የቡና ምርታቸውን ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች ይልካሉ፤አሜሪካ፣ አውሮፓና ጃፓን ትላልቆቹ የገበያ መዳረሻዎቻቸው ናቸው – ታዴ ጂጂ የደጋ ጫካ ቡና አምራች ባለቤትና ላኪ አቶ ተስፋዬ በቀለ፡፡
ድርጅቱ በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን ሻኪሶ ወረዳ ውስጥ እርሻ አለው፡፡ እንደ አገር ሲታይ የውጭ ንግድ በመቀዛቀዙ ምክንያት የውጭ ምንዛሬው እጥረት መኖሩን የሚናገሩት አቶ ተስፋዬ ፣ሥራቸውን በአግባቡ እየሠሩ ውጤታማ ከሆኑ ድርጅቶች መካከል አንዱ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ ድርጅታቸው ባስገኘው የውጭ ምናዛሬም በቅርቡ ከኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ሽልማት ማግኘት ችሏል፡፡
‹‹በአገር አቀፍ ደረጃ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱ ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት የውጭው ገበያ ዝቅተኛ መሆን ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ገዥ አገሮች የተለያዩ አማራጭ አገሮች እየመጡላቸው ስለሆነ ትኩረታቸውን ወደእነሱ በማድረጋቸው ነው፡፡›› የሚሉት አቶ ተስፋዬ፣በወጪ ንግዱ በተለመደው አካሄድ መጓዝ አዋጭ አለመሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡ ይህንንም በመረዳት በትጋት መሥራት ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
‹‹ከገበያው ጋር እንዴት መሄድ እንደምንችልም እንደ አገር ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ዋጋችንም ከፍተኛ ይሆንና ገዥዎቻችን ሌሎች አማራጮችን እንዲያዩ ይገደዳሉ፡፡››ይላሉ፡፡
ከምንም በላይ የምርቶችን ጥራት ማስጠበቅ ቅድሚያ ሊሰጥ የተገባው ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ አቶ ተስፋዬ እሳቸው እስፔሻሊቲ ቡና ላይ እንደሚሠሩ በመጥቀስም እምብዛም የገበያ ችግር አለመኖሩን፣ በውድድር ውስጥ ለማለፍ ጥራቱን ማስጠበቅ ግን የግድ እንደሚል ያስገነዝባሉ፡፡
ውጤታማ ለመሆን ሁሉም በዘርፉ የተሰማራ አካል ሥራውን አክብሮ በጥራት ከሠራ ማኛውንም ችግር መሻገር እንደሚችልም ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹በአገሪቱ የሚታየው አመለካከት በአጭር መንገድ መክበር ነው፡፡ መንግሥት በገበያው ያለውን ያልተገባ ስርዓት መቆጣጠር ድርሻው ነውና መዘንጋት የለበትም፡፡›› ብለዋል፡፡
የኦርጋኒክ ሥጋ ላኪ ባለቤት ወይዘሮ ዓለም መንግሥቱም አቶ ተስፋዬ ስለ ጥራት ያነሱትን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ ወይዘሮ ዓለም ሥጋ ወደ አረብ አገር ይልካሉ፡፡ የሚልኩበት አገር ለመገደቡ ምክንያቱ ጥራት አለመሻሻሉ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም አንዳንድ በሽታዎች ስላልጠፉ፣ መንግሥት የገበያ ትስስር ባለማድረጉ፣ በሚልኩት ምርት ላይ ያለው ስምና ጥራት መሻሻል አለማሳየቱን ይጠቅሳሉ፡፡
ጥቂቶች ብቻ በትጋታቸው የተነሳ በውጭ ንግዱ ውጤታማ መሆን እንደቻሉ ተናግረው፣ የውጭ ንግዱ ለመቀዛቀዙ በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ፡፡
እንደ እርሳቸው አነጋገርም፤ በመንግሥት መሠራት የነበረባቸው ሥራዎችም አልተሠሩም፡፡ የኢትዮጵያን ምርት በማሻሻል ዓለም አቀፍ ይዘትና ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግና የመሳሰሉ ሥራዎች በመንግሥት መሠራት ያለባቸው ናቸው፡፡
‹‹በቻይና ሰፊ ገበያ አለ፡፡ ግን እንደ ሌላው አገር ዘመናዊ የአሠራር ዘዴ ስለሌለና አርሶ አደሩም ጥሩ ግንዛቤ ስለሌለው ምርት እየቀነሰ ነው ያለው፡፡›› ያሉት ወይዘሮ ዓለም፣ በዚህ የተነሳም ኢትዮጵያ ማግኘት ያለባትን ገቢ እያገኘች አይደለችም ሲሉ ያብራራሉ፡፡›
‹‹ድንበርም መከበር አለበት፡፡ ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሪ እየተቸገረች ምርቷ ግን ጎረቤት አገር ሄዶ እነሱ በአራትና በአምስት እጥፍ ከኢትዮጵያ በላይ በኢትዮጵያ ንብረትና ሀብት እየተጠቀሙ ነው።›› ሲሉ ነው በቁጭት የሚናገሩት፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ አሁን ባለው አካሄድ እንዲያውም ኢትዮጵያ ላኪ ሳትሆን አስመጪ የምትሆንበት መንገድ እየጎለበተ ነው፡፡ ለምሳሌ እንስሳቱ በድንበር በኩል ሲሄዱ ምንም ቁጥጥር ባለመኖሩ ወንዱም ሴቱም ከብት እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ ይሁንና ምርታማነቱ እንዲቀጥል ስለሚፈለግ መታረድ የነበረበት ወንድ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ሴት እንስሳም በመውጣት ላይ ነው፡፡ ጎረቤቶቻችን አራብተው መልሰው ለኢትዮጵያ ሊሸጡ ነው ማለት ነው፡፡
ወይዘሮዋ ዓለም ‹‹እኔ ድንበር ይከበር በሚል በየመድረኩ ነው የምጮኸው፡፡ ምክንያቱም እንስሳቱ ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ሀብት የሚወጣው በድንበር አካባቢ ነውና ነው፡፡ጎረቤት አገሮች ከእኛ ሀብት በመጠቀም ላይ ናቸውና መንግሥት ድንበርን ማስከበር አለበት፡፡›› ይላሉ፡፡
የእርሳቸው ኩባንያ በራሱ ይህ ሁሉ ከተስተካከለ አሁን ካለበት በአራት እጥፍ ማምረት እንደሚችል ያምናሉ፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ሥጋ ኦርጋኒክ በመሆኑ ከሁሉም የበለጠ ጤናማ ነው፡፡ ይህን ዓይነት ሥጋ ግን የምንሸጠው እየለመንና እያለቀስን ገንዘባችንንም በብድር እየሰጠንና ብራችን ውጭ አገር እየቀረ ነው፤ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሌላ የገበያ በር ባለመፈጠሩ ነው፡፡ የሚሉት ወይዘሮ ዓለም፣ ድርጅታቸው በቀን እስከ መቶ ቶን ሥጋ ማምረት እንደሚችል ነው የሚናገሩት። ይህም ሲሰላ በዓመት እስከ መቶ ሚሊዮን ዶላር ማስገባት የሚችል መሆኑን ጠቅሰው፣እሳቸው ግን ሃያ በመቶም እንዳልሠሩ ያብራራሉ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የገበያ በር አለመኖሩን ይናገራሉ፡፡ በቀደመው አካሄድ መጓዝ ብዙ ርቀት አያስኬድም፡፡ሲሉም እሳቸውም ያስገነዝባሉ፡፡
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የወጪ ንግድ ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ሙሉጌታ ለወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ የተለያዩ ምክንያቶች እንደሚጠቀሱ ይናገራሉ፡፡ ለውጭ ንግድ የሚቀርቡ የግብርናና እንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች ጥራት መጓደል አንዱ ችግር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
በጥራት ረገድ ያለውን ችግር ለመፍታት የተደረገው ጥረት በቂ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ከሎጅስቲክስና ከግብይት ስርዓት ጋር የተያያዙ ከፍተኛ ችግሮች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡
የኮንትሮባንድ ንግድም ሌላው የወጪ ንግዱ ፈተና መሆኑን በመጠቅስ የላኪዎቹን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡
የወጪ ንግዱን ችግሮች ለዘለቄታው ለመፍታት በግብይት ሰንሰለት ውስጥ ያሉትን ምርቶች ለማሳለጥ በየደረጃው ካሉ ባለደርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ፡፡ የምርጥ ጥራትን የሚጎዱ አሠራሮችንም እንዲሁ በቅንጅት መከላከል ይገባል ይላሉ፡፡
በ2010 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የወጪ ንግድ አፈጻጸም እንደሚያሳየው፤ አገሪቱ ከወጪ ንግድ ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘች መሆኑ ይታወሳል፤ ይሁንና አፈጻጸሙ ከዕቅዱ አኳያ ሲታይ አነስተኛ ነው፡፡
በተያዘው በጀት ዓመትም በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት አንድ ነጥብ 96 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ ማሳካት የተቻለው አንድ ነጥብ 21 ቢሊዮን ዶላር መሆኑ ታውቋል፡፡ ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት ከተገኘው አንድ ነጥብ 35 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር 135 ነጥብ 82 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል፡፡ምክንያቱ ደግሞ በዋናነት የግብርና ምርት በሚፈለገው መጠንና ጥራት ያለመመረት፣ ህገወጥ ንግድንና ኮንትሮባንድን በሚፈለገው ደረጃ መግታት ያለመቻልና ሌሎችም መሆናቸውን ንግድ ሚኒስቴር በቅርቡ ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 28/2011
በአስቴር ኤልያስ