አዲሱ ገረመው
የስነ ፅሑፍ ሀብቶች ተጠብቀውና በስርዓት ተሰድረው ዘመን ተሻጋሪ ፋይዳ ማበርከት እንዲችሉ ማድረግ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው የአገሪቱ ስነ ጽሑፋዊ ሀብት፣ እውቀት፣ባህል፣ ታሪክና የማህበረሰብ አኗኗር መገለጫ የሆኑትን የመረጃ ሀብቶች በማዕከል በማሰባሰብና በመጠበቅ ዜጎችን እኩል ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል በዚህም የአገሪቱ የጽሑፍ ሀብቶች ብሄራዊ ቢብሊዮ ግራፊ (መዝገበ መረጃ ) በማዘጋጀት የጽሑፍ ሀብቶቿን ለዓለም ለማስተዋወቅ፣ እንደ አገር የጋራ የመረጃ ቋት በመፍጠር በተለያየ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ተገልጋዮችን ተጠቃሚ ማድረግ ወሳኝ ነው ።
ስነ ፅሑፋዊ ጠቀሜታቸው የጎላና ለአገር ትልቅ ፋይዳ ሊያበረክቱ የሚችሉ የመረጃ ሀብቶች በግለሰቦች እጅ ወይም በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው ሲቀመጡ ሊከሰት የሚችል ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ ጉዳቱን ከፍ ያደርገዋል ታሪካዊ ፅሑፍ ወይም የስነ ፅሑፍ ውጤት እንደ ነበር ለመመለስ አልያም የመረጃ ሀብቱ ባለቤት ከረጅም ዘመን በኋላ እንደገና ማሳተም ቢፈለግ በስርዓት ከተሰደረና እነዳይበላሽ ከተጠበቀ ከማዕከሉ በቀላሉ ማግኘት ከመቻሉም በላይ ሌሎች በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የስነ ፅሑፍ ሀብቶች በተለይ መፅሐፍትና ሌሎች መዛግብት የሚጠበቁበትና ዘመናት ሳይበላሹ እንዲቆዩ የሚደረጉበት መንገድ አለ ዓለም አቀፍ የሕትመት መለያ ቁጥር ከዛሬ 56 ዓመታት በፊት ሥራ ሲጀምር በዘጠኝ አኀዝ ባላቸው ቁጥሮች የጀመረ ቢሆንም (ለአንድ መጽሐፍ የሚሰጥ ) ዛሬ ላይ 13 አኀዝ ላይ ደርሷል ይህም በዓለም ላይ ያለውን የሕትመት መበራከትና ቁጥሩን የሚወስዱ አባል አገራት ቁጥር መበራከትን ያመላክታል ከ 200 በላይ ከሚሆኑት የኤጀንሲው አባል አገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷናት።
በኢትዮጵያ የብሄራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጽሐፍት ኤጀንሲ በአዋጅ ቁጥር 179/91 የሀገሪቱ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ የመጽሐፍትና መጽሔት መለያ ቁጥር ሰጪ አካል ሆኖ እንዲሠራ በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ የዓለም አቀፉ ድርጅት ተወካይ ሆኖ ሥራ ጀምሯል ይሁን እንጂ የተከታታይ ሕትመቶችንና የሙዚቃ ሕትመቶችን ገና ያልጀመረ ቢሆንም በሃገሪቱ ውስጥ ለሚታተሙ መጻሕፍት የመለያ በመስጠት ላይ ይገኛል።
በዚህ መሰረት የሃገሪቱን የሕትመት ሀብቶች ዓለም አቀፍ የሕትመት ደረጃ በማስጠበቅ የመረጃ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ የመረጃ ሀብቶቹ ባለቤቶች እውቅና እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል።
በብሄራዊ ቤተመዛገብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ የቤተመጻሕፍት የመረጃ ሀብቶች አስተዳደር ዳይሬክተር ወይዘሮ መሉእመቤት ጌታቸው እንደሚሉት፤ የዓለም ስልጣኔ እያደገና የሰዎች የመረጃ ፍላጎት እየጨመረ ሲመጣ መረጃን በጽሑፍ መያዝና ለሌላው ማስተላለፍ የተሻለ መንገድ ሆኖ በመገኘቱ የጽሑፍ ሥራ ተጀመረ የሕትመት ሥራ እስከ ተጀመረበት ጊዜ ድረስ በርካታ የጽሑፍ መረጃ ማስተላለፊያ መሳሪዎች እንደየ ዘመኑ የእድገት ደረጃ ጥቅም ላይ ውለዋል ከእነዚህም፤ ድንጋይ፣ ሸክላ፣ ፓፒረስና ብራና በዋናነት ይጠቀሳሉ እነዚህ የመረጃ ማስተላለፊያ መሳሪያዎች መረጃን በስፋት ለማሰራጨት ምቹ ባይሆኑም በየዘመናቸው መረጃን ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላው፣ ከሰው ወደ ሰው፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲያስተላለፉ የቆዩ ናቸው።
ከጊዜ ወደ ጊዜ በጽሑፍ የሚተላለፉ መረጃዎች በመበራከታቸው መረጃዎቹን ለማስተዋወቅና ለሌሎች ለማስተላለፍ የተለያዩ የአዘገጃጀት ስልቶችን ይጠቀሙ እንደ ነበር ወይዘሮ ሙሉእመቤት መዛግብትን ዋቢ አድርገው ያሰረዳሉ ቀስ በቀስ የስነጽሑፍ እድገትንና የመረጃ ፈላጊውን መበራከት ተከትሎ 1450 እ.ኤ.አ የማተሚያ ማሽን ተፈለሰፈ የሚሉት ወይዘሮ ሙሉእመቤት፤ ይህም ለስነጽሑፍ እድገትና እውቀትን በስፋት ለማሰራጨት ካበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባሻገር ከሕትመት ውጤቶች በብዛት መመረት ጋር ተያይዞ አንዱን ከሌላው የመለየት፣ የባለቤትነት መብትን የማስከበር፣ መረጃን ከመረጃ ፈላጊው ጋር የማገናኘትና ሌሎች የህትመት አዘገጃጀትን አስመልክቶ ይታዩ ለነበሩ ችግሮች መፍቻ የሚሆኑ የህትመት አዘገጃጀት ስልቶችን ሥራ ላይ ለማዋል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ያስረዳሉ።
የአገሪቱን የመረጃ ሀብቶች በአዋጅ / በሕግ ማሰባሰብ
እንደ ወይዘሮ ሙሉእመቤት ማብራሪያ፤ የብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ በአገሪቱ ውስጥ ከሚዘጋጁ ፣ ከሚታተሙ ፣ አገር ውስጥ ተዘጋጅተው በውጭ አገር ከሚታተሙ የሕትመት ውጤቶች ሁሉ ሦስት ሦስት ቅጂዎችን በማሰባሰብ ፣ በማደራጀት፣ ጠብቆ ለትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት አለበት በተለይ ለጥናትና ምርምር ተደራሽ በማድረግ የአገሪቱ መረጃ ማዕከል ሆኖ እንዲሠራ በአዋጅ ጭምር ድርሻ ተሰጥቶታል በዚህ መሰረት እያንዳንዱ ደራሲ፣ አሳታሚ፣ አርታኢ ወይም ማንኛውም የሕትመቱ ባለቤት ሕትመቱ በታተመ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከያንዳንዱ እትም ሦስት ቅጂዎችን ወደ ኤጀንሲው እንዲያስገባ ሕጉ ያስገድዳል።
የክልል አብያተ መጻሕፍት
የሃገሪቱን ባህል፣ ታሪክና እውቀት ዛሬን ጥቅም ላይ ለማዋልና ለነገ ጠብቆ ለማቆየት የብሄራዊ ቤተዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ በአዋጅ እንደተቋቋመው ሁሉ፤ የክልል አብያተ መጻሕፍትን ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ወይዘሮ ሙሉእመቤት ይጠቁማሉ ይህም በየክልሉ ያሉ የእውቀት ሀብቶች የማሰባሰብ፣ የማደራጀትና ጠብቆ ለትውልድ የማስተላለፍ ጠቀሜታ እንዳለው ይናገራሉ መረጃን ለመጋራትና ለመለዋወጥ፣ ቴክኒካዊ ድጋፍ ለማግኘት፣ ከብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ ጋር በመተባበርና በመቀናጀት የሚሠራ ለብሔራዊ ቤተመጻሕፍት በሃር ደረጃ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት በክልል ደረጃ ተሰጥቶት የሚያከናውን የክልል ቤተመጻሕፍት ለማቋቋም ኤጅንሲው እየሠራ ስለመሆኑም ይጠቁማሉ።
በመሆኑም ብሄራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲም ሆነ ወደፊት የሚቋቋመው የክልል ቤተመጻሕፍት አዋጁን ለማስተግበር ደራሲዎች፣ አሳታሚዎች፣ ከየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የጥናትና ምርምር ተቋማትና ከሙያ ማህበራት ጋር በመተባበር እንደሚሠሩም አስታውቀዋል።
በወረቀትም ሆነ በተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ቁሶች ላይ የታተሙ መረጃ የሚይዙ እውቀትን፣ ጥበብን፣ ባሕልን፣ ታሪክንና ስልጣኔን ከሰው ወደሰው፣ ከአገር ወደ አገር ከክፍለ ዘመን ወደ ክፍለ ዘመን የሚያሻግሩ የመረጃ ተሸካሚ መሳሪያዎች ናቸው።
መሰረታዊ ጉዳዮች
በመዛግብት ስነዳ ወቅት ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ መሰረታዊ ጉዳይ አለ የሕትመቱ ባለቤት ደራሲ ፣አሳታሚ፣ አርታኢ እና ሌሎች ህትመቱን በባለቤትነት የያዙ ወይም በሥራው ላይ በተባባሪነት የተሳተፉ ካሉ)፤ የሕትመቱ ዋና ርዕስ፣ ንኡስ ርዕስ ካለው፤ ሕትመቱ ከሌላ ቋንቋ የተተረጎመ ከሆነ ተነጻጻሪ ርዕስ፣ ዋናው ርዕስ የሚካተቱበት ይሆናል።
በተጨማሪም በመረጃው የመጀመሪያው ደራሲና ተርጓሚው፤ የዕትም ድግግሞሽ ቁጥር፣ ድጋሚ ያሳተመው አካል የመጀመሪያው ባለቤት ካልሆነ፤ አታሚው ድርጅት፤ የሕትመት ቦታው፤ የሕትመት ጊዜው /ዓመተ ምህረቱ፤ ኢንዴክስ (የፊደላት ማውጫ)፤ የሕትመቱ መረጃ የተገኘባቸው ሌሎች የመረጃ ምንጮች /የማጣቀሻ መጻሕፍት፤ ዓለም አቀፍ የመጻሕፍት መለያ ቁጥር፤ ሕትመቱ የሚዘጋጅበን ቋንቋ የአካባቢው ማህበረሰብ የማይረዳው ከሆነ በሚታወቅ ቋንቋ መተርጎም ለህትመት አዘገጃጀት መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው ከዚህም ባሻገር የወረቀት፣ የፊደል፣ የጥራዝና የቀለም ጥራት ዋሳኝነት ካላቸው መሠራተዊ ጉዳዮች መካከል መሆናቸውን ባለሙያዎች ያመለክታሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 23/2013