
የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በበርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ታግዞ እና በመንግሥት አደረጃጀት ጭምር ተደግፎ እየተጓዘ ያለ ተግባር ሆኗል። በእዚህ ሂደትም የሚሊዮኖችን ሸክም ማቅለል፣ ችግር መካፈል፣ ድካም መቀነስ ተችሏል።
በተለይ የክረምቱ ወር በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ የሚሆኑበት እንደመሆኑ እና ታዳጊዎችና ወጣቶችም ለማህበራዊ ኃላፊነት ልምምድ ራሳቸውን የሚያዘጋጁበት ወቅት ነው። እናም ክረምቱን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማሳለፍ የመጀመሪያው አማራጭ ይሆናል።
ይሄን መሰል ተግባር ታዲያ ከግለሰብ የውስጥ ስሜትና ፍላጎት የሚመነጭ፣ የማህበረሰብን ድጋፍና ማበረታቻ የሚሻ፣ የመንግሥታዊ መዋቅሩን እገዛና ማስተባበር የሚፈልግ ነው። ለእዚህም ነው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይሄን መሰሉ ጉዳይ እያደገ፣ ሥራውም በውጤት ታጅቦ እየተጓዘ የሚገኘው።
ምክንያቱም፤ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በአንድ እና ሁለት መስኮች ብቻ የሚገለጥ አይሆንም። ለምሳሌ የክረምቱ አንዱ መገለጫ ዝናብና ጎርፍ ነው። ይሄ ዝናብን ተከትሎ የሚመጣ ጎርፍ በበርካታ አካባቢዎች ጉዳትን ሊያስከትል ይችላል። ሲያስከትልም ተመልክተናል።
ይሄን መሰል የጎርፍ ስጋትና አደጋ ከማቃለል አኳያ፤ ወጣቶችም ሆነ ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደየሙያና አቅማቸው የውሃ ማፋሰሻዎችን በመሥራትም ሆነ በማጽዳት የነቃ ተሳትፎን ማድረግ አንዱ የበጎ ተግባር መገለጫ ነው።
ሌላው የክረምቱ መልክ፣ በርካታ ሰብሎች እና ችግኞች ከመሬት ተዋድደው ለፍሬ እንዲበቁ መሠረት የሚጣልበት መሆኑ ነው። በእዚህ ረገድ በገጠሩ በእርሻና ሌሎችም መስኮች፣ በከተማውም በችግኝ ተከላና መሰል ተግባራት ተሰማርቶ ለምርታማነቱም፣ ለደን ሽፋን እድገቱም የየድርሻቸውን ማበርከት የበጎነት ተግባር ነው።
ከእዚህ በተጓዳኝ ክረምቱ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ የሚሆኑበት ብቻ ሳይሆን እንቅስቃሴዎች የሚያደርጉበት እንዲሁም ለቀጣይ የትምህርት ዘመን ዝግጅት የሚያደርጉበትም ነው። ከእዚህ አኳያ በአንድ በኩል እንቅስቃሴን የሚያውኩ የትራፊክ ፍሰቶችን እንዲሳለጡ በማድረግ በኩል መሳተፍ፣ በሌላ በኩል ተማሪዎች የታች ክፍል ተማሪዎችን የክረምት ትምህርት ማጠናከሪያ ትምህርት እንዲያገኙ ለማድረግ በበጎነት መሳተፍ የተገባ ነው።
ከእዚህ ባሻገር በክረምቱ የወጣቶችና ታዳጊዎችን ተሳትፎ የሚሹ በርካታ ሥራዎችም የኅብረተሰብ ክፍሎችም አሉ። ለምሳሌ አረጋውያንን መንከባከብ፣ ደም መለገስ፣ የትራፊክ ቁጥጥር ሥራን ማገዝ፣ ማስተማር፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ንቁ ተሳትፎ ማድረግ፣ በሌሎች ራስን ማበልጸጊያ ስፍራዎች መዋልን የመሳሰሉ ተግባራት ተጠቃሽ ናቸው።
ከእዚህ ባሻገር የክረምቱ መገለጫ ዝናብን አስከትሎ የሚመጣው ብርድ ነው። ዝናብና ብርድ ተጣምረው ሲከሰቱ ደግሞ፣ እነርሱን ለመቋቋም የሚያስችል መጠለያ ያስፈልጋል። በተለይ አቅም የሌላቸው ግለሰቦች፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች በእዚህ በኩል ከፍ ያለ የችግሩ ተጋላጮች ናቸው።
በመሆኑም ክረምቱ እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ማዕከል ያደረገ ሥራ የሚሠራበት ሊሆን የተገባ ነው። ከእነዚህ ሥራዎች መካከል አንዱ ደግሞ የእነዚህን ሰዎች ቤት ማደስ፣ የሌላቸው ካሉም መጠለያ እንዲያገኙ ማገዝ ነው። በእዚህ ረገድ ከሰ ሞኑ የአዲስ አ በባ ከተማ አ ስተዳደር፣ ከተማ አ ቀፍ የክረምት በ ጎ ፈቃድ አ ገልግሎትን አስጀምሯል።
ይሄን መርሃ ግብር ያስጀመሩት የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩትም፤ ከሰሞኑ የተጀመረው ከተማ አቀፍ የክረምት በጎ ፍቃድ ሥራዎችን የአቅመ ደካማዎች ቤት ግንባታ የሚከናወንበት፤ በደም ምክንያት ሕይወታቸውን የሚያጡ ወገኖችን ለመታደግ የሚያስችል የደም ልገሳ ሥራም የሚከናወንበት ነው።
ይሄን መሰሉ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ታዲያ፣ ከለውጡ ወዲህ እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን፤ ይሄም የበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት የአንድ ወቅት የንቅናቄ ሥራ ብቻ ሳይሆን የሁሌ ተግባር እና ባሕል ማድረግን ታሳቢ በማድረግ ተቋም መስርተን፣ ተቋማዊ አሠራርን በመዘርጋት በሠራነው ሥራ የሚሊዮኖች እንባ ታብሷል ሲሉም ነው ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ያሰፈሩት።
በእዚህ ክረምት እንዲከወን በታሰበው እና በይፋ በተጀመረው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎትም፤ የበርካቶች እንባ የሚታበስበት፣ ለአቅመ ደካሞች ሁለት ሺህ 500 ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶች በመገንባት የዘመሙ ጎጆዎች የሚቃኑበት፣ ለ500 ሺህ ሰዎችም ማዕድ በማጋራት የክረምት የኑሮ ጫናን ማለፍ የምናስችልበት፤ ወላጅ የሌላቸው 440 ሕጻናት አሳዳጊና ተንከባካቢ ቤተሰቦች የሚያገኙበት፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ከተማችንን አረንጓዴ የምናለብስበት ነው። በሂደቱም ከሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ በጎ ፍቃደኞች የሚሳተፉበት በርካታ ተግባራትን ያቀፈ ነው ሲሉም አብራርተዋል።
ይሄን መሰል ተሳትፎና ተግባር ታዲያ ከጊዜ ወደጊዜ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ እያደገ የመጣ ሲሆን፤ ከንቲባዋ እንዳሉትም፤ በእዚህ ረገድ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ባለሀብቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ተቋማት መኖራቸው እሙን ነው። ይሁን እንጂ ሥራው ለተወሰኑ አካላት የሚሰጥ ባለመሆኑ፤ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ክረምቱን ለእዚህ መሰሉ መልካም ተግባር ማዋል እና ክረምቱን ለበጎነት ማዋል ይገባዋል!
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም