ጌትነት ምህረቴ
በቅርቡ በእነ አቶ ጃዋር መሃመድ ላይ ከቀረቡ ተደራራቢ አስር ክሶች ስድስቱ እንዲቋረጡ ፍርድ ቤት ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል::እነዚህ ግለሰቦች የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ፤ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ፤ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ የመተላለፍ ክሶች ከተመሰረቱባቸው ክሶች መካከል ሲሆኑ፣ በፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲቋረጡ የተደረጉት ክሶች ከጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ጋር የተያያዙ መሆናቸውም ይፋ ተደርጓል።
ፍርድ ቤቱ ጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም በነበረው ችሎት፣ አቃቤ ሕግ ክሶቹን አሻሽሎ እንዲያቀርብ ማዘዙ ይታወሳል። ነገር ግን አቃቤ ሕግ ሌሎቹን ክሶች እንዳሻሻለ ገልጾ፣ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ መሰረት በማድረግ የተከፈቱትን ክሶችን ግን ማሻሻል እንደማይፈልግ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
ፍርድ ቤቱም፤ክሶቹ በተጠቀሰው አዋጅ ስር መታየት እንደማይችሉ በመጥቀስ፣ ስድስቱ ክሶች እንዲቋረጡ ውሳኔ አስተላልፏል።ከዚህ አኳያ ክሶች በፍርድ ቤት እንዴት ሊቋረጡ እንደሚችሉ በፌዴራል ማናቸውም ፍርድ ቤት ጠበቃና የህግ አማካሪ አቶ ቁምላቸው ባልቻ ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጠይቀናቸዋል::
እሳቸው እንደሚሉት በፍርድ ቤት ክሶች እንዴት ሊቋረጡ ይችላሉ የሚለውን በዝርዝር ለማስረዳት መዝገቦችን ማየት ያስፈልጋል::ሆኖም በአጠቃላይ ክስ ማቋረጥ ማለት ምን እንደሆነ መረዳት ይገባል:: በከሳሽም ሆነ በተከሳሽ ወገን የክስ መቃዋሚያ ከቀረበ በኋላ ፍርድ ቤቱ መቃወሚያውን መሰረት አድርጎ የተወሰኑ ክሶችን ሊያቋርጥ የሚችልባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ በህጉ ተቀምጠዋል::
ለምሳሌ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነ ስርዓት ቁጥር 122 ብናይ ከባድ የግፍ አገዳደል ወይም ከባድ የውንብድና ተግባር ወንጀል ካልሆነ በስተቀር በተከሳሹ ላይ የሚቀርብ ማንኛውም ክስ በፍርድ ቤቱ በሚሰማበት ወቅት ወይንም በክርክርም ጊዜ ክስ እንዲነሳ አቃቤ ህግ ማቅረብ ይችላል::ከእነዚህ ሁለት ወንጀሎች በስተቀር አቃቤ ህግ ክሱ እንዲነሳ አቤቱታ ለፍርድ ቤት ማንኛውም ጊዜ ማቅረብ ይችላል ይላሉ::
ምክንያቱም ክሱ እንዲነሳ በመንግሥት ታዝዣለው ሊል እንደሚችል ይጠቅሳሉ::ይህ የሚሆነው በአቃቤ ህግ አነሳሽነት ክስ ሲነሳ ነው::የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ስነ ስርዓት ቁጥር 122 መሰረት ፍርድ ቤቱ እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲያጋጥመው ክሱን ለማቋረጥ ሆነ ላለማቋረጥ ለሚሰጠው ውሳኔ ምክንያቱን በግልጽ ማስቀመጥ አለበት ባይ ናቸው::
ሌላው በወንጀል ህግ ቁጥር 130 ደግሞ ተከሳሾች በጠበቆቻቸው በኩል ወይንም ራሳቸው የሚያቀርቡት የክስ መቃወሚያ እንዳለ ይገልጻሉ::እነዚህ መቃወሚያዎች በግልጸ ህጉ ላይ ተቀምጠዋል::ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ከዚህ ቀደም ተከሶ ነጻ የወጣ፣ወይንም የጥፋተኝነት ውሳኔ የተሰጠ ከሆነ መቃወሚያ ሊቀርብ ይችላል::ሁለተኛ የቀረበው ክስ በይርጋ የታገደ፣ምህረት የተደረገበት ሲሆን ነው::
ለምሳሌ ክሱን ለማቅረብ በህጉ መሠረት ፍቃድ ያልተሰጠ መሆኑን፤ ለፈጸማቸው ተግባሮች ኃላፊ ያለመሆኑን እነዚህ መቃወሚያዎች ቀርበው ፍርድ ቤቱ እነዚህን መቃወሚያዎች መርምሮ ክስ ይቋረጥ የሚል ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል::ሦስተኛ በርካታ ወንጀሎች ተያይዘው ቀርበው ከሆነ በእያንዳንዱ ላይ መቃወሚያዎች ቀርበው ፍርድ ቤት መርምሮ የተወሰኑ ክሶችን ሊያቋርጥ ይችላል ሲሉ ክስ ሊቋረጥ የሚችሉባቸውን ህጋዊ መሠረቶች አቶ ቁምላቸው አብራርተዋል::
ስለዚህ ፍርድ ቤቶች በእነዚህ ሦስትና ሎሎች ምክንያቶች ነው ክሶችን ማቋረጥ የሚችሉት ይላሉ::ከዚህ ውጭ ግን ህጉ ላይ በግልጽ የተቀመጡ ነገሮች ባይኖሩም ፍርድ ቤቶች አቃቤ ህግ የወንጀል ክስ አቅርቦ በሚከስበት ጊዜ ፍርድ ቤቶች ትኩረት የሚሰጡባቸው ሁለት
ጉዳዮች አሉ:: አንደኛ በህገ መንግሥቱና በወንጀል ህጉ ላይ የተቀመጡ የሰብዓዊ መብት መርሆዎች ለማስከበር የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ያሟሉ ወይም ያላሟሉ መሆኑን መመርመር አለባቸው::እነዚህም አንዱ ክስ መጣያዎች መሆናቸውን አስረድተዋል::
ለምሳሌ አሉ አቶ ቁምላቸው በህገ መንግስቱን አንቀጽ 5/ንዑስ አንቀጽ 2፣አንቀጽ 13/1፣አንቀጽ 22/1 የወንጀል ህጉን 414/96፣ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች የቃል ኪዳን ስምምነትን በሙሉ አይተው ነው አቃቤ ህግ ያቀረበው የወንጀል ክስ አግባብ ነው ወይንስ አይደለም ብለው ብይን መስጠት የሚኖርባቸው ብለዋል::
ስለዚህ በፍርድ ቤት ክሶች የሚቋረጡባቸው ጉዳዮች ሰፊ ናቸው::በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ ላይ ወንጀል ናቸው ተብለው ያልተቀመጡ ነገሮች ወንጀለኛ አያስብሉም::ለምሳሌ አንድ ግለሰብ ወንጀል ፈጸሞ ግን ወንጀሉ በህጉ ውስጥ ያልተካተተ ከሆነ በህግ አያስከስስም ፤በህግም አያስቀጣም::
ለአብነት ያህል በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ ውስጥ መስረቅ የሚል ነገር ባይኖር የሰረቀ ሰው ፍርድ ቤት ብታቀርብ በህግ ሊያስከስስም፤ሊቀጣም አይችልም::ምክንያቱም መስረቅ የሚለው ነገር ህጉ ወስጥ ባለመኖሩ ነው ::
ስለዚህ ተደራራቢ ክሶች አነ አቶ ጅዋር ላይ ቀረቡ እነዚያ ውስጥ ግን በዚህ ወንጀል ህጉ ውስጥ የማይሸፈኑ ካሉ ክሶቹ ሊቋረጡ ይችላሉ:: እናም ፍርድ ቤቱ እነዚህ ክሶችን ያስወጣል:: ምክንያቱም በህግ ሊያስከስሱ ባለመቻላቸው ነው::
እነዚህ ክሶች ህጉ ውስጥ መቀመጥ አለባቸው እንጂ በማመሳሰል ክሱ ውስጥ መክተት አይቻለም::ለምሳሌ ውንብድና በህጉ ውስጥ ወንጀል ተብሎ ካልተቀመጠ መስረቅ ህጉ ውስጥ ስላለ ውንብድናም ያው መስረቅ ነው ብለህ ክስ ልትመሰርት አትችልም ሲሉ አስረድተዋል::
ስለዚህ በህጉ የወንጀል ተግባሮች በግልጽ መቀመጥ አለባቸው::በወንጀል ህጉ ውጭ የሆኑ የክስ ጉዳዮች ካሉ ህግ አውጭው እነዚህን ወንጀሎችን ጨምሮ የማሻሻያ ህግ ማውጣት አለበት:: ይህ ባልሆነበት ሁኔታ በማመሳሳል ክስ ውስጥ ማካተት አይቻልም የሚሉት የህግ ምሁሩ አቶ ቁምላቸው ናቸው::
ተደራራቢ ሆነ ተደጋጋሚ ክሶች ሊቀርቡ የሚችሉት በአቃቤ ህግ ክፍተት መሆኑን የሚገልጹት አቶ ቁምላቸው አቃቤ ህግ ክስ ሲመሰርት እውነት እነዚህ ወንጀሎች በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ ውስጥ ተካተዋል ወይስ አልተካተቱም የሚለውን በግልጽ መለየት አለበት:: ስለዚህ በዝርዝር እነዚህ ጉዳዮች ቢታዩ የክስ መቋረጥ ሁኔታ ሊያጋጥሙ አይችሉም ነው ያሉት::
ስለዚህ የዚህ አይነት ችግር እንዳያጋጥም አቃቤ ህግ ጥርት ያለ ክስ ማቅረብ አለበት የሚል ሀሳብ አላቸው:: በተለይ ወንጀል ናቸው ብሎ ለፍርድ ቤት ክሶችን ሲያቀርብ በህጉ ላይ እያንዳንዱ ፍሬ ነገር አለ ወይ ወይንስ የለም የሚለውን በጥልቀት ማየት ይጠበቅበታል እንጂ በማመሳሰል የወንጀል ክስን መመሰረት አይቻልም ይላሉ::
እንደዚህ አይነት ችግር ሊከሰት የሚችለው በሁለት መልኩ ነው የሚሉት አቶ ቁምላቸው አንዱ ከሙያ ክፍት የሚመነጭ ሲሆን ሌላው ሆንተብሎ ሊሆን ይችላል ብለዋል::ተደራራቢ ክሶችን ፍርድ ቤት እነዚህ ክሶች አግባብነት የሌላቸው ናቸው ብሎ እስኪያቋርጥ ድረስ ሰዎች ይጉላላሉ::
ሰዎች ከህግ ውጭ ይታሰራሉ፤የዋስትና መብታቸው ይከለከላል:: እነዚህ ክፍተቶች ደግሞ ተከሳሶችም ሆነ አጠቃላይ ህብረተሰቡ በህጉ ላይ ያላቸው እምነት እየተሸረሸረ ይመጣል :: ስለዚህ አቃቤ ህግ ክሶች ሲያዘጋጅና ክስ ከመመስረቱ በፊት በተቻለ መጠን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል::በተለይ ዋስትናን የሚከለክሉ ወንጀሎች ላይ ክሶች ሲመሰረቱ በጣም ጥንቃቄ ያስፈልጋል ሲሉ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል::
በእነ አቶ ጃዋር መሃመድ ላይ ከቀረቡ ተደራራቢ አሥር ክሶች ስድስቱ እንዲቋረጡ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሲያስተላልፍ የቀሩት አራት ክሶች “ብሔርንና ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት በመቀስቀስ፣ አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ እንዲነሳሳ በማድረግ፣ የፀረ ሽብር አዋጅና የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጅን የሚመለከቱ መሆናቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ጥር 21/2013