በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
ልብ ካላየ አይን አይፈርድም!
ልብ ካላየ አይን አይፈርድም ይባላል። ምሳሌያዊ አባባሉ ስለ ትኩረት የሚናገር ነው። ለአፍታ የጋዜጣ ንባባችንን ገታ አድርገን ዙሪያችንን ለመቃኘት እንሞክር። በዙሪያችን ብዙ ድምጽ እንዳለም እናስተውል።
በእርግጥም አለ። በዙሪያችን ላለው ድምጽ በሙሉ ምላሽ እንስጥ ብንል ምን ይፈጠር ይሆን? ቢያንስ ጊዜ እንደማይበቃን እንስማማ። በእውቁ ፈላስፋ ሶቅራጠስ እንጀምር። ፈላስፋው እንዲህ አለ”የለውጥ ሚስጥሩ ያለህን ሃይል በሙሉ ያለፈውን በመዋጋት ላይ ማተኮር ሳይሆን አዲስ በመገንባት ላይ ነው።” እንግሊዘኛው በቀጥታ እንዲህ ይላል “The secret of change is to focus all of your energy, not on fighting the old, but on building the new.” — Socrates
ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቲዎስ በጻፈለት ደብዳቤ በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢሆን፥ እንደሚገባ አድርጎ ባይታገል፥ የድሉን አክሊል አያገኝም። ሲል እንደሚገባ ስለ መታገል ያነሳል። እንደሚገባ የታገለው ከፍሬው ቀዳሚው ተቋዳሽ እንደሚሆን ሲያመላክት የሚደክመው ገበሬ ፍሬውን ከሚበሉት መጀመሪያ እንዲሆን ይገባዋል ይላል (2 ጢሞቲዎስ 2፡5-6)።
በተሰማራንበት ማንኛውም ዘርፍ ውስጥ ፍሬን መፈለጋችን እርግጥ ቢሆንም ይህ ግን ለሁሉም ሲሆን አይታይም። ምክንያቱ ብዙ ቢሆንም ትኩረት አለማድረግ ግን ከምክንያቶቹ መካከል ሊጠቀስ የሚችል ነው። ትኩረት በማድረግ ውስጥ የምንሰራውን ወደ ፍሬ መቀየር አለ። ትኩረት በማድረግ ውስጥ የድካማችን ፍሬው ተቋዳሽ ቀዳሚው እንሆናለን። ዛሬ ትኩረት ስለማድረግ እናነሳለን። የቴክኖሎጂ አብዮተኞችን እናስቀድም።
የቴክኖሎጂ አብዮተኞች
የኢንተርኔት ዘመን ሰላሳ አመት ገና በቅጡ አልሞላውም። ኢንተርኔትም ሆነ በጥቅሉ ቴክኖሎጂ መዘመን ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የቴክኖሎጂው ግለሰቦች የአለምን የሥራ፣ የፖለቲካ፣ የባህል፣ የማህበራዊ ህይወት መስተጋብር ወዘተ ቀያይረውታል ብንል ማጋነን አይሆንም። የቴክኖሎጂ አብዮተኛ ግለሰቦች ከሌሎች ሰዎች ከሚለዩበት አስተሳሰቦቻቸው ውስጥ ትኩረት ስለመስጠት ያላቸው ፍልስፍና አንዱ ነው፤ ምናልባትም ቀዳሚው። ማሳያ ከሚሆኑት ነገሮች መካከል አንዱን እናንሳ።
የአለባባስ ባህላቸውን። ሁልጊዜ አንድ አይነት ልብስ ለብሰው የሚታዩት የቴክኖሎጂ አብዮተኞች የሚናገሩት ቁምነገር ልብስ በማማረጥ ለምን ጊዜ እንፈጃለን የሚል ሆኖ እናገኘዋለን። ታላቁ የፈጠራ ሰው አልበርት አንስታይን፣ የአፕሉ ስቲቭ ጆብስ እና የፌስቡክ ማርክ ዙከርበርግ በግንባር ቀደምትነት በዚህ አስተሳሰባቸው የሚታወቁ ናቸው። የእኒህ የፈጠራ አብዮተኞች አስተሳሰብ በልብስ መረጣ ላይ አላስፈላጊ ጊዜን ማባከን ሆነ ትኩረትን መስጠት ተገቢ አይደለም የሚል ነው።
የተወሰነ ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው በማመን ውስጥ የደረሱበት የአለባበስ ስርዓት መሆኑ ነው። ስለ ትኩረት አንስተን ወደ ሌላኛው የቴክኖሎጂ አብዮተኛ የማይክሮሶፍቱ ቢል ጌትስ ዘንድ ብንሄድ የሚሰጠን ምላሽ የእኔ ስኬት በተወሰኑ ነገሮች ላይ በሚገባ ማተኮሬ ነው የሚል ሆኖ እናገኘዋለን (My success, part of it certainly, is that I have focused in on a few things.” — Bill Gates)።
ትኩረት ማድረግ ማለት
ትኩረት ማድረግ ማለት እቅድ ያደረግነው ነገር ወደ ውጤት እንዲደርስ በዙሪያችን ካሉ ልዩ ልዩ ነገሮች ሃይላችንንና ፍላጎታችን አቅበን ግብ ላደረግነው ነገር ላይ ማዋል ስንችል ነው። ትኩረት ማድረግ ትርጉሙ ሙሉ የሚሆነው ትኩረት ስላደረግነው ነገር የምንከፍለው ዋጋ (opportunity cost) ሲኖረን ነው።
መጽሐፍ መጻፍ ትኩረት ያደረገ ሰው መጽሐፉን ዳር ለማድረስ የሚመድበው ጊዜ ለሌላ ስራ ሊያውል የነበረውን ጊዜ ወስዶ ከሆነ ትኩረት በማድረግ ውስጥ የተጻፈ መጽሐፍ እንደሆነ እንረዳለን። የምንሰራው ስራ አጥተን በተረፈን ጊዜ የምንጽፈው መጽሐፍ ግን ትኩረት የማድረግ ምሳሌ ላይሆን ይችላል። ትኩረት ማድረግ ከሌሎች ነገሮች አስቀድመን በቀዳሚነት የምናስቀድመው ነገር ስለሆነ።
በዙሪያችን ያሉ ነገሮች ትኩረታችንን ስለፈለጉ ብቻ ትኩረት የምናደርግባቸው ናቸው ማለት አይደለም። ውጫዊ ድምጽ በአንድም በሌላም መንገድ ትኩረታችንን የሚስብ ሆኖ ወደ እኛ ሊቀርብ ይችላል። አንዳንዴ ትኩረት የሚስብ ድጋፍ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ትኩረት የሚስብ ተቃውሞ። ሁለቱም ትኩረታችን ፈላጊ እንጂ ትኩረታችን ሊሆኑ አይችሉም። ትኩረታችን መሆን ያለበት በእቅዳችን ውስጥ ልናሳካው የምንሄድበት ጉዳይ ነው። ትኩረት የማድረግ ትርጉምን በሚገባ ስንረዳ ትኩረት ማድረግ ባለብን ጉዳይ ላይ ትኩረት በማድረግ ትኩረት የማድረግን ፍሬ የምናገኝ እንሆናለን።
ትኩረት ማድረግ ያለብን ምን ላይ ነው?
ሁልጊዜ በተመሳሳይ ነገር ላይ ትኩረት ልናደርግ አንችልም። ነገርግን በግልም፣ በቤተሰብም፣ በሥራም ሆነ በማህበራዊ ህይወት ውስጥ ውጤታማ ለመሆን ትኩረት ማድረግ ያሉብን ነገሮች አሉ።
1. በግል ሕይወት ውስጥ ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮች፣
እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱ የሆነ ጠንካራና ደካማ የሆነ ጎን አለው። በየትኛውም የህይወታችን ክፍል ውስጥ የሚመነዘረው ግላዊ ጥንካሬያችንና ድክመታችን ነው። ራሳችንን በተመለከትን ጊዜ ግብ የምናደርገው ፍሬያማ የሆነ ግለሰብ መሆን በመሆኑ ለፍሬያማነት ጠንካራ ጎናችንን ማሳደግ እንዲሁም ደካማ ጎናችንን መቀነስ አስፈላጊ ነው። እውቁ ጸሃፊና ተናጋሪ ማእክስ ዌል ስለ ትኩረት ሲጽፉ የሚጠቀሙበት 70%፡25%፡5% የሚል ቀመር አላቸው። በእዚህ ቀመር መሰረት 70% ትኩረትን በጥንካሬ ላይ፤ 25% ትኩረትን በአዳዲስ ነገሮች ላይ እና 5% ትኩረትን በደካማ ጎናችን ላይ ማድረግ እንዳለብን የሚመክር ቀመር ነው።
70% ትኩረትን ጥንካሬ ላይ ማድረግ፣
ውጤታማ መሪዎች ብዙዎች ጊዚያቸው በእነርሱ ጥንካሬ ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። የሥነ-አመራር አስተማሪው ፒተር ድራከር ታላቁ ተቃርኖ ሰዎች ነገሮችን በመጥፎ መንገድ መስራታቸው ሳይሆን አልፎ አልፎም ቢሆን በጥሩ ሁኔታ የሚሰሩበት አግባብ መኖሩ ነው። ብቃት ማነስ በሁሉም ቦታዎች ላይ የሚገኝ ነው።
ጥንካሬ በግልጽነት መለየትና መታወቅ የሚችል ነው። በአንድ ነገር ጠንካራ አቅም ያለው ሰው በሌላ ነገር የግድ አቅም አለው ማለት የሚቻል አይደለምና በማለት ተናግሯል። ውጤታማ ለመሆን ከፈለግህ በጥንካሬህ ላይ አተኩር እርሱንም አሳድግ። ጊዜህን፣ ሃይልህን፣ እና ሃብትህን ጥንካሬህ ላይ በዋናነት አውለው።
25% ትኩረትህን በአዳዲስ ነገሮች ላይ ማድረግ፣
እድገት ከ ለውጥ ጋር እኩያ ነው። እየተሻሻልክ መሄድን የምታስብ ከሆነ መለወጥን እና ነገሮችን እያሻሻልክ መሄድ አለብህ። አዳዲስ ነገሮችህ ከጥንካሬህ ጋር የተገናኙ ይሁን። ለምሳሌ አንድ ስፖርተኛ የእርሱ ጥንካሬ በሆነው ነገር ላይ ምን አዲስ ነገር ለመጨመር ትኩረት ማድረግ አለበት? ይህን ነው 25% ትኩረትህን በአዳዲስ ነገሮች ላይ ማድረግ የምንለው። ጊዜህን ከጥንካሬህ ጋር በሚሄዱ አዳዲስ ነገሮች ላይ የምታተኩር ከሆነ እንደ መሪ እንድታድግ ያደርግሃል። በመሪነት ህይወትህ ውስጥ እድገት በአዳዲስ ነገሮች ውስጥ መሆናቸውን ልብ በል።
5% ትኩረትን በድክመት ላይ ማድረግ፣
ማንኛውም ሰው ድክመቱ ላይ ፈጽሞውኑ ከመስራት ሊቀርለት አይችልም፤ ድክመት ሁሉም ሰው ውስጥ የሚገኝ ስለሆነ። በዙሪያችን ያሉ ሰዎችን በስራዎች ላይ መወከል በመቻል የእኛ ድክመት የምንመራውን ስራ እንዳይጎዳ ልናደርግ ይገባል። አንድ የመድረክ ላይ ተጽእኖ ፈጣሪ ተናጋሪ የእርሱ ጥንካሬ መድረክ ላይ ተገኝቶ አስተማሪና አነቃቂ ንግግርን ማድረግ ነው።
ይህ ከሆነ ትኩረቱን በሚያደርገው ንግግር ላይ ከማድረግ ባሻገር በሌሎች ስራዎች ማለትም የአውሮፕላን ትኬት መቁረጥ፣ የመድረክ ዝግጅት፣ የሰዎች ጥሪ ወዘተ ስራዎች ውስጥ እራሱን ሙሉ ለሙሉ ጨምሮ መገኘት ውጤታማ አያደርገውም። በመሆኑም እኒህ አቅጣጫዎች የእርሱ የድክመት አቅጣጫዎች ተደርጎ የእርሱን ጊዜም ሆነ አቅም መውሰድ ያለባቸው 5% ትኩረት መሆን አለበት ማለት ነው። ሌሎች ሰዎችን ለእኒህ ስራዎች በመወከል ስራው እንዲሰራ ማድረግ ግን አስፈላጊ ነው።
2. በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ነገሮች፣
ከእዚህ ቀደም ፍቅር- የቤተሰብ መልህቅ የሚል ጽሁፍ በእዚሁ አምድ ላይ ታትሟል። አንድ ግለሰብ ከግለሰባዊ ሕይወቱ ቀጥሎ የሚያገኘው የቅርቡ ሕይወት ቤተሰብ በመሆኑ በቤተሰብ ውስጥ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ትኩረት ካልተሰጠው ተጽእኖው ቀላል አይደለም ብቻ ሳይሆን ለውስብስብ መጠላለፍ የሚዳርግ ነው። ቤተሰባዊ ሕይወት አደጋ ውስጥ በሚገባበት ጊዜ የሚፈጠረው ቀውስ ማህበራዊም ይባል ሀገራዊ አስከትሎት የሚመጣው ሰቆቃ አስከፊ ነው።
ማህበረሰብ ተረጋግቶ እንዲኖር የተረጋጋ ቤተሰብ አስፋላጊ ነው። በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ደግሞ ፍቅር ትልቅ ትርጉም አለው። ከጾታዊ ግንኙነት ያለፈ ሃላፊነትን ለመወጣት በመጣር ውስጥ የሚገለጥ ፍቅር የቤተሰብ መልህቅ ነው። ትኩረት መደረግ ባለበት ጉዳይ ላይ ትኩረት ስናደርግ በቤተሰብ ውስጥ ሊኖር የሚገባው ጥብቅ ቁርኝትን የሚቀድም ቤተሰባዊ አጀንዳ ሊኖር አይችልም።
3. በሥራ ሕይወት ውስጥ ትኩረትን የሚፈልጉ ነገሮች፣
በሥራ ሕይወት ውስጥ ዙሪያ ሊኖር ስለሚገባ ትኩረት ስናስብ ቁልፉ ሁለት ነገሮችን ማድረግ ይገባል። ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ መስጠት (Priorities) እና ቀልብን-መሰብሰብ መቻል (concentration) ነው። ቅድሚያ መስጠት የሚገባውን የሚያውቅ ነገር ግን ቀልቡን ሰብስቦ ከእዚያ አንጻር መስራት ያልቻለ ግለሰብ ምን መስራት እንዳለበት ያወቀ ግን ደግሞ መስራት ያልቻለ ማለት ነው።
በተቃራኒው ደግሞ ትኩረቱን መሰብሰብ የሚችል ነገር ግን ቅድሚያ የሚሰጠውን መለየት ያልቻለ ከሆነ ልቀት ያለው ግለሰብ ነገር ግን እድገት የሌለው ነው የሚሆነው። ነገር ግን ሁለቱን አጣምሮ መሄድ የሚችል ከሆነ ትልልቅ ነገሮችን ማሳካት የሚችል ይሆናል።
በአመራር ቦታ ላይ ያሉ ግለሰቦች ቦታቸው በአመራርነት ቢሆንም ጥቃቅን የሚባሉ ጉዳዮችን ዋና ጉዳይ አድርገው በጥቃቅን ጉዳዮች ተጠምደው የሚውሉ ሰዎች ብዙ ጊዜ ይታያሉ። በጨዋታ ውስጥ የእርሱ ትልቁ ችሎታ ያለው ኳስ መቀማት ላይ ሳይሆን ኳስን መምታት ላይ የሆነ ተጫዋች ኳስ መቀማት ላይ አተኩሮ ቢውል እንደማለት ነው።
4. በማህበረሰባዊ ሕይወት ውስጥ ትኩረትን የሚፈልጉ ነገሮች፣
ስምምነት ያለው ትርክት እንደ ማህበረሰብ መኖር ያለውን አስፈላጊነት ለመረዳት ኢትዮጵያን መመልከት የሚመከር ይመስላል። ውድ የሆነውን ጊዜያችንን በመበሻሸቅና አንዳችን በሌላችን ላይ የበላይነትን ለማሳደር በሚሻ ጉንጭ አልፋ ክርክር ውስጥ እንድንገኝ ያደረገን ማህበረሰባዊ ትርክታችን ውስጥ ያለው ዝንፈት ነው።
ማህበረሰባዊ ትርክትን ተመሳሳይ ማድረግ ባይቻል እንኳን ማቀራረብ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን እንረዳለን። አንድ የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ማህበረሰብ በአንድ ልብ በመተንፈስ ግብ ወደሚያደርገው በሰላምና በእድገት ውስጥ የመኖር ደረጃ ላይ ለመድረስ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባውን መለየት ተገቢ ነው።
እኔ እያንዳንዱን ሰው በአምላክ ፊት ልዩና ውብ ፍጡር ሆኖ እንደሚታይ ለሚያምን ግለሰብ የትርክት መዛነፍ የሰውን ዋጋ አሳንሶ ስመለከት ትኩረት ለሚገባው ትኩረት ስለመስጠት ሳነሳ ይህን በፍጹም ልዘለው አልችልም።
ማህበረሰባዊ ሕይወት ውስጥ የትርክት መቀራረብ፣ የሥራ ባህል፣ የጊዜ ባህል፣ የሰው ዋጋ፣ ታላላቆችን ማክበር፣ ለተጎዱ ደጀን መሆን ወዘተ ያሉ እሴቶች በበዓል ሰሞን የምንተገብራቸው ወቅታዊ ጉዳዮች ሳይሆኑ የእለት ተእለት ህይወታችን መገለጫ መሆን አለባቸው።እንዲጎለብቱ ደግሞ ትኩረት ሊደረግባቸው በሚገቡ ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ላይ ይጠቀሳሉ።
መነሻውና መድረሻው፣
በቤተሰብም፣ በሥራም ሆነ በማህበረሰባዊ ሕይወት ውስጥ ትኩረት ሊደረግ የሚገባውን ጉዳይ ትኩረት በማድረግ ውስጥ ለውጥን ማምጣት ሲታሰብ መነሻው ግለሰብ ነው። በቤተሰብም፣ በሥራም ሆነ በማህበረሰብ ውስጥም እንዲሁ ትኩረት የሚሻው አካል ያው ግለሰብ ሆኖ እናገኛለን።
ግለሰባዊ የትኩረት ማድረግ ጥንካሬ በቤተሰብ፣ በሥራና ማህበረሰብ ውስጥ የሚታይ በመሆኑ ማጠቃለያችንን የጆን ማእክስዌልን የትኩረት ማድረግ የተግባር እርምጃ ምክር ለአንባቢው በማድረስ ይሁን።
• አንባቢ ሆይ ግለሰባዊ ጥንካሬህን ተመልከት- በምትሰራው ስራ ውስጥ አንተ በተሻለ ሁኔታ ልትሰራቸው የምትችላቸውን ሦስት ወይንም አራት ነገሮችን ለይተህ ጻፍ። የዘረዘርካቸው ነገሮች ላይ የጊዜህን ምን ያህል ሰዓት ታጠፋለህ? ያለህን ሃብት ምን ያህሉን በዘረዘርካቸው ጥንካሬዎችህ ላይ ታጠፋለህ? 70% ጊዜህን በጥንካሬህ ላይ ማድረግ እንድትችል የሚረዳ እቅድ ይኑርህ። ይህን ማድረግ የማትችል ከሆነ ስለ ስራህ ዳግም ማሰብ ያለብህ ጊዜ ሊሆን ይችላልና ምክሬ እነሆ።
• አንባቢ ሆይ ድክመቶችህ ላይ አሰልፍ – በምትሰራው ስራ ውስጥ በአግባቡ ልትሰራቸው ያልቻልካቸውን ሦስት ወይንም አራት ነገሮችን ለይተህ ጻፍ። እኒህን ስራዎች ለሌሎች ለመወከል ምን ማድረግ እንዳለብህ ወስን። እኒህን ለማድረግ ሰራተኛ መቅጠር ይኖርብህ ይሆን? አብሮህ የሚሰራ ሸሪክ መፈለግስ ያስፈልግህ ይሆን? እቅድ አዘጋጅለት።
• አንባቢ ሆይ መንገዱን ፍጠር – አሁን ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ ስለመስጠት እና ቀልብን ሰብስቦ ስለመስራት ተረድተናል። ወደ ጥንካሬህ የሚቀጥለው ምእራፍ ለመሄድ ምን ማድረግ ያስፈልግሃል? ምን አዲስ መሳሪያ መጠቀም ይኖርብሃል? ነገሮችን እንዴት እንደምትሰራና የተሻለ አድርገህ ለመስራት መስዋእት ማድረግ ያለብህን ለማቅረብ አስብ። ጊዜ እና ገንዘብን አውጥተህ ወደ ቀጣዩ ደረጃ መውጣት የሚያስችልህ ከሆነ እርሱ ትክክለኛ ኢንቨስትመንት ነውና መንገዱን ፈልግ።
ትኩረትን በትኩረት መፈለግ በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በሥራ እንዲሁም በማህበረሰባዊ ሕይወታችን ውስጥ የሚጠይቅ በመሆኑ ልብ ካላየ አይን አይፈርድም አልን።
አዲስ ዘመን ጥር 22/2013