የሃይማኖት ተቋማት ለሀገራዊ ሰላም ለሚያደርጉት ጥረት የዜጎችን ቀና ትብብር ይጠይቃል!

የሰው ልጅ ሰፊ የሞራል እሴቶች ያሉት ፤ በእነዚህ እሴቶች እየተገራ ዘመናትን የተሻገረ ፍጥረት ነው ። ከነዚህ እሴቶች የሚቀዳው ሠብዓዊነቱም ፤ በዘመናት ውስጥ በተለያዩ አስተምህሮዎች እያደገ ፤ በጊዜ ሂደት ከሞላ ጎደል በሰላም ፤ በፍቅር እና በአብሮነት የሚኖርበትን ዓለም መፍጠር አስችሎታል ። ቀጣይ እጣ ፈንታውም በእነዚህ አሴቶቹ ላይ የተመሠረተ እንደሚሆን ይታመናል ።

በሞራል እሴቶች በአግባቡ የተገራ ትውልድ ከራሱ እና ከሚኖርበት ማኅበረሰቡ ጋር ተናብቦ እና ተስማምቶ እንዲኖር ያስችለዋል ፤ ራሱን እና የወጣበትን ማኅበረሰብ ሆኖ የዕለት ተእለት ሕይወቱን እንዲያሸንፍ ሰፊ ዕድል ይሰጠዋል ። ይህ የተገራ ሥብዕናው በማኅበረሰብ ውስጥ ዘላቂ ሰላም እና ማኅበረሰባዊ መረጋጋት ለመፍጠር የሚኖረው አስተዋጽኦ መተኪያ እንደማይኖረው ብዙዎች ይስማማሉ።

በተለይም ካልተገባ ማንነት የሚቀዳ ከፍያ ለራስ ወዳድነት እና ከዚሁ የሚመነጩ መልከ ብዙ ማኅበረሰባዊ አደጋዎችን ለመሻገር ፤ ከዛም ባለፈ በማህበረሰብ ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ የባህሪ መዛነፎችን ለዘለቄታው በመግራት የሰከነ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሞራል እሴቶች እና አስተምህሮዎች ወሳኝ አቅሞች ናቸው ።

እነዚህን የሞራል እሴቶች በማህበረሰብ ውስጥ በማስረጽ ሂደት ከሁሉም በላይ የሃይማኖት ተቋማት ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ። አብዛኞቹ መንፈሳዊ እሴቶችም ቢሆኑ በመሠረታዊነት ከማኅበረሰባዊ የሞራል ግንባታ ጋር የተሳሰሩ መሆናቸው ተቋማቱ የተገራ ማኅበረሰብ በመፍጠር ሂደት ውስጥ ያላቸውን አበርክቶ የማይተካ ያደርገዋል ።

የየትኛውም ሃይማኖት አስተምህሮዎች በአንድም ይሁን በሌላ ሠብዓዊ የሞራል እሴቶችን መሠረት ያደረጉ ናቸው። “ከአድርግ ሆነ አታድርግ” ትእዛዛት በስተጀርባ ያሉ መንፈሳዊ አስተምህሮዎች አስተሳሰባዊ መሠረቶች የግለሰብን ፤ ከዚያም አልፎ የማኅበረሰብን የእለት ተእለት ሕይወት በአዎንታዊ መንገድ መግራት የሚያስችሉ እና የሚያጸኑ ናቸው ።

ከሁሉም በላይ ፍቅርን እና አብሮነትን፤ መከባበርን እና መቻቻልን ፤ ከዚህም ከፍ ሲል ራስን መካድን እና ለሌሎች መኖርን በመሠረታዊነት የሚያስተምሩ ፤የመታዘዝ ዋጋቸውም የላቀ ፤ ከዚህ ዓለም ተሻጋሪ መሆንን የሚሰብኩ ፤ ይህንን የሚሸከም ማኅበረሰብ ለመቅረጽ የሚተጉ ናቸው።

እነዚህን በአብዛኛው ከመንፈሳዊ አስተምሮ የሚቀዱ ማኅበረሰባዊ እሴቶች በተጨባጭ በማኅበረሰብ ሕይወት ውስጥ ገዝፈው እንዲታዩ ፤ የሕይወት መርህ ሆነው እንዲቀጥሉ፤ የትውልድ ግንባታ አልፋ እና ኦሜጋ ሆኖ እንዲጸና በሁለንተናዊ መንገድ/ባላቸው አቅም ሁሉ የሚንቀሳቀሱ ናቸው።

የሃይማኖት ተቋማት ዋነኛ ተልዕኮ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ፤ በአሁናዊ ዓለም ከከፋ ራስ ወዳድነት እና ከተዛነፈ አስተሳሰብ የሚመነጭ አክራሪነት እና ጽንፈኝነትን ለዘለቄታው ለመዋጋት እና የተረጋጋ እና የሰከነ ማኅበረሰብ በመፍጠር ሂደት ውስጥ ወሳኝ አቅም ነው።

ይህ ተጨባጭ እውነታ በተለይም እንደኛ ባሉ ሰፊ ሃይማኖተኛ ማኅበረሰብ በውስጣቸው ይዘው በግጭት አዙሪት ውስጥ አላስፈላጊ ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ሀገራት እና ሕዝቦች አሁን ላይ እያጋጠማቸው ያለውን የሰላም እጦትም ሆነ በትውልድ መካከል እየተፈጠሩ ያሉ አሉታዊ የሞራል ክፍተቶችን በማጥበብ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት ትልቅ አቅም እንደሚሆናቸው ይታመናል።

ሀገራቱ እና ሕዝቦቻቸው ለሃይማኖታዊ አሴቶች እና አስተምህሮዎች ያላቸው ቀናኢነት እና ከዚህ ቀናዒነት የሚመነጨውን የመታዘዝ መነሳሳታቸው ለማኅበረሰብ ብሩህ ነገዎች በአዎንታዊ መንገድ የመግሪያ መሣሪያ አድርጎ መጠቀም እና ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ያስፈልጋል ።

ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያ የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን መሠረት አድርገው፤ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን፤ ማኅበረሰባዊ ስክነት እንዲፈጠር እያደረጉት ያለው ጥረት እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ብሎም የእያንዳንዱን ዜጋ ቀና ትብብር የሚጠይቅም ነው!

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You