሊዝ ለንደን፣ በ1919 በፈረንሳይ ፓሪስ እንዲሁም በ1921 በአሜሪካ ኒውዮርክ የአፍሪካ መሪዎች እና አፍሪካውያን ዳያስፖራዎች የተሳተፉባቸው ትልልቅ ጉባኤዎች ተካሂደዋል።
በመቀጠል እነ ኩዋሜ ኑክሩሁማ፣ ጁሊየስ ኔሬሬ የአፍሪካዊያን ነፃ መውጣትን እና የሕብረቱ መመሥረትን በተመለከተ አቀንቅነዋል። አፍሪካውያን አንድ ነን የሚል ንቅናቄን ይዞ የተነሳው ይህ እሳቤ፤ ሕብረቱን መስርቶ አሁንም በኢትዮጵያ አዲስ አበባ አፍሪካውያን ተገናኝተው የሚመክሩበት ሆኖ ቀጥሏል።
ከሕብረቱ ጎን ለጎን ወጣቶች የዘላቂ የልማት አጀንዳዎች በማራመድ እና ሊተመኑ የማይችሉ ሀብቶችን በማደስ በአሁኑ እና በመጪው ትውልድ ላይ መነሳሳትን መፍጠር በእጅጉ እንደሚያስፈልግም እየተነገረ ይገኛል። ይህን መሠረት በማድረግ ከሰሞኑ ኢትዮጵያ ወጣቶች በአኅጉር አቀፍ ደረጃ ሁሉን አቀፍ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ አይተኬ ሚናቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ከመጋቢት 25 እስከ 27 ቀን 2017 ዓ.ም የፓን አፍሪካ ወጣት አመራሮች ጉባኤ እንደምታካሂድ የሴቶች እና ማኅበረሰዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የፓን አፍሪካኒዝም ወጣት አመራሮች ጉባኤ ዘላቂ የልማት አጀንዳዎችን በማራመድ እና አፍሪካ ያሏትን ሰብአዊና ቁሳዊ ሀብቶችን በአግባቡ እንድትጠቀምበት መንገድ ይሆናል ተብሎለታል። እንዲሁም የወደፊት የጋራ ትልሞችን በማሳካት ረገድ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ወጣት አመራሮችን ለማበረታታት እና ለማሳተፍ ትልቅ ሆኖ እንደሚያገለግል ተነግሮለታል።
በሴቶች እና ማኅበረሰባዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ማብቃት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ባንቹ ሙሉጌታ እንደተናገሩት፤ ሚኒስቴሩ ከተሰጡት ተግባራት እና ኃላፊነቶች ውስጥ የወጣቶች ጉዳይን አስመልክቶ በማኅበረሰቡ እንዲሁም በራሳቸው በወጣቶች ዘንድ ግንዛቤ እና የንቅናቄ ተግባራትን እንዲሁም የእርስ በእርስ ትስስራቸውን የማጠናከር ሥራ አንደኛው ነው።
በመሆኑም በሀገር አቀፍ ደረጃ የዓለም ወጣቶች ቀን እና የሀገሪቱ መሪዎች በተገኙበት በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጣቶች ኮንፈረስን የማካሄድ ተግባር ሲያከናወን ቆይቷል ብለዋል። ከሰሞኑ ደግሞ በአኅጉር አቀፍ ደረጃ በአይነቱ የተለየ እና የመጀመሪያ የሆነ የፓን አፍሪካ ወጣቶች ጉባኤ ለማካሔድ ሰፊ የዝግጅት ተግባራትን በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ጉባኤውን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ጋር በመከሩበት ወቅት ተናግረዋል። ይኸው ጉባኤ ዝግጅቱ ተጠናቆ ከትናንት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ፓን አፍሪካኒዝም የአፍሪካውያን እና ትውልደ አፍሪካውያን የታሪክ ባለቤትነትን፣ እጣ ፈንታ እና የጋራ ጥቅም መያዙን የሚናገሩት ወይዘሮ ባንቹ፤ ዕሳቤው በትብብር እና በጋራ መስራትን የሚያበረታታ በመሆኑ ይህንን ለማሳካት ወጣቶች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ሲሉ አብራርተዋል።
ጨምረውም ወጣቶች የዛሬ እና የወደፊት መሪዎችና የልማት አንቀሳቃሾች እንደመሆናቸው መጠን የዘላቂው የልማት አጀንዳ ለመምራት እና በአጀንዳ 2063 ላይ የተቀመጠው የምንፈልጋትን አፍሪካን እውን ለማድረግ የበኩላቸውን አይተኬ ሚና መጫወት እንደሚችሉ መዘንጋት የለበትም ሲሉ፤ ወጣቶች በአፍሪካ ብልፅግና ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው መረሳት እንደሌለበት አሳስበዋል።
የፓን አፍሪካኒዝም ወጣት አመራሮች ጉባኤ እንደፓን አፍሪካኒዝም ካሉ ታሪካዊ እንቅስቃሴዎች ጋር በመተሳሰር መነሳሳትን በመፍጠር የአፍሪካዊ ዕሴቶችን አወንታዊ ሚና የሚያጎላ መሆኑንም አመላክተዋል። ወይዘሮ ባንቹ፤ በመሠረቱ ፓን አፍሪካኒዝም የአንድነት እና የነፃነት መርሆችን እና የበለፀገች አፍሪካ የተጠናከረ ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ትስስር እና ዕድገትን ያካትታል። በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የመረጃ ዘመን ለአፍሪካ እድገት ወሳኝ የሆኑትን ማኅበረ-ባሕላዊ እና ታሪካዊ እሴቶችን ለማንፀባረቅ መድረኮችን በማዘጋጀት ወጣቶች ከቅርሶቻቸው ጋር እንዲገናኙ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ሆኖም አፍሪካ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነቡ ማኅበራዊና ባሕላዊ እሴቶች፣ ታሪክ እና ጥበብ የበለፀገች የወጣቶች አኅጉር ብትሆንም፤ አሕጉሪቱ አንገብጋቢ የሰላም ማጣት እና የደህንነት ችግር፤ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተግዳሮቶች እያጋጠሟት መሆኑን ተናግረዋል።
እነዚህን ችግሮች በብቃት ለመፍታት የአፍሪካ ወጣቶች ትልቅ አቅም ቢኖራቸውም እንደ ወይዘሮ ባንቹ ገለፃ፤ የአፍሪካ ወጣቶች ሥራ አጥነት፣ ድህነት የአየር ንብረት ለውጥ፣ ትርጉም ያለው የተሳትፎ ውስንነት፣ ውስብሰብ የአስተዳደር ጉዳዮች፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ሙስና እና ሌብነትን ጨምሮ ትልልቅ መሰናክሎች እያጋጠሟቸው በመሆኑ አህጉሪቷን ካለባት ችግር ለማላቀቅ አዳጋች ሆኗል።
በወይዘሮ ባንቹ የተገለፁት ተግዳሮቶች፤ የአፍሪካን ወጣቶች የግል እድገታቸውን ሁለንተናዊ ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን፣ የተሻሻለ የኑሮ ደረጃን ከመምራት አኳያ እንዲሁም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ከተቀረፀው ፈጣን ዓለም አቀፋዊ ለውጥ ጋር የመላመድ ችሎታቸውን በእጅጉ እየገደቧቸው መሆናቸውንም አስረድተዋል።
እነዚህ ሰፊ የአህጉሪቷን ሕዝቦች የሚሸፍኑ የአፍሪካ ወጣቶች የትምህርት፣ የስብዕና ልማት፣ የሥራ ተሳትፎ ዕድሎች ከተመቻቹላቸው ዘላቂ ልማትን ከማረጋገጥ ባለፈ በአህጉራዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ወሳኝ የለውጥ ወኪሎች የመሆን አቅማቸው ከፍተኛ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የአፍሪካ ወጣቶች ስጋቶቻቸውንና ተግዳሮቶችን እንዲገልፁ ምቹ ሁኔታዎችንና የመፍትሔ ሃሳቦችን እንዲያስተዋውቁ በራሳቸው የበለፀገችና የምንፈልጋትን አፍሪካ እውን ለማድረግ በትብብር ለመሥራት እንደ ፓን አፍሪካኒዝም ወጣት አመራሮች ጉባኤ ዓይነት ፕሮግራሞች መዘጋጀታቸው ወሳኝ ነው ብለዋል። በተጨማሪ ጉባኤው የአፍሪካ ወጣቶች በዲጂታል ዘመን የቀረቡትን እድሎች በመጠቀም የፓን አፍሪካኒዝምን ትርክት በማጉላት አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ትስስርን ለማሳደግ ያግዛል ሲሉም ገልፀዋል።
የሴቶች እና ማኅበረሰባዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ተሳትፎ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ አድነው አበራ በበኩላቸው፤ በአሁን ጊዜ ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች ያሉ ወደ 70 በመቶ እንዲሁም ከ15 እስከ 24 ወደ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊየን የሚደርሱት ወጣቶች በአህጉሪቱ ውስጥ የሚኖሩ ሲሆኑ፤ ይህ ከዓለም ሕዝብ ወደ 13 በመቶ የሚይዝ ነው። ወጣትነት ደግሞ በራሱ ኃይል ነው። በዛ ላይ ትምህርት እና ስልጠና ሲታከልበት ትልልቅ ግኝቶችን ጨምሮ ብዙ ተዓምር መሥራት ይቻላል። ስለዚህ የአፍሪካ ወጣት ሲባል ስሙ ብቻ ሳይሆን ጥቅሙም መታየት አለበት ብለዋል።
ከወጣቶች አንፃር አፍሪካ ብዙ አቅም ያላት አህጉር ናት። ሆኖም ብዙ የሚቆጩ ነገሮች አሉ። ከዚህ በኋላ ግን ሰፊውን የአገሪቷን ሕዝብ የሚሸፍኑ የአህጉሪቷ ወጣቶች፤ በዓለም አቀፋዊ አህጉራዊ እና አገራዊ ውሳኔዎች ላይ ወሳኝ ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባ አያጠራጥርም ሲሉም ተናግረዋል።
ወጣቶች የወደፊቱ መሪዎች እና የልማት አንቀሳቃሾች እንደመሆናቸው መጠን፤ የምንፈልጋትን አፍሪካን ዕውን ለማድረግ አይተኬ ሚናን መጫወት ይኖርባቸዋል። ይህን ለማድረግ የሚታጠቋቸው ነገሮች መኖር አለባቸው። በዚህ ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ አጥብቃ መሥራት መጀመሯን አብራርተዋል።
ከሁሉም የአፍሪካ አገራት የተመረጡ ሰዎች የሚሳተፉበት ሲሆን፤ በአፍሪካ ያሉ የወጣቶች ችግሮች ዙሪያ ብቻ ሳይሆን ጎን ለጎን በሚካሄዱ መለስተኛ ፕሮግራሞች መፍትሔዎችም ይገለፃሉ ሲሉ ጉባኤው ለመፍትሔዎች ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አመላክተዋል።
አገራዊ ትሥሥርን ከማጠናከር በተጨማሪ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ መሪዎች እና ወጣቶች መካከል ቅንጅት በመፍጠር ትስስሩ ከሠፈር ወጥቶ በአገር ደረጃ እንዲሆንም ያለመ ነው ሲሉም ገልፀዋል። ይህ ሲሆን ዴሞክራሲን በመለማመድ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘትም ያስችላል። በተጨማሪ በወጣት አመራሮች መካከል ድንበር ተሻጋሪነትን ማሳደግ፤ አህጉራዊ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ዕውቀት የሚያገኙበትን ሁኔታም መፍጠርን ያካትታል ብለዋል።
በጉባኤው ወጣቶቹ ይነጋገራሉ፤ ችግሮች የሚፈቱባቸው ፕሮጀክቶች ይቀረፃሉ። ያሉት አቶ አድነው፤ ስለችግር ብቻ ከመናገር ይልቅ ከሥር ከሥር ስለሚፈቱባቸው ሁኔታዎችም ማሰብ እና መሥራት የተሻለ ነው። ጉባኤውም በዚሁ መልክ የሚካሄድ ነው። ይህ አፍሪካ ላይ መለመድ አለበት። ሲሉም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ ከምስራቅ፣ ከምዕራብ እና ከማዕከል ከአምስቱም ቀጠናዎች ወጣቶች ተገኝተው የሚወያዩ ሲሆን፤ በተጨማሪ የፖሊሲ አውጪዎች የወጣቶች ጉዳይን በተመለከተ የሚያካትቱበትን ሁኔታ እንዲያሻሽሉ ሃሳቦች ይንሸራሸራሉ ብለዋል። ተፅዕኖ ፈጣሪ የአገር መሪዎች ከሚያደርጉት ንግግር በተጨማሪ በተናጠል ጎን ለጎን ውይይት ሲደረግ፤ በተለይ በአፍሪካ ደረጃ ያለውን የትውልድ ክፍተት በተመለከተ ትኩረት ሰጥተው እንደሚነጋገሩ አመልክተዋል።
‹‹ አያቶቻችን ለአፍሪካ ታላቅ ውለታን ውለዋል። ጥቁሮች ማሸነፍ እንደሚችሉ አሳይተዋል። በዚህ እና በሌሎችም ምክንያቶች ኢትዮጵያ የአፍሪካ ልብ ናት።›› ያሉት አቶ አድነው፤ የፓን አፍሪካኒዝም ወጣት አመራሮች ጉባኤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ልጆችን አንድ ለማድረግ የሠራችውን ሥራ የምታስቀጥልበት ነው ሲሉም ገልፀዋል። በአፍሪካ ዘላቂ ልማት፣ ቀጣይነት ያለው ሰላም እና ብልፅግናን ለማምጣት በፓን አፍሪካኒዝም መንገድ ወጣቶች ማብቃትን ያለመው ይህ ጉባኤ፤ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ የገፅታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን አብራርተዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላትን የመሪነት ሚና የሚያጎላ እና በትውልድ መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላትም የሚያስችል ነው ሲሉ ሌለኞቹን የጉባኤውን ጥቅሞች ጠቁመዋል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም