አዲስ ሕይወት…

ከጊዜ በኋላ አካል ጉዳተኛ የሆነው የሕግ ባለሙያውና ባነቃቂ ንግግሩ የምናውቀው ዳግማዊ አሰፋ “መፍትሔ ያለው ችግር ውስጥ ነውና ማስተዋልና መገንዘብ የሚሉ መንፈሳዊ ፀጋዎች የወለዱት ብልሃት ራሴን እንዳገኝ ረድተውኛል” ይላል አዲስ ሕይወት በተሰኘው መጽሐፉ፤ እዚህ ቤትም “ለንቁ ፈረስ ያለንጋ ጥላ በቂው ነው” የሚለው ብሂል ነፍስና ሥጋ ሠርቶ ዓላማና ግቡ ሰምሮ እውን የሆነበት ነው። ዓይንና ጆሮ ጥርጣሬያቸው ምንድነው? ቢሉ “ማየት ማመን ነው” ይሆናልና መልሱ ከቦታው ተገኝቼ ካሜራዬንና መቅረፀ ድምፄን በማሰናዳት ምስልን ከድምፅ አስቀርቻለሁና ውድ አንባቢያን ሆይ የሞራል ትጥቅ የሕይወት ስንቅ ይሆናችሁ ዘንድ እንካችሁ ብያለሁ።

ሃሳብ በተግባር የተገለጠበት፣ እውቀት ፍሬ አፍርቶ የታየበት፣ የታጠፉ እጆች የተዘረጉበት፣ የተራቆተ የመንፈስ ጽናት በተስፋ ጥላ የለመለመበት፣ ፆም ያድር የነበረ ጉሮሮ በጥረቱና በላቡ ፍስሐ የተሞላበት እንጀራ የቆረሰበት፣ የደበዘዘ ትናንታቸው ዛሬ ላይ ፈክቶ ካለመኖር ወደመኖር የተሸጋገሩበት የዕድሜ ዘመን ድልድያቸው ነው አዲስ ሕይወት የዓይነስውራን ማዕከል። ከሁሉም አስቀድሞ በነበረኝ ጉብኝት ወቅት በመንግሥትና በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ከሚሠሩ ግብረሠናይ ድርጅቶች ያገኟቸው በርካታ ዋንጫዎችና ሰርተፍኬቶች ተሰድረው ስመለከት የሚኖረኝ ቆይታ ከወዲሁ አሳስቶኝ ከማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ ዓፄ ባዩሽ አበበ ቢሮ ዘለቅኩ። “ምን የተለየ ነገር ኖሮት ነው ሌላ ማኅበር የምትመሠርቱት?” በሚል እሳቤ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ፍቃድ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት እክል ሲገጥመው በጊዜው የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበሩት ካሳሁን ይበልጣል (ዶ/ር) “እኛ የምንሰጠው አገልግሎት በልጅነታቸው ዓይነስውር ለሆኑት ነውና እድሜያቸው ገፍቶ ከጊዜ በኋላ ዓይነስውርነት ለሚከሰትባቸው ዜጎቻችን የዚህ ማዕከል መቋቋም የግድ ያስፈልጋል” የሚል ፍቱን ሃሳብ ስላቀረቡ በወርሐ ግንቦት 1992 ዓ.ም የሕግ ማሕቀፍ አገኘ።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይና የፊንላንድ ኤምባሲዎች እንዲሁም በሀገረ ጀርመን የሚገኘው ሲቢኤም «ክሪስቶፎል ብላይንድ ሚሽን» የሰጡት ልግስና በእግሩ የተከለው አዲስ ሕይወት የዓይነስውራን ማዕከል የተደረገለት ድጋፍ ከአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ጋር ለመፈራረም ለነበረው የገንዘብ መስፈርት አቅም ሲሆነው አሁን ላይ በድምፅና በብሬል የተደራጀ ቤተመጽሐፍት ከማዘጋጀት ባሻገር ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት በብሬል የኅትመት ሥራዎችን በመጫረት ቋሚ የሀብት ምንጭ ለመፍጠር ችሏል።

ይህም አገልግሎቱን ለሚሹ አባሎቹ የትራንስፖርት እገዛ ለማድረግ ብርታት ሆኖታል። ከዚህም በተጨማሪ በማዕከሉ ውስጥ በሚገኘው የመዝናኛ ክበብ ከዝግጅት አንስቶ እስከ አቅርቦት ድረስ ያለው ሂደት ዓይነስውራን ሆኖ ስመለከት ተደንቄ ብቻ አልቀረሁም አወጋችሁ ዘንድ ሃሳባቸውንም ተቀበልኩ እንጂ። ሽኩሪያ ኑሩ በስልጢኛ አፏን ብትፈታም አማርኛ ለማውራት ስትኮላተፍ አንደበቷ ይጣፍጣል። እናትና አባቷ በሞት ሲያልፉ ከተቀበረችበት አስከፊ የገጠር ሕይወት አውጥቶ እዚህ ማዕከል ወንድሟ እንዳደረሳት ነገረችኝ ያዘዝኩትን ምግብ በቶሎ ልታደርስ ለሽንኩርት ከተፋ እየተጣደፈች። ይህ ሁኔታዋም እንግሊዝ ምድር የሚገኘውን ዳርክ ሆቴልን አስታወሰኝ።

የሚያስገርመው ነገር ምግቡን አዘጋጅተው የሚያቀርቡትና አስተናጋጆችም ዓይነስውራን ሲሆኑ ዳርክ ሆቴል የሚገባ ማንኛውም ሰው የእጅ ስልኩንም ይሁን ሌላ ምንም ዓይነት መብራት መጠቀም አይችልም። ከኮምፒውተር እንዲሁም ከብሬል ትምህርትና ከሞብሊቲ ሥልጠና በኋላ ፍላጎትና አቅማቸውን ባገናዘበ መልኩ ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩላቸው ዓፄ ባዩሽ አጫወቱኝ። ሽኩሪያም በጀመረችው የባልትና ሥራ ከጊዜ በኋላ የተከሰተባት ዓይነስውርነት ዙሪያ ገደል ያደረገው ሕይወቷ መቃናቱን ገለጸችልኝ።

አሰላ ለሚገኙ አባሎቻቸውም ከቀነኒሳ ቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ጋር በመተባበር ማሽኑን በመግዛት የሹራብ ሥራ እንዳስጀመሯቸው አያይዘው አነሱልኝ። “ትልቅ ከሆኑ በኋላ ዓይነስውር የሚሆኑ ዜጎቻችን ማኅበራዊ መስተጋብራቸው እንዳይጓደል ከነሱ በላይ የሥነልቦና ትምህርት የምንሰጠው አብረዋቸው ለሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው ነው” አሉና ሰብሰብ ብለው ከሚጫወቱ አባሎቻቸው ጋር ደረስኩኝ። ሚካኤል መኮንን ይባላል። በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ነው በፈንጅ ፍንጣሪ ምክንያት ብርሃኑን ያጣው፤ በማዕከሉ አማካኝነት አዲስ ሕይወትን ተላብሶ የተበላሹ ኤሌክትሪክና ቧንቧዎችን ሲሠራ መመልከት ትንግርት ያጭራል። ዛሬ ላይ የሁለት ሴት ልጆች አባት ሲሆን በራሱ ተነሳሽነት በመሠረተው ዕድር የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚቴ አመራር እንዲሁም በሚዲያ ተከታታዮችና የሬዲዮ አድማጮች ማኅበር በሰብሳቢነት እያገለገለ ይገኛል።

የወታደርነት ጥንካሬው ለዛሬ ሕይወቱ እርሾው ተርፎት በድሪም ላንድ ኮሌጅ በሰው ሀብት ልማት አስተዳደር የዲፕሎማ ትምህርቱን ሲከታተል የሜዳሊያና የዋንጫ ተሸላሚ በመሆኑ ዲግሪውን እንዲቀጥል ኮሌጁ ነፃ የትምህርት ዕድል አመቻቸለት፤ በአሁኑ ሰዓትም በማዕከሉ በብሬል መምህርነት ሲሠራ ነው ያገኘሁት።

ሌላኛዋ ደግሞ አስቴር ወልደማርያም ትባላለች። ዓይነስውርነት የገጠማት በጡረታ ሚኒስቴር በጸሐፊነት በመሥራት ላይ ሳለች ሲሆን አዲስ ሕይወት የዓይነስውራን ማዕከልን ከመሠረቱት 22 ሰዎች መሐል አንዷ ናት። በተፈጠረባት አዲስ ማንነት ሳትደናገጥ ተግታ ብሬል በመሠልጠን ከኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በሥነዜጋ ዲፕሎማ ተመርቃ ረዘም ላሉ ጊዜያት ስታስተምር ቆይታ ጡረታ ስትወጣ ቤት ከመዋል ብላ ማዕከሉን በብሬል አስተማሪነት እያገዘች ትገኛለች።

ቦታ በመስጠት አጋርነቱንና ኃላፊነቱን ያሳያቸው መንግሥት ብቻ ሳይሆን ያስተዋፅዖ ትንሽና ትልቅ የለውምና እያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት ድጋፋቸውን እንዲቸሯቸው የአዲስ ሕይወት የዓይነስውራን ማዕከል ሥራ አስኪያጅ ዓፄ ባዩሽ ባስተላለፉት የማብቂያ መልዕክት ጽሑፌን ቋጨሁ።

ሃብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You