ኢትዮጵያ በጥንታዊነቷ፤ ባላት ሰፊ የህዝብ ቁጥርና ካላት መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ አቅም አንጻር በምስራቅ አፍሪካ ወሳኝ ድርሻ ያላት ሀገር ነች:: ሀገሪቱ በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ ሀገራትም ጋር ባላት የኢኮኖሚ፤ ባህል፤ የሃይማኖትና የፖለቲካ ግንኙነትና ትስስር ምክንያት የቀጠናው የስበት ማዕከል ተደርጋ ትወሰዳለች:: ከኢትዮጵያ ጋር የሚዋሰኑ የጎረቤት ሀገራት በሙሉ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከኢትዮጵያ ጋር ዘመናትን የተሻገረ ጥብቅ የትስስር ታሪክ አላቸው::
በዚህ ረገድ በተለይ ከሱዳን ጋር ያለው ግንኙነት ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረና በተለያዩ ትስስሮሽ የተዋሃደ ነው:: ኢትዮጵያና ሱዳን ከኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ግንኙነታቸው ባሻገር በታሪክ፤ በባህልና በኃይማኖት ዘመናትን የተሻገረ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው::
ይህንኑ ሀቅ በመረዳትም ኢትዮጵያ በችግሮቿ ጊዜ ሁሉ ከሱዳን ጎን ቆማ መከራዋን ስትካፈላትና ለመፍትሄ ስትሰራ ቆይታለች:: ሱዳን ለ30 ዓመታት በቆየችባቸው የጦርነት ዓመታት በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን በማስጠለልና ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ ችግራቸውን ለመካፈል ጥረት አድርጋለች::
ሱዳንን ለ30 ዓመታት የመሩት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላም አጣብቂኝ ውስጥ ገብታ በህዝባዊ አመጽ ስትታመስ በቆየችባቸው ጊዜያት ኢትዮጵያ ከጎኗ አልተለየቻትም::
እንዲያውም የሱዳንን ጉዳይ ጉዳዬ ብላ በጠቅላይ ሚነስትር ዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነት ተወዛጋቢ ወገኖችን ወደ ስምምነት የሚያመጣ ሃሳብ ቀይሳ የሽግግር መንግሥት ተቋቁሞ አንጻራዊ ሰላም ሊሰፍን ችሏል::
በሽግግር መንግሥቱ ውስጥ ማን አብላጫ ወንበር ይያዝ የሚል ክርክር ተነስቶበት ወደለየለት ሁከት ለመግባት አፋፍ ላይ በደረሰችበትም ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባደረጉት እልህ አስጨራሽ የሽምግልና ጥረት ሲቪሎች አብላጫውን ይዘው ካውንስሉ እንዲመሰረትና ሰላም እንዲሰፍን ኢትዮጵያ የየበኩሏን ወሳኝ ሚና ተጫውታለች:: የሽግግሩ መንግሥት በሁለት እግሩ እንዲቆምምየሰብዓዊ እገዛዎችን ጭምር ስታደርግ ቆይታለች::
ኢትዮጵያ ለሱዳን በብዙ መልኩ የችግሯ ጊዜ ደራሽ ብትሆንም አሁን አሁን ከሱዳን በኩል የሚታየው ጠብ ጫሪነት የኢትዮጵያን ውለታ እና የየሁለቱን ሀገራት የቆየ ወንድማማችነት የሚመጥን አይደለም:: ሀገራቱ ከቅኝ ገዥዎች ጋር ተያይዞ የተፈጠረ እና ለ100 ዓመታት ሲንከባለል የመጣ የድንበር ማካለል ችግር እንዳለባቸው ቢታወቅም ችግሩ የሚፈታው ግን ሱዳን እየሄደችበት ባለው መንገድ ሊሆን አይችልም::
የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ በርካታ የእርሻ መሬቶችን በመቆጣጠርና ዝርፊያዎችን በመፈጸም፣ እንዲሁም አርሶ አደሮችን በማሰቃየት ላይ ይገኛል:: የሱዳን ጦር የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የነበሩበትን አል ፋሻጋ የተባለውን ሥፍራ በመውረርም በነዋሪዎች ላይ ጥቃት ፈጽሟል:: ይህ ሁሉ ሆኖ ግን አሁንም የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ሰላማዊ መፍትሄን አስቀድመዋል::
በተቃራኒ ግን ሱዳን ባልተረጋጋ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ትገኛለች:: የዳርፉር ቀውስ እየተባባሰና በቀውሱም በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ህይወታቸውን እያጡ ነው:: የዳርፉር ጉዳይ ሁነኛ መፍትሄ ካልተሰጠውም ሱዳንን ዘላቂ ወደ ሆነ አለመረጋጋትና መፈራረስ ሊወስዳት እንደሚችል ጉዳዩን ያጠኑ ምሁራን በመናገር ላይ ይገኛሉ:: በሌላም በኩል በነዳጅ ዘይት በበለጸገችው የአብዬ ግዛት ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለው ውጥረት አሁንም አልረገበም::
ከግብጽ ጋር ያለው የድንበር ይገባኛል ውዝግብ አሁንም በእንጥልጥል ላይ ያለ ጉዳይ ነው:: ከደቡብ ሱዳንም ጋር በድንበር አለመግባባት እሰጥ እገባዎች ይሰማሉ:: ከሁሉም በላይ ደግሞ በሀገሪቱ የተቋቋመው የሽግግር መንግሥት ተለውጦ ቋሚ መንግሥት እስኪመሠረት ሀገሪቱ ባለመረጋጋት ውስጥ መቆየቷ አይቀሬ ነው::
የሽግግር መንግሥቱ በተቻለ መጠን ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ አረጋግቶ የሕዝቡንም ጥያቄ መመለስ ቀዳሚው ሥራ ሊሆን ይገባል:: ካልሆነ ግን ያሉትን ውስብስብ ችግሮች ለማረሳሳትና አቅጣጫ ለማስቀየር በሚል ወይም ጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት ሲባል በሦስተኛ ወገን ግፊት የኢትዮጵያን ድንበር መውረሩ ሱዳንን ወደ ከፋ ችግር ከማስገባት የዘለለ ፋይዳ የለውም::
ስለሆነም ላለፈው አንድ ምዕተ ዓመት የቆየውን የሁለቱን ሀገራት ድንበር ውዝግብ በዘላቂነት ለመፍታት ምክክርንና ውይይትን በማስቀደም እና ልዩ የጋራ ኮሚቴ በማዋቀር በሁለቱም አገራት ተቀባይነት ያለው የመፍትሔ ሃሳብ ማምጣት ግድ ነው::
ከዚያ ውጭ ያለውና አሁን ሱዳን እየሄደችበት ያለው መንገድ ሱዳንን ወደ ከፋ ችግር ውስጥ የሚከት ከመሆኑም በላይ የሁለቱን ሀገራት የቆየ ወዳጅነትም ለዘለቄታው የሚያበለሽ ነውና የሱዳን የሽግግር መንግሥት ጉዳዩን ሰከንና ቆም ብሎ ሊያጤነው ይገባዋል!
አዲስ ዘመን ጥር 21/2013