አዲስ አበባ፡- የሚኒስትሮች ምክር ቤት /ካቢኔው/ ትናንት ባካሄደው 14ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ሁለት አዋጆችን ተመልክቶ ማሻሻያዎችን በማከል እንዲያ ጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ፣ ካቢኔው በአስቸኳይ ስብሰባው መንግሥት የቴሌኮሚኒኬሽን ገበያውን እንደገና ለማዋቀርና በቴሌኮሚኒኬሽን ገበያ ውድድርን ለማስፈን ያስቀመጠውን የፖሊሲ አቅጣጫ ለማሳካት የሚያስችል ተቆጣጣሪ ባላስልጣን ለማቋቋም የወጣን ረቂቅ አዋጅ፤ እንዲሁም በኢፌዴሪ መንግሥት እና በሕንድ ሪፐብሊክ መንግሥት መካከል የተደረሰውን የንግድ ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ ላይ ተወያይቷል፡፡ በረቂቅ አዋጆቹ ላይ ከተወያየ በኋላ ማሻሻያዎችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱን ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል፡፡
መግለጫው እንዳመለከተው፤ መንግሥት የኮሚኒኬሽን አገልግሎቶች በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ተገንዝቧል፡፡ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ለማሻሻል ይቻል ዘንድም የቴሌኮሚኒኬሽን የገበያ ስርዓቱን እንደገና ለማደራጀትና በውድድር ላይ የተመሰረተ አቅርቦት እንዲኖር ወስኗል፡፡
ውሳኔውን ለማስፈጸምና ያስቀመጠውን የፖሊሲ አቅጣጫ ለማሳካትም ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ማቋቋም አስፈላጊነቱ ስለታመነበት የገንዘብ ሚኒስቴር ስለ ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ለውሳኔ አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ማሻሻያዎችን በማከል ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቷል፡፡
በተመሳሳይ ምክር በቱ በኢፌዴሪ መንግሥት እና በሕንድ ሪፐብሊክ መንግሥት መካከል የተደረገውን የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነት ለማጽደቅ በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ መምከሩን መረጃው አመላክቷል፡፡ በውይይቱም ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የሚያስገኘውን ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት ረቂቅ አዋጁ እንዲጸድቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 28/2011
በወንድወሰን ሽመልስ