ኢያሱ መሰለ
ከአራት ኪሎ ወደ አምስት ኪሎ በሚወስደው አውራ መንገድ በስተቀኝ በኩል ከሀገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ ፊት ለፊት በሰላሳዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ አንድ ጎልማሳ ህጻን ልጁን ታቅፎ መሬት ላይ የተዘረጉ ሸቀጦችን ይሸጣል።በጠራራ ጸሃይ ህጻን ልጁን ታቅፎ የሚነግደው ይህ ታታሪ ሰው የስራ ተነሳሽነቱ አስደሰተኝና ቢያንስ እቃ በመግዛት ላበረታታው አስቤ ተጠጋሁት።
ሰውየው ጥቁር መነጽሩን ሰክቶ ህጻኑን ያጫውታል።ህጻኑ አፍ ባልፈታ አንደበቱ ትርጉም የሌለው ድምጽ ያሰማል። ምን ፈለግህ? ምን ልስጥህ? የሚለውን የተለመደ የነጋዴዎች ቃል በጆሮዬ እየተጠባበቅኩኝ አቀርቅሬ የምገዛውን እቃ መመልከት ጀመርኩኝ ። ነጋዴው ትኩረት አልሰጠኝም፤ ማስቲካ እንዲሰጠኝ ጠየቅሁት፤ ሰዎች ጸሃይ ላይ የተቀመጠ ማስቲካ ስለማይገዙ ማስቲካ እንደማይዝ ነገረኝ።
የሆነ ነገር ሳልገዛው መሄድ ስላልፈለግኩ ጥያቄዬን ወደ ጥፍር መቁረጫ ቀየርኩ። አንስቶ ከመስጠት ይልቅ የምፈልገውን መርጬ እንድወስድ ነገረኝ። ለምን አንስቶ ሊሰጠኝ እንዳልቻለ ያደረገውን ጥቁር መነጽር አይቼ ጠርጥሬያለሁ።
በእርግጥም ጥርጣሬዬ ትክክል ነበር፤ ሰውየው አይነ ስውር ነው።አብዛኛውን ጊዜ አይኔ መመልከት የለመደው በየጎዳናው ላይ ህጻን ልጃቸውን አቅፈው የሚለምኑ ሰዎችን እንጂ ልጅ ይዘው የሚነግዱን አይደለም፤ ይህ ሰው ግን ህጻን ልጅ አቅፎ ከመነገዱ በተጨማሪ አይነ ስውር መሆኑም አስገርሞኛል።
ከሰውዬው ጋር ትንሽ እያወራሁ ቆየሁ ።አስቀድሜ ለስራ ያለውን ከብር በማድነቅ አይነ ስውር ሆኖ ስርቆት በበዛበት ከተማ ውስጥ ማንን ተማምኖ እቃ ዘርግቶ ለመሸጥ እንዳሰበ ጠየኩት።ከህይወት ገጠመኙ ቆንጠር እያደረገ የሰዎችን መልካምነትና ያደረጉለትን ጥሩ ነገር ያወጋኝ ጀመር።አዲስ አበባ ከመጣ ጊዜ ጀምሮ እየለመነም ቢሆን እያኖሩት የነበሩት ሰዎች ናቸው።ብዙ ቅንና መልካም ሰዎች እንዳሉ ነገረኝ።
አላፊ አግዳሚው ተባባሪ ነው።አካል ጉዳተኛ ሰርቶ ለመብላት ሲጥር የሚያበረታታው ብዙ ነው።ሁልጊዜ እጅ እየዘረጉ ከሰው መለመን ያሰለቻል፤ ያሸማቅቃልም።እየነገዱ መብላት ግን የተሻለ ነጻነት ይሰጣል፤ ለዚህነው ነግጄ መብላትን የመረጥኩት አለኝ።
ባለቤቱ በፔርሙዝ ሻይ ቡና እያዞረች በመሸጥ በአቅራቢያው እንደምትገኝ አወሳልኝ።በምትዟዟርባቸው ቦታዎች ሆና ከርቀት አሻግራ እየተመለከተች ሁኔታዎችን ትከታተላለች፤ አንዳንዴም ብቅ እያለች ልጇን አየት አድርጋ እንደምትሄድ አጫወተኝ። ባለቤቱ ልጇን በኦፕሬሽን ተገላግላ ከአንድ ወር በላይ ሳታርፍና በወጉ ሳትታረስ ነበር የጎዳና ላይ ስራዋን የጀመረችው።
እጄን ለልመና አልሰጥም ብሎ የሚታትረው አይነስውር በጎዳና ላይ ንግድ ህገ ወጥ ተብሎ እስከ አምስት ሺህ ብር የሚያወጣ ሸቀጡ እንደተወረሰበትና አሁንም ማስፈራሪያ እንደሚደርሰው ሲነግረኝ ደግሞ የበለጠ ልቤ ተሰበረ።
አንዳንዶች ህይወታቸውን ለመምራት በሚያስችል ምቹ ሁኔታ ውስጥ እየኖሩ ተግቶ ባለመስራት ወይም በስንፍና ምክንያት ከጉስቁልና ሕይወት ጋር ተስማምተው ይኖራሉ።ከራሳቸው አልፈው ለሰው ሸክምና ጠንቅ ይሆናሉ። ሌሎች ደግሞ በህይወት መንገዳቸው ከተደነቀሩባቸው ጋሬጣዎችና እንቅፋቶች ጋር ብርቱ ትግል እያደረጉ ኑሯቸውን ለመምራት ይጥራሉ፤ በዚያች በትንሿ ጎጇቸው ውስጥ የሚታየውን ጎዶሎ ለመሙላት ደፋ ቀና ይላሉ እንጂ እጃቸውን አይሰጡም። ይህም ሰው መሰናክል በበዛበት የህይወት ጎዳና ላይ ሆኖ ከገጠሙት ችግሮች ጋር እየተፋለመ ኑሮውን ለማሸነፍ የሚጥር በመሆኑ ታሪኩን ለማጋራት ወደድኩ።
ታረቀኝ ሞላ ይባላል።ገና በልጅነቱ የቤተሰቦቹን ትእዛዝ በመፈጸም ላይ ሳለ የግራ አይኑን እንጨት ይወጋውና ይጠፋል። ቶሎ ብሎ ወደ ህክምና ባለመሄዱ ምክንያት የግራ አይኑ መጎዳቱን ተከትሎ የቀኝ አይኑም ይዳከማል። በሁኔታው የተደናገጠው ታረቀኝ የህክምና እርዳታ ፍለጋ ከሀገሩ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት
በዳግማዊ ሚኒልክ ሆስፒታል ህክምና ይጀምራል።ከሀገር ቤት እየተመላለሰ ህክምናውን ለመከታተል የሚያስችል አቅም በማጣቱና የህክምና ቀጠሮውን ለማክበር እንዲመቸው በማሰብ አዲስ አበባ መቀመጥን ምርጫው ያደርጋል።አዲስ አበባ መኖር ሲጀምር ማረፊያ ቦታና ምግብ ሲቸግረው ጎዳና ላይ ማደርንና ልመናን መለማመድ ግድ ይሆንበታል።
ታረቀኝ ለሁለት ጊዜ ያህል የዓይን ቀዶ ጥገና ቢያደርግም ለውጥ ማግኘት አልቻለም።ጭራሽ የቀኝ አይኑም ከጥቅም ውጭ ሆነ።የአይኑን ብርሃን ሙሉ ለሙሉ ያጣው ታረቀኝ ለጊዜው ምድር ቁና ብትሆንበትም የህይወቱን አቅጣጫ ለመወሰን የተገደደው ከመቅጽበት ነበር። ወደ ሀገሩ ተመልሶ የቤተሰቡ ሸክም መሆን ወይም ህይወቱን በልመና መምራት አልፈለገም።
ከሰዎች ባገኛት ጥቂት ገንዘብ ሚዛን ገዝቶ መንገድ ዳር በመቀመጥ ክብደት እየመዘነ በሚያገኘው ገቢ ለመኖር ሞከረ።ይህም ቤት ተከራይቶ ለመኖር የሚያስችለው አልሆነም።ጎን ለጎን እንደ ጥፍር መቁረጫ፣ የፊት መስታወት፣ የጺም መላጫና የመሳሰሉትን ቁሳቁስ በመሸጥ አቅሙን ለማሳደግ ቢሞክርም አሁንም ኑሮ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ሆነበት።
‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ ›› እንዲሉ ታረቀኝ ረዳት የምትሆነውን የትዳር ጓደኛ በመፈለግ የህይወቱን መንገድ ማቅለል እንዳለበት ተሰማውና በሚሰራበት አካባቢ ቡናና ሻይ አፍልታ በፔርሙዝ እያዞረች ከምትሸጠው የዛሬዋ ባለቤቱ ዳሳሽ ተስፋ ጋር ተዋወቀ።ትውውቃቸው ትዳር አስከመመስረት ደረሰ። እንደርሱው ጥራ ግራ የመኖር ፍላጎት ያላት በመሆኗ ሰርቶ የመኖር ተስፋው ለመለመ።
ታረቀኝ አዲስ አቅም አገኘ። ትዳር መስርቶ፤ በሁለት ሺህ ብር አነስተኛ ቤት ተከራይቶ መኖር ጀመረ።አይነ ስውርነቱ ሳያሸንፈው፤ እንዳይናማዎቹ መርካቶ ሄዶ ሸቀጣ ሸቀጦችን እየገዛ በመሸጥ ንግዱን አሳደገ። ነግዶ መኖር ሲጀምር ለምኖ የኖረበት ጊዜ ያስቆጨው ጀመር። ባለቤቱ እርሱ በሚሰራበት አቅራቢያ ሆና በዋናነት ሻይ ቡናዋን እያዞረች በመሸጥ አንዳንዴም ብቅ ብላ እያገዘችው የጋራ ህይወታቸውን መምራት ቀጠሉ።
ታረቀኝና ዳሳሽ በትዳር ሶስት ዓመት ከቆዩ በኋላ የአብራካቸውን ክፋይ አገኙ።የባለቤቱ የወሊድ ወቅት ፈታኝ ክስተቶችን ያሳለፈበት መሆኑንም ይናገራል። ባለቤቱ ወልዳ በተኛችባቸው ጥቂት ጊዜያትም ቢሆንታረቀኝ ጫና በዝቶበት ነበር። ከመርካቶ እቃ እያመጣ በመሸጥ በሚያገኛት ገቢ ለሳምንታትም ቢሆን ባለቤቱን ሊያርሳት ቢሞክርም፤ ወትሮም ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ ስለነበር በታረቀኝ አቅም ብቻ የቤት ኪራይ፤ ምግብና ዳይፐር መሸፈን ሳይቻል ቀረ።
ልጇን በቀዶ ጥገና የተገላገለችው ባለቤቱ ቁስሏ ሳይጠግ፤ አንጀቷ ሳይጠናና ብዙም ሳትታረስ ወደ ስራዋ ለመመለስ ተገደደች። ለልጃቸው ሰራተኛ የመቅጠር አቅም የሌላቸው ጥንዶች ህጻኑን ይዘው ወደ ስራ ቦታቸው መሄድ ጀመሩ።ህጻኑ ሰውነቱ ሳይጠና አስፋልት ዳር ተኝቶ ጸሃይና ብርድ እንዲፈራረቁበት ተፈረደበት።
እንቅልፉ ሲመጣ እዚያው ይተኛል፤ ከእንቅልፉ ሲነቃም ታረቀኝ ያቅፈዋል።እነርሱ የሚበሉትን ይበላል፤ እነርሱ የሚጠጡትን ይጠጣል።እንደልጅ ወተት አያውቅም፤ አይቅበጠበጥም ፤ በማይመች ሁኔታ ውስጥ ውሎ ማታ ወደ ቤቱ ይገባል።
ታረቀኝ የሰባት ወር ህጻን ልጁን ታቅፎ ኑሮውን ለማሸነፍ ቀኑን ሙሉ አስፋልት ዳር እየቸረቸረ መኖሩ ባይከብደውም በህገ ወጥ ንግድ ምክንያት የሚደርስበትን በደል መቋቋም አለመቻሉን ይናገራል።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በዚህም ኑሮ ላይ የእለት ገቢውን የሚያስተጓጉሉ ፈተናዎች እየበረቱበት መምጣታቸው ያበሳጨዋል። ከሶስት ወር በፊትም ደንብ አስከባሪዎች ከአምስት ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ ሸቀጣ ሸቀጥ ወስደውበት እስከ አሁን እንዳልመለሱለት ይገልጻል።
የተወሰደበት ንብረት እንዲመለስለት ከወረዳ አስከ ክፍለ ከተማ ለሚመለከታቸው አካላት ቢያመለክትም ሰሚ አላገኘም።አካል ጉዳተኝነቱን አይቶ የሚራራለት ሰው አለማግኘቱ ያበሳጨዋል።ንብረቱ ከተወሰደበት በኋላ እጁ ላይ ባለችው ገንዘብ ሸቀጦችን ገዛዝቶ ለመስራት ቢሞክርም ደንብ አስከባሪዎች የስራ ፈቃድ ደብዳቤ ከሌለህ አትሰራም በማለት ያስነሱታል።
ቀበሌው የፈቃድ ደብዳቤ እንዲሰጠው ሲጠይቅ ደብዳቤ መስጠት አቁመናል የሚል ምላሽ በማግኘቱ ሳልበላ ከማድር የፈለጋቸውን ያደርጉኝ በሚል ዘርግቶ እየሸጠ መሆኑን ይናገራል።ከነገ ዛሬ ደንብ አስከባሪዎች መጥተው ሸቀጤን ይወስዱብኛል በሚል ስጋት ውስጥ እንዳለ ይናገራል።
ታረቀኝ የስራና የመኖሪያ ቦታ እንዲሰጠው ከአካል ጉዳተኞች ማህበር ያጻፈውን የድጋፍ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ ቤቶች ኤጀንሲ አቅርቦ ኢጀንሲው ለክፍለ ከተማው የአመልካቹ ጥያቄው በልዩ ሁኔታ እንዲስተናገድ የሚገልጽ የትብብር ደብዳቤ ጽፎለት እንደነበርም ገልጾልናል። ያም ሆኖ በተደጋጋሚ እየቀረበ አቤቱታውን ቢያሰማም ጥያቄውን የሚሰማ አካል አለመኖሩን በምሬት ይናገራል።
ሰዎች የሚሰጡት የሞራል ግንባታ በስራው ላይ የበለጠ መነቃቃትን እንደሚፈጥርለት የሚናገረው ታረቀኝ ከመንግስት አካላት የሚደርስበት ማሳደድ ግን የስራ ተነሳሽነቱንና ፍላጎቱን እየጎዳው እንዳለ ይገልጻል። በተለይም የክፍለ ከተማው ደንብ አስከባሪዎች እንደርሱ አይነት አካል ጉዳተኛን ማገዝና መርዳት ሲገባቸው በችግሩ ላይ ሌላ ችግር መፍጠራቸው እንዳሳዘነው ይናገራል።የሚመለከተው አካል የአካል ጉዳተኞችን ችግር በተለየ መንገድ ተረድቶ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባውም ያሳስባል።
የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ሰርቶ ለመኖር የሚያደርጉትን ጥረት ማገዝ ወይም በተለየ መንገድ ማስተናገድ ሲገባ ማሳደዱ ኢሰብዓዊ ከመሆኑም በላይ የተቀመጠውን የአካል ጉዳተኞች ህግ የሚጻረር መሆኑን ይናገራል።ታረቀኝ አካል ጉዳተኝነትን አስመልክቶ ኢትዮጵያ የተስማማችባቸው ዓለማቀፍ ህጎች እየተተገበሩ አለመሆኑንም ይገልጻል።
የአካል ጉዳተኞችን ጥቅም ለማረጋገጥ የወጡ ህጎች የማይተገበሩ ከሆነ ደግሞ አካል ጉዳተኞች ከሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ተለይተው ባይታዩ እንደሚሻል ይመርጣል።አካል ጉዳተኞች ከሰው ጥገኝነት ተላቀው፤ የእለት ጉርሳቸውንና ኑሯቸውን አሸንፈው ከመኖር አልፈው ቤተሰብ መስርተው ለመኖር የሚያደርጉትን መፍጨርጨር ማገዝ እና ማበረታታት ሲገባ ማሳደድና ማሸማቀቅ የተረጂዎችን ቁጥር ከማብዛት ውጭ ጥቅም አይኖረውም ይላል ታረቀኝ።
አንድ አካል ጉዳተኛ እራሱን ቻለ ማለት ቤተሰቡን፣ ህብረተሰቡንና መንግስትን አገዘ ማለት እንደሆነ የሚገልጸው ታረቀኝ በስራ ላይ ያሉ አካል ጉዳተኞችን ማበረታታት በየጎዳናው በልመና ስራ ላይ የተሰማሩትን ወደ ስራ እንዲገቡ ማነቃቃት እንደሆነም ያስረዳል።
ህይወቱ በፈተና የታጀበች እንደሆነች የሚናገረው ታረቀኝ የተሻለ ጊዜን የመናፈቅና ጠንክሮ የመስራት ህልሙ እንዳይጨናገፍበት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንዲተባበሩት ጥሪ ያቀርባል። በመንግስት ተቋማት የተጻፉለትን የትብብር ደብዳቤዎች እየተመለከቱ አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ አንዲያደርጉለትና በነጻነት ሰርቶ የሚበላበት ሁኔታ እንዲያመቻቹለት ታረቀኝ ባለድርሻ አካላትን ይማጸናል።
አዲስ ዘመን ጥር 22/2013