ምንም እንኳን በሚፈለገው ደረጃ ባይሆንም፤ እኛ ኢትዮጵያውያን መልካም የሠራን የማመስገን፣ ያጠፋንም የመገሰጽ ባህሉ አለን። ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የዚህ ባህል ከልብ የሆነ የመመሰጋገኛ ወይም መተራረሚያ እሴትነቱ እየተሸረሸረ፤ ለሐሰትና እኩይ ዓላማ የመሞካከሻ መሳሪያ ሲሆን ይስተዋላል። ለዚህም በልማታዊና ግንባር ቀደም በሚሉ ካባዎች በዘመነ ኢህአዴግ የነበረውን መሞጋገስና መሸላለም ማንሳቱ በቂ ነው።
ይህ ደግሞ በቀና ልብ ለእውነት የሚሠሩ፣ ከራስ ይልቅ አገርና ህዝብን በማስቀደም ሌት ከቀን የሚተጉ ሐቀኛ ኢትዮጵያውያንን አንገት ያስደፋ፤ ከአገርና ህዝብ ይልቅ ስለ ግልና ቡድን ህልውና የሚታትሩ፤ ለዚህም እውነትን ቀብረው ሐሰትና ሌብነትን ያነገሡ እኩያን ከፍ ብለው እንዲታዩ፤ አገርን በመመዝበር፣ ህዝቦችንም እንዳይተማመኑ በማድረግ ላይ አበክረው እንዲሠሩ አድርጓል።
ትጋታቸውም የራስና የቡድን ጥቅምን ለማስቀጠል የሚያስችል የፖለቲካ ሚዛንን ለማስጠበቅ እንጂ አገርን ቀና ለማድረግና ህዝብን ለማስተሳሰር አልነበረም። ለዚህ እኩይ ሴራቸው እውን መሆንም በአመራሩ ጭምር ጎልቶ የተስተዋለው ጽንፈኝነት አንዱ መሳሪያ ተደርጎ ነበር። ለዚህ ዓላማቸው ደግሞ ተከፋይ የማህበራዊ ሚዲያ ዘዋሪዎችን በመሰየም ጭምር በመንቀሳቀሳቸው አገር ለቅርጫ እንድትታጭ፤ ህዝቦችም በግፈኞች እጅ ለእስር፣ ለስደት፣ ለእንግልትና ሞት እንዲዳረጉ ሆኗል።
ከዚህ ሁሉ በኋላ በመጣው አገራዊ ለውጥ ማግስትም ቢሆን የዚህ እኩይ ተግባር አቀንቃኞች እጅ በቀላሉ የሚታጠፍ አልሆነም። ይልቁንም ለይቅርታና ለፍቅር የተዘረጉ መልካም እጆችን ቆርጦ ለመጣል በእጅጉ ሲተጉ ተሰተውሏል። ሰኔዎችን እየጠበቁም የሚችሉትን ሲያደርጉ ቆይተዋል። የጥፋት ዕቅዳቸውን በ2010 ሰኔ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ በተሰነዘረው ጥቃት በለስ ባይቀናቸውም፤ ሰኔ 2011 ላይ ወንድማማቾችን ባጠፋፋው የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ላይ እውን አድርገውት ነበር።
አዲስ ዘመን ጥር 23/2013