ከሰሜን ደቡብ፤ ከምዕራብ ምስራቅ፤ በልዩነት ውስጥ በደመቀ አንድነት በሚኖሩ ህዝቦች የደመቀች፣ ለዘመናት ሉዓላዊነቷን አስከብራ የኖረች፣ የታላላቅ ታሪኮችና ገድሎች አውድ፣ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት፣ የበርካታ ብርቅና ደንቅ ሰው ሰራሽ ተፈጥሯዊ ቅርሶች መገኛ፣ ዓባይን ጨምሮ የታላላቅ ወንዞች ምንጭ፤ የኦሎምፒኩ መድረክ ፈርጥ፣ የጀግኖች እናት፣ የሰው ልጆች መገኛ ወዘተ ወዘተ በሚሉ ቃላት የኢትዮጵያን ታላቅነት ለመግለጽ ቢሞከርም ይህንን እውነታ ለመግለጽ ብዕር እንኳን አቅም ያጣል።
ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ናት ሲባል እንዲሁ ለሞራል ብቻ የሚባል ነገር አይደለም። ይህንን ታላቅነቷን እንድትጎናጸፍ በየዘመናቱ ዋጋ የከፈሉና የሚከፍሉ እልፍ ልጆች ስላሏት እንጂ! የኢትዮጵያ ታላቅነት ያልገባቸው ትናንሾች ከራሳቸው የፖለቲካ ትርፍ ጋር አስልተው ይህ ካልሆነ ወይም ይህ ካልተደረገ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ብለው ቢያሟርቱም ሟርቱ እነሱን ጠርጎ ከመሄድ ውጪ ኢትዮጵያ እንደብረት ጠንክራ ዛሬም አለች።
ሉዓላዊነቷ በተከበረ አገር ላይ መኖር የቻልነው ጠላት ጠፍቶና ተንኳሽ ሳይኖር ቀርቶ አይደለም። ከራሳቸው ህይወት ይልቅ አገርንና ህዝብን የሚያስቀድሙና ለዚህ ደግሞ ክቡር ህይወታቸውን ጭምር የሰጡ እልፍና እልፍ የቁርጥ ቀን ልጆች ኢትዮጵያ ስለወለደች እንጂ! በሺዎች ዓመታት የኢትዮጵያ ታሪክ አገራችን የደረሰባትን ወረራ ለመቀልበስ ካካሄደችው ፍትሃዊ ጦርነት ውጪ አንድም ጊዜ የሰውን ድንበር ተጋፍታ አታወቅም። ይልቁኑ ጎረቤት ሱዳንና ሶማሊያን ጨምሮ በርዋንዳ ብሩንዲ ለወንድምና እህት አፍሪካውያን በሰላም መኖር ትልቅ ላቅ ያለ ዋጋ ከፍላለች።
ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ከሰሞኑ ባስተላለፉት መልዕክት “ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት። ሐሳባችን፣ ሥራችንና ንግግራችን ሁሉ ታላቅነቷን የሚመጥን መሆን ቢችል መልካም ነው። ካልሆነ በኢትዮጵያ ሚዛን ተመዝነን እንቀላለን። ኢትዮጵያ መዝና ታላቅነቱን የመሰከረችለትን ማንም አያቀልለውም። ኢትዮጵያ ያቀለለችውንም ደግሞ ማንም አያከብደውም። ታሪካችን ይሄንን ይመሰክራል፤ ዛሬም እየመሰከረ ነው።
ኢትዮጵያ ታላቅ ናት ስንል ከዜጎቿም፣ ከመሪዎቿም፤ ታላቅ ገድል ፈጽመናል ከሚሉ ሰዎች ሁሉ በላይ ታላቅ ናት ማለታችን ነው። በየትኛውም ዘርፍ ያሉ ልሂቃን፣ የትኛውንም የተቀደሰ አጀንዳ አንግበው የተመሠረቱ ድርጅቶች፣ ሐሳብና ርዕዮተ ዓለሞች ሁሉም ከኢትዮጵያ በታች ናቸው። ኢትዮጵያ ለሺዎች ዘመናት ሠርተውና ተጋድለው ያለፉ መሪዎችና ዜጎች ድምር ውጤት ናት።
ኢትዮጵያ – ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ ሰፍተውና መልተው የሚኖሩ፣ የሚሠሩና የሚጋደሉ ልዩ ልዩ ሕዝቦች ውጤት ናት። ታሪክ ያልመዘገባቸው፣ የታሪክ ድርሳናት የማያውቋቸው እልፍ አእላፍ ታሪክ ሠሪዎች በደምና በአጥንት፣ በላብና በወዝ በጽኑዕ መሠረት ላይ የገነቧት ሀገርም ናት። ግለሰቦች ለኢትዮጵያ የማይናቅ አስተዋጽዖ ያደርጋሉ፤ የኢትዮጵያ ህልውና ግን በግለሰቦች አይወሰንም። ግለሰቦች ለክብሯ ሲሉ ደማቸውን ሊያፈስሱ፣ አጥንታቸውን ሊከሰክሱ፣ መስዋዕት ሆነው ሊያስቀጥሏት ይወስኑ ይሆናል፤ ነገር ግን “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለችው የቤት እንስሳ፣ ለግለሰቦች ሲባል ሀገር እንድትሞት ወይም እንድትኖር ለድርድር አትቀርብም።”
አባባሉ ትልቅ እውነታነት አለው። የሁሉም ጀግንነትም ሆነ አኩሪ ሥራ ከኢትዮጵያ ጋር በምንም ሚዛን አብሮ ሊመዘንና ሊስተካከል ወይም፣ ደግሞ፣ ልቆ ሊገኝ አይችልም። የሁሉ ኢትዮጵያዊ አኩሪ ገድልና ጀግንነት በኢትዮጵያ የታሪክ ማህደር ውስጥ ተመዝግቦ ይቀመጣል እንጂ ከኢትዮጵያ ጋር በፍጹም አይወዳደርም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን በዚህ ዓለም ካሉ ነገሮች ሁሉ ልቃ የምትገኝ ውድ ነገር ናትና።
ይሁንና የኢትዮጵያ ታላቅነት እውን ሆኖ የሚቀጥለው ደግሞ መላ ዜጎቿ ለዚህ ስምና ደረጃ በሚመጥን መልኩ ሲንቀሳቀሱና ለታላቅነቷ ሲታትሩ ብቻ እንደሆነ ደግሞ ሊዘነጋ አይገባም። ይህ እውን የሚሆነው ለእውነት በመቆም፣ አሉባልታን በመጠየፍ፣ ለሥራ በመትጋትና ለሉዓላዊነቷ ሳያወላውሉ በመቆም ብቻ ነው!
አዲስ ዘመን ጥር 24/2013