የኢፌዴሪ መንግሥት ህወሓት ላይ የሕግ ማስከበር እርምጃ እየወሰደ ባለበት ወቅት የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ የተቆጣጠረው የሱዳን ሠራዊት የተለያዩ ጦርነት ነጋሪ መልዕክቶችን ሲያስተላልፍ ይስተዋላል።
ከዚህ ቀደም ሰላማዊ ጉርብትና የነበራቸው ሁለቱ ሀገራት አሁን የታየው የሱዳን ሰራዊት የድንበር ጥሰት ወደ ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ሊያስገባ የሚችል ክፍተት እንደሆነ በርካቶች ምልከታቸውን እየገለጹም ይገኛሉ፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረው የድንበር ውዝግብ በሌላ ሦስተኛ አካል የተዘጋጀ የጦርነት ድግስ መሆኑንም ብዙዎች ሲተነትኑ ይታያል።
ይህን ተከትሎ ሰሞኑን የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ሱዳን በሦስተኛ ወገን የተደገሰላትን የጦርነት ወጥመድ ወደ ጎን በመተው የድንበሩን ጉዳይ በድርድር ለመፍታት ቁርጠኛ መሆን እንዳለባት አሳስበዋል።
ኢትዮጵያና ሱዳን የሚገጥማቸው የውስጥ ችግር ያልበገረው ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ወዳጅነት እንዳላቸው ይታወቃል። ከአንድ ዓመት በፊት ሱዳን የገጠማት ፖለቲካዊ ችግር ሱዳናውያንን ሳይጎዳ በሰላም እልባት እንዲያገኝ በማድረግ የኢትዮጵያ ሚና ከፍተኛ ነበር።
ይህንን የጠበቀ ወዳጅነት ችግር ውስጥ የከተተው የሱዳን መንግሥት ድርጊቱ የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች የማይመጥንና ከወዳጅ ጎረቤት ሀገር የማይጠበቅ አሳዛኝ ተግባር ነው። አሁንም ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጊዜው አልረፈደም።
የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሩን በሰላም ለመፍታት እየሄደበት ያለው እረጅም እርቀት ከጦርነት የሚያተርፍ እንደሌለ የሁለቱም ሀገራት የትናንት ታሪኮች በተጨባጭ የሚናገሩትና የሚመሰክሩት እውነታ ስለሆነ ነው።
የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ከፍ ያለ የልማት ፍላጎት ያላቸው፣ ድህነት ካስከፈላቸውና እያስከፈላቸው ካለው ከፍ ያለ ዋጋ አንጻር ይህንኑ ወደሚያባብስ ግጭት መግባት ለሕዝቦቻቸው መሠረታዊ ፍላጎት ምላሽ የሚሆን አቅም ስለሌለው ነው።
በርግጥ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የድንበር ውዝግብ የትናንት ሳይሆን ከ100 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው ነው። በነዚህ ረጅም ጊዜያት ሀገራቱ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሄዱበት መንገድ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ትክክለኛው መንገድ እንደሆነ ለመገመት የሚከብድ አይደለም፡፡
ችግሩን በኃይል ለመፍታት በሱዳን መንግሥት በኩል የተሄደበት መንገድ በሁለቱ ሀገሮች ሕዝቦች መካከል የነበረውን ረጅም ዘመን ያስቆጠረውን የወንድማማችነት እና የጉርብትና መንፈስ ያልተከተለ፣ የነበረውን ግንኙነት ችግር ውስጥ የሚከትና ነባራዊ ሁኔታውን እየቀየረ ያለ ክስተት ነው።
ይህ አጉራ ዘለል የሱዳን ሰራዊት ተግባር በኢትዮጵያ ያለውን አለመረጋጋትና የትግራይን የሰላም ማስከበር ዘመቻን እንደ ክፍተት ከመጠቀም ፍላጎት የመነጨ አስነዋሪ ተግባር ቢሆንም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የሀገሩን ሉአላዊነት ለማስከበር በቂ አቅምና ቁመና ያለው መሆኑን ማሰብ ተገቢ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብም በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ቢሆን የሀገሩን ሉአላዊነት ለማስከበር የሚያስችል ከፍ ያለ የሀገር ፍቅርና የአትንኩኝ ባይነት ከፍ ያለ ታሪክ ባለቤት ነው። ይህንንም የቀደሙት ዘመናት ታሪኮች ተጨባጭ ምስክሮች ናቸው።
የድንበር ጉዳዩን በሠላማዊና ዲፕሎማሲያዊ አማራጭ ለመፍታት በቅድሚያ የሁለቱም ሀገራት መንግሥታት በትብብር ለመሥራት መዘጋጀት ይኖርባቸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን በሠላማዊና ዲፕሎማሲያዊ አማራጭ ለመፍታት ቅድሚያ እንደሰጠ ሁሉ የሱዳን መንግሥትም በኃይል የያዛቸውን ቦታዎች ለቆ ለሰላም ድርድር በሩን መክፈት ይኖርበታል። በዚህም የሚታደገው የራሱን ሕዝቦች ደህንነትና የሀገራቱን ሰላም የቀደመ ጉርብትና ጭምር ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 25/2013