ግርማ መንግሥቴ
መጪውን አስር አመት አስመልክቶ የተደረጉ ጥናቶችንና በጥናቶቹ መሰረት የተደረሰባቸውን ግኝቶች የአለም ጤና ድርጅት (አጤድ) ይፋ አድርጓል። ችግሮቹን ለመፍታትም የአለም ህዝብ፤ በተለይም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት ይጠበቅባቸዋል። የመጪው አስር አመት የጤናው ዘርፍ ተግዳሮቶች በቁጥር 13 ሲሆኑ እንደሚከተለው ማየት ይቻላል።
የአየር ንብረት ቀውስ (Climate crisis)
አጤድ እንደሚለው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚከተለው ቀውስ የህዝቦች ጤና በከፍተኛ ደረጃ ይቃወሳል። በአመት በአማካይ ሰባት ሚሊዮን ሰውም በዚሁ ምክንያት ህይወቱን ያጣል። በአጠቃላይም 25 በመቶ የሚሆነው የአለም ህዝብ ህይወቱን የሚያጣው ማለትም በአመት ከሚመዘገበው ሞት ውስጥ ሩቡ የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትላቸው የተለያዩ ቀውሶች ምክንያት ነው። በመሆኑም ይህ አደጋ እየከፋ ከመሄዱ በፊት በመተባበርና ባንድነት፤ መንግስታትም ፖሊሲያቸውን መልሰው መላልሰው በማየትና በመከለስ ችግሩን ከወዲሁ ለመቋቋም ጥረት ማድረግ ይገባል።
ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የጤና አገልግሎቱን ለመስጠት ችግር የሚያጋጥም መሆኑ በአለማችን ግጭቶችና ቀውሶች እለት በእለት እየተስተናገዱ ይገኛሉ። የእነሱ መከሰት ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ለደረሰባቸውና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች መድረስ እንዳይቻል አድርገዋል።
ለምሳሌ በ2019 ብቻ በ11 አገራት ለእርዳታ በተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች ላይ 978 ጥቃቶች ተሰንዝረውባቸው፤ ለ198 ባለሙያዎች ሞት ምክንያት ሆነዋል። ይህ ብቻም አይደለም ግጭቶቹና ቀውሶቹ በበርካታ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለስደት ስለሚዳርጉና በዛም ምክንያት ለተለያዩ በሽታዎች ስለሚጋለጡ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል።
ይህእንዳይደገም ሁሉም ወገን ከግጭት ርቆ ለችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን ሊፈልግ ይገባል ብሏል አጤድ።
ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት ማግኘት
ይህ በቀጥታ ከአገራት፤ ባጠቃላይም ከአለም ምጣኔ ሀብት ጋር ግንኙነት ያለውና ኢ-ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍልን የተመለከተ ሲሆን፤ እንደ አንድ የጤና አገልግሎትን በእኩልነት ያለማግኘት ችግር ሆኖ የሚታይ ነው። በመሆኑም ይላል አጤድ ይህን ኢፍትሀዊነት ለማስቀረትና ሁሉም እኩል የጤናው ዘርፍ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል።
አስፈላጊ የጤና ግብአቶችን ማግኘት የሚገባ ስለመሆኑ
ሰዎች ጤናቸውን ለመጠበቅ፣ ለመከላከልና ከታመሙም ለመዳን የሚያስችሏቸውን ምርቶች (ትጥቆች፣ መድሃኒቶች ወዘተ) እጥረት የተጋለጡ ናቸው፤ ወይም አያገኙም። ይህንን ችግር ከወዲሁ መፍታት ካልተቻለ መጪው አስር አመት በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ችግር ማጋጠሙ የማይቀር መሆኑን አጤድ ያሳስባል።
የኢንፌክሽን ህመሞችን መከላከል
ኤችአይቪ/ኤድስ እና በመሳሰሉት ምክንያት በአመት በአማካይ አራት ሚሊዮን ህዝብ ይሞታል። የመከላከሉ ስራ በከፍተኛ ደረጃ ተጠናክሮ ካልቀጠለ ይህ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ያድጋል። በመሆኑም ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ መንግስታትም በፖሊሲዎቻቸውና ፖሊሲዎቹን ተግባራዊ በማድረግ በኩል ተጋግዘው እንዲሰሩ አጤድ ጥሪ ያቀርባል።
ወረርሽኝን ለመከላከል ዝግጅት መደረግ ያለበት ስለመሆኑ
አጤድ “አይቀሬው” (Inevitable) ሲል የገለፀው የቫይረስ ወረርሽኝ የመከሰቱን ጉዳይ ሲሆን ይህን ለመከላከል የሚደረግ ዝግጅት ከወዲሁ መጀመር አለበት። አገራት ይህንንና ድንገተኛ (የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ) አደጋን፣ ከመከላከል አኳያ እያደረጉት ያለውን ተግባር አጠናክረው መቀል አለባቸው። ለዚህም ሲባል የጤና ስርአታቸውን እንደገና በመፈተሽ በመረጃ ላይ
የተመሰረተ ዝግጅት ከወዲሁ ካላደረጉ ልክ እንደ አሁኑ ኮቪድ ሁሉ ህዝባቸውን ለሌላ እልቂት ይዳርጋሉ። ስለዚህ አገራት ሊያስቡበት የግድ ነው በማለት የጤና ድርጅቱ ያስጠነቅቃል።
ደህንነታቸው የተጠበቀ ስላልሆኑ ምርቶች
ይህ ጥራት፣ ደረጃቸውና ደህንነታቸው ያልጠበቁ ምርቶች የሚያደርሱትን አደጋ የሚመለከት ነው። እንደ አጤድ ጥናት በአሁኑ ሰአት በአለም ላይ የሰውን ልጅ ከሚያጠቁ በሽታዎች መካከል አንድ ሶስተኛው በዚህ እና መሰል ችግሮች አማካኝነት የሚመጣ ነው።
የጤና ባለሙያዎችን ማፍራት ላይ አለማተኮር
እንደ አጤድ ማስረጃ በ2030 በቂ የጤና ባለሙያ ይኖር ዘንድ ሌሎች ተጨማሪ 18 ሚሊዮን የጤና ባለሙያዎችን ማፍራት የግድ ነው። ከፍተኛ መዋእለ ንዋይን በመመደብ ይህን ማድረግ ካልተቻለ የሚፈለገው የህብረተሰብ ጤናን የመጠበቅ ደረጃ ላይ መድረስ አይቻልም።
የወጣቶች ደህንነት ጉዳይ
የወጣቶችን ደህንንት በተመለከተም የተብራራ ሲሆን በየአመቱ እድሜአቸው ከ10 እስከ 19 የሆኑ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ይሞታሉ። የመሞታቸው ምክንያቶችም የመንገድና ትራፊክ አደጋዎች፣ ራስን ማጥፋት፣ በመጠኑ ያነሰ የመተንፈሻ አካል ችግር፣ በእርስ በርስ ግጭት፣ ከመጠን ያለፈ አልኮሆል መጠጥ፣ ጥንቃቄ በጎደለው ወሲብና ኤችአይቪ/ኤድስ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባለማድረግ እና የመሳሰሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ይህ ደግሞ እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል ይጠበቃል።
በመሆኑም አጤድ በዚህ ዙሪያ በወጣቱ ላይ በከፍተኛ ደረጃ የባህርይ ለውጥ ለማምጣት እሰራለሁ ያለ ሲሆን አገራትም ይህንኑ በማድረግ እንዲተባበሩት አሳስቧል።
ህብረተሰቡ በጤና ባለሙያዎች ላይ ያለውን እምነት ማጠናከር
የጤና ባለሙያዎች በተገልጋዩ ማህበረሰብ ዘንድ ታማኝነታቸው እንዲጨምር በሚገባ መስራት እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን ይህም በአብዛኛው የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት ማህበረሰቡን ከባለሙያው
የመለየት ስራን የሚሰሩ ወገኖች መኖራቸው፣ “መድሀኒት አትውሰዱ” የሚል ዘመቻ ድረስ የመሄድ ሁኔታ እንዳለ፤ ይህም በጤና አገልግሎቱ ዘርፍ በከፍተኛ ችግርነት የተጋረጡ ናቸው። በመሆኑም ይላል ድርጅቱ አገራት፣ መንግስታት፣ የጤና ተቋሟት፣ ባለሙያዎችና አጠቃላይ ማህበረሰቡ ይህንን ችግር በመዋጋት በኩል አስፈላጊውን ሁሉ ሊያደርጉ ይገባል።
የላቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም የጤና አገልግሎቱን ማሻሻል
የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሻሻል የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ማስፋት ይገባል የሚለው አጤድ ህክምናን፣ አስቀድሞ መከላከልን፣ የምክር አገልግሎትን፣ በጤናው ዘርፍ ያሉ አጠቃላይ ችግሮችንና የመሳሰሉትን ለመፍታት ቴክኖሎጂን በላቀ ደረጃ መጠቀም ተገቢ መሆኑን ያስረግጣል፤ አገራትም ወደዚሁ ዘርፍ እንዲያተኩሩ ይመክራል።
ፀረ-ባክቴሪያ የሆነ ህክምናን በተመለከተ
የባክቴሪያ በሽታ አስተላላፊ የሆነ ባክቴሪያን ለመቋቋም የሚያስችሉ ህክምናዎችን ተግባራዊ በማድረግ በመጪው አስር አመት ውስጥ የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ውጤታማ ማድረግ ተገቢ ነው።
የጤና ተቋማት አካባቢ ንፅህና
በአለማችን በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ንፅህናው ባልተጠበቀ አካባቢ የሚኖሩ ናቸው። ለምሳሌ በአለም ላይ ካሉት የጤና ተቋማት አንድ አራተኛዎቹ ውሀ እንኳን የሌላቸው ናቸው። ይህ ደግሞ በተለያዩ በሽታዎች ለመጠቃት ዋናው መንስኤ ነው። እንደ አጤድ ከሆነ መንግስታት ለዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል።
በአጠቃላይ አጤድ ከላይ የተዘረዘሩት 13 ነጥቦች በሚቀጥለው አስር አመት ውስጥ የጤና አገልግሎቱን ዘርፍ የሚፈታተኑ፤ የአለምን ህዝብ ለከፍተኛ የጤና እክል የሚያጋልጡ፣ በተለይ በታዳጊ አገራት የሚኖረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የሚያናጉ ወዘተ መሆናቸውን አምኗል። በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከወዲሁ ሊያስቡበትና መመሪያውን ተግባራዊ ሊያደርጉት እንደሚገባ መገንዘብ ይቻላል።
አዲስ ዘመን ጥር 20/2013